Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከቡና ንግድ ባሻገር ባሉ ንግዶች የተስፋፋው አልፎዝ ኩባንያ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለ22 ዓመታት በተለያዩ የንግድ ሥራዎች በመሠማራት በተለይም ቡናን ወደ ውጭ በመላክ ቀደምት ከሚባሉ ድርጅቶች ተርታ ይሠለፋል፡፡ በላኪነትና በአስመጪነት ንግድ መስኮች ሰፊ ተሞክሮ ያዳበረው አልፎዝ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ በአሁኑ ወቅት የኢንቨስትመንት አድማሱን እያስፋፋ ይገኛል፡፡  

ሁለት አሥርታት ባስቆጠረው የንግድ ጉዞው በቦንጋና በጅማ የቡና እርሻ ልማት ላይ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል፡፡ በአዳሚ ቱሉ የእንስሳት ሀብት ልማትና የሥጋ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ገንብቷል፡፡ በድሬዳዋና በአዲስ አበባ፣ እያንዳንዳቸው 30,000 ቶን ቡና ማከማቸትና ማደራጀት የሚችሉ መጋዘኖች ሲኖሩት፣ ቡና ቆልቶና ፈጭቶ ለውጭ የሚያቀርብ ድርጅትም በቃሊቲ ተክሏል፡፡ በእነዚህ የንግድ እንቅስቃሴዎቹ ለሁለት ሺሕ ሰዎች የሥራ ዕድልና ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማስገኘት የቻለው አልፎዝ፣ የኮንስትራክሽን ማሽኖችና የብረት ጥሬ ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባትም ተጠቃሽ ነው፡፡

ይኼው ድርጅት የተቆላ ቡና በኮንቴይነር ወደ ውጭ በመላክ ቀዳሚ እንደሆነ የአልፎዝ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ፕሬዚዳንት ሼክ አሊ ሁሴን መሐመድ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ወደ ጃፓን ተቆልቶ፣ ተፈጭቶና ታሽጎ በኮንቴይነር ለመጀመርያ ጊዜ እንዲላክ ያደረግነው እኛ ነን፤›› ያሉት ሼክ ዓሊ ሁሴን፣ ይህም ሆኖ አሁን ላይ ቡና ገዥ እየጠፋ፣ ገበያውም አልገኝ እያለ ማስቸገሩን ይናራሉ፡፡ ‹‹በውጭ ያሉ የቡና አቅራቢዎች ሁሉ ነገሩ ያለቀለት ምርት ከእኛ እንድንልክላቸው አይፈልጉም፡፡ ገበያቸውን እንዳንሻማቸው ፍርኃት አላቸው፤›› ብለዋል፡፡  

አክለውም ከመንግሥት ጋር በትብብር በመሥራትና ያለቀለትን ቡና ለውጭ ገበያ ማቅረብ ቢቻል፣ የኢትዮጵያ ቡና ከማስተዋወቅ ባሻገር የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ከመቅረፍ አኳያ ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡ የቡናውን የእሴትና የገበያ ሰንሰለት ሒደት ሲያብራሩም፣ ከለቀማ ጀምሮ በራሳቸው ድርጅት በኩል እንደሚያከናውኑ፣ ሆኖም የገበያ ችግር እንደገጠማቸው አውስተዋል፡፡ ይህ ችግር ከመንግሥት ጋር በመሥራት እንደሚፈታ ጉዳይ እንደሆነም ሼክ አሊ ያምናሉ፡፡

የ2012 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የድርጅታቸውን አፈጻጸም በተመለከተ እንደገለጹት፣ 3,000 ሜትሪክ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ አሥር ሚሊዮን ዶላር ገቢ አስገኝቷል፡፡ በድርጅታቸው የሚመረተው ቡና የመዳረሻ ገበያዎቹን በተመለከተ ሲገልጹም፣ መካከለኛው ምሥራቅ በተለይም ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ጃፓን፣ አውሮፓና አሜሪካ ቡናዎች እንደሚላኩ ጠቅሰዋል፡፡

ከቡና ንግድ ባሻገር ባሉ ንግዶች የተስፋፋው አልፎዝ ኩባንያ

 

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በአምስት ወራት ውስጥ ከ120,000 ሜትሪክ ቶን በላይ ቡና ለዓለም ገበያ ማቅረቡን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በዓመቱ መጨረሻ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ከ300 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ቡና ለውጭ ገበያ እንደሚቀርብ መታቀዱን ይተወቃል፡፡

አልፎዝ ኩባንያ ከቡና ንግድ ባሻገር በሆቴል፣ በሪል ስቴትና በገበያ ማዕከል ግንባታ ሥራዎች ላይ ለመሠማራትና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ ፋብሪካ ለመክፈት ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ የድርጅቱ ባለቤት አስታውቀዋል፡፡ በዚህ መሠረት ቅዳሜ የካቲት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ወደ ሥራ ስለሚያስገባው ባለስምንት ወለል የገበያ ማዕከል ሕንፃ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡

ከቀድሞው ኤምፔሪያል ሆቴል ወደ ገርጂ በሚወስደው መንገድ ዳር የተገነባው የገበያ ማዕከሉ ሕንፃ፣ በ3,000 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን፣ 400 ሱቆችንና 300 ቢሮዎችን በውስጡ እንዳካተተ ሼክ አሊ ገልጸዋል፡፡ ለ300 ወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠረው አልፎዝ ፕላዛ ግንባታው ስድስት ዓመታት እንደፈጀ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች