Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየማይዘነጋው ሰማዕትነት

የማይዘነጋው ሰማዕትነት

ቀን:

“ራስን ካንገት ላይ ቆራርጦ እየጣለ
በችንካር ቸንክሮ ሰው እየገደለ
ሰውን ከነቤቱ አብሮ እያቃጠለ
ማነው እንደ ፋሽስት በሰው ግፍ የዋለ?
ሥጋችንን ገድለው ሊቀብሩት ከጀሉ
በዚህ ያልነበሩ ሐሰት እንዳይሉ
እሊህ አስክሬኖች ይመሰክራሉ፡፡”

83 ዓመታት በፊት የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በፋሺስት ጣሊያን ጭፍራ ማርሻል ሮዶልፎ ግራዚያኒ አማካይነት በአዲስ አበባ ከተማና በዙርያዋ ለሦስት ቀናት በዘለቀው ጭፍጨፋ ሰማዕት ለሆኑት 30 000  ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በቆመው ሐውልት ግርጌ ከሰፈረው ግጥም ከፊሉ ነው፡፡

ይህ ሐውልት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ 14 ዓመት የዘውድ በዓላቸውን ሐሙስ ጥቅምት 23 ቀን 1937 .. ሲያከብሩ በተመረቀውና ለአርበኞችም የተጋድሎ ሜዳሊያ ባበረከቱበት አዲሱ ሐውልት ግርጌ በግእዝ ቋንቋ የተጻፈው ጽሑፍ ዘመነ ፍዳውን የሚያስታውስ ነው፡፡
ይህ የአፅሞች ማረፊያ በጣሊያን ፋሺስታውያን እጅ በግፍ የካቲት 12 ቀን 1929 .. የተገደሉ የብዙኃን ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ ነው በሚል የሚንደረደረው በግዕዝ የተጻፈው የሐውልቱ ጽሑፍ አገዳደላቸው በድንጋይ በመወገር፣ በዱላ በመቀጥቀጥ፣ በአካፋ፣ በዶማ በመብረቀ ሐፂን/የብረት መብረቅ (መትረየስ) በየቤታቸው ውስጥ በእሳት በመቃጠል፣ ወዘተ እንደሆነ ይዘረዝራል፡፡ የግፍ አገዳደሉ በተፈጸመ በአራተኛው ዓመት ከብሪታኒያ በድል አድራጊነት የተመለሱት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የነፃነት ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ካቆሙ በኋላ በግፍ የተገደሉትን አፅሞች ከየቦታው እንዲሰበሰቡ ሹማምንቱን በማዘዝ ለዝክረ ነገር እንዲሆንም በቅዱስ ስፍራም መታሰቢያውን አቆሙላቸው፡፡

በሐውልቱ ላይ የሚገኘው ተከታዩ ግጥምም እንዲህ ያስተጋባል፡፡

“ይህን ታላቅ ስቃይ መከራና ግፍ
ሲያስታውስ ይኖራል የታሪክ መጽሐፍ
አትርሱት አንርሳው ያስታውሰው ዘራችን
ኢጣሊያ መሆኗን መርዛም ጠላታችን፡፡
እላንት አእጽምቶች ዕድለኞች ናችሁ
በኃይለ ሥላሴ ትንሣኤ አገኛችሁ፡፡”

ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ 1848 እስከ 1966›› በተሰኘውና 1989 .. በታተመው መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ የኢጣሊያ ፋሺዝም ጽልመታዊ ገጽታ ቁልጭ ብሎ የወጣው በየካቲት 12 ቀን 1929 .. ነው፡፡ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ሁለት ወጣቶች በግራዚያኒ ላይ ቦምብ ጥለው ካቆሰሉት በኋላ አዲስ አበባ ላይ መዓት ወረደባት፡፡ ‹‹ጥቁር ሸሚዝ›› እየተባሉ የሚታወቁት የፋሽስት ደቀመዛሙርት መንግሥት አይዟችሁ እያላቸው አዲስ አበባን ቄራ አደረጓት፡፡ የሰው ልጅ ጭንቅላት እንደ ዶሮ እየተቀነጠሰ ወደቀ፡፡ ቤቶች ከነነዋሪዎቻቸው ጋዩ፡፡ እርጉዝ ሴቶች በሳንጃ ተወጉ፡፡ የጭፍጨፋው ተቀዳሚ ዒላማ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ በተለይም የጥቁር አንበሳ አባላት ከራስ እምሩ ጋር እጃቸውን ከሰጡ በኋላ በከተማይቱ ይገኙ ስለነበር በወረንጦ እየተለቀሙ ተረሸኑ፡፡ ይህ የምሁራን ጭፍጭፋ አንድ ትውልድ እንዳለ ያጠፋ በመሆኑም ባገሪቱ የፖለቲካና ምሁራዊ ታሪክ ላይ የማይሽር ቁስል ጥሎ አለፈ፡፡

የዓይን እማኙ ‹‹ሊቀ ጠበብት እውነቱና የካቲት 12›› የተሰኘ ጽሑፍ የጻፉት ተመስገን ገብሬም እንዲህ ጽፈዋል፡– ‹‹ከሦስት ቀን የከተማ ጥፋት በኋላ ከሆለታ የመጡ የፋሽስት አውሬዎች በሚመለሱበት ካሚዮን በኋላው በኩል አቶ አርአያን እግራቸውን ጠርቅመው አሰሯቸው፡፡ ካሚዮኑ ሳይጐትታቸውእኔ ወደ ሰማይ እንድገባ ሰማይ ተከፍቶ ይጠብቀኛል፡፡ ኢየሱስንም በዚያ አየዋለሁ፡፡ ደስ ይለኛል፡፡ ደስ ይለኛል፡፡ ደስ ይለኛል!› የሚለውን የሚሲዮን መዝሙር ዘመሩ፡፡ ፋሽስቶቹም የተሻለውን መዝሙር ብትሰማ ይሻልሃል አሏቸውና ዱኪ ዱኪ የሚለውን መዝሙራቸውን ዘመሩ፡፡ ካሚዮኑም ሞተሩን አስነስቶ ሲነዳ ታስረው ቁመው ነበርና ያን ጊዜ ዘግናኝ አወዳደቅ አቶ አርአያ ወደቁ፡፡ ካምዮኑም እየፈጠነ ጐተታቸው፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ሆለታ አርባ ኪሎ ሜትር ይሆናል፡፡ ካምዮኑ ከዚያ ሲደርስ ከካሚዮኑ ጋር የታሰረው እግራቸው ብቻ እንደተንጠለጠለ ነበርና የካሚዮኑ ነጂ ከካሚዮኑ ፈታና ለውሾች ወረወረው፡፡ እኔንም ያለሁበትን ቤት ሰብረው ከዚያ ቤት ያለነውን አውጥተው ከየመንደሩም ሕዝቡን አጠራቅመው ኑረዋል፡፡ ከዚያም መሐል ጨመሩን፡፡

‹‹ስምንት መትረየስ በዙሪያችን ጠምደዋል፡፡ በዚያም ቦታ ቁጥራቸው በብዙ የሆኑ ሐበሾችን አስቀድመው ገለዋቸዋል፡፡ ሬሣቸውም ተቆላልፎ በፊታችን ነበረ፡፡ እኛንም በዚያ ሊገድሉን ተዘጋጁ፡፡ ለመትረየስም ተኩስ እንድንመች ያንዳችንን እጅ ካንዱ ጋር አያይዘው አሰሩን፡፡ አሥረውን ወደ መተኰሱ ሳይመለሱ አንድ ታላቅ ሹም መጣ፡፡ የርሱም ፖለቲካ ልዩ ነበረ፡፡ ፋሽስቶች የሚያደርጉትን የሰላማዊ ሕዝብ መግደል፤ ሕፃናቶችን ከአባትና እናታቸው ጋራ በቤት ዘግቶ ማቃጠል መልካም ብሎ ቢወድ እንኳን እኒያ ቦምብ በቤተ መንግሥቱ ስብሰባ የወረወሩት ሐበሾች ሳይታወቁ እንዲቀሩ አይወድም ነበርና ስለዚህ ካሚዮኖች ይዞ እየዞረ ፋሽስቶች የሚገድሉትን እያስጣለ ወደ እስር ቤት ለምርመራ ይወስድ ኑረዋል፡፡ እኛንም እንዲተኮስብን ታሰረን ከቆምንበት ከቅዱሰ ጊዮርጊስ ጠበል አጠገብ ካለው ሸለቆ እስራታችንን አስፈትቶ በአምስተ ረድፍ ወደላይኛው መንገድ ለመድረስ ስንሄድ በአካፋ ራሳቸውን የተፈለጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ምራቄ ደረቀ፡፡ በካሚዮኑ ወደ እስር ቤት አስወሰደን፡፡ ለጊዜው እስር ቤት ያደረጉት ማዘጋጃ ቤትን ነበር፡፡››

ስድስት ኪሎ በሚገኘው የያኔው ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ያሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በወቅቱ የነበረውን የፋሽስት ጣሊያን ጭፍጨፋ የታዘበው ሀንጋሪያዊው ሐኪም ላዲስላስ ሳቫ ዓይኑ ያየውንና የታዘበውን በማስታወሻው መግለጹን በጳውሎስ ኞኞ ‹‹የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት›› መጽሐፍ ላይ እንዲህ ተመልክቷል፡

‹‹…ከዚህ በኋላ በግቢውና በአካባቢው ወዲያውኑ ጅምላ ጭፍጨፋ ተጀመረ፡፡በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ ከነበሩት ኢትዮጵያውያን አንድም በሕይወት የተረፈ ሰው አልነበረም፡፡ ቦታው ላይ የተካሄደው የጅምላ ጭፍጨፋ የተሰበሰቡት ሰዎች ዕድሜያቸው የገፋ፣ ዓይነ ስውራን፣ አካል ጉዳተኞች፣ የኔብጤዎችና ሕፃናትን የያዙ ድሃ እናቶች ስለነበሩ በዚህ ቦታ የተፈጸመው ሰቆቃ ትርጉም የሌለው፣ የሚሰቀጥጥና የሚያሳፍር ነበር፡፡››

83ኛው የሰማዕታት መታሰቢያ ቀን ስድስት ኪሎ በሚገኘው የካቲት 12 መታሰቢያ አደበባይ የካቲት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ከንጋት እስከ ረፋድ የተከበረው የነበሩ እናትና አባት አርበኞች፣ የመዲናዪቱ ነዋሪዎች በተገኙበት ነው፡፡ ተማሪዎች ዕለቱን የሚያንፀባርቁ ተውኔታዊና ሙዚቃዊ ትርዒት ያቀረቡ ሲሆን፣ የፖሊስ ማርሽ ባንድም ታሪካዊና ፍቅረ አገራዊ ዜማዎችን አሰምቷል፡፡

የክብር እንግዳው የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አቶ እንዳወቅ አብጤና የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ከሐውልቱ ግርጌ ላይ የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል፡፡

ይኸው የሰማዕታት ዕለት፣ ከቀድሞው ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተጎራበተው መንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያንና አፅማቸው ተሰብስቦ ባረፈበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰማዕታቱ በጸሎትና በዝማሬ ታስበዋል፡፡

የሰማዕታት ቀን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን (1923-1967) ከ1934 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ በብሔራዊ በዓልነት ሲከበር የቆየ ሲሆን፣ የደርግ መንግሥት በ1967 ዓ.ም. ሲመጣ ግን ዕለቱ ታስቦ እንዲውል መወሰኑ ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...