Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመንግሥት በባለቤትነት በያዛቸው ድርጅቶች ቦርዶች ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ 50 በመቶ እንዲሆን ተጠየቀ

መንግሥት በባለቤትነት በያዛቸው ድርጅቶች ቦርዶች ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ 50 በመቶ እንዲሆን ተጠየቀ

ቀን:

በኢንተርፕራይዞች ውስጥ የሴቶች የቦርድ ውክልና 13.7 በመቶ ያህል ነው

በአመራር ውስጥ ጥንካሬን ሊፈጥሩ ከሚያስችሉ መሠረታዊ ጉዳዮች የፆታ ስብጥር አንዱ በመሆኑ፣ መንግሥት የሚያስተዳድራቸውን ተቋማት በሚመሩ ቦርዶች ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ 50 በመቶ እንዲሆን ተጠየቀ፡፡

ከመጋቢት 2011 ዓ.ም. ጀምሮ መንግሥት በባለቤትነት የሚያስተዳድራቸውን ተቋማት የሚመሩ ቦርዶች ውስጥ ሴቶች 50 በመቶ ውክልና እንዲኖራቸው የሚያደርግ መመርያ እንዲወጣ የቅስቀሳ ዘመቻ የጀመረው የሴቶች ትስስር መድረክ ኤውብ፣ ይህንኑ አስመልክቶ ዓርብ የካቲት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ባዘጋጀው መድረክ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄውን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ሴቶች መንግሥት በሚያስተዳድራቸው የልማት ተቋማት ውስጥ በቦርድ ውስጥ ያላቸውን ውክልና አስመልክቶ በኢሩያን ሶልዩሽን የተጠናውን የመጀመርያ ጥናት ያቀረቡት ፅኑ ዓምደ ሥላሴ፣ በ24 በመንግሥት ይዞታ ሥር ባሉ ኢንተርፕራይዞች ላይ የተሠራው ዳሰሳ የሴቶች የቦርድ ውክልና ከ13.7 በመቶ እንደማይበልጥ ገልጸዋል፡፡

ስኳር ኮርፖሬሽን፣ ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ጨምሮ በጥናቱ በተካተቱ ድርጅቶች ውስጥ ከስድስት እስከ 11 የሚደርሱ የቦርድ አባላት ቢኖሩም፣ አራት ሴቶች በቦርድ አባልነት ተወክለው የተገኙት በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ውስጥ ብቻ ነው ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን ዘጠኝ፣ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ሰባት የቦርድ መቀመጫ ቢኖራቸውም፣ የሴቶች ውክልና በሁለቱም ተቋማት ዜሮ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በሌሎቹ ተቋማት አንድ ወይም ሁለት ሴት የቦርድ አባላት የተወከሉ መሆናቸውን ጥናቱ አሳይቶ ይህ አሠራር የፆታ እኩልነትን የማያረጋግጥ ስለሆነ፣ ሹመት የሚሰጡ የበላይ ኃላፊዎች ፆታን ያገናዘበ ሹመት እንዲሰጡ ሐሳብ ቀርቧል፡፡

የኤውብ መሥራችና ዳይሬክተር ናሁሰናይ ግርማ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች በአመራር ላይ ያላቸውን ውክልና አስመልክቶ እ.ኤ.አ. ከ2015 እስከ 2016 ባዘጋጁት ሲምፖዚየም የሉም በሚያስብል ደረጃ እንደነበር ሲያመላክቱ፣ የጥናቱ አቅራቢ ፅኑ ደግሞ በቦርድ አመራሮች ላይ ያለው የፆታ ስብጥር ለበርካታ ዓመታት ለውጥ ሳያሳይ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡

ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ የካቢኔያቸውን 50 በመቶ ለሴቶች ማድረጋቸው፣ በተለያዩ ተቋማትም ሴቶች ወደ ኃላፊነት እየመጡ መሆናቸው የሚበረታታ ቢሆንም፣ ሴቶች በውሳኔ ሰጪነትና በመምራት ላይ ያላቸው ተሳትፎ አናሳ ነው፡፡

በጥናቱም በቦርድ ውስጥ የሚገቡ ሴቶች ጥቂት በመሆናቸው ድምፃቸው ተቀባይነት እንዳያገኙ ማድረጉ፣ ልምዳቸውን ከማዳበርና ትምህርታቸውን ለማሻሻል የተደቀኑባቸው ውስንነቶች፣ ተገቢውን የሥራ ዕድገት አለማግኘታቸውና ቦርድ ውስጥ የሚካተቱ አባላት በሥራ ልምድ የካበቱና ከፍ ካለ ማዕረግ የሚመረጡ በመሆናቸው ሴቶች ወደ ቦርድ አባልነት እንዳይመጡ ከምክንያቶቹ የሚጠቀሱ መሆናቸው ታይቷል፡፡

በመንግሥት ከሚተዳደሩ ኢንተርፕራይዞች በአንዳንዶቹ የቦርድ አባል  ለመሆን የአሥር ዓመት ልምድ መጠየቃቸው፣ ይህንን ልምድ የሚያሟሉ ሴቶች ማግኘት አዳጋች መሆኑ፣ ወሊድን ጨምሮ የቤተሰብ ኃላፊነት በሴቶች ላይ መውደቁ ሴቶች ወደ ኃላፊነት እንዳይመጡ ካደረጉ ምክንያቶችም ተካተዋል፡፡

መንግሥት ይህንን ተግዳሮት ሴቶች በመንግሥት የልማት ተቋማት ውስጥ በቦርድ አባልነት እንዲወከሉ የሚያስችሉ አሠራሮችን እንዲዘረጋ ኤውብ ጠይቆ፣ የፆታ እኩልነት ምጣኔው የተሻለ የሆነባቸው አገሮች በልማት ሥራዎች ላይ ሴቶችን ለማሳተፍ ግድ ከሌላቸው አገሮች ይልቅ የተሻለ የበለፀጉና ተወዳዳሪ መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...