Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሲኖዶስ ሁለት ወጣቶች ሕይወታቸው ያለፈበት ቦታ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራበት ጠየቀ

ሲኖዶስ ሁለት ወጣቶች ሕይወታቸው ያለፈበት ቦታ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራበት ጠየቀ

ቀን:

የክህደት ትምህርት ያስተምራሉ ያላቸውን ካህናት ሥልጣነ ክህነት አገደ

በቦሌ ክፍለ ከተማ ሃያ ሁለት አካባቢ ከቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል በስተጀርባ በተለምዶ 24 ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፣ ከእምነት ጋር በተያያዘ ጥር 24 ቀን 2012 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት ላይ ሁለት የአካባቢው ነዋሪ ወጣቶች የተገደሉበት ሥፍራ ላይ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጠየቀ፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ሰብሳቢ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 እና 5 ነዋሪዎች ለቅዱስ ሲኖዶስ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ነዋሪዎቹ በአቤቱታቸው ጥር 24 ቀን 2012 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት በቦሌ ቅዱስ ገብርኤልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን በርካታ ምዕመናን በምህላና ፀሎት ላይ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ወቅት የፀጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጭስና ተኩስ በመጠቀም እንዲሁም በዱላ በበርካታ ምዕመናን ላይ የአካል ጉዳት ከማድረሳቸውም በተጨማሪ፣ ሁለት ወጣቶች መገደላቸውን ለሲኖዶሱ ባቀረቡት  አቤቱታቸው መግለጻቸውን ፓትርያርኩ አስረድተዋል፡፡ ተሠርቶ የነበረውን ቤተ ክርስቲያን (መቃኞ) ማፍረሳቸውን፣ በካህናት ተባርኮ የነበረው የቃል ኪዳን ጽላት መወሰዱንና ንዋያተ ቅድሳት መዘረፋቸውንም በአቤቱታቸው መግለጻቸውን ፓትርያርኩ አክለዋል፡፡

ከምዕመናኑ የደረሰውን የአቤቱታ ደብዳቤ የተመለከተው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ አጠቃላይ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንና ምዕመናን ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍና ጭካኔ የተሞላበትን ድርጊት ከማውገዝም ባለፈ፣ ከየካቲት 9 እስከ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ፓትርያርኩ ተናግረዋል፡፡ በተለያዩ ገዳማት፣ አብያተ ክርስቲያናትና ምዕመናን ላይ እየደረሰ ያለው ችግር ዝም ተብሎ የሚታይ አለመሆኑን የጠቆሙት ፓትርያርኩ፣ ሃያ ሁለት አካባቢ በተለምዶ ቀበሌ ሃያ አራት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሁለት ወጣቶችን በገደሉና በርካታ ምዕመናን ላይ የአካል ጉዳት ባደረሱ አካላት ላይ መንግሥት ጥብቅ ምርመራ በማድረግ፣ ወንጀለኞቹን ለይቶ ለፍርድ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል፡፡ ፍርዱንም ለምዕመናን በመገናኛ ብዙኃን እንዲገልጽም አሳስበዋል፡፡

ምዕመናኑ የተደበደቡበትና ወጣቶቹ የተገሉበት ቦታ ከአራት ዓመታት በፊት ጀምሮ ለአካባቢው ምዕመናን ማምለኪያ እንዲሆን ከመንግሥት ጋር በመነጋገርና በመጻጻፍ ላይ እንደነበሩ የጠቆሙት ፓትርያርኩ፣ አማንያኑ ጨለማን ተገን ባደረጉ የመንግሥት የፀጥታ አስከባሪዎች በግፍ ደማቸው የፈሰሰበትና ሕይወታቸው ያረፈበት ቅዱስ ቦታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የተወሰዱ ንዋየ ቅድሳት፣ የቃል ኪዳን ጽላትና ሌሎች ንብረቶች እንዲመለሱና ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንም ተሠርቶ ምዕመናን በሰላም መንገድ አምልዕኳቸውን እንዲፈጽሙ የሚመለከተው የመንግሥት አካል መመርያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውና ከሞቱት ምዕመናን በተጨማሪ በየምክንያቱ የታሰሩ ምዕመናንና ወጣቶች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ሲኖዶሱ ውሳኔ ማሳለፉን ተናግረዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እንደተናገሩት፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ሌላው ያሳለፈው ውሳኔ በኦሮሚያ ክልል በሕገወጥ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ‹‹የክህደት ትምህርት›› ማስተማራቸውን በመረጃ በማረጋገጡ ክህነተ ሥልጣናቸውን ማገዱን ነው፡፡

ሥልጣነ ክህነታቸው የታገደው ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን፣ አባ ገብረ ማርያም ነጋሳ፣ መምህር ኃይለ ሚካኤል ታደሰና ቄስ በዳሳ ቶላ የሚባሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ናቸው፡፡ አገልጋዮቹ ከቤተ ክርስቲያኗ ሕግና ደንብ ውጪ፣ ‹‹በኦሮሚያ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት እናቋቁማለን›› በማለት በሕገወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ፓትርያርኩ ገልጸዋል፡፡ ቀሳውስቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ተባርኮ የተሰጣቸው ጽላት እንዳላቸውና በአሜሪካ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ስም ቤተ ክርስቲያን እንዳቋቋሙ በመግለጽ፣ ቤተ ክርስቲያኗ በማታውቀው መንገድ ምዕመናንን ግራ እያጋቡና እያሳሳቱ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ውጪ የክህደት ትምህርት እያስተማሩ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ እንደደረሰም ፓትርያርኩ አብራርተዋል፡፡ አገልጋዮቹ ከድርጊታቸው ተቆጥበውና ንስሀ ገብተው እስከሚመለሱ ድረስ ክህነተ ሥልጣናቸው ከየካቲት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የታገደ መሆኑን፣ ቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑን ፓትርያርኩ አስታውቀዋል፡፡

ከየካቲት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳይሰጡም መታገዳቸውንም አክለዋል፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ ተባርኮ ታቦተ ጽላት እንደተሰጣቸው በመግለጽ ምዕመናኑን ሲያሳስቱ የከረሙት፣ በሐሰት መሆኑንና ምዕመናኑም ተሳስተው ከሚያሳስቱ አሳሳቾች ራሳቸውንና የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት እንዲጠብቁ አሳስበዋል፡፡ በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሊቦን ዝቋላ ገዳም፣ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም፣ በሰላሌ ሀገረ ስብከት ደብረ ሊባኖስ ገዳም፣ በአንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች እየደረሰ ያለውን ችግርና ታሪክ የማጠልሸት ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆምና ችግር ፈጣሪዎቹንም መንግሥት ለሕግ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል፡፡ ገዳማቱ የአገር ቅርስ በመሆናቸው መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሊጠብቃቸው እንደሚገባም አክለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ለሥራ ባቀኑበት ወቅት በስደት ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የማምለኪያ ቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ቦታ በማስፈቀዳቸው ፓትርያርኩ አመሥግነዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኗን ታሪክ እያበላሹ፣ ለአገርና ለወገን ባለውለታ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን ስም የማጥፋት ዘመቻ በማካሄድ ላይ ናቸው ያሏቸውን ኦኤምኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ ኤልቲቪና ኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስን  በሕግ እንዲጠየቁ፣ ለወደፊቱም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መንግሥት አስፈላጊውን ውሳኔ እንዲያሳልፍም ሲኖዶስ መጠየቁን ፓትርያርኩ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...