Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በግማሽ ዓመቱ የመንግሥት ተቋማት ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ አተረፉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ልማት ባንክ ከ950 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ አስመዝግ

በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት በ2012 ግማሽ ዓመት ከታክስ በፊት 10.7 ቢሊዮን ብር እንዳተረፉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክም ከኪሳራ ወጥቷል ተብሏል፡፡

እንደ ኤጀንሲው መረጃ ከ10.7 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ያስመዘገቡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ መድን ድርጅት አብዛኛውን ድርሻ ሲይዙ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክም ተቀላቅሏቸዋል፡፡ ሦስቱ የፋይናንስ ተቋማት በግማሽ ዓመቱ ከታክስ በፊት ለማትረፍ ያቀዱት መጠን 9.67 ቢሊዮን ብር እንደነበር የኤጀንሲው መረጃ አስታውሶ፣ ክንውናቸው ከዕቅዳቸው አኳያ ሲታይ ከ11 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳሳየ ጠቅሷል፡፡

በሦስቱ የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ላይ የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በተካሄደበት ወቅት እንደታየው፣ በግማሽ ዓመቱ የተጠቀሰውን ያህል ትርፍ ሊያስመዘገቡ የቻሉት የገቢ መጠናቸው በመሻሻሉ ነው፡፡ ሦስቱ ተቋማት የፋይናንስ አገልግሎቶችን በማቅረብ በግማሽ ዓመቱ 34.35 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማስመዝገብ አቅደው፣ 36.64 ቢሊዮን ብር ወይም የዕቅዳቸውን 107 በመቶ ማከናወናቸው ተጠቅሷል፡፡ ተቋማቱ ካገኙት የ10.71 ቢሊዮን ብር ትርፍ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ያስመዘገበው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲሆን፣ ከሦስቱ ተቋማት ትርፍ ውስጥ የንግድ ባንክ ድርሻ 9.33 ቢሊዮን ብር ወይም 87 በመቶ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

በኤጀንሲው መረጃ መሠረት ኪሳራ ሲያስመዘግብ በመቆየቱና ከፍተኛ የተበላሸ ብድር መጠን በመሸከም የሚተቸው ልማት ባንክ፣ በ2012 ዓ.ም. ከኪሳራ በመውጣት ትርፋማ እየሆነ መውጣቱ እየተገለጸ ነው፡፡ የልማት ባንክን ወቅታዊ አቋም በሚያመለክተው መረጃ መሠረት፣ ከ2012 የመጀመርያው ሩብ ዓመት ጀምሮ አፈጻጸሙን አሻሽሎ ከኪሳራ እየወጣ መምጣቱ ይጠቅሳል፡፡

በዚህ መሠረት ልማት ባንክ በአጠቃላይ በስድስት ወራት ውስጥ 951.60 ሚሊዮን ብር ወይም የዕቅዱን 483 በመቶ ማትረፍ ችሏል፡፡ በዚህም ሳቢያ ከዘርፉ አጠቃላይ የትርፍ መጠን ውስጥ የዘጠኝ በመቶ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ ሌላው አትራፊ መንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋም የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሲሆን፣ በግማሽ ዓመቱ የ427.89 ሚሊዮን ብር ትርፍ አስመዝግቧል፡፡ ይህም የዕቅዱን 101 በመቶ አፈጻጸም የሚወክል ሲሆን፣ በፋይናንስ ዘርፉ ከተመዘገው ትርፍ የአራት በመቶ ድርሻ እንደያዘ ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡

የተቋማቱን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸምና የመጪዎቹን ክንዋኔዎች በማስመልከት የኤጀንሲው ኃላፊዎችና የሦስቱ የልማት ድርጅቶች አመራሮች በተገኙበት ግምገማ መካሄዱ ታውቋል፡፡ የግማሽ ዓመቱ አፈጻጸም ውጤታማ በመሆኑ በቀሪዎቹ ወራት የሚኖሩት የትግበራ ምዕራፎች ይህንኑ ውጤታማነት አጠናክረው እንዲቀጥሉና በበጀት ዓመቱ መጨረሻም የላቀ ውጤት እንዲያስመዘግቡ መመርያ ተሰጥቷቸው ግምገማቸው እንደተጠናቀቀ ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡ የግምገማ መድረኩን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ገብረ መስቀልና ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሀብታሙ ኃይለ ሚካኤል እንደመሩት ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች