Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጁነዲን ሳዶ ‹‹ሸገር›› የተሰኘ ባንክ ለመመሥረት እንቅስቃሴ ጀመሩ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኦሮሚያ ክልልን በፕሬዚዳንት ከመመራት ባሻገር የተለያዩ መሥሪያ ቤቶችን በሚኒስትርነት ያስተዳደሩትና በስደት ከኢትዮጵያ ውጭ የነበሩት አቶ ጁነዲን ሳዶ ‹‹ሸገር›› ባንክ የተባለ አዲስ ባንክ ለማቋቋም እንቅስቃሴ በመጀመር የባንኩን የአክሲዮን ሽያጭ አስጀምረዋል፡፡

አቶ ጁነዲን ሸገር በሚል መጠሪያ የሰየሙትን ባንክ ለማቋቋም የተሰባሰበውን አደራጅ ኮሚቴ በአስተባባሪነት እየመሩ ሲሆን፣ ባንኩን ለመመሥረት የሚያስፈልገውን ካፒታል ለማሟላት ከተለያዩ ባለሀብቶች ጋር ከመከሩና አክሲዮን የሚገዙ በርካቶችን ከጎናቸውን ካሰለፉ በኋላ ወደ ካፒታል ማሰባሰብ ሥራ መግባታቸው ይጠቀሳል፡፡

ከሸገር ባንክ የአክሲዮን ሽያጭ በተሠራጨው መረጃ መሠረት፣ እንደ ሕጉ አግባብ አንድ አክሲዮን የአንድ ሺሕ ብር ዋጋ ይኖረዋል፡፡ አንድ ባለአክሲዮን ከአሥር አክሲዮኖች ጀምሮ መግዛት ይችላል ተብሏል፡፡ ባንኩን በተያዘው ዓመት መጨረሻ  ሥራ ለማስጀመር መታቀዱን ከአደራጅ ኮሚቴው ለመረዳት ተችሏል፡፡ ሸገር ባንክን ለመመሥረት አቶ ጁነዲን ጨምሮ 150 አደራጆች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ሲገለጽ፣ ካፒታል በማሰባሰቡ ረገድ ባንኩ ውጭ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚሠራም ተጠቅሷል፡፡ የባንኩን አብላጫ ድርሻም በገጠሩ ኅብረተሰብ ላይ ትኩረት በማድረግ የአክሲዮን ሽያጩ እንደሚከናወን ይጠበቃል፡፡

የባንኩ አደራጆች፣ ከባንኩ ጋር ለመሥራት ፈቃደኛ የሆኑና ታዋቂ ግለሰቦችን በማካተት ሐሙስ፣ የካቲት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል የባንኩን አቅጣጫ የሚያመላክት ትንታኔ አቅርበዋል፡፡

በዚሁ ወቅትም የባንኩ የአክሲዮን ሽያጭ እንደተጀመረ ተገልጾ፣ ከታዋቂ ግለሰቦች መካከል ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ፣ አቶ ጁነዲን ሳዶ፣ አቶ ጌቱ ገለቴ፣ አቶ ድንቁ ደያስና ሌሎችም ተገኝተዋል፡፡ የተለያዩ ከተሞችን የሚያስተዳድሩ ኃላፊዎችና  ከንቲባዎች እንዲሁም አባ ገዳዎች ተሳትፈዋል፡፡  

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት ባንክ ለማቋቋም 500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ተከትሎም የሸገር ባንክ የተፈቀደ ካፒታል እስከ ሁለት ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ ተገልጿል፡፡ የባንኩ አደራጆች ቢሮ ቦሌ መንገድ ላይ በሚገኘው ጌቱ ኮሜርሻል ሕንፃ ላይ መከፈቱም ታውቋል፡፡

የሸገር ባንክ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጁነዲን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የባንኩ ባለአክሲዮኖች ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲያቅፍ እንደሚደረግ በተለይ ግን ለገበሬው ክፍልና በተለያዩ ከተሞች በአነስተኛ ንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑና ተደራሽ የፋይናንስ አቅርቦቶችን እንዲያገኙ ይታሰባል፡፡ ባንኩ የገጠሩን ክፍል ከከተማው ጋር በማስተሳሰር የገቢ ምንጩ እንዲሰፋ የማገዝ ዓላማ እንዳለውም አቶ ጁነይዲ ጠቅሰዋል፡፡

የባንኩ ባለአክሲዮን መሆን ብቻ ሳይሆን በአነስተኛ ደረጃ ያለውን የገቢ ምንጩን ማሳደግ ለሚፈልገውም ከብድር ማስያዣ ውጭ ፋይናንስ እንዲያገኝ በመደገፍ ሸገር ባንክ የሚሠራ ሲሆን፣ ሌሎች ጠቃሚ የሆኑ የባንክ አሠራሮችንም ይተገብራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አሁን እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ባንክ ለማቋቋም የሚያስችለውን 500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ከማሰባሰቡ ሥራ ጎን ለጎን ባንኩ የበለጠ አዋጭ የሚሆንባቸውን ሥራዎች በባለሙያዎች እያስጠና የሚዘጋጅበት እንደሚሆን ከአቶ ጁነዲን ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የባንኩ የአክሲዮን ሽያጭ በአሥር ባንኮች መሸጥ የተጀመረ መሆኑን የገለጹት አቶ ጁነዲን፣ እነዚህ ባንኮች በመላ አገሪቱ ባሏቸው ቅርንጫፎች ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል አክሲዮኖች ለሽያጭ እንዳቀረቡም አስታውሰዋል፡፡

አቶ ጁነዲን በስደት ከአገር እስከወጡበት ጊዜ ድረስ የመገናኛና ትራንስፖርት ሚኒስትር ቀደም ብለውም የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር በመሆን ማገልገላቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች