Tuesday, December 5, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በትዕዛዝ  የሚመረቱ  የግብርና  ምርቶችን  ግብይት  የሚያስተዳድር  የውል  ሕግ ሊወጣ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግብርና ምርቶችን የሚፈልጉ ተጠቃሚዎች ምርቱን በትዕዛዝ አስመርተው በቋሚነት ለመግዛት የሚችሉበት የውል ሕግ ለማውጣት እንደታቀደ፣ ዝግጅቶችም እንደተጠናቀቁ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ አመለከተ።

የግብርና ሚኒስቴር ያረቀቀው ይህ የሕግ ሰነድ ‹‹ስለግብርና ምርት ውል የወጣ አዋጅ›› የሚል ስያሜ የያዘ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም ረቂቁ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደተላከ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ከረቂቅ አዋጁ ዋና ዓላማዎች መካከል ድርጅቶችና ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጓቸውን የግብርና ምርቶችና ግብዓቶች በትዕዛዝና በቋሚነት ተመርተው እንዲቀርቡላቸው የሚያስችል የሕግ ሥነ ሥርዓትን ማቋቋም፣ በሕግ የሚታሰር የምርትና የውል ሥርዓትን ማበጀት መሆኑን ረቂቅ የሕግ ሰነዱ ያስረዳል፡፡  

የግብርና ምርት አምራቾች ገበያ ተኮር የግብርና ምርቶችን ወደ ማምረት በማሸጋገር የግብርና ምርት ከሚያዘጋጁ፣ ከሚያቀነባብሩ፣ እሴት ከሚጨምሩ አግሮ ኢንዱስትሪዎች፣ እንዲሁም ከትልልቅ ገዥዎች ጋር ቀጣይነት ያለው ትስስር መፍጠር ሌላው በረቂቅ ሰነዱ የተቀመጠ ወሳኝ ዓላማ ነው።

 በተጨማሪም የግብርና ምርት ጥራትን፣ የአመራረት ቅልጥፍናና ተወዳዳሪነትን፣ እንዲሁም የግብርናና አግሮ ኢንዱስትሪ ተመጋጋቢነት በማሳደግ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ዕውን ማድረግ በዓላማነት ከተቀመጡት መካከል ተጠቃሽ ነው። የግብርና ምርትን በተመለከተ ረቂቅ አዋጁ በሰጠው ትርጓሜ መሠረት፣ በጥሬው ተመርቶና ወይም ተዘጋጅቶ የሚቀርብ የእርሻ፣ የመኖ፣ የእንስሳት፣ የዓሳና የሐር ምርትና ዘር፣ እንዲሁም የቁም እንስሳት ናቸው።

 በተመሳሳይ እንስሳትን በተመለከተ በተቀመጠው ትርጓሜ የዳልጋ ከብት፣ በግ፣ ፍየል፣ የጋማ ከብት፣ ግመል፣ ዶሮ፣ ንብ፣ ዓሳ፣ የሐር ትል፣ አሳማ፣ ጥንቸልና ወደፊትም ሊላመዱ የሚችሉት እንደሚጠቃለሉ ተመልክቷል።

 የግብርና ምርት ውል አመሠራረት የሚጀምረው አስመራቹ ወይም አምራቹ በሚያቀርበው የውል ሐሳብ መነሻነት እንደሚሆን፣ ነገር ግን ማንኛውም መንግሥታዊ ተቋም ወይም መንግሥታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶች የግብርና ምርት ውል ሐሳብ ማቅረብ ወይም ማመቻቸት እንደሚችል የረቂቁ ድንጋጌ ያመለክታል።

የግብርና ምርት ውል ግን ግልጽና በማያሻማ ሁኔታ በጽሑፍ ተዘጋጅቶ፣ በምስክሮች እማኝነት መፈረምና ሥልጣን በሚሰጠው ውል መዝጋቢ እንደሚመዘገብ ረቂቁ ያስረዳል።

ሁለት የግብርና ምርት ውል ዓይነቶች እንደሚኖሩ ረቂቁ የሚያመለክት ሲሆን፣ አንደኛው የውል ዓይነት አስመራች ከአምራቹ ጋር የሚዋዋለው የልማትና የምርት ግብይት ውል ነው፡፡ በዚህም አስመራቹ ለአምራቹ ተፈላጊውን ግብዓት የማቅረብ ግዴታ ይኖርበታል።

ሁለተኛው የግብርና ውል ዓይነት ግብዓት የማቅረብ ሁኔታ ላይ ግዴታን የሚጥልና የግብዓት ጉዳይ በተዋዋይ ወገኖች ስምምነት ብቻ እንደሚወሰን ሰነዱ ይጠቁማል። ግብዓት ማለት ለግብርና ምርት ማሳደጊያ የሚውል ቴክኖሎጂ፣ የቴክኒክ ድጋፍና የፋይናንስ አቅርቦት እንደሆነና እንዳስፈላጊነቱም የሰው ጉልበትን ሊያካትት እንደሚችል በረቂቁ የትርጓሜ ክፍል ተገልጿል።

 የግብርና ምርት ውል አካል ሆነው መካተት የሚገባቸውን ይዘቶች ረቂቁ ይዘረዝራል፡፡ የአምራቹና የአስመራቹ ስምና አድራሻ፣ የግብርና ምርት ውሉ ዓላማና ግብ፣ የማሳው ወይም የማራቢያ ቦታ ስፋትና አዋሳኞች ወይም የሚራባው ብዛት፣ የአምራቹና የአስመራቹ መብትና ግዴታዎች፣ የምርት ጥራትና የመጠን መሥፈርቶች ይገኙበታል።

የግብዓትና የምርት ዋጋ አወሳሰን፣ የቴክኒክ ድጋፍ ዓይነቶች፣ እንዳግባብነቱ የአዕምሮአዊ ንብረት ባለቤትነትን የተመለከቱ ድንጋጌዎች፣ ውሉ እንዳይፈጸም ማድረግ የሚችሉ ከአቅም በላይ የሆኑ ምክንያቶች፣ የተዋዋይ ወገኖች ወራሾች ወይም ተተኪዎች መብትና ግዴታን ስለማስተላለፍ የሚመለከቱ ድንጋጌዎችንም በውሉ ይዘት መካተት እንደሚኖርባቸው ያመለክታል።

ከዚህ በተጨማሪም የግብርና ምርት ውሉ ፀንቶ የሚቆይበት ጊዜ፣ ስለሚሻሻልበት ወይም ስለሚቀየርበት፣ ስለሚቋረጥበት ሁኔታዎችና ሥነ ሥርዓት የሚመለከቱ ድንጋጌዎች፣ አለመግባባቶችን መፍቻ መንገዶችና የግብርና ምርት ውሉ የተፈጸመበት ጊዜና ቦታ በውሉ መካተት ይኖርባቸዋል። ተዋዋይ ወገኖች የግብርና ምርቱን ዋጋ መወሰን ሲኖርባቸው፣ እንዲሁም የዋጋ አከፋፈልና የክፍያ ጊዜን በግልጽ ማስቀመጥ ይጠበቅባቸዋል።

የምርት ገበያ ዋጋ በውል ከተገለጸው በላይ ከፍ ያለ እንደሆነ፣ ሁለቱ ተዋዋይ ወገኖች በድርድር የዋጋ ማሻሻያ ሊያደርጉ እንደሚችሉና ይህ የሚፈጸምበት ዝርዝር በመመርያ እንደሚወጣ ያመለክታል።

አስመራቹ የሚያቀርበው የግብዓት ዓይነት፣ ጥራት፣ መጠን፣ ዋጋ በግልጽ በግብርና ምርት ውሉ ላይ ተዋዋዮች ማስቀመጥ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ አስመራች የሚያቀርበው የግብዓት ዋጋ በወቅቱ የአካባቢ ገበያ ከሚገኝ ተመሳሳይ ግብዓት ዋጋ መብለጥ እንደማይችል ረቂቁ ያመለክታል።

የግብርና ዘርፍ ገበያ ተኮር ምርቶችን ወደ ማምረት እንዲሸጋገርና የግብርና ምርት ከሚያዘጋጁ፣ ከሚያቀነባብሩ፣ እሴት ከሚጨምሩ አግሮ ኢንዱስትሪዎችና ከትልልቅ ገዥዎች ጋር ቀጣይነት ያለው ትስስር መፍጠርን ዓላማ ካደረገው ከዚህ ረቂቅ ጋር የሚዛመድ ድንጋጌ፣ በቅርቡ በፀደቀው የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ ውስጥ መካተቱ ይታወሳል።

 በፀደቀው የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ የቢራና የወይን መጠጦች ላይ 40 በመቶ ኤክሳይስ ታክስ በቅርቡ የተጣለ ሲሆን፣ እነዚህ የአልኮል ምርቶች 75 በመቶ የሚሆነውን ግብዓት ማለትም ገብስ፣ ብቅልና የመሳሰሉትን ከአገር ውስጥ ምርት በመጠቀም ያመረቱ ከሆነ ግን የሚጣለው ታክስ ወደ 30 በመቶ ዝቅ እንደሚል አዋጁ ላይ ተመልክቷል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች