Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየቡራዩ ግድያና የአምቦ ቦምብ ውርወራ የተፈጸመው በኦነግ ሸኔ መሆኑን ክልሉ አስታወቀ

የቡራዩ ግድያና የአምቦ ቦምብ ውርወራ የተፈጸመው በኦነግ ሸኔ መሆኑን ክልሉ አስታወቀ

ቀን:

ስድስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውም ተገልጿል

ዓርብ የካቲት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ከረፋዱ አምስት ሰዓት አካባቢ በኦሮሚያ ክልል የቡራዩ ከተማ ፖሊስ አዛዥን የገደለውና እሑድ የካቲት 15 ቀን 2012 ዓ.ም. በአምቦ ከተማ ውስጥ ለድጋፍ ሰላማዊ ሠልፍ በወጡ ነዋሪዎች ላይ ቦምብ በመወርወር የአካል ጉዳት ያደረሰው፣ ከኦነግ ተገንጥሎ የተለያዩ የሽብር ጥቃቶችን በመፈጸም ላይ የሚገኘው ኦነግ ሸኔ የተባለው ቡድን መሆኑን የኦሮሚያ ክልል አስታወቀ፡፡

የወንጀል ድርጊቱን የፈጸመው ኦነግ ሸኔ የሚባለው ቡድን መሆኑን የተናገሩት፣ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ ናቸው፡፡ ኮሚሽነር ጄኔራሉ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ በቡራዩ ከተማ ፖሊስ አዛዥና በሌሎች ሦስት ሰዎች ላይ ጥቃት ያደረሱት፣ እንዲሁም በአምቦ ከተማ ቦምብ በመወርወር ከፍተኛና መለስተኛ የአካል ጉዳት ያደረሱትን ለማጣራት በተደረገ ጥናት፣ ቡድኑ መፈጸሙ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

ዓርብ የካቲት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. የቡራዩ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ሰለሞን ታደሰ በሥራ ላይ እያሉ በድንገት በተከፈተባቸው ተኩስ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ሦስት ሰዎች ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በሕክምና ላይ መሆናቸውን ሪፖርተር አረጋግጧል፡፡

ጥቃት አድራሾቹ ለጊዜው የተሰወሩ ቢሆንም፣ በፀጥታ ኃይሎች ክትትልና በሕዝቡ ትብብር ስድስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑም ታውቋል፡፡ የቡራዩ ከተማ ፖሊስ አዛዥን ለምን መግደል እንደፈለጉ ለማወቅ ገና በምርመራ ላይ በመሆኑ ለጊዜው ባይታወቅም፣ ምናልባትም በምዕራብ ወለጋ አካባቢ ጥቃት እየፈጸመ ያለው ኦነግ ሸኔ የሽብር ተግባር ተልዕኮ ሊሆን እንደሚችልም ጥርጣሬ መኖሩን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የክልሉ ፖሊስ አመራሮች ገልጸዋል፡፡

በአምቦ ከተማም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና እየታየ ላለው ለውጥ ድጋፍ ለማድረግ ሰላማዊ ሠልፍ ወጥተው በነበሩ ነዋሪዎች ላይ ቦምብ በመወርወር በ29 ግለሰቦች ላይ ጉዳት ማድረሱንም ኮሚሽነር ጄኔራሉ አስረድተዋል፡፡ ጉዳት ከደረሰባቸው ውስጥ 28 ነዋሪዎች ሕክምና ተደርጎላቸው ወደ ቤታቸው የተመለሱ መሆኑን፣ አንድ ግለሰብ ጉዳቱ ከፍ ያለ በመሆኑ በሕክምና ላይ እንደሆነ አክለዋል፡፡

በጊንጪ ከተማም የካቲት 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት በፖሊስ ካምፕ ላይ በተወረወረ የቦምብ ጭስ ሁለት ፖሊሶች መጎዳታቸውን፣ በቅርቡ የተሾሙት የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ አስታውቀዋል፡፡

በአጠቃላይ ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል እየፈጸመ ያለው የግድያ ወንጀልና ቦምብ ወርወሮ ጥቃት የማድረስ እንቅስቃሴ፣ ክልሉ ችግር ውስጥ የገባ ለማስመሰል በሚጥሩ ተስፋ የቆረጡ  ቡድኖች መሆኑን ሕዝቡ ተረድቶ ጥንቃቄ በማድረግ አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎችን ሲያይ ለፀጥታ ኃይሎች በመንገር ትብብር እንዲያደርግም ኮሚሽነር ጄኔራሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በቡራዩ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ሰለሞን ሞት በርካታ የክልሉ ባለሥልጣናትና የሥራ ባልደረቦቻቸው በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ቁጭታቸውንና ሐዘናቸውን እየገለጹ ነው፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...