Tuesday, January 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትጠባብ የነጥብ ልዩነት ያላቸው የፕሪሚየር ሊግ ቡድኖች የውጤት ትንቅንቅ

ጠባብ የነጥብ ልዩነት ያላቸው የፕሪሚየር ሊግ ቡድኖች የውጤት ትንቅንቅ

ቀን:

ካፍ በመጪው ሚያዝያ የባህር ዳር ስታዲየምን በሚመለከት ውሳኔ ይሰጣል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዓመቱ የአንደኛ ዙር ጨዋታ ተጠናቋል፡፡ ይሁንና ቡድኖቹ ያላቸው ጠባብ የነጥብ ልዩነት በሁለተኛው ዙር የሚኖረውን የውጤት ትንቅንቅ ተጠባቂ አድርጎታል፡፡ በሌላ በኩል የብሔራዊ ቡድኑን ጨዋታ ጨምሮ  ፕሪሚየር ሊጉን ሲያስተናግድ የቆየው የባህር ዳር ስታዲየምን በሚመለከት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በሚያዝያ ወር በሚያደርገው የመጨረሻ ግምገማ ሜዳው ኢንተርናሽናል ጨዋታ የማስተናገድ አቅም ‹‹አለው የለውም›› የሚለውን ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡

ፕሪሚየር ሊጉ ከምሥረታው አሁን እስከሚገኝበት ድረስ ‹‹ፕሪሚየር ሊግ›› የሚለውን ስያሜ ይዞ ከመቀጠሉ ባለፈ በተሳታፊ ቁጥሩም ሆነ በውጤቱ መሠረት ሳይኖረው ዘልቋል፡፡ ፕሪሚየር ሊጉ ሲጀምር የተሳታፊዎቹ ቁጥር አንዴ ከፍ አንዴ ዝቅ ሲል ቆይቶ አሁን 16 ላይ ይገኛል፡፡ በአንድ ወቅት የዓለም አቀፍ እግር ኳስ አስተዳዳሪ (ፊፋ) ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሊጉን ቁጥር በሚመለከት በ12 እና በ14 መካከል ሊሆን እንደሚገባ ምክረ ሐሳብ የሰጠበትን አጋጣሚ የሚያስታውሱ አሉ፡፡

የተሳታፊ ቁጥሩን ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ 16 አድርጎ የቀጠለው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፣ ባለፈው ሰኞ የካቲት 16 ቀን 2012 ዓ.ም. የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስና በደረጃ ሰንጠረዡ ዘጠነኛ ላይ የሚገኘው አዳማ ከተማን በአዲስ አበባ ስታዲየም ባስተናገደበት ጨዋታ አንደኛው ዙር ጨዋታ መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ ቡድኖቹ ሁለተኛውን ዙር ጨዋታ ከመጀመራቸው በፊት የአንድ ሳምንት ዕረፍት ይኖራቸዋል፡፡

ሁሉም ቡድኖች በአንደኛው ዙር ጨዋታ ያላቸው ውጤት ተቀራራቢ መሆኑ ደግሞ ሁለተኛውን ዙር የበለጠ እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡ በ2010 ዓ.ም. እና በ2011 ዓ.ም. የውድድር ዓመት ከዋንጫ ውጪ ሆኖ የቆየው ቅዱስ ጊዮርጊስ የዘንድሮ አጀማመሩ የቀደመ ታሪኩን ለማስጠበቅ ለመሆኑ ከወዲሁ የሚናገሩ አሉ፡፡ ይሁንና በመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስና በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ካለው አኳያ ሲታይ በሁለተኛው ዙር ምን ሊከሰት እንደሚችል መገመት ያዳግታል፡፡

በመሆኑም መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ 28፣ ፋሲል ከተማ 26፣  መቐለ 70 እንደርታ 25፣ ሲዳማ ቡና 24፣ ባህር ዳር ከተማ 23፣ ሐዋሳ ከተማ 22፣ ወላይታ ድቻ 21፣ ስሁል ሽረ 21 በጎል ክፍያ ተበልጦ፣ አዳማ ከተማና ወልቂጤ ከተማ በጎል ክፍያ ተበላልጠው እኩል 19፣  ኢትዮጵያ ቡና፣ ሰበታ ከተማና ጅማ አባ ጅፋር በጎል ክፍያ ተበላልጠው እኩል 18፣ ለጊዜው ወራጅ ቀጣና ውስጥ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማ 17፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ 15 እና የመጨረሻው ሐድያ ሆሳዕና 13 ነጥብ ይዘው ይገኛሉ፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች ግንባታ በመከናወን ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁንና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በቅርቡ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት አገሪቱ አኅጉራዊም ይሁን ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ማስተናገድ የሚችል ስታዲየም እንደሌላት፣ ያሉትም የካፍን ዝቅተኛ መሥፈርት ‹‹የሚያሟሉ አይደሉም›› በሚል ማገዱ አይዘነጋም፡፡

በዋናነት የፕሪሚየር ሊጉን ጨዋታ ጨምሮ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ሲያስተናግዱ የቆዩት የአዲስ አበባ ስታዲየም፣ የመቐለና የባህር ዳር ስታዲየሞች ይጠቀሳሉ፡፡ ሆኖም ካፍ የባህር ዳርንና የመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየሞች መለስተኛ ጥገኛ እንዲያደርጉ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጦ ነበር፡፡ የመቐለው የተባለውን ቅድመ ሁኔታ ሊያሟላ ባለመቻሉ አሁን ላይ ኢንተርናሽናል ውድድሮች እንዳያደርግ ዕገዳ ሲጣልበት፣ የባህር ዳሩ ግን ቅድመ ሁኔታው እንደተጠበቀ ኢንተርናሽናል ውድድሮችን እንዲያስተናግድ መፍቀዱ ይታወሳል፡፡

የባህር ዳር ስታዲየም የሚገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ከሰሞኑ በሰጠው መግለጫ፣ ካፍ የጠየቀውን መሠረተ ልማት ማሟላቱን አስታውቋል፡፡ በመጪው ሚያዝያ ወር የካፍ ገምጋሚ ቡድን በባህር ዳር ተገኝተው የስታዲየሙ መሠረተ ልማት የሚገኝበትን በመመልከት ውሳኔ የሚሰጡ ስለመሆኑ ጭምር ስፖርት ኮሚሽኑ በመግለጫው አካቷል፡፡

መግለጫው በኮሚሽኑ የስፖርት ፋሲሊቲ ዳይሬክተር አቶ ባንተ አምላክ ሙላትን ጠቅሶ እንዳብራራው ከሆነ፣ ከ580 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የባህር ዳር ስታዲየም እንዲሟላ የተጠየቀው የተጨዋቾች፣ የአሠልጣኞች፣ የዳኞችና ኮሚሽነሮች መልበሻ ቤቶች፣ የስብሰባ አዳራሾች፣ የጋዜጠኞች መከታተያ ክፍሎችና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ ተጨዋቾች ሕክምና ምርመራ የሚያደርጉባቸው ክፍሎች፣ ሁለት የመለማመጃ ሜዳዎች፣ የተጨዋቾች ልብስ መቀየሪያ ክፍሎችም ይገኙበታል፡፡

ስታዲየሙ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ፖሊሶችን ጨምሮ በድምፅና በመብራት ጥሪ የሚሰሙና ምልክት የሚሳዩ መከላከያ መሣሪያዎችና 26 የደኅንነት ካሜራዎች ገጠማ የተጠናቀቀ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የማታ ጨዋታዎች ለማድረግ የሚያስችሉ የመብራት ፓውዛዎች ገጠማ በሚመለከት ግን ከስታዲየም ጣሪያና ወንበር ገጠማ ጋር ተያይዞ በቀጣይ ለሚሠራው ግንባታ አስቸጋሪ ስለሚሆን እንዳልተሟላ በመግለጫው ተካቷል፡፡

ከዚህ ባለፈ የፍሳሽ ማጠራቀሚያና ሴፍቲ ታንከር ውኃ በማያሰርግ ኬሚካል ማልበስ ከመቻሉም በላይ፣ ሁለቱንም ፆታዎች ያማከሉ 360 መፀዳጃ ቤቶች ግንባታም ተጠናቋል ተብሏል፡፡ በዚህ መሠረት የባህር ዳር ስታዲየም ካፍ እንዲያሟላ ከጠየቀው በላይ የማስተካካያ ግንባታ ያጠናቀቀ በመሆኑ ቅድመ ክልከላው እንደሚነሳለት ይጠበቃል፡፡              

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...