Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየደቡብ ሱዳን የአንድነት መንግሥት

የደቡብ ሱዳን የአንድነት መንግሥት

ቀን:

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ላለፉት ስድስት ዓመታት ታጣቂዎችን በመምራት ሲቃወሟቸው የነበሩት የቀድሞው የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር፣ የእርስ በርስ ውጊያው ዳግም እንዳይመለስ የሚያስችለውን የአንድነት መንግሥት መሥርተዋል፡፡

ላለፉት ስድስት ዓመታት በተቀናቃኞቹ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት 400‚000 ያህል ሱዳናውያን የሞቱ ሲሆን፣ ሦስት ሚሊዮን ያህል ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ የሱዳናውያንን በተለይ የሴቶችና ሕፃናትን ሕይወት ያመሰቃቀለውንና ደቡብ ሱዳን ከሱዳን እ.ኤ.አ. በ2011 ተነጥላ ራሷን ማስተዳደር ከጀመረች ሁለት ዓመታት እንኳን ሳይቆጠሩ የተቀሰቀሰው የርስ በርስ ጦርነት፣ ከዚህ በኋላ ሊያከትም እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

በደቡብ ሱዳን የተፈጠረውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ለመቀልበስ በኢትዮጵያ፣  በዩጋንዳና በሱዳን አደራዳሪነት ተደጋጋሚ ውይይቶች ሲደረጉ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡

በሁለቱ ተቀናቃኞች በኩል የተገቡ ከአምስት ያላነሱ የተኩስ አቁምና ሌሎች ስምምነቶች ቢፈርሱም፣ ማቻርን ምክትል ፕሬዚዳንት ለማድረግ የተደረሰው ስምምነት ዕውን ሆኗል፡፡ ይህም በደቡብ ሱዳን ለዓመታት የዘለቀውን የእርስ በርስ ጦርነት ከማስቀልበስ ባለፈም፣ ሰላማዊ ምርጫ ለማድረግ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡

ማቻር ባለፈው ቅዳሜ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ቃለ መኃላ የፈጸሙ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርም  እማኝ ሆነው ከፊት ለፊታቸው ተገኝተዋል፡፡ ማቻርን ምክትል ፕሬዚዳንት ለማድረግ የተደረሰው ስምምነት የተያዘለት ቀነ ቀጠሮ ከማለፉ በፊት ተግባራዊ የተደረገው ማቻርን ወደ ሥልጣን የማምጣት ዕርምጃም ለሱዳን ሰላምን የሰነቀ ነው፡፡ የተደረሱ ስምምነቶች ተግባራዊ ካልተደረጉ ጦር አልጥልም ብለው የነበሩት ማቻር፤ ቃለ መኃላውን ከፈጸሙ በኋላ ባደረጉት ንግግርም ‹‹የሱዳን ሕዝቦች የጉዳታችሁ ዘመን ያበቃ ዘንድ አብረን እንሠራለን›› ብለዋል፡፡

ከሳልቫ ኪር ጋር በመጨባበጥ አንድነታቸውን ያሳዩ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ኪርም፣ ‹‹እርስ በርስ ይቅር መባባል አለብን፤ የዲንካና የኑዌር ተወላጆችም እርስ በርሳችሁ  ይቅር ተባባሉ፤›› ብለዋል፡፡

ሦስት ተጨማሪ ምክትል ፕሬዚዳንቶች በዕለቱ ቃለ መኃላ የፈጸሙ ሲሆን፣ ከእነዚህ አንዷ የደቡብ ሱዳን መሥራች አባት የሚባሉትና እ.ኤ.አ. በ2005 በሂሊኮፕተር አደጋ የሞቱት የጆን ጋራንግ ባለቤት ሬቤካ ጋራንግ መሆናቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

መተግበር በጀመረው ስምምነት መሠረት፣ የነበረው ካቢኔ የሚፈርስ ሲሆን፣ ይህም በርካታ አዳዲስ ተፎካካሪዎች በካቢኔው እንዲካተቱ ያስችላል ተብሏል፡፡ ማቻር ምክትል ፕሬዚዳንት ቢሆኑም ምን ያህል ውሳኔ የማሳለፍ አቅም ይኖራቸዋል የሚለውና በሁለቱም ወገን ያሉ ወታደሮች የሚዋሃዱበትን በተመለከተ ደግሞ በቀጣይ እልባት የሚያገኙ አጀንዳዎች ይሆናሉ፡፡

ሁለቱ ተቀናቃኞች የአንድነት መንግሥቱን የመሠረቱት የተሰጠው ቀነ ገደብ ሊያበቃ ሲልና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለቱም ወገኖች ለሥልጣን ጥማቸው ብለው ዜጎቻቸውን እያስራቡ ይገኛሉ ብሎ መግለጫ ባወጣ በሰዓታት ልዩነት ውስጥ ነው፡፡

የደቡብ ሱዳን የአንድነት መንግሥት

 

የስምምነቱ ሚና

በስምምነቱ መሠረት ለሦስት ዓመታት የሚቆይ የሽግግር መንግሥት የሚኖር ሲሆን፣ ይህም በተመሠረተው የአንድነት መንግሥት የሚመራ ይሆናል፡፡ በቆይታ ዘመኑም በጦርነቱ ምክንያት አገራቸውን ለቀው የተሰደዱትንም ሆነ ከቀያቸው የተፈናቀሉትን ለመመለስ ዕድል ይሰጣል፡፡ ፕሬዚዳንት ኪር እንደሚሉትም፣ ለመግለጽ በሚከብድ ስቃይ ውስጥ የነበሩትንና የተራቡትን ለመካስ ያስችላል፡፡ የሰላም ስምምነቱ ፀንቶ ከቆየም አዲሲቷን ደቡብ ሱዳን ለመገንባት ዕድል ይሰጣል፡፡

ሊያጋጥሙ የሚችሉ ፈተናዎች

በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማስፈን የፕሬዚዳንት ኪርና የማቻር መስማማት ቅድሚያውን ቢይዝም፣ በአገሪቱ መስመር መያዝ ያለባቸው ነገር ግን ፈተና ሊሆኑ የሚችሉ ችግሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡ በኢንተርናሽናል ክሪያሲስ ግሩፕ ከፍተኛ የፖለቲካ ተንታኝ አለን ቦስዌል ለአልጀዚራ እንዳሉት፣ የተጠናከረ የደኅንነት አካል አለመኖሩ አንዱ ችግር ነው፡፡ ከዚህ በፊት የተደረጉ በርካታ ስምምነቶች የከሸፉትም በደቡብ ሱዳን የተጠናከረ የደኅንነት አካል ባለመኖሩ ነው፡፡

አዲስ በተደረሰው የሰላም ስምምነት 41‚500 ያህል በሁለቱም ወገን በኩል ያሉ ወታደሮችን ማዋሃድ ይገኝበታል፡፡ እነዚህን አጣምሮ አንድ የመከላከያ ሠራዊት መፍጠሩ ግን ከባድ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡

ለባለሥልጣናት ጥበቃ የሚያደርጉ የደኅንነት አካላት በፕሬዚዳንቱ እንደሚመደቡ በስምምነቱ ከተደረሱ አጀንዳዎች አንዱ ነው፡፡ የማቻር ቃል አቀባይ ‹‹ለደኅንነታችን የጽሑፍ ማስረጃ እንፈልጋለን›› የሚል ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጣቸው ደግሞ ሌላ እክል ሊሆን ይችላል፡፡

ሥጋት ተብለው የተቀመጡ አጀንዳዎች በጊዜ ሒደት የሚፈቱ እንደሆነ በማመን የኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ አገሮች መንግሥታት ስምምነቱን አድንቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...