Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህል‹‹የክብረ ዓድዋ›› ድግስ

‹‹የክብረ ዓድዋ›› ድግስ

ቀን:

በጋዜጣው ሪፖርተር

‹‹ዓድዋ የክብር ማምሻ

የጠብ የግፍ ማርከሻ

- Advertisement -

የቂም የቁጣ ማስታገሻ

የበደል የንዴት መርሻ

የመለያየት መድኃኒት፣ የመበታተን መፈወሻ

ዓድዋ የፍቅር ግርሻ

ድልሽ ይሁነን፣ ወደ ብርሃን መድረሻ

ታሪክሽ ፈዋሽ ይሁነን፣ አንድነታችን ማደሻ….››

ሲል በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ የከተበው፣ ባለ ግጥም መድበሉ አበባው መላኩ ነው፡፡

‹‹የክብረ ዓድዋ›› ድግስ

 

ከ124 ዓመታት በፊት ወራሪውን የጣሊያን ሠራዊት ለማስወገድ ከኢትዮጵያ ምድር ከዳር እስከ ዳር ቀፎው እንደተነካ ንብ፣ በዳግማዊ ምኒልክ ጠቅላይ አዝማችነት የዘመቱት ኢትዮጵያውያን ዓድዋ ላይ ድል የመቱበትን ሕያው ውርስ በግጥሙ የዘከረበት ነው፡፡

ከሰባት ዓመታት በፊት ጀምሮ ይህንኑ በጥቁሩ ዓለም አንፀባራቂ የሆነ ድል ለማክበር፣ ከአዲስ አበባ እስከ ዓድዋ የእግር ጉዞ ማድረግ የጀመሩት በነ ያሬድ ሹመቴ የሚመሩት ወጣቶች ዘንድሮም ጉዞውን ተያይዘውታል፡፡

ሰሞኑን የመቐለ እንዳየሱስ ታሪካዊ ምሽግ ያለፉ ሲሆን፣ ከአምስት ቀናት በኋላ ዓድዋ እንደሚደርሱ ይጠበቃል፡፡ የጉዞው አስተባባሪ ያሬድ ሹመቴ በገጹ እንደገለጸው፣ ከተጓዦቹ መካከል የፎቶግራፍ ባለሙያው ሚካኤል መታፈሪያ እንዳለበት ጠቅሶ በጉዞውና በበዓሉ ላይ ያነሳቸውን ፎቶዎችና አስደናቂ ምስሎች ስብስብ ዓውደ ርዕይ በአዲስ አበባ እንደሚዘጋጅ ገልጿል፡፡

የመኪና ተጓዦች

እንደወትሮው ሁሉ የዘንድሮውን የዓድዋ ጦርነት የድል በዓል ለማክበር ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተጓዦች የካቲት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ በተሽከርካሪዎች ጉዞ ጀምረዋል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያዘጋጀው የዓድዋ ጉዞ መነሻውን አዋሬ አካባቢ በሚገኘው ‹‹የዓድዋ ዘመቻ መታሰቢያ ድልድይ›› በማድረግ ረፋድ ላይ በተከናወነ ሥርዓት ነው ጉዞው የተጀመረው፡፡

የጉዞው ቡድን አንጎለላ፣ ወረኢሉ፣ ውጫሌ፣ አምባላጌ፣ ማይጨው፣ መቐለ እንዳየሱስና የተለየዩ ታሪካዊ ቦታዎችን እየጎበኘ መዳረሻውን ዓድዋ እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡

ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ተጓዦቹ የተውጣጡት ከየክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ነው፡፡

ክብረ ዓድዋ ፌስቲቫል

‹‹ዓድዋ የዘመናዊ ዓለም ጉልህ የታሪክ ዕጥፋት የሆነ የተዛባ ሀቲት ያቀና፣ የሰው ልጅ ክብር የተገለጠበት የሰውነት ማህተም ነው›› የሚለው ሰውኛ ፕሮዳክሽንና ኢንተርቴይመንት ነው፡፡

124ኛውን ዓመት የዓድዋ ጦርነት ድል ምክንያት በማድረግ ‹‹ክብረ ዓድዋ›› የሚል መጠሪያ ያለው የቴአትር፣ የፊልምና ቴሌቪዥን ፌስቲቫልን ከየካቲት 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ እያከበረ ነው፡፡

ሰውኛ በሰጠው መግለጫ እንዳሳወቀው፣ በሥነ ጥበብ መርህ መሠረት የዓድዋ ድልን ትዕምርታዊ ዋጋ የሚያጎላ ‹‹ዓድዋ የሰውነት ማህተም›› በሚል ዓምድ ላይ የቆመ ዓመታዊ ክብረ ዓድዋ ከየካቲት 16 እስከ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ተዘጋጅቷል፡፡

በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት (ወመዘክር) አዳራሽ መክፈቻውን የካቲት 16 ቀን አድርጎ ዓድዋ የፊልም እና ቴሌቪዥን ፌስቲቫል (ከየካቲት 17 እስከ 23 በወመዘክር)፣ የሊቃውንት ጉባዔ (የካቲት 20 አመሻሽ በወመዘክር)፣ ዋዜማ ቴአትር የካቲት 22 በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ከ11፡30 ጀምሮ)፣ ከዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ ወደ ዓድዋ ዘመቻ መታሰቢያ ድልድይ በባዶ እግር ጉዞና የጎዳና ላይ ትርዒት የካቲት 23 ከጠዋቱ 1፡30-5፡30)፣ እንዲሁም በዕለቱ በእንጦጦ ቤተ መንግሥት ከ7 ሰዓት ጀምሮ፣ ልዩ ልዩ መሰናዶዎችን ከአጋሮቹ ጋር በትብብር ያቀርባል፡፡

ከ124 ዓመታት በፊት፣ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ዓድዋ ላይ የጣሊያን ወራሪ ሠራዊት ድል መመታቱ ይታወሳል፡፡

ያሬድ ጌታቸው “ዓድዋ” በሚለው ግጥሙ እንዲህ አሠረ፡፡

“ዓድዋ ቅኔ ነው!

ሰንደቅ ባ´ሰረው ቃል፣ በአረንጓዴ ቢጫ፣ በቀይ ብዕር ተጽፎ

ባ´ንድነት ሕብረ-ቃል፣ ከመሐል እስከጥግ፣ በዘራፍ ተዘርፎ

ዘመንን ተሻግሮ፣ በ´ኛው በራስ ቋንቋ፣ ዛሬን ምንቀኘው

ሺዎች ለሚሊዮን፣ በከፈሉት ዋጋ፣ ነፃነት ወርሰን ነው፡፡

ዓድዋ ፈውስ ነው!

ያ´ዋቂ እጅ-ሥራ፣ ድንቅ ረቂቅ ጥበብ፣ ነጭን ያሰደመመ

ሸውራራ ዕይታን፣ ጥመትን የገራ፣ ብሌንን ያከመ፡፡

ዓድዋ ብርታት ነው!

ድንበር ያልገደበው፣ ለጥቁር ሕዝብ ሁሉ፣ ብርታትን ያደለ

ካ´ገር የገዘፈ፣ ኢትዮጵያዊ ዓርማ፣ አፍሪቃን ያከለ፤

ማሸነፍን ማልዶ፣ ጎስሞ ነጋሪት፣ ነፃነት ያወጀ

እንደ ጥላ ሁሉ፣ አትከተል ቢሉት፣ ከቶ ´ማይል በጀ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...