Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርአዲስ አበባ በርካታ ሥራና ትግል የምትሻ ከተማ ናት!

አዲስ አበባ በርካታ ሥራና ትግል የምትሻ ከተማ ናት!

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

ባለፈው ሳምንት የሪፖርተር የእሑድ ዕትም ላይ ከተማ የተባሉ ጸሐፊ ለአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ይድረስ ያሉትን ደብዳቤ አስነብበዋል፡፡ ይዘቱም በከተማዋ እየታየ ያለውን ለውጥ ጠቅሶ ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን ከመሬትና ከመሬት አስተዳደር ጋር በተያያዘ የሚታየውን ሙስናና ወረራ፣ በየመሥሪያ ቤቱ እየተቀጠሩ፣ እየተመደቡና እየተሾሙ ስላሉ ሰዎች በስፋት በማንሳት ከንቲባ ታከለ ኡማ የተጣለባቸውን ታሪካዊ አደራ ተጠንቅቀውና በጥብቅ እንዲመሩ የሚያሳስብ ነው፡፡ ከእዚህ ሂስ ጀርባ በጎሳ ፌዴራሊዝሙ ጠገግ እየተመነዘረ አንዱ ብሔር ያላግባብ ተጠቀመ፣ ሌሎችም እየተገፉ ነው፣ በተለይ ከምደባና አሿሿም ጋር በተያያዘ የመድልኦ አሠራር አለ የሚሉ ሐሳቦች ተነስተዋል፡፡

ጽሑፉን ካነበብኩ በኋላ በግሌ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአሁኑ ከንቲባ ታከለ ኡማ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን፣ ከተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በመዳሰስና በራሴ ምልከታ ጠቃቅሼ በበጎ በማንሳት በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ አስቀምጬ ነበር፡፡ ‹‹ካገዝነው ከንቲባ ታከለ ኡማ ተስፋ የተጣለበት መሪ ነው!›› በሚል ርዕስ፡፡

- Advertisement -

በአዲስ አበባ ታሪክ ራሱን ወደ ሕዝብ ያቀረበ ልበ ሙሉ ከንቲባ ሊባል የሚችለው የአሁኑ ታከለ ኡማ ይመስለኛል፡፡ ይህን ስል በአድርባይነት ወይም ሌላ ጥቅም ከመፈለግ ሳይሆን፣ ሀቅ ላይ በመመሥረት ለመናገር ብቻ ነው፡፡  በአሁኑ ወቅት አንድ ለአገር ከሚቆረቆር ዜጋ ያለፈ ሚናም፣ ፍላጎትም የለኝም፡፡ ግን የእዚህ ሰው በጎ ጅምሮች ይበረታቱ ዘንድ መነገር ስላለበት እናገራለሁ በማለት ነበር የተንደረደርኩት፡፡ እርግጥ የአስተዳደሩ ድክመት ላይ ያላተኮረ ጽሑፍ በመሆኑ እንጂ ሊነሱ የሚገባቸው እጥረቶችም ቀላል እንዳልሆኑ እገነዘባለሁ፡፡

  1. በአዲስ አበባ ለሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ሥራ መጀመር፣ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች የደንብ ልብስ፣ የጽሕፈት መሣሪያ ድጋፍና የምገባ ሥራው የሚያኮራ ተግባር ነው፡፡ ስለምግብ ዋስትና በአገር ደረጃም ሆነ በመዲናው በአፍ እየተለፈፈና እየተራባ የሚውል፣ የሚያድር በበዛበት ከተማ ይህን አለማድነቅ አዳጋች ነው፡፡ ለዘላቂነቱም ሥራውን የሚመራ ኤጀንሲ እየተቋቋመ ነው መባሉ የተግባሩን ዘላቂ አካሄድ የሚያሳይ ነው፡፡
  2. በከተማዋ መስፋፋት ምክንያት ያለበቂ ካሳ የተፈናቀሉ የዙሪያዋ ነዋሪ ዜጎችን ምትክ መሬትና የጋራ ኮንዶሚኒየም ቤቶች እንዲሰጡዋቸው አድርጓል፡፡ በማንነቱ ብቻ ከእየ አቅጣጫው መጥቶ መሬት ልቀራመት ያለውንም ሕገወጥ አዝማሚ ቢያንስ በለሆሳስ አስቁሟል፡፡ ይህን የሚቃወሙ አንዳንድ ወገኖች ባለማወቅም ቢሆን ኢፍትሐዊነትን የሚጋሩና ለውጡ ያልገባቸው ብቻ ናቸው፡፡
  3. በመዲናዋ ለዓመታት ተዳፍነው የቆዩ የማኅበርና የግል ቤቶች የካርታ ውሳኔ (በተለይ ቦሌ፣ ኮልፌና የካ) እንዲሰጡ አድርጓል፡፡ ከሁሉ በላይ የቀድሞው አስተዳደር ‹‹ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ ወዲህ ለተገነቡ ቤቶች ካርታ አይሰጥም፣ ይፈርሳሉ›› እያለ ነዋሪዎችን ሲያሳቅቅ ቢቆይም፣ እሱ ግን በውስን ሀብት ቤት ሠርተው ለዓመታት የኖሩ ዜጎች ዕልባት እንዲያገኙ እየሠራ ነው፡፡ በቅርቡ እንኳን የታሰበውን የማፍረስ ዕቅድ አስቁሞ፣ የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴዎችን ጠርቶ ደንብና መመርያዎች ጭምር እንዲፈተሹ እያደረገ ነው፡፡
  4. አንዳንድ የኦዴፓና የአዴፓ አመራሮች “ኦሮማራ”ን (ይህ ስብስብ ሁሉንም ሕዝቦች ማካተት እንዳለበት ግልጽ ሆኖ) ለመበጠስና በሴራ ፖለቲካ ለመሰለብ ሲዳዳቸው፣ አቶ ታከለ ግን ‹‹የኦሮሞ ደም የእኛም ደም ነው›› ያሉ የጎንደር ወጣቶችን (በኢሬቻ በዓል ላይ ሳይቀር) አስታውሶ ያጋመደ፣ የአዲስ አበባን የመላው ኢትዮጵያዊነት የጋራ ቤትነት አምኖና በድፍረት ተናግሮ  በተግባር እየሠራ ያለ ነው (ይኼ ጉዳይ እንደ ዳቦ ከላይና ከታች እሳት ያለበት መሆኑን ልብ ይሏል!)፡፡
  5. በጥቂት ዘራፊዎችና ሞኖፖሊስቶች ቅርምት ተይዘውና ለዓመታት ታጥረው የኖሩ ሰፋፊና ውድ የመሬት ይዞታዎችን ነጥቆ፣ ለጊዜው ለተደራጁ ወጣቶች የዕለት ገቢ ማግኛ፣ በዘላቂነትም ለግዙፍ የመኖሪያ መንደሮች፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶችና የዓድዋ ሙዚየምና ሁለ ገብ ፓርክ ልማት እንዲውል ያደረገ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ፕሮጀክት የሚባለው የከተማ ማዋብና የወንዝ ዳር ፕሮጀክቶችም ትውልድ የሚኮራባቸው መሆናቸው አይቀርም፡፡
  6. እንደ ቀደሙት ከንቲባዎች እየተኮፈሰ በሩን ሳይዘጋ፣ ዘላቂነት ባይታይበትም ባለጉዳይን እያዳመጠ፣ ታች ድረስ ወርዶ ችግር ለመፍታት እየሞከረ፣ በተለይም የተደራጁና በጥቃቅን የተሰማሩ ወጣቶች በነበረው ብልሹ ቢሮክራሲ እንዳይገፉ በዓይነ ቁራኛ እየጠበቀ መሆኑን የሚገልጹ ጥቂት አይደሉም (የቃሊቲ፣ የንፋስ ስልክ ላፍቶና የየካን ችግሮች የፈታበት መንገድ ይጠቀሳል)፡፡ አንዳንዶች ለታይታና የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ነው ቢሉትም፣ በአቅመ ደካሞችና ደሃዎች ቤት እየተገኘ ማፅናናቱና ማገዙም ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
  7. የታከለ ካቢኔ ከዚህ ቀደም ለዓመታት በጋራ መኖሪያ ቤቶች በኪራይ ይኖሩ የነበሩና አገራቸውን በተለያዩ መስኮች ያገለገሉ ዜጎችን፣ ሌላ ቤት እንደ ሌላቸው እያጣራ ዕዳውን ከፍለው እንደ ዜጋ እንዲወስዱ፣ በዚያውም አስተዳደሩ ያላግባብ የባንክ ወለድ ከመገፍገፍ እንዲድንም አድርጓል፡፡ እዚሁ ላይ ለድሆች፣ ለአንጋፋ አርቲስቶች፣ መነቃቃት ላለባቸው ዜጎች ብሔር ሳይለይ ቤት ሰጥቷል፣ አስተባብሮ ቤታቸውን አድሷል፡፡ የሚገፋበትም ይመስለኛል (እዚህ ላይ በ13ኛው ዙር በተለይ በኮየ ፈጬ የጋራ መኖሪያ ኮንዶሚኒየም ወጥቶላቸው የታገዱቱንም መፍትሔ መስጠት አለበት)፡፡
  8. ከሰሞኑ እንዳየነው ደግሞ በሴራም ይባል፣ በቤተ እምነት ስም የሕዝብ መሬት ለመውረር በተካሄደ ሙከራና ሕግ ለማስከበር በተወሰደ ዕርምጃ፣ ያለፈው የንፁኃን ሕይወት ከንቲባውን አስደንግጦ በትኩሱ ሐዘን ቤት ድረስ የወሰደው ነው፡፡ በቀጣይ ችግሩ እንዳይደገምና የንፁኃን ሕይወት እንዳይቀጠፍ የወሰደው ዕርምጃም የሚያስመሠግን ነው፡፡
  9. መዲናዋ ከእነ ዋሽንግተን ዲሲ ጋር ሳይቀር እህትማማችነት መሥርታ፣ አደባባይ  እስከማቆም ከማድረሷ ባሻገር በስኮላርሺፕ፣ በቴክኖሎጂና በፋይናንስ እያገኘች ያለው ድጋፍም የእሱ ጥረት እንዳለበት ጥርጥር የለውም፡፡ እንግዲህ አሥርና አሥራ አንድ እያልን ብንቀጥል ብዙ እናነሳለን፡፡ ነገር ግን ቀሪ ሥራዎችንም (የዴሞክራሲ ምኅዳር ማስፋት፣ ሥራ መፍጠር፣ ገበያ ማረጋጋት፣ ዘረፋን መቋቋም፣ ሰላምና ደኅንነትን ማረጋገጥ፣ ሕገወጥነትን መታገል. . .) በስፋትና በሞራል አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ የሸዋ ምድር ያበቀለው ከንቲባ ታከለን “በርታ!” ማለት መርጠናል የሚል ነው፡፡

በዚህ ጽሑፍ ላይ በርከት ያሉ አስተያየቶች የተሰነዘሩ ሲሆን፣ አብዛኛው በነቀፌታና ከንቲባውም ሆነ የከተማ አስተዳደሩ ባላከወኗቸውና ተከውነውም ፍትሐዊ ባልሆኑት ተግባራት ላይ ያተኮሩ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ በዚህ መነሻም ለአንድ ከተማ አስተዳደር መሳለጥና የሕዝብን ተዓማኒነት ያገኘ መሆን ከንቲባው ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ መዋቅሩ፣ ፌዴራል መንግሥና ሕዝቡም ሚና ያላቸው እንደ መሆኑ ዓለም አቀፍ የከተማ አስተዳደር ተሞክሮና ፈተናዎችን በተለይም ከአዲስ አበባ አንፃር ለመመልከት ተገድጃለሁ፡፡

በእርግጥ በየትም አገር ቢሆን የከተሞች ሥራ አመራርና አስተዳደር፣ እጅግ በጣም አስቸጋሪና ውስብስብ ከሆኑ መንግሥታዊ ሥራዎች መካከል ዋንኛው ነው፡፡ ከተሞች በከተማ አስተዳደሮች ወይም ማዘጋጃ ቤቶች አማካይነት መተዳደር ከጀመሩ ረጅም ጥንታዊ፣ ታሪካዊ፣ ልምድና የተግባር ተሞክሮ ያላቸው ቢሆኑም፣ እነሆ እስከ ዛሬ ድረስም ቢሆን የተሳለጠ የሥራ አመራርና መልካም አስተዳደር ኖሯቸው  የሚያውቁት ጥቂት የበለፀጉ አገሮች መዲናዎች ናቸው፡፡ አመራር አይዋጣላቸውም፣ ደህና ሰው አይበረክትላቸውም በመባል የሚወቀሱ አብዛኛዎች መዋቅሮች ከተሞች ናቸው፡፡

ራሳቸው ከተሞቹም  አስቸጋሪዎች ናቸው፡፡ በመሠረቱ እንኳንም በበርካታ ችግር የተተበተቡ የአፍሪካ መዲናዎች ይቅሩና የትም ቢሆን፣ ፍርጃ ካልሆነበት በስተቀር ከተሞችን ማስተዳደር የሚፈልግ ሰው የለም፡፡ ከዚህ አንፃር እንዲያው ለመሆኑ ከተሞች ምንድናቸው? አፈጣጠራቸውስ እንዴት ነው? ሥራቸውስ ምንድነው? ብሎ መፈተሽ ተገቢ ይሆናል፡፡ ማየቱ የሚጠቅመን የአስተዳደር ሥርዓታቸውን ከአመራራቸው፣ ከሠራተኞቻቸውና ከተቋሞቻቸው አኳያ እያየን ችግሮቻቸውን ተረድተን የመፍትሔ ሐሳቦችን ለመሰንዘር ነው፡፡

ይህንን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደረጃ በተለይም በአገሪቱ ከተፈጠረው ለውጥ አንፃር ስንመለከተው ደግሞ፣ ‹‹ከተሞች በተለወጠ አመራር፣ በተለወጠ ሠራተኛ፣ በተለወጠ ተቋም››  እንዲቃኙ ማድረግ ካልተቻለ አደጋው መክፋቱ አይቀርም፡፡ የማሻሻያ ዕርምጃው ዓላማ  ደግሞ  ሰው መለዋወጥ ብቻ ሳይሆን፣  አመራሮችና ሠራተኞቻቸው አገሪቱ የምታራምደውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድና ሌሎች ሕዝባዊ መነሳሳቶችን መሸከምና መምራት በሚችሉበት አኳኋን መደራጀት ይኖርባቸዋል፡፡ በመሆኑም ከንቲባውና ካቢኔው በተለወጠ አመራር ለለውጥ የሚሠራ ሠራተኛና የተለወጠ ተቋም እንዲኖራቸው ማድረግ ላይ ማተኮራቸው ግድ የሚል ይሆናል፡፡

የታከለ ኡማ አዲስ አባባ ግን ቀደም ሲል ከነበረው የድሪባ ኩማ ካቢኔና መዋቅር በተለያዩ መንገዶች የተቀየረ ቢሆንም፣ ከእዚያኛው ሥርዓት የተሸከመው ቢሮክራሲና አሠራር አሁንም ሚዛን የሚደፋ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ ስለሆነም በአሁኑ ወቅት የፈዘዘ ልግመኛና ሙሰኛ አሠራርና ሠራተኛ መበራከቱ ብቻ ሳይሆን፣ አዲስ እየተሰገሰገና እየተሾመ ያለውም ቢሆን፣ በእዚያው የተዛባ አመለካከትና ተግባር እንዳይሰለብ የማድረግ ጉዳይ ወሳኝ ዕርምጃ ሆኖ ይገኛል እዚህ ላይ ከምርጫ በኋላ የመዲናዋ አስተዳደር ሌላ መልክ ይኑረውም ወይም ይኼው ይቀጥል ሥርዓት ማበጀቱ ግን ለአገር የሚጠቅም ይሆናል፡፡

በመሠረቱ አዲስ አበባም ሆነች ሌሎች የፌዴራል የከተማ አስተዳደሮች በራሳቸው የሕግ ዕውቅና በሰጣቸው የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ የአመራር፣ የሠራተኛና የተቋም ብቃት እንዲኖራቸው መደረግ ይኖርበታል፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ ከተሞች ለመኖሪያ የሚሆን ቤት፣ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ የደረቅና የፈሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ፣ ኤሌክትሪክንና ቴሌኮም ስለሚያስፈልጋቸው ብቻ አይደለም፡፡ ወይም መዝናኛና  መናፈሻን የመሰሉት እንዲኖራቸው ማድረግ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ በሌሎች የሥራ ዘርፎች ለሚሠሩ ሙያተኞች፣ ለብረትና ለእንጨት ሠራተኞች፣ ለዕደ ጥበብ ሠራተኞች፣ ለተማሪዎችና ለሠልጣኞች፣ ለባለቅኔዎች፣ ለፈላስፎችና ለመምህራን፣ ለዕቅድ አውጭዎች፣ ለጸሐፊዎች፣ ወዘተ. የሚሆን ከገበሬው ቀለብነት የተረፈ የእርሻ ምርት አቅርቦትና ማጓጓዣ ስለሚያስፈልግም ነው፡፡

አንድ ከተማ በየትኛውም የታሪክና መልከዓ ምድር ቢቆረቆር የቅንጦቱ ፍላጎት እንኳን ቢቀር፣ የአቅርቦት ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ለእዚህ የመጀመርያ ነገር አመቺ ምኅዳር ነው፡፡ ሁለተኛው አስፈላጊ ጉዳይ ደግሞ የተራቀቀ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ቴክኖሎጂ ሲራቀቅ የእርሻ መሣሪያዎች ይሻሻላሉ፡፡ ኢንዱስትሪ ይበለፅጋል፡፡ ብዙ ምርት ይገኛል፡፡ የተረፈውን ምርት የማከማቻ ቴክኖሎጂ ለበርካታ ዓመታት እህልን ለማቆየት ያስችላል፡፡ ታላላቅ የመስኖ ቴክኖሎጂ መስፋፋት፣ የውኃ ማውጫ የጎማ መዘውር፣ የብረት ማቅለጥ ሥራ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ማሻሻል፣ የንግድ ሥራ በከተማና በገጠር መካከል እንዲሠራጭ ማድረግ ማስቻልን ያስከትላል፡፡ ይህም ለከተማ ሕይወት ምሰሶ ይሆናል፡፡

ለከተሞች መኖር ሦስተኛው አስፈላጊ ነገር የዳበረ ማኅበራዊ አደረጃጀት ነው፡፡ ይህ በተለይ የሚመለከተው የፖለቲካውን አደረጃጀት ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ምርቶች ከከተማ ወደ ገጠር መሄድ አለባቸው፡፡ ከገጠርም ምርቶች ወደ ከተማ መምጣት አለባቸው፡፡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባራት ተቀናጅተው መሄድ አለባቸው፡፡ ገበያ መቆምና መድራት አለበት፡፡ በሰላም መገበያየት መቻል አለበት፡፡ አሁን እንደምናየው የከተማን ገጽታ የሚበላሽ በየዋና መንገድ ላይ ሳይቀር አስቀያሚ ሸራ ማንጠልጠል ሳይሆን፣ የገበያ ቦታ መከለል አለበት፡፡ እነዚህ ተግባራት ደግሞ ከተማን እመራለሁ ብሎ የሚያስብ ፖለቲከኛን ሁሉ የሚመለከቱ ናቸው፡፡

እነዚህ እውነታዎች ሳይሸራረፉ ዕውን ለማድረግ፣ የሰላምና የፀጥታ ኃይል በየደረጃውና በተሟላ ሥነ ምግባር መኖር አለበት፡፡  የፅዳትና የጤና አጠባበቅ ሥራ የሚሠሩ ሠራተኞች ያስፈልጋሉ፡፡ ለእዚህ ደግሞ ከተሞች ገንዘብ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የከተሞች ዋነኛ ገቢ ደግሞ ግብር መሰብሰብ፣ መሬትን የመሰሉ ውስን ሀብቶች በአግባቡና በፍትሐዊነት ለጋራ ጥቅምም ለማዋል መትጋት ግድ ይላል፡፡ ይህን ግብርና የሕዝብ ሀብት ለመሰብሰብና ለተሻለ ልማት ለማዋልም፣ ከተማዋን ለመምራት የተደራጀ የፖለቲካ መዋቅርና ጠንካራ የከተማ አስተዳደር ያስፈልጋል፡፡ ከተሞችና የከተማ አስተዳደሮች ተገናኙ ማለት ይኼኔ ነው፡፡ በመሠረቱ አዲስ አበባን ጨምሮ የዓለማችን ዋና ዋና ከተሞች፣ ሕዝብ ተቀራርቦና ተጠጋግቶ የሚኖርባቸው ሰፊና ውስብስብ የሰው ዓይነት የሚገናኝባቸው፡፡ ከሰባ እስከ ዘጠና፣ ከእዚያም በላይ  በመቶ ያህል እርሻ (ግብርና) ነክ ባልሆኑ ሥራዎች የሚተዳደሩባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ ግንዛቤና ሥልጣኔውም በዚያው ልክ ከፍ ያለ ነው፡፡

በሕግ የታወቀ የራሳቸው መልከዓ ምድራዊ ክልል (ወሰን) ያላቸው. . . የሕግ ማውጣት፣ የግብርና ታክስ የመሰብሰብ ሥልጣን የተሰጣቸው በሕግ መሠረት የተቋቋሙ፣ የተመረጡ፣ ወይም የተሾሙ አለቆች ያሏቸው ግዛቶች ናቸው፡፡ እዚህ ላይ አዲስ አበባ ያልተፈታ የወሰንና የክልል ጥያቄ የወደቀባት ከተማ እንደ መሆኗ ፈጣን መፍትሔ ሊሰጥ ይገባል፡፡ ከተሞች ለነዋሪዎች ፍጆታ የሚውሉ ምርትና አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ የኢኮኖሚ አካሎች ናቸው፡፡ የፖሊስ፣ የእሳት አደጋ፣ የውኃና ፍሳሽ፣ የመናፈሻ፣ የመዝናኛ፣ ፅዳትና ውበት፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የመሬት አስተዳደርና ይዞታ ልማት፣ የኢንዱስትሪ፣ የገበያና የመኖሪያ ሥፍራዎችን የመወሰንና የመከለል፣ የሥልጠናና የበጎ አድራጎት፣ ወዘተ. አገልግሎቶችን ያቀርባሉ፡፡

ይኼ ሰፊ ተግባር ደግሞ የሚጠይቀው የግልጽነትና የተጠያቂነት ሥርዓት አገር ከመምራትም ባልተናነሰ ጥንቃቄ የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡ ከተሞች የሕዝቦች መስተጋብር ማጠናከርያ አራማጆች ናቸው፡፡ የሰዎች፣ የቁሳቁሶች፣ የምርቶች፣ የሐሳቦች መሰባሰቢያ ማዕከላት ናቸው፡፡ ብዙ አማራጮች ያሉባቸው ሥፍራዎች ናቸው፡፡ ሁሉንም ነገር ምግቡንም፣ መጠጡንም፣ ሸመታውንም፣ ቴአትር፣ ሙዚቃ፣ ወዘተ. በቅርብ አካባቢ ለማግኘት የሚያስችል ዕድል የሚሰጡ፣ የመጓጓዣ ወጪንና ጊዜን የሚቀንሱ አካባቢዎች ናቸው፡፡ ለዚህም ዘርና ቀለም ወይም የኑሮ ደረጃና መደብ ሳይለያዩ በፍትሐዊነት መትጋትን ግድ ይላሉ፡፡

ከተሞች የዕውቀት ምንጭ ማዕከላት ናቸው፡፡ ለዕውቀት ጠቀሜታ ቅድሚያ የሚሰጥባቸው ሥፍራዎች ናቸው፡፡ ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሙዚቃዎች፣ አብያተ መጻሕፍት፣ ቤተ እምነቶች፣ ቁሳዊ ያልሆነው የሰዎች ፍላጎት ጥበብ የሚስተናገድበት የሚደራጅባቸው ሥፍራዎች ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ምሁራንን የሚያሳትፍ የምርምርና የፈጠራ ብሎም የነቃ ተሳትፎ ሥርዓትን መገንባት ግድ ይላቸዋል፡፡

ከተሞች የሥልጣኔ መነሻ ምንጭ የሆኑ ሥፍራዎች ናቸው፡፡ የሰው ዘር የባህል ላባራቶሪዎች ናቸው፡፡ የአዳዲስ ሐሳቦች መፍለቂያ፣ የዳበሩ ግኝቶች መታወቂያ፣ የምርምር ውጤቶች መበልፀጊያዎች፣ የዕድገት ሐሳቦች መነሻዎችና ማራመጃዎች፣ የለውጥና የዕድገት የዘላቂ ውጤት ማረጋገጫ ሥፍራዎች፣ የቋንቋ፣ የብሔር ብሔረሰቦች ማንነት ሳይለይ መኖሪያዎች ናቸው፡፡

የከተሞች መንግሥታዊ የአገልግሎት መስጫ፣ የመንግሥት መቀመጫ፣ የመንግሥት ሥራ ማካሄጃ፣ የታላላቅ ኩነቶች ማከናወኛ፣ የአኅጉርና የዓለም አቀፋዊ ክንዋኔዎች ማራመጃ ሥፍራዎች ናቸው፡፡ ለዓለም አቀፍ ሚዲያ የተጋለጡ (በተለይ በዋና ከተማነት ያሉት) ሥፍራዎች ናቸው፡፡ የንግድ፣ የማምረቻ፣ የኢንዱስትሪ፣ የአየርና የምድር ትራንስፖርት ኔትወርክ መገናኛ ናቸው፡፡ ከተሞች የመንግሥት ጉዳዮች አስፈጻሚ አካላት ናቸው፡፡ ማዕከላዊ መንግሥት ሕዝቡን የሚያገኘው በከተማ አስተዳደሮች በኩል ነው፡፡

ከዚህ አንፃር የከተሞች አስተዳደር ድክመቶች በቀጥታ ሕዝቡን ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር የሚያላትሙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በግብር አተማመንና የአፈጻጸም ዳተኝነት ወይም በመሬት አስተዳደርና ኮንስትራክሽን መስኮች የሚታዩ ዝንፈቶች፣ ከተሞች የሚያሳዩት ድክመትና የብቃት ማነስ የሕዝቡን ቁጣ በማዕከላዊው መንግሥት ላይ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር አዲስ አበባን ጨምሮ ዋና ዋና ከተሞች ብዙ መልካም ነገሮች ያሏቸውን ያህል  ህፀፆችም አሏቸው፡፡ ከተሞች የጥቅም ሥፍራዎች፣  የክህደት፣ የወንጀል፣ የማኅበራዊ ችግር ማስፋፊያዎች መሆናቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡

በመዲናችን በግልጽ እንደምናስተውለው ማታ ብቻ ሳይሆን በቀን የሚዘርፉ፣ ሰው ገድለው የሚጠፉ ማጅራት መቺ ነጣቂዎች፣ ዝሙት አዳሪዎች፣ የመጠጥ ቤቶች የተበራከቱባቸው ሥፍራዎች ናቸው፡፡ የስርቆቱና የፎርጅዱ ሥራ በየጊዜው ዘዴውን እያቀያየረ የሚያድግባቸው ሥፍራዎች ናቸው፡፡ ከተሞች የብልሹ አስተዳደር የሚበዛባቸው፣ ደመወዝ የሚከፈላቸው ሠራተኞች ሳይቀሩ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በሙስና የተዘፈቁባቸው ሥፍራዎችም ናቸው፡፡ እነዚህን ሁሉ ፈተናዎች በሥርዓት ደረጃ ማረም እንጂ፣ አንድ ከንቲባ ላይ ወይም የተወሰነ አመራር ላይ መጣል ልክ አይደለም፡፡

እነዚህን መጥፎ ድርጊቶች ተቆጣጥሮ ከተሞችን ሰላማዊ የመኖሪያ ቦታዎች ለማድረግና ለአጠቃላይ ለአገሪቱ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የበኩላቸውን ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ፣ ሕዝቡና የፌዴራል መንግሥትም ድርሻቸው የጎላ ነው፡፡ የከተማ አስተዳደሮች ኃላፊነት አሁን ባለው ሁኔታ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ ዛሬ እየተሠራ ያለው ነገ የሚያስከትለውን ጉዳትና የሚያመጣውን መዘዝ ከወዲሁ እያዩ የማከናወን ግዴታ አለባቸው፡፡ ለዚህም ሁሉንም ነገር በጥንቃቄ እንዲሠሩ ይገደዳሉ፡፡

ዛሬ የሚዘረጋው የባቡር ሃዲድ ወይም አውራ መንገድ በጥናት ሳይከናወን ቀርቶ ከሁለትና ከአምስት በኋላ ‹‹ይፍረስ›› የሚባል መሆን የለበትም፡፡ እዚህ ላይ የአዲስ አበባ አመራር የሆነ የዘርፉ አካል ሁሉ የተጣለበት ኃላፊነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

ዛሬ ለመልሶ ማልማት ለሚነሱ ነዋሪዎች የሚሠራው ኮንዶሚኒየም ከዓመት በኋላ ወደ ሌላ ቦታ ሊዛወር ነው ‹‹ይፈርሳል›› መባል የለበትም፡፡ ቤቱ ለራሱ ዘላቂ እንዲሆን ተደርጎ በጥንካሬ መሠራት ይኖርበታል፡፡ ቦታውም በጥንቃቄ የተጠናና የተመረጠ ሊሆን ይገባል፡፡ የአንድ አካባቢ ነዋሪዎች ወደ ሌላ አካባቢ እንዲዛወሩ ሲደረግ፣ ቀደም ሲል እዚያ ቦታ ከነበሩ ነዋሪዎች ጋር የማይስማሙ ወይም በበፊቱ ነዋሪዎች ጊዜ ያልነበሩ ብዙ ጎጂ ተሞክሮዎችን ይዘው ይመጣሉ፡፡ ማኅበረሰቡ በመጥፎ ነገሮች የሚበከልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ በአዲስ አበባ ሁኔታ ደግሞ የዴሞግራፊ ፖለቲካም የወደቀበት አጀንዳ እንደ መሆኑ፣ ለዚህ ሁሉ ዘዴ እየተፈለገ በማስተዋልና በመደማመጥ መመራት አለበት፡፡

በመሠረቱ የከተማ አስተዳደሮች ትኩረት ይኼ ብቻም አይደለም፡፡ የከተማው ቴክኖሎጂ፣ የነዋሪው ሕዝብ ዕውቀትና የሕዝብ ብዛት፣ በየጊዜው እያደገ ስለሚሄድ ይህን ያገናዘበ አቅም በሰው ኃይልም በአመራርም፣ በተቋምም እያዘጋጁ ከከተማው ዕድገት ጋር የሚመጣጠን አስተዳደራዊ ሥርዓት ዘርግተው መገኘት አለባቸው፡፡ በአዲስ አበባ ደረጃ ስንመለከት የክልል ከተሞች በሥራ ፈጠራና አቃፊነት ያልዳበሩ በመሆናቸው በየጊዜው ከገጠር እየመጣ በከተማ የሚኖረው ሕዝብ ቁጥር ቀላል አይሆንም፡፡ ይህን ሕዝብ የማስተናገድ ችሎታ ያስፈልጋል፡፡ ማንነታቸውን ማወቅ፣ መኖሪያ ቤት መስጠት፣ የገበያ ቦታ ማስፋት፣ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የመሠረታዊ አገልግሎት መስጫዎችንና የንግድ ሥርዓቶችን ማስፋፋትና ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡

 ከዚህ አንፃር አሁን ባለው ሁኔታ ብቻ ተወስኖ መቀመጥ ላያዋጣ ይችላል፡፡ ከአዲስ አበባ አንፃር ነገሩን ስናይ ከተማዋ ወደ ሜትሮፖሊታን ደረጃ እያደገች መሆኗን ማጤን ይገባል፡፡ በመሆኑም ሥራዎች ሁሉ በአንድ ማዘጋጃ ቤት አቅም ሊከናወኑ አይችሉም፡፡ በዋና ማዘጋጃ ቤት ሥር በርካታ ንዑሳን ማዘጋጃ ቤቶች የሚኖሩበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ለአገልግሎት አሰጣጥና ለስኬል ኢኮኖሚ (አገልግሎትን ለበርካታ ሰዎች በመስጠት የእያንዳንዱን አገልግሎት ነጠላ ዋጋ በመቀነስ የሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን) ለማረጋገጥ፣ ሕዝቡን አራርቆ ከማስቀመጥ ይልቅ የበለጠ ማቀራረብ የሚያስፈልግበት ሁኔታ ይመጣል፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት እንደተሰማው ሁለት ሦስት ክፍለ ከተሞችን በአንድ ማዘጋጃ ቤት ሥር ማድረግና ከሃያ በላይ ቀበሌዎችን በአንድ ክፍለ ከተማ ሥር ማጠቃለል፣ የቢሮክራሲውን ደረጃ በማሳጠር ሊጠቅም ይችላል፡፡ በእርግጥ እንዲህ ማድረጉ የራሱ ችግሮችም አሉት፡፡ ቢሆንም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሊጠቅም ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ከተሞች ለውጡን ማስተናገድ በሚችሉበት ሁኔታ የሚደራጁበትን አሠራር ከወዲሁ እየፈተሹ መንቀሳቀስ ማስፈለጉን ከግንዛቤ ማስገባት ነው፡፡

በየጊዜው እየናገረ ለሚመጣው የሕዝብ ቁጥር የሚሆን መኖሪያ (መጠለያ) ከማዘጋጀት ባሻገር፣ የቁሳቁስና የአገልግሎት አቅርቦትን በተቀላጠፈ ሁኔታ አንቀሳቅሶ ለማቅረብ ለኢንዱስትሪ ዞን የሚሆኑ ቦታዎችን የመከለልና የማስተዳደር፣ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በተቀናጀ ሁኔታ ማስተባበር፣ የውኃና ፍሳሽ መስመሮችን በዘላቂነት መሥራት፣ የደረቅ ቆሻሻ የማንሳት ብቃትን ማሳደግ፣ የመዝናኛ ሥፍራዎችን ማመቻቸት፣ ከ50 በመቶ ያህል የሚሆነውንና ከድህነት ወለል በታች የሚኖረውን ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል፣ የአስተዳደሩን ሠራተኞች አቅም ለመገንባት ተወዳዳሪና ብቃት ያላቸው እንዲሆኑ በማድረግ አስተዳደሩ አቅሙንና ኃይሉን ለማጎልበት ብዙ መሥራት የሚጠበቅበት ቢሆንም፣ ማዕከላዊው መንግሥትም ከፍተኛና ያልተቋረጠ ዕገዛና ማበረታቻ የማድረግ ግዴታውን መወጣት አለበት፡፡

በአጠቃላይ ከንቲባ ታከለ ኡማንም ሆነ የከተማ አስተዳደሩን ስለጅምር ጥረቶቹ አበረታታን እንጂ፣ እንደ ደሃ አገር መዲና አዲስ አበባ ገና በርካታ ሥራና ትግል የምትሻ የጋራ መዲናችን ነች፡፡ ስለሆነም ሁሉም የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ታሪክ ለመቀየር መትጋት አለበት፣ ይገባልም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው   [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...