Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሁለተኛው የፈርኒቸርና ቤተ ውበት ዓውደ ርዕይ 50 የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎችን ያሳትፋል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሁለተኛው የፈርኒቸር፣ ቤተ ውበትና ግንባታ አጨራረስ የተሰኘው ዓውደ ርዕይና ጉባዔ፣ ‹‹ፊንቴክስ 2020›› በሚል መጠሪያው ከየካቲት 26 እስከ የካቲት 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

ከ5,000 በላይ ጎብኚዎች እንደሚታደሙበት የሚጠበቀው ዓውደ ርዕይ፣ ከ50 በላይ የፈርኒቸርና ቤተ ውበት ግንባታ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች እንደሚሳተፉበት የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ፋሲካ ደበበ ተናግረዋል፡፡

በመንግሥት ለፈርኒቸር ግዥ የሚውለው ዓመታዊ ወጪ 10 ቢሊዮን ብር ይገመታል፡፡ ይህን ያህል ወጪ በአገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት ለሚደረጉ ጥረቶች ዓውደ ርዕዩ ሚና እንደሚኖረው ታምኖበታል፡፡

የአገር ውስጥና የውጭ አምራቾች፣ አቅራቢዎች አገልግሎት ሰጪዎች በሚሳተፉበት ዓውደ ርዕይ፣ ከጀርመን፣ ከጣሊያን፣ ከፖላንድ የተውጣጡ ኩባንያዎችን ጨምሮ ከአፍሪካ፣ የኬንያ የታንዛኒያና የኡጋንዳ ኩባንያዎችም እንደሚሳተፉበት ታውቋል፡፡

እንዲህ ያሉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት በመሆኑ የቴክኖሎጂና የምርት ጥራት ዕድገት ደረጃ፣ ልምድና ተሞክሮ እንደሚቀሰምበት ይጠበቃል፡፡

በኢትዮጵያ ጥራት ያለው የፈርኒቸር ውጤት አምራቾች ቢኖሩም፣ ለዓለም ገበያ ማቅረብ ባለመቻላቸው ኢትዮጵያ ከዘርፉ የምታገኘውን ጠቀሜታ እንዳሳነሰው ወ/ሮ ፋሲካ ተናግረዋል፡፡

የዋሪት ፈርኒቸር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ትህትና ለገሰ በበኩላቸው፣ ዘመናዊና ጥራት ያለው ምርት በማምረት ተወዳዳሪ ለመሆን የአገር ውስጥ አምራቾች ምን ደረጃ ላይ እንደምንገኝ የምንመዘንበት አመላካች መድረክ ይሆናል ብለዋል፡፡

በአገሪቱ ለእንጨት ሥራና ለፈርኒቸር ምርት ግብዓት የሚሆን ሀብት በብዛት ቢገኝም፣ ከዓለም ባንክ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የደን ጥበቃና የአቅርቦት መጠን በተቀናጀ መልኩ ስለማይተገበሩ የእንጨት ውጤት አቅርቦቶችን ከሌሎች አገሮች በማስመጣት በግብዓትነት መጠቀም ግድ ይሆናል፡፡

ለዚህ ማሳያ ከሚሆኑት ጉዳዮች መካከል ኢትዮጵያ ከአፍሪካ 67 በመቶ እንዲሁም ከዓለም ሰባት በመቶ ድርሻ በመያዝ የቀርከሀ ሀብት መገኛ በመሆኗ፣ በሦስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ ልታገኝ የምትችለውን የአምስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንዲሁም የ1.3 ሚሊዮን የሥራ ዕድል አልተጠቀመችበትም፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት UN COMTRADE የተባለ ተቋም እ.ኤ.አ. 2016 ይፋ ባደረገው ጥናት፣ ኢትዮጵያ የፈርኒቸር ምርቶችን ከውጭ በማስገባት በአኅጉሩ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከናይጄሪያ፣ ከአንጎላና ከሴኔጋል በመከተል በአምስተኛ ደረጃ ስትቀመጥ፣ ከምሥራቅ አፍሪካ ኬንያን ተከትላ በመቀጠል ሁለተኛዋ ግዙፍ የፈርኒቸር አስመጪ አገር ነች፡፡

የዓለም የገንዘብ ድርጅት ያወጣው ሪፖርትም፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለመሆን ያስቻላት ሰፊ መሠረተ ልማት ፈጣንና አስተማማኝ ዕድገት ላይ ስለመገኘቷ ጠቅሶ፣ በመኖሪያ ቤትና በግንባታው ዘፍር ያሳየችው እመርታ በአወንታዊነት ተመልክቷል፡፡

ይህም ዕድገት የማኅበረሰቡን የፈርኒቸር፣ የቤተ ውበትና የግንባታ አጨራረስን ያካተተው የአኗኗር ሁኔታ ፍላጎትን ከፍ አድርጎታል፡፡

‹‹ፊንቴክስ›› የአገሪቱ የአኗኗር ዘይቤ ፈጣን ለውጥ ላይ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ለዚህ ክስተት ትኩረት በመስጠት ዘርፉን የማዘመን፣ በስፋት የማስተዋወቅና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት እንዲያግዝ ታስቦ የሚዘጋጅ መድረክ ስለመሆኑ በአዘጋጆቹ ተብራርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች