Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዓለም አቀፍ ደረጃ በሚሰጠው የቡና ቅምሻ ውድድር ለመሳተፍ ከ1,400 በላይ ናሙናዎች ቀረቡ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ ሊካሄድ ዝግጅቱ እየተገባደደ የሚገኘው የልዩ ጣዕም ቡናዎች የቅምሻ ውድድር ላይ ለመሳተፍ 1,459 የቡና ናሙዎች ከወዲሁ መቅረባቸው ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ለሪፖርተር በላከው መግለጫ፣ በውድድሩ ለመሳተፍ ከጥር  25 ቀን እስከ ጥር 29 ቀን 2012 ዓ.ም. በጅማ፣ በሐዋሳ፣ በድሬዳዋና በአዲስ አበባ ለውድድሩ የሚቀርቡ ቡናዎችን ለመሰብሰብ ወደ ተዘጋጁ ማዕከላት የተጠቀሱት የቡና ናሙናዎች ገቢ ተደርገዋል፡፡ እንደ ባለሥልጣኑ መረጃ ከሆነ፣ ይህ የቡና መጠን በ20 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበ ከፍተኛው አሃዝ ነው፡፡ የጥራት ቅምሻ ውድድሩ በ11 ቡና አምራች አገሮች ውስጥ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ የባለልዩ ጣዕም ቡናዎች የጥራት ውድድር ላይ እስካሁን ከተመዘገበው ይልቅ ለመጀመርያ ጊዜ የታየና ከፍተኛ ቁጥር ያለው የቡና ናሙና ቀርቧል፡፡

ውድድሩ እ.ኤ.አ. በ1999 በብራዚል ተጀምሮ፣ በኮሎምቢያ፣ በፔሩ፣ በኤልሳልቫዶር፣ በኮስታሪካ፣ በኒካራጓ፣ በጓትማላ፣ በሆንዱራስ፣ በሜክሲኮ፣ በብሩንዲ እና ሩዋንዳ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ከአሜሪካው ተራድኦ ተቋም ‹‹ፊድ ዘ ፊውቸር›› ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ የቡና ጥራት በዓለም አቀፍ ዳኞችና በኢትዮጵያውያን ተሳትፎ የሚካሄድ ‹‹ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ›› በመባል የሚታወቀውን የልዩ ጣዕም ቡናዎች የቅምሻ ውድድር ወደ ኢትዮጵያ አምጥቷል፡፡

ተወዳዳሪዎች በተለይም ቡና አምራች ገበሬዎች በጥንቃቄ ጥራት ያለው ቡና እስካቀረቡ ድረስ የተሻለ ዋጋ እንደሚያገኙ ይጠበቃል፡፡ አቀናባሪዎችና ሌሎችም የቡና ኢንዱስትሪ ተሳታፊዎች የተሻለ ገበያና ዋጋ እንደሚያገኙ ስለሚታመን በውድድሩ ተጠቃሚዎች እንደሚሆኑ ከሚጠበቁት መካከል ናቸው፡፡ ውድድሩ የዓለም የቡና ኢንዱስትሪ ተዋንያንና ሚዲያዎችን ትኩረት ስለሚስብ ዕውቅ የኢትዮጵያ ቡናዎች የበለጠ ዕውቅና ማግኘት የሚችሉበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡

ቡናና ሻይ ባለሥልጣን እንዳስታወቀው፣ የውድድሩን የመጀመሪያ ዙር የሚያልፉ ናሙናዎች ወደ አዲስ አበባ ተልከው በአገር ውስጥ ቀማሾች የጥራት ደረጃቸው ይለካል፡፡ ከእነዚህ ቡናዎች ውስጥ 150 አሸናፊዎች ተመርጠው በአገር ውስጥ ቀማሾች በድጋሚ ተቀምሰው፣ 40 የላቁ ቡናዎች ለመጨረሻ ዙር ውድድር የሚያልፉ ይሆናሉ፡፡ ውድድሩን የሚዳኙት ከመላው ኢትዮጵያ ተውጣጥተውና ተገቢውን ሥልጠና ወስደው ብቃታቸው የተረጋገጠላቸው ዳኞች ሲሆኑ፣ ከተለያዩ አገሮች የሚሳተፉት ዳኞችም በሌሎች አገሮች የተካሄዱ ውድድሮች ላይ የተሳተፉና የዳኙ፣ ልምዱና ዕውቀቱ ያላቸውን ቡና ገዢዎችና ዳኞችን ያካተተ ስብስብ ስለመሆኑ የባለሥልጣኑ መረጃ ይጠቅሳል፡፡ በጥራታቸው አሸናፊ የሚሆኑ ቡናዎች፣ ውድድሩ በተካሄደ በስድስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ድረገጽ አማካይነት በሚከናወን ዓለም አቀፍ ጨረታ አማካይነት ለገዢዎች እንደሚሸጡ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ቀደም በተደረጉ ውድድሮች በጥራት አሸንፈው የተሸጡ ቡናዎች በተደጋጋሚ የዓለም የቡና ዋጋ ሪከርድ መስበራቸው ይጠቀሳል፡፡

ከየካቲት 16 ቀን እስከ የካቲት 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ለውድድር በገቡት ቡናዎች ላይ የቅድመ መረጣ ሥራ እንደሚከናወን፣ ቡናዎችን ወደ መጋዘን የማስገባት ሥራውም ከየካቲት 23 ቀን ጀምሮ እስከ መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚከናወን፣ አገር አቀፍ ውድድሩም ከመጋቢት 21 ቀን እስከ መጋቢት 25 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚካሄድ ብሎም ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኩ ከመጋቢት 29 ቀን እስከ ሚያዝያ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚከናወን ሲታወቅ፣ ዓለም አቀፍ የሽያጭ ጨረታ ደግሞ በግንቦት እንደሚካሄድ ባለሥልጣኑ ይፋ አድርጓል፡፡

በቅርቡ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር)፣ በተቋሙ ኃላፊነታቸው ወቅት ከሠሯቸውና መታሰቢያቸው ከሚሆኑ ተግባራት መካከል ይህንኑ የልዩ ጣዕም ቡናዎች የጥራት ውድድር ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት መቻላቸው እንደሆነ ገልጸው ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር የአገሪቱን የቡና መለያ ወይም ብራንድ በማዘጋጀትና የቡና የወጪ ንግድ ግብይት አስተዳደር መመርያ እንዲዘጋጅና እንዲተገበር በማድረግ በኩል የአዱኛ አመራር ሚናውን ተወጥቷል፡፡

በቡናና ሻይ ባለሥልጣን ኃላፊነታቸው ከሠሯቸው አንኳር ተግባራት እንደ ሌጋሲያቸው ስለሚቆጥሩት ክንውን ሲጠየቁ፣ ‹‹የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ የቡና ጥራት ቅምሻ ውድድር ወደ አገራችን እንዲመጣ በቡድን መሥራታችን ለእኛ ትልቅ ውጤት ነው፡፡ እስከ ታች በመውረድ አርሶ አደሮችን በማስተማርና በማገዝ ቡናቸውን እስካሁን ታይቶ በማይታወቅ ዋጋ እንዲሸጡና እንዲጠቀሙ በማድረጋችን ለእኔ ከዚህ በላይ የሚያረካ ሥራ የለም፤›› ብለው ነበር፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ኢትዮጵያን በብሔራዊ ደረጃ የሚገልጻትና የሚወክላት የቡና መለያ (ብራንድ) ለማዘጋጀት የተከናወነው ሥራ ከሁሉም ይበልጣል፡፡ ‹‹ምክንያቱም የአገርህን ምርት ብራንድ አስደረግክ ማለት መብትህን አስከበርክ ማለት ነው፡፡ ይህ ትልቅ ጉዳይ ነው፤›› በማለት እነዚህ አንኳር ሥራዎች የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ትልቅ ውጤት ያስመዘገበባቸው ሥራዎች እንደሆኑ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች