Monday, July 22, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ቻይና የሄደችበት መንገድ

በው ቲንግ

የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ኒሞኒያ በቻይናዋ የውሀን ከተማ መከሰት የዓለምን ትኩረት የሳበ ክስተት ሆኗል፡፡ ሆኖም ቻይና እያደረገች ያለችው የመከላከልና የመቆጣጠር እርምጃ ለሌሎች የዓለም አገሮች መልካም የመማሪያ አጋጣሚ ነው፡፡ ይህን ተከትሎም የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር)፣ የቻይና አካሄድ የቫይረሱን ወረርሽኝ በሚገባ ለመቆጣጠርና ብሎም በሂደት ለማስወገድ እንደሚያስችል ማመናቸውን ተናግረዋል፡፡

የወረርሽኙን ፍጥነትና ከሚያሳዩ ጉዳዮች

በ31-12-2019 (ታህሳስ) በውሀን ከተማ 27 ሰዎች ምንነቱ ባልታወቀ የሳንባ ምች በሽታ መጠቃታቸውን የሚያሳይ ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፣ በ8-1-2020 (ጥር ወር) የቫይረሱ አምጪ (መንስዔ) ተህዋስ አዲስ የኮሮና ቫይረስ መሆኑ ተረጋገጠ፡፡  

በ11-1-2020 (ጥር ወር) የቫይረሱ ወረርሽኝ የየዕለቱ የተሻሻለ ሪፖርት መቅረብ የጀመረበት ነው፡፡ በ14-1-2020 ውሀን ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚያስችል የሰው ኃይል በማደራጀት የሙቀት መጠን መለኪያዎችን በተግባር ላይ አዋለች፡፡

በ19-1-2020 የአዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዘረ መልን ቅደም ተከተል ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር ለዓለም ማጋራት ተጀመረ፡፡ ከዚያም ለመጀመሪያ ጊዜ በሽታው ከሁቤይ ክፍለ ሀገር (ግዛት) ውጪ መታየቱም ተረጋገጠ፡፡ 

በ20-1-2020 የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንግ ፒንግ የዜጎች ጤናና ሕይወት ደህንነት መጠበቅ ቀዳሚው ተግባር መሆኑን አሳሰቡ፡፡ የወረርሽኙን መስፋፋት ለመግታት /ለመቀልበስ/ ውጤታማ የሆኑ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን አሳወቁ፡፡ ደግሞም በየክፍለ ግዛቱ የሚከሰቱ የወረርሽኙን አዳዲስ ክስተቶች ቁጥር የየዕለቱን ማጠቃለያ ሪፖርቶች ማቅረብ ተጀመረ፡፡

በ23-1-2020 የውሀን ከተማ የአውቶቡሶችንና የረጅም ርቀት የትራንስፖርት ጉዞዎችን እንዲቋረጡ አገደች፣ አየር መንገዶችን ዘጋች፣ ከውሀን የሚነሱ የባቡር መስመሮችንም ዘጋች፡፡ በጠቅላላው በቻይና የሚገኙ 29 ግዛቶች የወረርሽኙን መከሰት ሪፖርት አደረጉ፡፡ ውሀን ከተማ በሽታውን በአንድ ማዕከል ደረጃ ለማከም እንዲቻል የሁሼንሻን ሆስፒታል እንዲገነባ ውሳኔ ተላለፈ፡፡  

በ24-1-2020 ክፍለ ግዛቶችና ከተማዎች ውሀን ከተማን ለመርዳት የሕክምና ቡድኖቸን መላክ ጀመሩ፡፡ ሠራዊቱም የሁቤይ ግዛትን ለመርዳት የመጀመሪያውን ዙር የሕክምና ቡድን ላከ፡፡ የውሀን ከተማ ወደ 6000 የሚሆኑ ታክሲዎችን ሰብስባ በማሰራጨት ለማህበረሰቡ ጥቅም እንዲውል አደረገች፡፡  

በ25-1-2020 ማዕከላዊው መንግስት ወረርሽኙን መመከት የሚችል መሪ ቡድን አቋቋመ፤ በሀገሪቱ የሚገኙ 30 ክፍለ ግዛቶች የመጀመሪያው ደረጃ ምላሽ የሚሰጥ ዋና ዋና የማህበረሰብ ጤና ድንገተኛ መጀመሩን አበሰሩ፡፡ ውሀን ከሁሼንሻን ሆስፒታል በተጨማሪም ለማዕከላዊ ሕክምና የሚያግዝ ሌይሼንሻን  የሚባል ሌላ ሆስፒታል ለመገንባት ወሰነች፡፡

በ26-1-2020 የቻይናው ብሔራዊ የጤናና የተሀድሶ ኮሚሽን ወረርሽኙ እስካሁን ድረስ ገና በመሰራጨት ላይ መሆኑን አወጀ፡፡ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ ብሔራዊ የገንዘብ ተቋማት ወረርሽኙን ለመቆጣጠርና ለመከላከል እንዲውል ወደ 11.21 ቢሊዮን የቻይና ዩአን ድጎማ ማድረጋቸውን አሳውቀዋል፡፡

በ27-1-2020 ጠቅላይ ሚንስትር ሊ ኬቂያንግ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር  የተቋቋመውን ቡድን በመምራት ወደ ውሀን አምርተዋል፡፡ የቻይናውን የጸደይ ወር ላይ ይከበር የነበረውን ክብረ በዓል እስከ የካቲት 2 ድረስ እንዲራዘም አድርገዋል፡፡

በ28-1-2020 ከዚህ ቀደም ለሕክምና በዜጎች በግል ይሸፈን የነበረው ወጪ በመንግሥት እንዲደጎም ታውጇል፡፡ ስለሆነም በወረርሽኙ ወቅት ሕክምናው በነፃ እንዲሰጥ ተወስኗል፡፡ ለወረርሽኙ መከላከያ የሚሆን የክትባት ምርምር እንዲካሄድ በሕግ ጸድቋል፡፡

በ29-1-2020 በጠቅላላው 52 የሚሆኑ የሕክምና ቡድኖችና ከ26 ክፍለ ግዛቶች የተውጣጡ 6097 ሰዎች እንዲሁም ሦስት ወታደራዊ ሆስፒታሎች የሁቤይን ግዛት እንዲያግዙ ተልከዋል፡፡ በሁሉም ደረጃ የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍም ቀጥሎ ለወረርሽኙ መከላከያና መቆጣጠሪያ እንዲውል ወደ 27.3 ቢሊዮን ዩአን የሚደርስ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ እንደዚያም ሆኖ የወረርሽኙ መከሰት በ31 የመላው ቻይና ግዛቶች ታይቷል፡፡ ሁሉም ግዛቶች ለዋና ዋና የማህበረሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች የመጀመሪያ ደረጃ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በ31-1-2020 የዓለም ጤና ድርጅት ወረርሽኙ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ጉዳይ ችግር ነው ብሎ አውጇል፡፡ የቻይና መንግስት በውጪ አገሮች የሚገኙ የሁቤይ ዜጎችን ወደሀገራቸው መልሶ ለመውሰድ አውሮፕላን ልኳል፡፡  

በ1-2-2020 ለወረርሽኙ መከላከያና መቆጣጠሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ለእርዳታ የሚገቡ ማናቸውም ነገሮች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ታወጀ (ተወሰነ)፡፡ የወረርሽኙን ቁጥጥር የበለጠ የተሻለ ለማድረግ የተጠናከረ የገንዘብ ድጋፍ ተደረገ፡፡ የዜጎችን ሕልውና ለመጠበቅና የተረጋጋ እውነተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠልም ተሠርቷል፡፡ 

በ2-2-2020 በውሀን የተገነባው የሆሼንሻን ሆስፒታል ግንባታው ተጠናቆ ሁቤይ ግዛት የሚገኙ በቫይረሱ የተጠረጠሩት ሁሉ በልዩ ማቆያ ጣቢያ (ኳራንታይን) እንዲቆዩ ተደረገ፡፡

በ3-2-2020 የወታደሩ ክፍል 1400 የሕክምና ሰዎችን በውሀን የሆሼንሻን ሆስፒታል ተገቢውን ሕክምና እንዲሰጡ አሠማራ፡፡ ውሃን መለስተኛ የሕመሙ ተጠቂዎችን ለማከም የሚያስችሉ በርካታ ጊዜያዊ የጎጆ ሆስፒታሎችን በአንድ ጀንበር ገነባች፡፡   

በ4-2-2020 የመጀመሪያዎቹ ታማሚዎች ወደ ሆሼንሻን ሆስፒታል እንዲዛወሩ ተደርገዋል፡፡ በዓለም ደረጃ ሕመሙ እንደተከሰተባቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር ከ20,000 አልፏል፡፡ ስለሆነም ተጨማሪ 2000 የህክምና ባለሙያዎች ሁቤይን እንዲያግዙ ተልከዋል፡፡

በ5-2-2020 የውሀን የጎጆ ሆስፒታሎች ሕክምናውን መስጠት ጀመሩ፡፡ ደግሞም የህዝቡን ኑሮ ለመደገፍና መተዳደሪያ እንዲኖራቸው ለማድረግ እንዲሁም አነስተኛና መካከለኛ ሥራ ፈጣሪ ሰዎችን ለመደገፍ የሚያስችሉ በርካታ ፖሊሲዎችን አወጣች፡፡ ለምሳሌም በመንደር ውስጥ በእርሻ ሥራ ላይ የተሠማሩና የከብት ውጤቶችንና መኖ የሚያመላልሱ ተሽከርካሪዎች እንዳይስተጓጉሉ የሚያደርጉ ፖሊሲዎች ወጥተዋል፤ ደግሞም በአነስተኛና መካከለኛ ሥራ ፈጠራ ላይ በተሠማሩት ላይ የሚጣለው የግብር ክፍያ እንዲቀነስ ተደርጓል፤ ለተማሪዎች ትምህርት የሚጀምሩባቸው ቀናት እንዲዘገዩ ተደርጓል፤ ተማሪዎች በኦን ላይን ኮርሶችን የሚወስዱባቸው ሁኔታዎች ተመቻችተዋል ወዘተ፡፡     

በ8-2-2020 በውሀን የሌሼንሻን ሆስፒታል ሕክምና ጀምሯል፡፡

በ10-2-2020 የዓለም ጤና ደርጅት ከፍተኛ ቡድን ቤጂንግ ደርሷል፡፡ በሁቤይ የሚገኙ16 ግዛቶችን ለመርዳት (ለመደገፍ) 19 ግዛቶችን አስተባብሯል፡፡

በ11-2-2020 በጠቅላላው 4,740 ሰዎች ከሆስፒታል ወጥተዋል፡፡ የመዳን ዕድል በጥር 27/2020 ከነበረው ከ1.3% ወደ 10.6% ከፍ ብሏል፡፡ በድሃ ማህበረሰብ አካባቢዎች የእርሻ ምርቶችን ሽያጭ ለማበረታታት የሚያስችሉ 6 መለኪያዎች ይፋ ሆነዋል፡፡  

በ13-2-2020 ከሁቤይ በተጨማሪ በሽታው በአዲስ የተከሰተባቸው ሰዎች ቁጥር ለተከታታይ 10 ቀናት ቀንሶ ታይቷል፡፡ በሁሉም ደረጃ የሚደረገው ብሔራዊ የገንዘብ ድጋፍ 80.55 ቢሊዮን የቻይና ዩአን ደርሷል፡፡ ትክክለኛ ወጪው ደግሞ 41 ቢሊዮን ዩአን ደርሷል፡፡ የሲቪል የበረራ አስተዳደር 33 የቻርተር አውሮፕላን በረራዎችን አስተባብሮ 18 የሕክምና ቡድኖችንና በጠቅላላው 3000 የሚሆኑ የሕክምና ባለሙያዎችን እንዲሁም 180 ቶን ከሚደርሱ አስፈላጊ አቅርቦቶች ጋር ወደ ሁቤይ አጓግዟል፡፡ ወተደሩ ክፍልም በራሱ 2600 የሚሆኑ የሕክምና ባለሙያዎችን ለእርዳታ ወደ ውሀን ልኳል፡፡                                          

እስከ የካቲት 14/2020 ወረርሽኙን ለመመከት በተደረገው ጥረት በጠቅላላው 25,633 የሚሆኑ ዶክተሮች ሁቤይን ደግፈዋል፡፡ ከሁቤይ ውጪ የተረጋገጡ የሕመሙ አዳዲስ ክስተቶች ለ11 ተከታታይ ቀናት ቀንሰው ታይተዋል፡፡ የመዳን ዕድል በከፍተኛ ፍጥነት ከፍ ብሏል፡፡ ከ 7,000 የሚሆኑ ሰዎች ድነው ከሆስፒታል ወጥተዋል፡፡ ብሔራዊ የሞት መጠኑም በ2% ያህል በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡ ይህም በሁቤይ ግዛት 0.49% ነው፡፡ እነዚህ መረጃዎችና እውነታዎች የሚያሳዩት የቻይና በሽታውን የመከላከልና የመቆጣጠር እርምጃዎች ትክክለኛና ውጤታማ መሆኑን ነው፡፡ ወረርሽኙ በቁጥጥር ሥር መዋልና መዳንም የሚችል መሆኑንም ያመለክታል፡፡

ወደ ኋላ እንሂድና በውሀን ያለውን ሁኔታ እንመልከት፡፡ የውሀን የከተማ ስፋት 8,500 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ነው፡፡ የሕዝብ ብዛቱም 14 ሚሊዮን ነው፡፡ እስከ የካቲት 15 ድረስ በውሀን በሽታው የተከሰተባቸው ሰዎች ቁጥር 37,914 ሲሆን የዳኑት 2,519 ሲሆኑ የሞቱት ቁጥር 1,123 ነው፡፡ ይህም በጠቅላላው በአገሪቱ ውስጥ በሽታው ከተከሰተባቸው አካባቢዎች 57% የሚሆነውን ቁጥር የሚሸፍን ሲሆን ሞት ከተመዘገበባቸው አካባቢዎች ውስጥ ደግሞ 73.7% የሚሸፍን ነው፡፡

በውሀን በመጀመሪያው በወረርሽኙ የተጠቁት ቁጥር የሚያሳየው ከፍተኛ የሆነ ጭማሪን ነበር፡፡ ይህም የሆነው አዲሱ የሳንባ ምች የኮሮና ቫይስ ጥቃት ሰዎች በሚበዙበት አካባቢ በቀላሉ የሚስፋፋ በመሆኑ ነው፡፡   

በዚህ አግባብ ውሀን በ2003 ዓ.ም. የሳርስን ጥቃት ለመከላከል በቤጂንግ የተገነባውን የሻኦታንግሻን ሞዴል ሆስፒታልን በማመሳከር ከ2500 በላይ አልጋዎች ያሏቸውን የውሃን ሆሼንሻንና ሌሼንሻን የተባሉ ሁለት ልዩ ሆስፒታሎችን ግንባታ በአስር ቀናት ውስጥ አጠናቃለች፡፡ ውሀን በመለስተኛ ደረጃ ለተጠቁ ሕመምተኞች በማዕከል ደረጃ ሕክምና ለመስጠት የሚያስችሉ 6960 አልጋዎች ያሏቸው 9 የሕክምና ጎጆዎችንም አስገንብታለች፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ አሥረኛውን ለማስገንባት እየተዘጋጀች ነው፡፡  

የቻይና መንግስት ወረርሽኙ የሚያስከትውን አሉታዊ የኢኮኖሚ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም ተከታታይ የሆኑ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምሯል፡፡ ይህ እየተሻሻለ ያለው አዝማሚያ ከዚህ ቀደም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ በተወሰዱ እርምጃዎች እየተደገፈ ወደፊትም ይቀጥላል፤ ይህም ለራሱ ለቻይና ኢኮኖሚ ማገገም ያግዛል፡፡  በዚህ ወር መጀመሪያው ላይ የቻይናው ማዕከላዊ ባንክ የገንዘብ ገበያውን ለማረጋጋት ሲል 1.7 ትሪሊዮን ዩአን (243 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር) ወደ ገበያው ረጭቷል፡፡ ይህም በኋላ ላይ የሸቀጥ ገበያውን ወደነበረበት ከመመለስ ባሻገር ድንበር ዘለል የካፒታል ፍሰትና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትና ፍላጎት እንዲረጋጋ ያደርጋል፡፡ አሁን በቻይና ያለው የገንዘብ ገበያ እንቅስቃሴ የሚያሳየው ኢንቬስተሮች የቻይና መንግስት ወረርሽኙን ለመግታት ባለው ብቃት ላይ መተማመን እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት የቻይና ኢኮኖሚ ለዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት 30% አስተዋፅኦ አድርጓል፤ ለዓለም ኢኮኖሚ የዕድገት ሞተር መሆኑንም ቀጥሏል፡፡ ይሁንና አሁን እየተከሰተ ያለው ወረርሽኝ የተወሰነ ተፅዕኖ ማሳደሩ ባይካድም የኢኮኖሚ ዕድገቱ መሠረታዊ ነገር ግን አልተለወጠም፡፡ ምክንያቱም የቻይና ፖሊሲና የቁጥጥር መሳሪያዎቹ ብርቱና ብቁ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው የዓለም ባንክና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሁለቱም በቻይና ኢኮኖሚ ላይ ያላቸውን መተማመን በዚህ ዓመት የገለጹት፡፡        

ወረርሽኙ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ቻይና ያደረገችው የበሽታውን አምጪ ተህዋስ መለየት ብቻ ሳይሆን ስለቫይረሱ ዘረ መል ቅደም ተከተል ከዓለም ጤና ድርጅትና ከሌሎችም አገሮች ጋር በመተባበር ወቅታዊ መረጃዎችን ለዓለም አጋርታለች፡፡ በተጨማሪም ስለወረርሽኙ ከአገር ውጪ ያሉትንም ሁኔታዎች በይፋ አሳውቃለች፤ ደግሞም የቫይረሱን የስርጭት ሁኔታ ለመቀልበስ ወሳኝ የሆኑ እርምጃዎችን ወስዳለች፡፡ ይህም ጥረቷ በሰፊው ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና ተችሮታል፡፡       

ነገር ግን አንዳንድ የምዕራባዊያን ፖለቲከኞችና የመገናኛ ብዙሃን ቻይና ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወሰደችውን እርምጃ አስፈላጊነትና አስቸኳይነት ቸል ብለውታል፡፡ በተደጋጋሚ የሀሰት መረጃዎችን በመልቀቅ እነዚያን የተወሰዱ እርምጃዎችን ተቃውመዋል፡፡ ይህም ቻይና የወሰደችውን እርምጃ ማቃለል ነው፡፡ ይህም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ የሚደረጉ ትብብሮችን ሁሉ ድንጋጤ ላይ የሚጥል ነው፡፡

በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ቶም ከተን የተባለው ሪፐብሊካን ቫይረሱ የወረርሽኙ ማዕከል ከሆነችው በውሀን ከሚገኝ ላቦራቶሪ ያመለጠ የጥፋት ባዮ-ኬሚካዊ መሳሪያ ነው ሲል ሀሳቡን ሰጥቷል፡፡     

በሐፍፖስት የተጻፈው መጣጥፍ ነገሩን በሚያሟሙቁ ጋዜጠኞችና ወግ አጥባቂ በሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ዘንድ የሚነዙትን ሴራዎች በማጋለጥ እውነቱን አውጥቷል፡፡ ይህ መጣጥፍ ቫይረሱ የባዮሎጂካል መሳሪያ ውጤት ነው የሚለውን ሐሳብ የጤና ባለሙያዎች እንዳልተቀበሉትም አጋልጧል፡፡ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስም ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ ለማስወገድ የተወሰዱ እርምጃዎችን (ለምሳሌ የቤት-ለቤት ቁጥጥር፤ ለሕክምና የሚረዳ ማዕከላዊ የማቆያ ስፍራን (ኳራንታይን) ማዘጋጀትን ወዘተ የሚገልጽ መጣጥፍ አሳትሟል፡፡ ምንም እንኳን እነዚህ እርምጃዎች ውጤታማ በሆነ መልኩ የቫይረሱን ምንጭ ለመቆጣጠርና በተሻለ መልኩ የህብረተሰቡን ጤና ለመከላከል ያስችላሉ ብሎ ለማመን የሚያዳግት ቢሆንም)  በሌሎች የዓለም ክፍሎች ለምሳሌ ዴር እስፒገል የሚባል የጀርመን መጽሔት ርዕሱ፡ “ኮሮና ቫይረስ በቻይና የተሠራ” የሚል መጣጥፍ በሽፋን ገጹ ላይ አውጥቷል፡፡ ልክ ቫይረሱ ሆነ ተብሎ በቻይና የተሰራ በሚያስመስል መልኩ፡፡ በሌላም በኩል የደች ሬድዮ ዲጄ ሆነ ብሎ ዘረኝነትን የሚያሳይ ይዘት ያለው ከኮሮና ቫይረስ ጋር የተገናኘ ዘፈን ለቋል፡፡

እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ምሳሌዎች የሚያሳዩት አንዳንድ ምዕራባዊያን ለቻይና ያላቸውን ሥር የሰደደ ጥላቻና ማግለል ያሳዩበት ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለረዥም ዘመን የቆየና በአንዳንድ ኃላፊነት በጎደላቸው የምዕራቡ ዓለም የመገናኛ ብዙኃን የሚሰራጭ ምዕራባውያን ተኮር የሆነ የዘረኝነት አካሄድ ነው፡፡  

የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር)  ድርጅቱ ትክክለኛውን መረጃ የሚያሰራጩና የሀሰት ሴራዎችን የሚያጋልጡ እውነትን የሚናገሩ ቡድኖችን እየመሰረተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህም ስለ አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዋና ዳይሬክተሩ  እንደሚሉት፣ የድርጅቱ ተግባር ቫይረሱን ብቻ መዋጋት ሳይሆን ነገር ግን የተዛባ የሀሰት ወሬ የሚነዙትንና በወረርሽኙ ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎችን የሚያጣጥሉትንም ጭምር መዋጋት ነው፡፡ መሠረቱን በጀርመን  ያደረገ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አማካሪ የሆነና ሺለር ኢንስቲትዩት የተባለ ተቋም መስራችና ፕሬዚዳንት የሆኑት ሔልጋ ዜፕ-ላሮች እነዚያን የምዕራባውያንን መገናኛ ብዙሃንን በምዕራባዊያን ስም ስለፈጸሟቸው ሥር የሰደደ ዘረኝነትና የሥነ ምግባር ጉድለት ነቅፈዋቸዋል፡፡ ደግሞም ማሪዮ ካቮሎ የተባለው አሜሪካዊው ደራሲና ኮሜንታተር (አታች) እንደገለጸው በ2009 ዓ.ም. በአሜሪካ የተከሰተው የኤች-1 ኤን-1 የኢንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ የትም የሌለ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ያኔ ማንም ሰው ሲዲሲ(CDC) የተባለውን የአሜሪካ የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ድርጅት አልነቀፈም ነበር፡፡ ሰውየው እንዳለው “በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት እጅግ የሚያስፈራ ነው፡፡ ይህ በቻይና ላይ ያነጣጠረው ፀረ ቻይና  እንቅስቃሴ እጅግ የሚያስፈራ ነው፡፡ ይህም ፖለቲካዊ ገጽታ ያለው ነው፤” ብለዋል፡፡ 

በተመሳሳይ መልኩ ቻይና በእርግጥ ብዙ ማበረታቻዎችም ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተችረዋታል፡፡ በ33ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሐመድ፣ ከቻይና ጋር መተባበር ተገቢ እንደሆነ በስብሰባው መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ተናግረዋል፡፡ ኮሚሽኑም በጽናት ቻይናን በመደገፍ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኔዎ ጉቴሬስም በፕሬስ ኮንፈረንስ ላይ በሰጡት መግለጫ፣ ቻይናዎች በተከሰተው የሳንባ ምች ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ምንም ዓይነት የመገለል ስሜት እንዳይሰማቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ከኢትዮጵያም ፕሬዚዳንቷ፣ ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለቻይና የድጋፍ ደብዳቤ ልከዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አምስት የቻይና ዋና ዋና ከተማዎች የሚያደርገውን በረራ ቀጥሏል፡፡  እነዚህ ሁሉ ከአፍሪካ ሕዝቦች ለቻይና ሕዝብ የቀረቡ ስጦታዎች ቻይናውያን የእውነተኛ ወዳጅነት ስሜት እንዲሰማቸው አድርጓል፡፡ ከአፍሪካ ውጭም ለቻይና ድጋፋቸውን         ያሳዩ ሌሎችም መሪዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ  ለመጥቀስ ያህል የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ የዘር ጥላቻን ልክ እንደ ቫይረሱ ሁሉ ተቃውመውታል፡፡ የሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ሂሲየን ሉንግ ምንም እንኳን ቫይረሱ ከውሀን ቢጀምርም የማንንም ዘር ወይም ዜጋ አያከብርም ካሉ በኋላ ወረርሽኙ የሁሉም አገሮች ችግር ስለሆነ ሁሉም አገሮች ለጋራ መፍትሔ በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡   

በምድራችን ቫይረሱ የሰው ልጆች ሁሉ የጋራ ጠላት ነው፡፡ ለዚህም ቻይና የተመረጠና ሁሉን አቀፍ የሆነ የመከላከያና የመቆጣጠሪያ እርምጃዎችን ተግባር ላይ አውላለች፡፡ የቻይና ዜጎችን ብቻ ሳይሆን የዓለም ዜጎችን ሁሉ ለመከላከል የሚያስችል እርምጃ  ሥራ ላይ አውላለች፡፡ አገሮች ሁሉ የጋራ ስጋት እንደመጋፈጣቸው መጠን ወረርሽኙ ያለበትን ሁኔታ በዓላማና በብቃት መገምገምና ሪፖርት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚያም ቫይረሱን ለመቆጣጠር ዓለም አቀፋዊ ትብብርን በማጠናከር ተግባራዊ የሆነ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡ ማንም ሰው ቢሆን ዝም ብሎ ተመልካች መሆን የለበትም፡፡ ደግሞም ማንም ሰው ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሚደረገው ጥረት በተቃራኒነት መቆም የለበትም፡፡ 

ከአዘጋጁ፡-  ጸሐፊዋ የቻይና ሚዲያ ግሩፕ (ሲሲቲቪ) በአዲስ አበባ ወኪል ሲሆኑ፣ መጣጥፉ የሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles