Monday, May 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የጋራ ታሪካችን ትውስታ በዓድዋ ድል ምልከታ

በጌታቸው መኰንን

ታሪክ ከየት ተነስተን& ምን አጋጥሞን፣ ምንን ይዘን ቆይተን ምንን ይዘን ለወደፊቱ እናስባለን& የሚሉትን ጥያቄዎች የሚመልስልን ነው፡፡ ያለፈው ትውልድ ለዛሬው ትውልድ ያስተላለፈው ውርስ ምንድን ነው? ምን የኩራትና የክብር ምንጭ የሚሆን አለ? ምን የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ውርስ አለ? የዛሬው ትውልድስ ለሚቀጥለው ትውልድ ምን የኩራትና የክብር ምንጭ ያወርሳል? የሚሉትን ጥያቄዎች ይመልሳል፡፡ ከዚህ አንፃርም የሺሕ ዘመናት ታሪክና ማኅበራዊ መስተጋብሮች ኢትዮጵያን አጥብቀው ያስተሳሰሩና የጋራ ማንነታችንና ምንነታችንን በረዥሙ ዘመን የገነቡና ያደራጁ ብሔራዊ ትውስታዎች አሉን፡፡ ካለፉት ታላላቅ የኢትዮጵያ አኩሪ ታሪኮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የዓድዋ ድል እንደሆነ ይታወቃል። የዓድዋ ድል የዓለም የታሪክ ትርክት አንዲቀየር ያደረገ የአፍሪካና የመላው ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ መኩሪያና መመኪያ ነው። የዓድዋ ድል ቀደምት ኢትዮጵያውያን ተባብረው ከውጭ የሚመጡባቸውን ማናቸውንም ወራሪዎችንና ጠላቶችን ድባቅ እንደሚያስገቡ ያሳዩበት ገድላቸው ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያውያን በጀግንነት ጠላቶቻቸውን የሚፋለሙ፣ ለነፃነታቸው ቀናዒ መሆናቸውንም ለዓለም ያስመሰከሩበት በወርቅ ቀለም የተጻፈ ታሪክ ነው። ዛሬ ደግሞ፣ ባለፈ ታሪካችን ስንኮፈስ  በተሠራው በዚህ የዓድዋ  ድል ላይ ቆመን ለሀገረ ብሔር ግንባታ እንሠራ ዘንድ የዓድዋን ድል አስመልክቶ የራሴን ምልከታ ለመግለፅ ወደድኩኝ፡፡

እርግጥ ስለዓድዋ ጦርነትና ድል ታላቅነት ብዙ ተብሏል፡፡ በታላቅ መስዋዕትነት የተገኘ ድል መሆኑን ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያንና የውጭ አገር ሰዎች በዓድዋ ጦርነት ድል ዙሪያ ጽፈዋል፡፡ ከአገር ውስጥ አቶ ተክለ ፃድቅ መኩሪያ፣ ቀኛዝማች ታደስ ዘወልዲ፣ ባህሩ ዘውዴ (ኘሮፌሰር) ለአብነት የሚጠቀሱ ሲሆን ከውጭ ደግሞ ሃሮልድ ማርክስ፣ ሬይሞንድ ጆናስ፣ ክሪስ ኘራውቲ እና ፓል ሄንዝ ወዘተ ይገኙበታል፡፡ ታዋቂው የፊልም ባለሙያም ኃይሌ ገሪማም (ኘሮፌሰር) “ዓድዋ” (Adwa; An African Victory) የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም እ.ኤ.አ በ1999 ሠርቷል፡፡ በርካታ ዘመናዊ ገጣሚያንም ስለዓድዋ ጽፈዋል፡፡ ብዙዎቹ የድሉን ዓመታዊ መታሰቢያ በዓል ተከትለው ሥራዎቻቸውን በጋዜጦችና በመጽሔቶች አሳትመዋል፡፡ በሬዲዮና በቴሊቪዥን አቅርበዋል፡፡ ከቀደምት ደራሲያን መካከል ፀጋዬ ገብረመድህንና ሰይፉ መታፈሪያና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ በዓድዋና በጀግኖቿ ታሪክ ላይ ተመሥርተው ከተፃፉ ተውኔቶች መካከል የደጃዝማች ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት “ዓድዋ”፣ የሻምበል ታምራት ገበየሁ “ውጫሌ”፣ የጌትነት እንየው “እቴጌ ጣይቱ” ወዘተ ይገኙበታል፡፡ ስለዓድዋ ጦርነትና ድል በዜማ የቀረቡ ሥራዎችን ስንመለከት ጥላሁን ገሠሠንና እጅጋየሁ ሺባባው (ጂጂ) እና ቴዎድሮስ ካሳሁንን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ከዓድዋ ድል በፊት አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ ለመከፋፈልና ለመቀራመት አውሮፓውያን በበርሊን ጉባዔ አካሂደው ነበር፡፡ ይህ የበርሊን ጉባዔ ምንድን ነው? አውሮፓውያን ወደ አፍሪካ የዘለቁት ጥሬ ሀብት ለማግኘትና የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብቶች ለመበዝበዝ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ አፍሪካን የመከፋፈሉና የግዛት ማስፋፋት ዕጣ ፈንታና የግዛት መስፋፋት እንዲሳካላቸው አውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች በበርሊን ተሰበሰቡ፡፡ የበርሊን ኮንፈረንሰ ዓላማ የበለፀጉ አውሮፓውያን አገሮች የነበራቸውን የጥሬ ዕቃና የገበያ ፍላጐት ለማርካት ሲሉ አፍሪካን የመቀራመት ውሳኔ የወሰኑበት ጉባዔ ነው፡፡  ከዚህ ጉባዔ በኋላም አፍሪካና ሕዝቧቿን የቅኝ አገዛዝ ፅልመት ወረሳቸው፡፡ አፍሪካን የመከፋፈሉ ዕጣ ፈንታ በርሊን የተወሰነው እ.ኤ.አ በ1884 እስከ 1885 ሲሆን አፍሪካን በመደፋቸው ስር አስገብተው ሀብቷን ያጣጣሙት ቅኝ ገዥዎች አንድም አፍሪካዊ ነፃ አገር እንዳይኖር ለማድረግ በነበራቸው ውጥን መሠረት አገራችን ኢትዮጵያንም ይማትሩ ጀመር፡፡

የአፍሪካን አኅጉር በይበልጥ የተካፈሉት እንግሊዝና ፈረንሳይ በአፍሪካ ቀንድ ላይ የማይታረቅ ቅራኔ ስለነበራቸው እንግሊዝ ከፈረንሳይ ጋር ለምታደርገው ውድድር እንግሊዝ የጣሊያን ሞግዚት እየሆነች ጣሊያን በኢትዮጵያ መቆናጠጫ መሬት እንድታገኝ ረድታታለች፡፡ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ጣሊያን በኢትዮጵያ ዙሪያ መሬት ተቆጣጥረው ይዞታቸውን ለማስፋት ጉልበታቸውን ለማሳየት ተጣድፈውም ነበር፡፡ በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከልም የውጫሌ ውል ተፈርሞ ነበር፡፡ የውጫሌ ውል ድንገት የመጣ ነገር አልነበረም፡፡ ዳግማዊ ምኒልክና ጣሊያን ቀደም ሲል የውጫሌ ጥንስስ ሊባሉ የሚችሉ ሁለት የወዳጅነት ውሎች ተፈራርመው እንደነበር ታሪክ ያወሳል፡፡ የውጫሌ ውል የማታለል ዓላማ ነበረበት፡፡ የዚህ ውል አሥራ ሰባተኛው አንቀፅም በአማርኛ እንዲህ ይላል፡፡

የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮፓ ነገሥታት ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ በኢጣሊያ መንግሥት አጋዥነት መላላክ ይቻላቸዋል፡፡

ይህ አንቀጽ በጣሊያንኛ የሚለው በጣም የተለየ ነው ሲተረጐም፡-

የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከሌሎች የአውሮፓ መንግሥታት ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት ሁሉ በጣሊያን በኩል እንደሆነ ተስማምተው ተቀብለዋል፡፡

የጣሊያን መንግሥት በጣሊያንኛ የተጻፈውን ይዞ ኢትዮጵያ የጣሊያን መንግሥት ጥገኛ መሆንዋን ለሌሎች የአውሮፓ መንግሥታት አስታወቀ፡፡ ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ ያገኘች የመስላትን አዲስ ሥልጣን አስታወቀች፡፡ በውጫሌ ውል አንቀፅ 17 በጣሊያንኛ ትርጓሜው አማካይነት አፄ ምኒልክ የውጭ ግንኙነቱን በመሉ በጣሊያን በኩል ማድረግ ይገባዋል ሲሉ የመጨረሻ የቅኝ ግዛት ዕቅዳቸውን ገሀድ አውጡት፡፡ ነገሩ ሥር እየሰደደ ሲሄድ አፄ ምኒልክ የወጫሌ ውል አሥራ ሰባተኛው አንቀፅ በአማርኛ የተጻፈው በጣሊያንኛ ከተጻፈው የማይስማማ መሆኑን በመግለፅ ከመንግሥታት ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት በጣሊያን በኩል ብቻ እንዲሆን የሚያስገድድ ውል አለመፈረማቸውን ስለዘረዘሩና ጣሊያንም በዚያው ስለፀናችና ኢትዮጵያን ቅኝ ተገዥ አድርጋ ለመያዝ በማስቧ ምክንያት ሁለቱም ወደ ዓድዋ ጦርነት አመሩ፡፡ የዓድዋ ጦርነትን ለማካሄድ በአፄ ምኒልክ መሪነትና በእቴጌ ጣይቱ ብጡል አስተባባሪነት ኢትዮጵያውያን፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው ቋንቋ፣ አካባቢ፣ ሃይማኖትና ፆታ ሳይለያያቸው በአንድነት በመትመም ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀና የሠለጠነ ሠራዊት ይዞ የመጣውን የጣሊያን ወራሪ ኃይል በባዶ እግራቸው ተጉዘው በተለያዩ የጦር መሣሪያዎች ጦርና ጎራዴን ጨምሮ ድምጥማጡን አጥፍተው ደምስሰውታል። በኢትዮጵያና በጣሊያን ጦር መካከል የመጀመሪያው ውጊያ አምባ አላጌ ላይ ነበር፡፡ የዘመቻው ሁለተኛ ምዕራፍ የሆነው የመቀሌ ከበባ ነው፡፡ ጄኔራል ባራቴሪ የተባለው የጣሊያን ጦር አዛዥ ይመራ የነበረው ሠራዊት እ.ኤ.አ የካቲት ቀን 23 1896 በጀግኖቹ ቅድመ አያቶቻችን ዓድዋ ላይ ድል ተመታ፡፡ በዓድዋ ታሪካዊ ፍልሚያ የኢትዮጵያ የጦር አዛዦች ራስ አሉላ፣ ራስ ሚካኤል፣ ራስ መኮንን፣ ራስ መንገሻና ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ሲሆኑ በጣሊያን በኩል ደግሞ የነበሩት ጄኔራሎች ጁሴፔ ኤሌና፣ ቪቶርዩ ዳቦርሚዳ፣ ጁሴፔ አሪሞንዲና ሜቴኦ አልቤርቶኒ ነበሩ፡፡

ታሪክ ያለፈውን ትውልድ ገድል ሲያወሳ ሰላምን የተጐናፀፈው ትውልድ ምን ሠራ? ሰላምን ላወረሱ አባቶችና እናቶች ውለታውን በተግባር እንዴት መለሰ? በሌላስ በኩል ነፃነትንና ክብርን የወረሰው ትውልድ ለሚቀጥለው ትውልድ ምንን አወረሰ? ምን አዲስ ነገርን ፈጠረ? የሚሉትን ጥያቄዎች እንድናብሰለስል እንድናውጠነጥን የዓድዋ ድል ያስገኘውን ዓለም አቀፍ፣ አኅጉር አቀፍና አገር አቀፍ ፋይዳ ከዚህ እንደሚከተለው ተገልíDል፡፡

የዓድዋ ጦርነት ድል የፓን አፍሪካኒዝም መሠረት ነው፡፡ የዓድዋ ድል ለፀረ ኪሎኒያሊዝም ትግል መጠናከር የአፍሪካውያንን የትግል መንፈስ ያነሳሳ ከመሆኑም በላይ በቅኝ ግዛት ተይዘው ይማቅቁ ለነበሩ ካሪቪያንና አሜሪካ ውስጥ ለሚኖሩ ጭቁን ሕዝቦች ለነፃነታቸው መታገልና የሚያስፈልገውን መስዋዕት መክፈል ብቸኛው የነፃነታቸው መቀዳጃ መንገድ እንደሆነ በተግባር ትምህርት የሰጠ ክስተት ነው፡፡ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ፀረ ቅኝ አገዛዝ ተጋድሎ ወደ አዲስ ምዕራፍ የተሸጋገረው ከዓድዋ ጦርነት ድል በኋላ ነው፡፡ በዓድዋ ጦርነት ድል ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ በቅኝ ገዥ መዳፍ ከመውደቅ ነፃ ወጡ፡፡ የቅኝ ገዥነት ፍላጐት የነበራት አገር ከፍተኛ ሀፍረት ተከናነበች፡፡ ድሉ የአፍሪካ ጥቁር ሕዝቦች ድል ነው፡፡ ለአፍሪካውያንና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የአንድነትና የነፃነት ተምሳሌት ነው፡፡ በአውሮፓ ደግሞ የዓድዋ ድል አውሮፓውያንን ቅስማቸውን ሰብሯል፡፡ በአፍሪካ የመኖራቸውን የወደፊት ዕጣ ፈንታ አሳጥሯል፡፡ በቅኝ ገዥዎች ላይ መደናገጥና ፍርሃት ፈጥሯል፡፡ የቅኝ አገዛዝ ሥርዓት ከአፍሪካ እንዲወገድ አሳስቧል፡፡ በብዙ አፍሪካዊያን ልቦና የነበረውን ሥጋት በማስወገድ ተስፋንና ኩራትን በራስ መተማመንን አሰርፆባቸዋል፡፡ ታላቅ የተባሉትን አውሮፓውያንን በመፋለም ማሸነፍ ድል መቀዳጀት እንደሚቻል የዓድዋ ጦርነት ድል አደፋፍሯቸዋል፡፡ የዓድዋ ጦርነት ድል ለአፍሪካውያን የነፃነት ተጋድሎን የፈነጠቀ ነው፡፡ ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ግርማ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ እንድትሆን የተደረገው በዓድዋ ጦርነት ድል በመጐናፅፍ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት በመሆኗ ነው፡፡

የዓድዋ ድል የፓን አፍሪኒዝም ጉዞ መነሻና መቀስቀሻ እንዲሁም ያለፈው ትውልድ የክብር& የኩራትና የነፃነት ተጋድሎ ምልክት እንደሆነው ሁሉ አሁን ላለው ትውልድ ደግሞ ኮርቶ& በዓድዋ ድል የጋራ ታሪክ ተሳስሮ፣ የሀገረ ብሔር ግንባታውን የሚያፀናበት፣ በመንደርተኝነት አስተሳሰብ የማይደለልበት፣ አገራዊ አንድነቱን የሚጠብቅበት ከዓድዋ ድል ታሪክ ትምህርት መውሰድ አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡ ከምንም በላይ ድሉን ታላቅ የሚያደርገው መላ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ቆመው የጋራ ክንዳቸውን በጋራ ጠላታቸው ላይ መሰንዘራቸው ነውና በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምንኖር ኢትዮጵያውያን ስለአንድነት ትምህርት ልንወስድ ይገባል፡፡ በተጨማሪም ድሉ ዓይናችንን ገልጦልናል፣ የእኛም ድል ነው ከሚሉ አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ተባብረን ልናከብረውም ይገባል፡፡ የቀደሙ አባቶቻችንና እናቶቻችን ትተውልን ያለፉትን ታሪክ በመዘከር ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍና ለተተኪው ትውልድ ትምህርት እንዲሰጥ በውጭው ዓለም የተወለዱና ያደጉ ትወልደ ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ታሪክ እንዲያውቁና እንዲኮሩበት ማድረግን አስመልክቶ ያስተወሰኝን አንድ ነገር ልግለፅ፡፡ ይኸውም የኢትዮጵያ ውርስና  ቅርስ ማኅበር በሰሜን አሜሪካ የዋሽንግተን ዲሲ ከተማንና የሜሪላንድ ክፍለ አገር ሞንትገሞሪ አውራጃ አስተዳዳሪዎችን የዓድዋ ድል የተደረገበትን የማርች ወር “የዓድዋ መታሰቢያ ወር” ሆኖ እንዲያውጁ በማስደረግ ላለፉት ስምንት ዓመታት አመርቂ ዝግጅቶችን አካሂዷል። ዘንድሮም ለዘጠነኛ ጊዜ በዓሉን ሞንትገሞሪ አውራጃ ማርች 2020 የ“ዓድዋ መታሰቢያ ወር” ሆኖ እንዲዘከር ማወጁ የኢትዮጵያውያንና የትውልደ ኢትዮጵያውያን አስተዋፅኦ ያሳያል፡፡ የዓድዋን ድል በአዲስ አበባ ከሚገኙ የብዙ አገሮች ኢምባሲዎች ጋር በመተባበር ብናከብረው ድሉ ካለው የአገር ግንባታ ፋይዳ አልፎ ዲÝሎማሲዊ ፋይዳው ከፍተኛ ይሆናል፡፡ በመጨረሻም የዓድዋን ድል ዓመት ጠብቀን ከማክበር ባለፈ አገራዊ ተምሳሌትነቱንና ኢኮኖሚያዊ (የቱሪዝም ምንጭነቱን) አጉልተን ለሀገረ ብሔር ግንባታ እንጠቀምበት፡፡

ከአዘጋጁ– ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለፅን በኢይሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles