ኢትዮጵያ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ከ124 ዓመታት በፊት ከወራሪው የጣሊያን ሠራዊት ጋር የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. በዓድዋ ባካሄደችው ጦርነት ድል ማድረጓ ይታወሳል፡፡ ይህን በጥቁሩ ዓለም አንፀባራቂ የሆነውን ድል የሚዘክሩ መሰናዶዎች ከውጊያው ቦታ ዓድዋ እስከ አዲስ አበባ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ተዘጋጅተዋል፡፡
በዋዜማው በዓድዋ ከተማ ሶሎዳ ሆቴል የአክሱም ዩኒቨርሲቲ “የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የአንድነት መገለጫ ነው” በሚል መሪ ቃል የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል፡፡ በሌላ በኩል የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ “በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶችና የኢትዮጵያውያን ተጋድሎ ከጥንት እስከ ዛሬ” በሚል ርዕስ ዓውደ ጥናት ማዘጋጀቱ ታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማም በዋዜማው የካቲት 22 ምሽት 11፡30 ሰዓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር “ምሕረት ዋዜማ” የተሰኘ ሙዚቃዊ ቴአትር ለሕዝብ ይቀርባል፡፡ ቴአትሩን ያቀረበው ሰውኛ ፕሮዳክሽንና ኢንተርቴይመንት ሲሆን ተባባሪው የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ነው፡፡
ድርሰቱን ሚካኤል ሚሊዮን፣ ምንተስኖት እና መዓዛ ታከለ ሲጽፉት፣ ሚኪኤል ሚሊዮን አዘጋጅቶታል፡፡ ተዋናዮቹ ተፈሪ ዓለሙ፣ ተስፋዬ ገብረሃና፣ ሰለሞን ዓለሙ፣ መዓዛ ታከለ፣ ሚካኤል ሚሊዮን እና ሌሎች 150 ኢትዮጵያውያንና የውጪ አገር ባለሙያዎች ናቸው፡፡
ሰውኛ ፕሮዳክሽንና ኢንተርቴይመንት ‹‹ዓድዋ የዘመናዊ ዓለም ጉልህ የታሪክ ዕጥፋት የሆነ የተዛባ ሀቲት ያቀና፣ የሰው ልጅ ክብር የተገለጠበት የሰውነት ማህተም ነው›› በሚለው መሪ ቃሉ የዘንድሮውን የዓድዋ ድል በዓል ምክንያት በማድረግ የሰጠው ስያሜ ‹‹ክብረ ዓድዋ›› የሚል ነው፡፡ ሰውኛ የሙዚቃዊ ቴአትር፣ የፊልምና ቴሌቪዥን ፌስቲቫልን ማክበር የጀመረው የካቲት 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ሲሆን፣ ዝግጅቱን የሚያጠናቀው የካቲት 23 ከጠዋቱ 1፡30-5፡30 ከዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ ወደ ዓድዋ ዘመቻ መታሰቢያ ድልድይ በባዶ እግር ጉዞና የጎዳና ላይ ትርዒት እንዲሁም ከ7፡00 ሰዓት በእንጦጦ ቤተ መንግሥት በሚኖረው መሰናዶ ነው፡፡
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የበዓሉ ቀን ሰኞ የካቲት 23 “ኢትዮጵያዊነት” ዝክረ ዓድዋ በሚል መጠርያ ግጥም፣ ወግ፣ መነባንብ፣ ዲስኩርና ኮሜዲ ይቀርብበታል፡፡
በተያያዘ ዜና ጸሐፌ ተውኔት አንዱዓለም አባተ የጻፈው “ክተት ለሰላም በወረኢሉ” የወሎ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት መምህራን ተማሪዎችና የላሊበላ የባህል ቡድን ሙያተኞች በወረኢሉ መሰንበቻውን የተወኑት ሲሆን ሙሉ ዝግጅቱ በአማራ ቴሌቪዥን በዕለተ ቀኑ እንደሚቀርብ ደራሲው ገልጿል፡፡ “የዓድዋው ክተት ዳር ድንበርንና ነፃነትን ለማስከበር ነው፣ የአሁኑ ክተት ለሰላም ነው፤” ሲልም አክሏል፡፡
ዳግማዊ ምኒልክ ወራሪውን የጣሊያን ሠራዊት ለመመከት የመሀል አገር ሠራዊታቸውን “ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት” አስብለው ታሪካዊቷ ወረኢሉ እንዲገኝ ከቤተመንግሥታቸው ያስነገሩት ዓዋጅ የሚከተለው ነበር፡፡
“እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላትን አጥፍቶ ሀገርን አስፍቶ አኖረኝ፣ እኔም በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነው፡፡ ስለእኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፡፡ ከእንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም ሀገር የሚያጠፋ፣ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት፣ እግዚአብሔር የወሰነልኝን የባህር በር አልፎ መጥቷልና አሁን ግን ሀገሬን አሳልፌ አልሰጥም፡፡ ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረኢሉ ከተህ ተገኝ፡፡”
የተለያዩ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የዓድዋን በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረውታል፡፡ ከነዚህም አንዱ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ “ታሪክን ከታሪኩ ነቅ እንጀምር” በሚል መሪ ቃል የካቲት 20 ቀን በዓውደ ጥናት ያከበረው ሲሆን “ዓድዋና አንድምታው”፣ “ዓድዋ በታሪክ ዕይታ” የሚሉ ጥናቶችች ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸው ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ንጉሥ ታደሰ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፣ ዓድዋ የባርነትና የቅኝ ተገዥነትን መንፈስ በመስበር አፍሪካውያንና ጥቁር ሕዝቦችን ለላቀ ድል ያነሳሳ ነው። “የጥንት አባቶቻችን አይበገሬነት ለአሁኑ ትውልድ ለፍትሕ፣ ለነፃነትና ለእኩልነት የሚከፍለውን መስዋዕትነት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚረዳ የድል በዓል ነው፤” ሲሉም አስምረውበታል፡፡
“ይሁን እንጂ ከቅኝ ግዛትና ባርነት ተላቀናል ብንልም አሁንም በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ውስጥ እየገባን አገራችንም ይሁን አፍሪካ በምሁራን ድርቀት፣ በመልካም አስተዳደር እጦት፣ በእርስ በእርስ ጦርነቶች፣ በሙስናና ብልሹ አሰራሮች ተተብትበን የኅብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ መለውጥ አልቻልንም፤” ብለዋል።