Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊኬንያ የአህያ ዕርድን አገደች

ኬንያ የአህያ ዕርድን አገደች

ቀን:

ኬንያ በአገሪቱ የአህያ ቁጥር መመናመንን ያስከተለውን የአህያ ዕርድ ንግድ አገደች፡፡ በኬንያ እ.ኤ.አ. በ2012 የአህያ ሥጋና ቆዳ ምርትን ለቻይና ለማቅረብ ይቻል ዘንድ ሕጋዊ ያደረገችውን የንግድ ሕግ የሰረዘችው በአገሪቱ በተለይ የሴቶችን ሸክም በማገዝ ላይ የሚገኙ አህዮች ቁጥር እየተመናመነ በመምጣቱ ነው፡፡

የኬንያ ግብርና ሚኒስትር ፒተር ሙኒያ የንግድ ሕጉን መታገድ አስመልክተው በሰጡት መግለጫም፣ ከዚህ ቀደም የአህያ ዕርድን ለመፍቀድ የወጣው ሕግ ስህተት ነበር ብለዋል፡፡

ቢቢሲ እንዳሰፈረው፣ በርካታ በገጠሪቷ የኬንያ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች የቀዱትን ውኃና የሰበሩትን እንጨት የሚጭኑት በአህያ ነው፡፡ ሆኖም በአገሪቷ የአህያ ዕርድ ተግባራዊ ከሆነ ጀምሮ በተለይ የአገሪቱ ሴቶች የሥራ ጫና ተፈጥሮባቸዋል፡፡

በገጠር የሚኖሩ ኬንያውያን የአህያ ዕርድ ያቆም ዘንድ ሰሞኑን በናይሮቢ በሚገኘው ግብርና ሚኒስቴር ፊት ለፊት ተቃውሞ ያደረጉ ሲሆን፣ ከያዟቸው የተቃውሞ መፈክሮች መካከል ‹‹አህያ ሲሰረቅ ወይም ሲገደል ሴቶች የአህያን ሥራ ጨምረው ይሠራሉ›› የሚለው የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ነበር፡፡

የግብርና ሚኒስትሩም አህያ የማረድ ፈቃድ ያላቸው ባለሀብቶች ሥራውን ወደ ሌላ እንዲቀይሩ አሊያም እንዲዘጉ እንደሚደረግ በተናገሩት መሠረት፣ ውሳኔው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡

ሚስተር ሙኒያ እንደሚሉት፣ አህያ አርዶ በመሸጥ ከሚገኘው ገቢ፣ አህያ እያለ የሚሰጠው አገልግሎት ለሕዝቡ በጣም ጠቃሚ ነበር፡፡

በኬንያ የአህያ ዕርድ በመስፋፋቱ የአህያ ስርቆት እንዲንሰራፋ ከማድረጉም በተጨማሪ፣ በአህያ ጥቁር ገበያ ውስጥ የሚሳተፉ ደላሎችም የራሳቸውን ኔትወርክ ዘርግተው ነበር፡፡

በኬንያ አራት ሕጋዊ የአህያ ማረጃ ጣቢያዎች ሲኖሩ፣ ብሮክ ኢስት አፍሪካ የተባለው ዓለም አቀፉ የእንስሳት ሕክምና ድርጅት እንደገመተው፣ በኬንያ በየቀኑ በትንሹ አንድ 1,000 አህዮች ይታረዱ ነበር፡፡

በቻይና ለባህላዊ ሕክምናና ለምግብ የሚውለው የአህያ ቆዳና ሥጋ (በቅደም ተከተል) ፍላጎት ለማሟላት፤ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አህዮች ይታረዳሉ፡፡ ዘ ዶንኪ ሳንክቸሪ የተባለው መቀመጫውን እንግሊዝ ያደረገ በጎ አድራጎት ድርጅት እንደሚለውም፤ በየዓመቱ 1.8 ሚሊዮን የአህያ ቆዳ ይሸጣል፡፡ ፍላጎቱ ግን ከአሥር ሚሊዮን በላይ ነው፡፡

በቻይና የአህያ ቁጥር እ.ኤ.አ. በ1990 ከነበረው 11 ሚሊዮን አሁን ላይ ወደ ሦስት ሚሊዮን ያሽቆለቆለ በመሆኑ፣ በአገሪቱ ያለውን ፍላጎት ለማሟላት ቻይና ምሥራቅ አፍሪካ ላይ ዓይኗን መጣሏ አልቀረም፡፡

በኢትዮጵያ የአህያ ቄራ ለመክፈት የነበረው ጥረት በገጠመው ተቃውሞ ባይሳካም፣ የአህያ ጥቁር ገበያ ግን የአገሪቱ ሥጋት ነበር፡፡ የኬንያ የንግድ ዘርፉን መዝጋት ደግሞ ከዚህ ቀደም በየቀኑ በሕገወጥ መንገድ  ወደ ኬንያ ይጋዙ የነበሩ አህዮችን የሚያስቀርም ይሆናል፡፡

ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ቦትስዋና፣ ኒጀር፣ ቡርኪናፋሶ፣ ማሊና ሴኔጋል ወደ ቻይና የሚደረግ የአህያ ወጪ ንግድን ማገዳቸው ይታወሳል፡፡

በኬንያ የተሠራ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፣ የሚታረዱ አህዮች ቁጥር ከአጠቃላይ ውልደት መጠኑ በአምስት እጥፍ ይበልጣል፡፡ በሁለት ዓመታት ውስጥ ብቻ አራት የአህያ ቄራዎች 301,977 የኬንያ አህዮችን አርደዋል፡፡ በዚህ ከቀጠለ እ.ኤ.አ. በ2023 የኬንያ የአህያ ሀብት ሙሉ ለሙሉ ሊሟጠጥ ይችላል፡፡ ሁኔታው አህያቸውን እንደ አንድ የገቢ ምንጭ ለሚጠቀሙት ኬንያውያን ትልቅ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ ‹‹አህያችንን አንሸጥም›› የሚሉ ኬንያውን መኖር ደግሞ ለጥቁር ገበያ መስፋፋት መንገድ ከፍቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2018 1,000 አህዮች መሰረቃቸውን ሪፖርት ተደርጓል፡፡

ሰፊ የአህያ ሀብት ካላቸው ጥቂት አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ በትግራይ ክልል 886,103፣ በአፋር 125,671፣ በአማራ 3,279,179፣ በኦሮሚያ 3,419,932፣ በሶማሌ 200,639፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 82,228፣ በደቡብ 811,105፣ በጋምቤላ 2,150፣ በሐረር ክልሎች 14,356፣ በድሬዳዋ ከተማ 24,226 በጥቅሉ 8,845,589 አህዮች በኢትዮጵያ ይገኛሉ፡፡

በኬንያ ያለው የአህያ ሀብት መመናመን በኢትዮጵያ ደግሞ ሰፊ ሀብት መኖር ያባበላቸው በኬንያ የሚገኙ የቻይና ኩባንያዎች፣ ከኢትዮጵያ ቢባረሩም በእጅ አዙር ከኢትዮጵያ አህያ መውሰዳቸውን ቀጥለዋል፡፡ አንድ የቻይና ኩባንያ የአህያ ቄራ የከፈተው በኬንያና ኢትዮጵያ ድንበር ላይ ነው፡፡ ይህንንም ያደረገው የኢትዮጵያን አህዮች ቀረብ ብሎ ለማግኘት ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ በርካታ አህዮች ወደ ኬንያ በሕገወጥ መንገድ ይጓዛሉ፡፡ አንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፣ ረዥምና አድካሚ ጉዞ ያለ በቂ ምግብና ውኃ ሲጓዙ ብዙዎቹ ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡ 20 በመቶ የሚሆኑት መንገድ ላይ ይሞታሉ፡፡ በሞያሌና በኦሞ ኩራዝ በኩል እየተነዱ የሚወጡት አህዮችን ከየአካባቢው የሚሰበሰቡ ደላሎች ተበራክተዋል፡፡ በኬንያ ለሚታረዱ አህዮች 80 በመቶ የሚሆነው ከኢትዮጵያ የሚጓዙ ናቸው፡፡ ለአንድ አህያ የሚጠራው ገንዘብም እየጨመረ የሚሄድ በመሆኑ ገበያው አጓጊ ሆኗል፡፡ ስለዚህም አርሶ አደሩ ውኃ ማመላለሻና መጫኛ ትራንስፖርቱን አውጥቶ ይሸጥም ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...