በቅርቡ ሪፖርት ያደረጉትን ሊባኖስ፣ ባህሬን፣ ኦማንና አፍጋኒስታንን ጨምሮ በ34 አገሮች ውስጥ የገባው ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ኢትዮጵያ እንዳይገባ የተጠናከረ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ከጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በሰባቱ መግቢያዎች 191,707 በላይ የሚሆኑ መንገደኞች በሙቀት ልየታ ማለፋቸውንና፣ ከእነዚህ ውስጥ 4,821 በሽታውን ሪፖርት ካደረጉ አገሮች የመጡ መሆናቸውን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡ ኮቪድ-19 ወይም ኮሮና ቫይረስን አስመልክቶ የካቲት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ወቅታዊ መግለጫ የሰጠው ኢንስቲትዩቱ፣ በሁሉም አገር ውስጥ መግቢያ ጣቢያዎች ኢቦላና ኮቪድ-19ን በማጣመር 324,555 ሰዎች በሙቀት መለያ ማለፋቸውን አክሏል፡፡
በክትትል ላይ የነበሩ ነገር ግን 14 ቀናት የሞላቸው 390 ሰዎች ክትትላቸው የተቋረጠ ሲሆን፣ 829 የሚሆኑት ደግሞ ባሉበት ቦታ ሆነው የጤና ክትትል አየተደረገላቸው ይገኛል፡፡
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ መግለጫ እስከተሰጠበት የካቲት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ 12 አዳዲስ ጭምጭምታዎች ለኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል የደረሱ ሲሆን፣ በሁሉም ጥቆማዎች ላይ ማጣራት ተደርጎ የበሽታውን ምልክት ያላሳዩ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
ከጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ 72 ጭምጭምታዎች ለማዕከሉ ደርሰው፣ በሁሉም ጥቆማዎች ላይ ማጣራት መደረጉን፣ ከእነዚህም ጥቆማዎች 18ቱ የበሽታውን ምልክቶች በማሳየታቸውና የቻይና ጉዞ ታሪክ ስለነበራቸው በተለያየ ጊዜ በለይቶ ማቆያ ማዕከል እንዲቆዩና ሆኖም 18ቱን የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው መረጋገጡ ተገልጿል፡፡
በኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ኤባ አባተ (ዶ/ር) የሚመራው የቴክኒክ ግብረ ኃይል ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዶ የተለያዩ አቅጣጫዎች አስቀምጧል፡፡ የኢንስቲትዩቱና የክልል የድንገተኛ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ ሰጪ ማዕከል አስተባባሪዎች ስብሰባ አካሂደዋል፣ በሲዲሲ አፍሪካ ድጋፍ ባለሙያዎች ወደ ውጭ አገር ሄደው ስለ ድንበር ቅኝትና ኬዝ ማኔጅመንት ሠልጥነዋል፡፡
ለሁሉም ከልሎች አስፈላጊውን ግብዓቶች በማሟላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች እየተሰጡ ይገኛል፡፡ የተለያዩ ፕሮቶኮሎች ተዘጋጅተው ለሚመለከታቸው መሠራጨቱንም ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡
በዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርት መሠረት እስከ የካቲት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ይህ መረጃ እስከ ተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ያለው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 80,142 ሲሆን 2,698 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል፡፡
የኮቪድ-19 (የኮሮና ቫይረስ በሽታ) ምርመራ እንዴት ነው?
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀው፣ የኮቪድ-19ን (የኮሮና ቫይረስ በሽታ) ለመለየት የሞለኪዩላር ምርመራ የሚደረግ ሲሆን፣ ለቫይረሱ ልየታ የበለጠ ጠቃሚ የሆነው ለምርመራው የሚወሰደው የናሙና ዓይነትና ናሙናውን የምንወስድበት ጊዜ ነው፡፡ ምንም እንኳ ከበሽታው ጋር ያሉ ተጓዳኝ በሽታዎችን ለመለየት ሌሎች ምርመራዎች ቢያስፈልጉም ለኮቪድ-19 ሞለኪዩላር ምርመራ ትክክለኛ ዓይነት ናሙና ከትክክለኛ ቦታና በትክክለኛ ጊዜ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ የሞለኪዩላር ምርመራ ዓለማችን ከደረሰችባቸው ውጤታማና ተመራጭ ምርመራ ነው፡፡
ቫይረሱን ከመተንፈሻ አካል የሚወሰዱ ናሙናዎች ማለትም ከአፍንጫ፣ ከጉሮሮ፣ አክታ፣ ለመተንፈሻ አካል እርዳታ ወደ ሳንባ ከሚገባ ቱቦ የሚወሰድ ናሙና ወይም ኢንዶትራኪያል አስፓይሬት (endotracheal aspirate)፣ ብሮንኮ አልቪዮላር ላቫጅ (broncho alveolar lavage) እንዲሁም ከደም ሊወሰድ ይችላል፡፡ ቫይረሱን በናሙና ውስጥ በተሻለ ደረጃ ለማግኘትም ከአንድ ታካሚ ከተገኘ ናሙና የበሽታ ምልክቱን ካሳየ በ14 ቀን ጊዜ ውስጥ እንዲወሰድ ይመከራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ክሊኒካ ዲያግኖሲስና የሲቲ ስካን ምርመራ (CT – scan) በመጠቀም የሳንባ ጤንነትና የሚያመጣውን ችግር በማየትና ከተጋላጭነት መረጃዎች ጋር በማጣመር በሽታ አምጭው ኮቪድ-19 መሆን አለመሆኑን መገመት ይቻላል፡፡
በኢትዮጵያ ምርመራው ከተጀመረበት ጥር 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ከአንድ የኮቪድ-19 ምልክት ካሳየ ታካሚ ናሙናውን ከተወሰደ በኋላ ምርመራው ተደርጎ ውጤት እስኪወጣ በአማካይ አንድ ቀን ይቆያል፡፡ የምርመራው ውጤቱ ከደረሰ በኋላ ለኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በመላክ ለሚመለከታቸው አካላትና ለተጠርጣሪው ወይም ለተጠርጣሪው ቤተሰብ የማሳወቅ ሒደት ይከናወናል፡፡ ኅብረተሰቡ ስለወረርሽኙ በነፃ የጥሪ መስመር 8335 ላይ በመደወል በቂ መረጃ በማግኘት በሽታውን መከላከል ይኖርበታል፡፡