ሰላም! ሰላም! ‹‹ዘንድሮ እንደ እውነተኞቹ ጀግኖቻችን ቆራጦች መሆን ካልቻልን በሴራ ገመድ ተጠልፈን መውደቃችን አይቀርም፤›› አለኝ በቀደም አንድ ወዳጄ። የዓለም ወሬ ለመስማት በእጁ ሬዲዮ ይዞ፣ ዓይኑን ቴሌቪዥን ላይ ሰክቶ ቢውል ቢያድር የማይሰለቸው ታውቃላችሁ? የመንደር፣ የአገርና የዓለም ጉዳይ አቅል ያሳጣው ወዳጄ ሥጋት ገብቶት ይጨነቃል፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ዓለማችን የተጠናወታት የኮረና ቫይረስ በሽታ ከሰው ልጆች ክፋት የሚለየው፣ ሳያሰቃየን የሚገድል በመሆኑ ብቻ ነው፤›› ብሎኛል። ማለት መቼ ይታክተውና እሱ። እናም ያን ወዳጄን ትኩር ብዬ እያየሁት፣ ‹‹ምንድነው ደግሞ የሴራ ገመድ?›› አልኩት። ለራሴ እንኳን ፖለቲካው ኑሮዬ እየጠፋብኝ ተቸግሬያለሁ እኮ። ወድጄ መሰላችሁ? አብሬው አፈር የፈጨሁትና ውኃ የተራጨሁት አብሮ አደጌ ምን ዓይነት ቫይረስ እንደሚገባበት አላውቅም፣ ‹‹አንዱ በኢትዮጵያዊነት ማንነት የተጣላ ወፈፌ ሐበሻ ብለህ አትጥራኝ!›› እያለኝ ነዋ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊነትን እዚያው ብቻህን ተሸከመው፤›› ያለኝም አለ። ‹‹ኧረ ምን ጉድ ነው?›› ብዬ ሳልወድግ በግድ መሰል አገኘሁ ስል ደግሞ፣ “እኛ ቢዚ ነን!” የሚሉን አሉ፡፡ ለነገሩ አንዳንዴ ገለል ብሎ ፅሞና ማድረግ ቢያስፈልግም፣ ሐሞተ ኮስታራ ጀግና ወገኖቼን ማግኘቴ ግን አልቀረም፡፡
“ምን ተገኘ?” ካልኩ የአገሬ ጉዳይ አላስችል ብሎኝ፣ ስንቀሳቀስ፣ ‹‹አንበርብር አንተ እኮ ደላላ አትመስልም። ዘንድሮ ቢዝነስ ማለት ራስን መሸጥ ነው፤›› ሲለኝ የኖረ ወዳጄ በዘረፋ ቅሌት አሁን ‘ሸቤ’ ነው። ግን ‘የታሰሩትን ጠይቁ!’ አልተባለም? ስጠይቃቸው፣ ‹‹የተሰቀለ ባንዲራ አውርደን የወረደ ባንዲራ እየሰቀልን ነው፤›› ይሉኛል። እኔ የማንም አይገርመኝም። ብቻ የተቀደደ ካልሲያቸውን ሳይቀይሩ የተከበረ ባንዲራ የመቀያየር ፋሽን ውስጥ የገቡ ሰዎች ናቸው የሚያስገርሙኝ። እንዳይገባን እንጂ እንዲገባን ስለማንታገስ አይመስላችሁም? አልተግባባንም መሰለኝ። እሺ እሱን ተውትና ‹‹ሐበሻው ራሱ ሐበሻነት ሰለቸኝ እያለ፣ የሰው ሰው ሐበሻ ሊሆን ነው መሰል. . .›› ያለኝ ወዳጄ፣ የሥጋቱን ምክንያት አብራራልኝ። ‹‹ወንድሜ እኛ አገር አለን ብለን ነው በዚህ አታካች ኑሮ ላይ ታች የምንለው፡፡ ሌላው ደግሞ በአገራችን ላይ ዕጣ እየተጣጣለ ነው ግራ የሚያጋባን፤›› ሲለኝ ደነገጥኩ። በስንቱ ነገር መሰላችሁ በባዶ ስንዘል የተሰበርነው፡፡ አገርን እንደ ተራ ሸቀጥ የሚደልሉ የባዕዳን ተላላኪዎች ናቸው እኮ የሚያተረማምሱን፡፡ ለማንኛውም እነዚህን ከንቱዎች ሳስብ ስንት ገድል የፈጸሙ የዓለም ጥቁሮች ኩራት የሆኑትን የዓድዋ ድል ጀግኖችን ሳስብ እኔም ከመጠን በላይ ኩራት ይሰማኛል፡፡ በጀግንነት ካልተኮራ በምን ይኮራል ታዲያ!
ኩራት ተሰማኝ ብያችኋለሁ። ‹‹ይገርምሃል እኛ ኢትዮጵያውያን እንዳሁኑ ጀግንነትና ስመ ጥርነታችን ለመጠጥ ማስታወቂያ በግብዓትነት ከማገልገሉ በፊት. . .›› እያልኩ ስቀጥል፣ ‹‹ኧረ በእሱ አይደለም ነው ያልኩህ፤›› ብሎ አቋረጠኝ። አቤት የዘመኑ ሰው ዕድሜ ልኩን ባልተያዘ ነገር እያበጠ ቱስ ቱስ ሲል ይኖራል? ቀላል አሟሸሸኝ እንዴ? ‹‹አንበርብር ጀግኖቻችን እኮ ወደር የማይገኝላቸው የምንጊዜም ምርጦች ናቸው፡፡ እኛ አደራ በሊታ ሆነን በብሔር፣ በቋንቋ፣ በእምነት. . . እየተከፋፈልን ራሳችንን መሳቂያ እያደረግን እንጂ፣ የእነሱን ሩብ ወይም ሲሶ ያህል የአገር ፍቅር ቢኖረን የት በደረስን? በእርሻ፣ በንግድ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በምህንድስና፣ በሕክምና፣ በቱሪዝም. . . የትና የት በገሰገስን? ምን ዋጋ አለው እርስ በርስ ስንናከስ የጠላት መጫወቻ መሆናችን አይቀርም፡፡ የት መድረስ እየቻልን የድህነት ጎተራ ሆነን የእኛ ኑሮ የተመሠረተው በ‘የለም’ ነው። መብራት የለም። ውኃ የለም። ፍትሕ የለም። ሰው የለም። ዴሞክራሲ የለም. . .›› እያለ ሲበሳጭ እኔም ተጋባብኝ፡፡ እልህ ይሁን ወይም ንዴት ቱግ አደረገኝ፡፡ የአገሬ ጉዳይ ሲነሳ ይነዝረኛል፡፡ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት አገሬ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን፣ ለአገሬ ምን አደረግኩላት የሚለው ነው የሚያሳስበኝ፡፡ አገሬን እየቦጠቦጠ እንደ ሰንጋ በሬ የሚሰባውና ሊያፈራርሳት ቀን ተሌት የሚረባረበውን ሳይ ደግሞ እንደ ዕብድ ያደርገኛል፡፡ የእነዚያ የዓድዋ ጀግኖች መስዋዕትነት ሲታወሰኝ አቅሌን ያስተዋል፡፡ ‹አገር መውደድ ማለት ምንድነው ትርጉሙ. . .› የሚለውን ዜማ ሳስታውስ ዕንባዬ በጉንጬ ላይ ይወርዳል፡፡ ምን ልበላችሁ ለእኔ የአገር ጉዳይ እንዲህ ነው፡፡ ምንም ማድረግ አይቻልም!
ግድ የለም ነገም ሌላ ቀን ብለን እንለፈውና ወዳጄ የጀመረው ጉዳይ ከበድ ያለ ስለነበር ቀጥል አልኩ። በዘንድሮ ንዴት እንኳንም ጪስ ማውጫ አልኖረን። ቢኖረን ኖሮ ግን አስባችሁታል? አየር በመበከል በኢንዱስትሪ ብዛት የትና የት ከደረሱት አገሮች በላይ አየር በመበከል ካሳ ከፋዮቹ እኛ ነበርን። ሳይደግስ አይጣላ እሱ! ታዲያ በመንገዴ ባሻዬን ሳገኛቸው አላስችል ብሎኝ የውሎዬን ነገር ስነግራቸው፣ ‹‹ልጅ አንበርብር! ምድረ ከሃዲ የአገርን ጉዳይ ከጥፍር ቆሻሻው በታች አድርጎ ሲመፃደቅና ባልተፈጸመ ታሪክ የሐሰት ወሬውን ሲነዛ ምን እንደሚሰማኝ ታውቃለህ? ለራሴም ሆነ አገራቸውን ለሚያፈቅሩ ትልቅ ኩራት ሲሰማኝ እነዚያን ደናቁርት ደግሞ እንቃለሁ፡፡ ዓለም ያከበረውና ባርኔጣውን አንስቶ እጅ የነሳለትን የጀግኖቻችንን የዓድዋ ገድል ሳስብማ ነፍሴ በሐሴት ትሞላለች፡፡ አየህ በአገሩ ታላቅነት የሚኮራና በበታችነት ስሜት የሚሰቃይ ደረጃቸው እኩል አይደለም፤›› ሲለኝ ውስጤን ደስታ ወረረው፡፡ ለካ ደስታም ያስለቅሳል? ዕንባዬ መንታ መንታ ሆኖ ወረደ! ይኼማ ጮቤ ያስረግጣል!
ያው እንግዲህ ለማይሞላው ኑሮ ታዲያ ተፍ ተፍ እንዳልን ነው። ሕይወታችን በምን ይመሰላል ቢባል አንዱ “በገብረ ጉንዳን” ብሎ መለሰ አሉ። “የትኛው ግብራችን ነው አንተ ካልጠፋ ነገር ከጉንዳን ያመሳሰለን?›› ሲባል፣ “ሠልፋችን!” ብሎ አረፈው። የትራንስፖርት ችግር ያማረረው መሆን አለበት መቼም። ‹‹አይ! በባቡር አይሄድም?›› ብዬ ነበር እኔም እንደ እናንተ። ‹‹ዘመኑ እኮ የ‘ኮምፒቲሽን’ ነው የ‘ፒቲሽን’ ማሰባሰቢያ አይደለም፤›› አለኝ ሌላው፡፡ “እንዴት?” ብዬ ሳልጨርስ፣ ‹‹አታየውም እንዴ ፍጥነቱን? እንኳን እኛ ኤሊም በአቅሟ ለዘመናት የተጫናት ድንጋይ እንዲቀልላት ከሆነም እንዲነሳላት የት ሄጄ ልለምን በምትልበት የጥንቸሎች ዘመን፣ የባቡራችን ፍጥነት ፊርማ ለማሰባሰብ ካልሆነ ‘ቻፓ’ ለመሰብሰብ መቼ ይሆናል?›› አይሉኝ መሰላችሁ። ለነገሩ ባቡሩ አሁን መገስገስ ጀምሯል እኮ፡፡ እኔ ደግሞ ለተንኮሌ፣ “የምን ፊርማ?” ብዬ ነገር መጠምዘዝ። “የብሶት!” መቀጠል እነሱ። “ማነው የባሰው?” እኔ። “የባሰበት ነዋ!” እነሱ። “እንዲያ ስንባባል አለብኝ ጭልምልም” አለች ስትዘፍን ውላ ብታድር የማትሰለቸዋ። ለነገሩ መሰልቸትን ምን አመጣው አሁን!
ውሎ ማደር ቀርቶ በቅጽበት ዕይታ አንቅረን የምንተፋው ነገር በዝቷል እኮ ዘንድሮ። ለማንኛውም እንደ እኔ እንደ እኔ ‹‹አልበር እንዳሞራ ሰው አድርጎ ፈጥሮኝ. . .›› ማለቱን ትተን ከባቡሩ ራስ ወረድ ብንል ጥሩ ነው። ‘በአንድ ራስ ሁለት ምላስ’ ያስተዛዝባል። በዚያ፣ ‘ፈጣኑ ኢኮኖሚያችን፣ ንፋሱ ዕድገታችን እያላችሁ አስደፈጠጣችሁን’ ብለን ሳንጨርስ በዚህ፣ ጉረኛዋን ጥንቸል ትሁቷ ኤሊ በሩጫ ውድድር ቀድማት መግባቷ ሲተረትለት እንዳላደገ ትውልድ ‘ተኝታችሁ አስተኛችሁን’ ማለት ‘ፌር’ አይደለም። ደግሞስ እንነጋገር ከተባለ ዝግታ ነው ፍጥነት እየጨረሰን ያለው? ባህልና ወጉን ያሳሳው? ሰውን በወጣበት በየመንገዱ ያስቀረው? አብዮቱንስ ‘የልጅ ነገር አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ’ ያስባለው? ዝግመት ነው ፍጥነት? የእናንተ ነገር እኮ አይታመንም። ተከታታይ ፊልምና ድራማ ሰቅዞ ይዟችሁ ‘የለም! አብዮቱን ተወው አላለቀም’ ትሉ ይሆናል እኮ። ‘ይኼኔ ነው መሸሽ’ አሉ ብልጦች!
ኋላማ ሁለት ሲኖትራኮች ላሻሽጥ የምሆነውን አላውቅም። መቼ ዕለት ነው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ድድ ማስጫዎች ከመንደራዊነት ወደ ‘ዲጂታል’ ማኅበረሰባዊ ድረ ገጽነት የተለወጡለት የፌስቡክ ትውልድ፣ የሚለጥፋቸውን ፎቶዎች ሲያሳየኝ ነበር። ይኼው ‘ሲኖትራክ’ የተባለ ጦሰኛ ከባድ መኪና የኋሊት ተገልብጦና ፊቱን ወደ ሰማይ ቀስሮ፣ “አውሮፕላን መግጨት አማረኝ” ተብሎ ተጽፎበት አየሁና ሳቅ ሳቅ አለኝ። ልብ አድርጉልኝ። ሳቅ ሳቅ አለኝ እንጂ አልሳቅኩም። ‹‹ግዑዝ አፍ የለውም ብሎ የሰው ልጅ በገዛ ራሱ ጥፋት ታዛዡን አዛዥ፣ አገልጋዩን ጌታ የሚያደርግበት ሥልቱ ሳቅ ሳቅ ያስብላል እንጂ ያስቃል?›› ብዬ ከባሻዬ ልጅ ጋር ሳወራ፣ ‹‹ወደፊት ሕግና ሕግ አስከባሪውን አላፍር አልፈራ ላለው ‘ሲኖትራክ’ መፍትሔ ሆኖ መገኘቱ አይቀርም ብዬ አስባለሁ፤›› አለኝ። ‘እኛማ ተናንቀን ምድር ጠቦናል’ ነው እኮ ነገሩ። እኔነት አልገራ ሲል ታዲያ ምን ይሁን? እስኪ ቆይ! ለመሆኑ ይኼ ሲኖትራክ የሚሉት ነገር ለከተማ የተሠራ ጥሩንባ የለውም እንዴ? በከተማ መሀል አስደንጋጭ ጥሩንባውን ሲለቀው እኮ አንዱን ከሌላው እያላተመ ፈጀን፡፡ ትራፊክ ፖሊስ ይሰማል!
አዛውንቱ ባሻዬ መቼ ዕለት ነው አንድ ምሳሌ አጫወቱኝ። ሰውዬው ኑሮ አሰልቺና ድግግሞሽ ሆነበት። የዕለት ተዕለት ውጣ ውረዱን ለመርሳት አውጠነጠነ። ወደ አንድ መምህር ሄዶ፣ ‹‹በዚህ ሁኔታ መቀጠል አልችልም። የዓለም ነገር ሞላ ሲሉት ይጎድላል፣ ጎደለ ሲሉት ይሞላል። ከዚህ ወዲያ ከሚታየው ነገር ባሻገር ወደማይታየው ዓለም ገብቼ በአዕምሮ ነቅቼ ለመኖር ቆርጫለሁና ይምሩኝ፤›› ይላቸዋል። ‹‹መልካም! አሁን በመንገድ ስትመጣ ምን አይተሃል? አዕምሮህ ውስጥ የሚመላለሰው ምንድነው?›› አሉት። ‹‹በመንገድ አንድ አህያ አይቻለሁ። በአዕምሮዬም ያለው እሱ ነው፤›› አላቸው። ‹‹በል ተቀመጥና መጀመርያ አህያውን ከሐሳብህ አውጥተህ ጣል፤›› ይሉታል። ቢለው ቢለው አልቻለም። ኋላም ወደ መምህሩ ቀርቦ፣ ‹‹መምህር ሆይ! አቃተኝ፤›› ቢላቸው፣ ‹‹በመንገድ ላይ ያየኸውን የትም የማታውቀውን ያንተ ያልሆነውን አህያ ከሐሳብህ ማውጣት ካቃተህ፣ ታዲያ አንተ እንዴት ነው እኔነትህን አውጥተህ መጣል የምትችለው?›› አሉት ይባላል። አደራ ደግሞ ደላላው አንበርብር ነግሮንን ነው ብላችሁ ነገር ዓለሙን ረስታችሁ ከራሳችሁ ጋር እየተወዛገባችሁ እንዳታሳሙኝ!
በሉ እንሰነባበት። እንደ ነገርኳችሁ ‘ሲኖዎቹ’ በቀላሉም ባይሆን አልፍተውኝ ተሸጡልኝ። የድለላዬን ኮሚሽንም ተቀበልኩ። የለፋሁበት ነዋ። ወደ ቤቴ ሱክ ሱክ እያልኩ መጓዝ ስጀምር ድንገት በአንድ ሕንፃ መስታወት ውስጥ ራሴን ታዘብኩት። ልብስ ቀይሬ አላውቅም። ካፖርቴንም የመተካካት ፖሊሲው ሲያልፍ አልነካውም። ምናምን መስያለሁ። ‘እስከ መቼ ነው እየሠራሁ እንደማይሠራ ሳያምርብኝ፣ ሳለብስ፣ ሳልዘንጥ፣ መኪና ሳልነዳ፣ ቪላ ሳልሠራ፣ እንደ ሰው ‘ቦትል’ እያወረድኩ በውስኪ ሳልራጭ የምገፋው?’ ብዬ አስቤ ከፋኝ። ከማን አንሼ ስሜት ናጠኝ። ይኼኔ በድንገት ስልኬ ጠራ። ባሻዬ ናቸው። የማንጠግቦሽ ቡና አጣጭ፣ በሠፈሩ የተከበሩና የተፈቀሩ ወይዘሮ ማረፋቸውን ባሻዬ አረዱኝ። ስከንፍ ወደ ባሻዬ። ስደርስ፣ ‹‹እንጃ ለማንጠግቦሽ እንዴት ብለን እንደምናረዳት አላውቅም፤›› አሉኝ። ‹‹ምን አገኛቸው ይባላል? ደህና አልነበሩ እንዴ ትናንት?›› ስላቸው ባሻዬ ‹‹ደህናማ ነበሩ። የሙዝ ልጣጭ ነው አሉ አንሸራቷቸው ወድቀው በዚያው የቀሩት፤›› ሲሉኝ ክው። የአንዱ ጥጋብ የአንዱ መውደቂያ የሆነበት ዓለም እንደ አዲስ አስደነገጠኝ። ለነገሩ ስንቱ ጥጋበኛ በጫረው እሳት አይደል እንዴ ንፁኃን ወገኖቼ የሚለበለቡት!
ከጥቂት ሰዓታት በፊት ሰው መሆኔ ሳይሆን በፋሽን፣ በአበላልና በአጠጣጥ ከሰው ማነሴ ሲያበሳጨኝ የነበርኩት ሰውዬ፣ የታቆረ ውኃ ውስጥ ተነክራ እንደ ወጣች ድመት ቀልቤ ተገፈፈ። ኋላም ብዙ ሰማሁ። አንዱ፣ ‹‹እንጀራ በልተው ከመጥገብ አልፈው ፍራፍሬ መመገብ የጀመሩት ጎረቤቶቻችን እነማን ይሆኑ?›› ሲል ሌላው ደግሞ፣ ‹‹ኪሎ ሙዝ ስንት ገባ ይሆን እናንተ?›› ሲባባል አይቻሉ ባዩ ደግሞ፣ ‹‹ሙዙን የበላው የሠፈር ሰው አይደለም አልፎ ሂያጅ ባለመኪና ልጦ ጥሎት ነው፤›› አለ፡፡ “አይተሃል?” ሲባል “አይቻለሁ!” ብሎ ሲምል ሲገዘት ብዙ ነገር አየሁ፣ ሰማሁ። ብዙ ብዙ ነገር ተገነዘብኩ፡፡ ዳሩ አለሁ ሲሉ መቀጨት ቅርባችን ሆነና ሰው ከመሆናችን በፊት በእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ለእሽቅድምድም ስንናጭ ትንታ አቅም ገዝታ፣ የሙዝ ልጣጭም ሰበብ ሆና ያዘዘበት ና ተብሎ ይህችን ዓለም ሳይወድ በግዱ ይሰናበታታል። ይኼን እየሰማ ይኼንን እያየ ቋሚ ዕንባን አብሶ ዳግም ይራመዳል፣ ዳግም ይነሳሳል፣ ይፎካከርማል። ለዚህ እኮ ነው በትዝታ ፈረስ ወደኋላ እየሄዱ ታሪክን መበርበር የሚያስፈልገው፡፡ የፈለገውን ያህል ዘመኑና ገዥው ቢከፋ ኢትዮጵያዊ ለእናት አገሩ መሰዋት ብርቁ አልነበረም፡፡ የዓድዋ ጀግንነት ሲታወስ የዚያን ዘመን መንፈስ ይታደሳል፡፡ እንደገና ያነቃቃል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ክብር ነው፡፡ ጀግንነትም ውርስ ነው፡፡ መልካም ሰንበት!