በተመስገን ተጋፋው
ብዙዎቹም የውኃ መያዣ ፕላስቲካቸውን ለሁለት ቆርጠውታል፡፡ ይህም በውስጡ የጨመሩትን ማስቲሽ እንደ ልብ ለመማግ አስችሏቸዋል፡፡ ወታደር ትጥቁ እንደማይለየው ሁሉም ሕፃናትና ወጣቶች ከእጃቸው የማይለየውን ፕላስቲክ አንዴ ባፋቸው አንዴ ባፍንጫቸው ይስቡታል፡፡ በየፊናቸው ቁጭ ብለዋል፡፡ አንዳንዶቹ ጫት አንዳንዶቹ ሲጋራ ይዘዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ አላፊ አግዳሚውን እየተከተሉ አንድ ብር ሙይልኝ፣ ሙላልኝ የሚሉ ናቸው፡፡
በቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ ከዚህ ቀደም በተለየ መልኩ የሚርመሰመሱት ጎዳና ተዳዳሪዎች ብዙ ናቸው፡፡ መሸት ሲል ደግሞ ብዛታቸው ይጨምራል፡፡ በቅርብ ጊዜ ወደ ጎዳና ሕይወት እንደተቀላቀሉ ፊታቸው ላይ ያለው ገጽታ የሚናገርባቸውን ሴቶችና ሕፃናት ማየቱም ተለምዷል፡፡ የሌሊቱን ብርድ ለመቋቋም ማስቲሽና ሌሎች ባዕድ ነገሮችን ከመጠቀም ውጭ አማራጭ ማጣታቸውንም በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡ ማስቲሽ የሚምጉትም ለብርድ ብቻ ሳይሆን ከረሀብና ከፀሐይ ለመሸሸግ ምናልባትም ያሳለፉትን ሕይወት ለመርሳት እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ አጠገባቸው ስንጠጋ ብዙዎቹ አንድ ላይ ግር በማለት ውርር አደረጉን፡፡
‹‹አባት ምግብ ግዛልኝ፣ እናት ብር ስጪኝ . . .፤›› የሚሉ ቃላትን በመወርወር የሚፈልጉትን መጠየቅ ጀመሩ፡፡ አብዛኛቹም ሕፃናትና ታዳጊዎች ሲሆኑ፣ ዕድሜያቸውም በአሥራዎቹ የሚገመት ነው፡፡ በግምት 11 ዓመት የሚሆነው ልጅ ጠጋ ብለን፣ ከየት ነው የመጣኸው ስንለው? ከዓላማጣ እንደመጣ በሚጎተት ድምፁ ነገረን፡፡ ሁኔታው ማስቲሽ መሳቡን ያሳብቅ ነበርና በማግሥቱ ጠዋት ላይ አግኝተን በድጋሚ አወራነው፡፡ በዚህ ጊዜ አነጋገሩ መደበኛ ነበር፡፡ ከቤተሰቡ ጋር በተፈጠረው ግጭት አዲስ አበባ እንደመጣም አስረዳን፡፡
ከበርካታ ወንድ ጎዳና ተዳዳሪዎች መካከል ሦስት ሴቶች አግኝተን ነበር፡፡ ሁለቱ ሴቶች የስድስት ወርና የአምስት ወር ነፍሰ ጡር መሆናቸውን ነግረውናል፡፡ የልጅነት ዕድሜያቸውን ብዙ ሳያጣጥሙ ወደ ጎዳና ሕይወት መግባታቸው ቢያናድዳቸውም፣ ከዚያ የበለጠ ግን የራሳቸውን ችግር ሳይፈቱ የልጅ እናት ለመሆን መንገድ ላይ መሆናቸውን ሲያስቡት እንደሚያበሳጫቸው ገልጸዋል፡፡
የራስ ነገር ሳይዙ ሌላ ሕይወት ውስጥ መግባት ከባድ በሆነበት በአሁኑ ጊዜ ማርገዛቸው ሐሳብ ውስጥ ከቷቸዋል፡፡ ቤተሰብ ላይ እያሉ ትምህርታቸውን ይከታተሉና የተሻለ ሕይወት ይኖሩ እንደነበር፣ ከቤተሰባቸው ጋር በመጋጨት ወደ ጎዳና ሕይወት እንደወጡና በጎዳና ላይ መኖር ከጀመሩ ዓመታት እንዳስቆጠሩ ያስረዳሉ፡፡
ጎዳና ተዳዳሪዎች ከሚያደርጓቸው ድርጊቶች አንፃር በኅብረተሰቡ ዘንድ ብዙም ተቀባይነት ባይኖራቸውም፣ ባደረጉት ድርጊት የሚፀፀቱ፣ ቤተሰብ ጋር መመለስ የሚፈልጉ፣ ነገር ግን ይህን ማሳካት ያቃታቸው አግኝተናል፡፡ ወደ ቤተሰቦቻቸው ተመልሰው ለመሄድም በጣም እንደሚከብዳቸውና ከዚህ በፊትም ለመመለስ ሞክረው እንዳልተሳካላቸውና አሁን ያሉበት ሁኔታም ልጅ ወልዶ ለማሳደግ ቀርቶ ለራሳቸውም እንዳቃታቸው ገልጸዋል፡፡ ለሚመጣው አዲስ ሕፃን ኢትዮጵያዊነትን ሳይሆን ጎዳናዊነትን ማውረሳቸውም ይቆጫቸዋል፡፡
እንደ አብዛኛዎቹ ሴት ጎዳና ተዳዳሪዎች እነዚህኛዎቹ ራሳቸውን ከተለያዩ ወንዶች ጥቃት ለመከላከል ብለው የራሴ ከሚሏቸው ተጠግተው፣ የጎዳና ሕይወትን እየገፉ የነበረ ቢሆንም፣ የአንዷ ጓደኛ እስር ቤት መግባቱ ሌላ ፈተና ከቷቸዋል፡፡
የሚወስዱት አደንዛዥ እፅ በእርግዝናው ላይ የጤና ችግር ይፈጥርብናል የሚል ሥጋት ቢፈጠርባቸውም፣ ማስቲሹን ከመማግ አልተቆጠቡም፡፡ የፅንስ ክትትል ደግሞ በእነርሱ ዘንድ የማይታሰብ ነው፡፡
አንድ እናት ከእርግዝና ጀምሮ እስክትወልድ ክትትል ማድረግ ለእሷም ሆነ ለፅንሱ ጤንነት ወሳኝ እንደሆነ ከጤና ሚነስቴር ጀምሮ እስከ ጤና ቢሮ ያሉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ የሚናገሩት ቢሆንም፣ ይህ ለጎዳና ልጆች የሚደርስበት መንገድ የለውም፡፡
ወረርሽኝ ከገባ ወይም ክትባትን አስመልክቶ አልፎ አልፎ ወደነሱ ጎራ የሚል ቢኖርም፣ በእንዲህ ዓይነቱ ጊዜ ግን ትኩረት የሚሰጥ የለም፡፡ ጎዳና ተዳዳሪዎቹም ጤና ተቋም መሄድን አስበውት የሚያውቁት ጉዳይ አይደለም፡፡
ከሆቴል ቤት በመለመንና ከሰዎች በሚቀበሉት ብር በመግዛት ረሃባቸውን የሚያስታግሱት ጎዳና ተዳዳሪዎች አንዳንድ ጊዜ የሚላስ የሚቀመስ ሲያጡ ማስቲሽና ቤንዚን በመሳብ ራሳቸውን በመርሳት እንደሚያሳልፉ ገልጸዋል፡፡ በዚህ መንገድ እየኖሩ የት እንደሚወልዱና ልጆቹም እንዴት እንደሚያድጉ ሲያስቡ ከፊታቸው ትልቅ ፈተና እንደሚገጥማቸው አስረድተዋል፡፡
ብርድ፣ ዝናብ፣ ፀሐይ ሲፈራረቅባቸውና የሚላስ የሚቀመስ ሲያጡ መፈጠራቸውን እንደሚጠሉ፣ በእነሱ የደረሰው ዕጣ ፈንታ በልጆቻቸው ላይ ሊደርስ እንደሚችል ሲያስቡ፣ ከፊታቸው ከባድ ፈተና እንደሚጠብቃቸው ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ጎዳና ላይ የሚኖሩ ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም እምብዛም ጎዳና ተዳዳሪዎች የማይታዩባቸው ሥፍራዎች ተበራክተዋል፡፡ ሕፃናት ጎዳና ተዳዳሪዎችም በየአካባቢው ሞልተዋል፡፡
በአገሪቱ መቶ ሺሕ ያህል ጎዳና ተዳዳሪዎች እንደሚኖሩ የሚገመት ሲሆን፣ በአብዛኛው አዲስ አበባ የሚገኙ ናቸው፡፡ ለበርካታ ዓመታት ጎዳና ተዳዳሪነትን ለመቆጣጠር ብሎም ለማስቀረት የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ቢባልም፣ ለዚህ የበቃ የአሠራር ሥርዓት እስካሁንም አልተዘረጋም፡፡
በአብዛኛው ከኦሮሚያ፣ ከባህር ዳር፣ ከዝዋይ፣ ከመቐለ፣ ከጎንደር፣ ከአዳማ (ናዝሬት) እና ከደቡብ ክልል ከተሞች የሚፈልሱትን ጎዳና ተዳዳሪዎች ሕይወት ለመቀየር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) አነሳሽነት በአዲስ አበባ የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎችን የማንሳት ሥራ መጀመሩ የሚታወስ ነው፡፡
ጅማሬውንም ከግብ ለማድረስ የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የጎዳና ተዳዳሪዎችን የማንሳት ሥራ ይሠራል፡፡
የማኅበራዊ ሴፍቲ ኔት ኑሮ ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ እንደሻው አበራ እንደገለጹት፣ በ2012 ዓ.ም. መንፈቅ ዓመት ላይ ከዓለም ባንክ ጋር በመሆን በጎዳና ላይ ያሉ በጎ ፈቃደኛ ሕፃናትን ለማንሳት እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
4,132 ሕፃናት ለማንሳት ዕቅድ የተያዘ ሲሆን፣ ከጥቅምት እስከ ኅዳር 2012 ዓ.ም. ድረስ 1,256 ጎዳና ተዳዳሪዎችን ማንሳት እንደተቻለና የቀሩትንም የጎዳና ተዳዳሪዎች እስከ ዓመቱ መገባደጃ ድረስ ለማንሳት እንደሚሠሩ አክለዋል፡፡
የተሰበሰቡት ሕፃናት የሚፈልጉትን መሠረታዊ ፍላጎት ለማሟላትና ክትትል ለማድረግ ስምንት ድርጀቶችን መምረጣቸውንና ወደፊት የጎዳና ተዳዳሪዎችን ቁጥር ለመቀነስ በዘርፉ ላይ ሁሉንም ያማከለ ሥራዎችን ለመሥራት ዕቅድ መያዛቸውንም አስታውሰዋል፡፡
የማኅበራዊ ደኅንነት ልማት ማስፋፊያ ዳይሬክተር ወ/ሮ አበበች ጥላሁን በበኩላቸው ዘንድሮ የጎዳና ተዳዳሪዎች ፍልሰት ለመቀነስ እየተሠራ ያለው ሥራ አመርቂ ውጤት እንዲኖረው ለማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ 2,000 ሰዎችን ለማንሳት ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ዕቅዱንም ተግባራዊ ለማድረግ 377 የጎዳና ተዳዳሪዎች ማንሳት መቻሉን፣ 1,643 ደግሞ እስከ ነሐሴ 2012 ዓ.ም. መጨረሻና ከዓለም ባንክ ጋር ተደምሮ 6,132 የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለማንሳት እየሠሩ እንደሚገኙም አክለዋል፡፡
ቼሻየር፣ ፊንፊኔ፣ የካቲት 66፣ የካ ግሎባል በሚባሉ ማገገሚያ ተቋማት ላይ 360 ጎዳና ተዳዳሪዎች እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡ 200 የሚሆኑት በኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ካምፓኒ፣ አዲስና ብድር ቁጠባ፣ ኤሲኤንቢ ጋር በመተባበር የተለያዩ የሙያ ሥልጠናዎችን መስጠቱና ሃያ ማኅበሮችን መቋቋማቸውን፣ በስምንት ክፍለ ከተሞች ውስጥ ተደራጅተው ለመሥራትና በተመረጡ የመሥሪያ ቦታዎች ላይ ያገለገሉ የከተማ አውቶቢሶችን በመጠቀም ወደ ሥራ ለመግባት በሒደት ላይ መሆናቸውን ወ/ሮ አበበች ተናግረዋል፡፡
35 የሚሆኑት በግል ተደራጅተው ከወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ተጠቃሚ በመሆን ሥራ በመጀመር ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለዋል፡፡ 40 የሚሆኑ ደግሞ በመንገድ ትራንስፖርትና በአዋሽ ወይን ጠጅ ድርጅቶች ላይ የሥራ ቅጥር ተፈጽሞላቸው ራሳቸውን ችለዋል ተብሏል፡፡ 85 በተለያየ ሙያ ሠልጥነው የሠለጠኑ ሥራ እየተፈለገላቸው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ወደ ቤተሰቦቻቸው በመመለስ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ቢደረግም አብዛኞቹ ጎዳና ተዳዳሪዎች ወደ ካምፕ ገብተው ለመኖር ፈቃደኛ አለመሆናቸውንና ከዚህ በፊትም ለማንሳት በተደረገው ሥርዓት ላይ ብዙ ችግሮች መፈጠራቸውን ወ/ሮ አበበች ተናግረዋል፡፡
የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ ፍሰቱ እየጨመረ በመምጣቱ መንግሥት ግንባታዎችን በማስገንባት ተደራሽ ሥራዎችን ለመሥራት ዕቅድ ይዟል፡፡
ሕፃናት፣ ሴቶችና ሌሎችም የማኅበረሰብ ክፍሎችን ከጎዳና ሕይወት ማንሳት ለመንግሥት ብቻ የማይተው መሆኑን ሁሉም ቆም ብሎ ማሰብ የሚጠበቅበት ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ሕፃናትና ታዳጊዎች ያሉበትን ሕይወት ማስተካከል የሁሉም ግዴታ እንደሆነ ይታመናል፡፡
ልጆቹ ጎዳና ላይ እንደወጡ የሚያሳይ የተጠናከረና መፍትሔ ጠቁሞ ወደተግባር የተለወጠ ጥናት ባይገኝም፣ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚዊ ችግሮች ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ለመገመት አይከብድም፡፡ ልጆቹም የኢትዮጵያዊነት ኑሮን ሳይሆን የጎዳናዊነት ኑሮን እየገፉ በመሆኑ መንግሥት ይህንን ለመቀልበስ ሥር ነቀል ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡