Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት በሲሚንቶ ኢንዱስትሪ የውጭ ኢንቨስትመንት ላይ የጣለውን ክልከላ አነሳ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በርካታ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በመገንባታቸው ምክንያት የገበያ እጥረት እንዳይፈጠር በመሥጋት፣ እ.ኤ.አ. በ2012 የውጭ ኢንቨስተሮች በሲሚንቶ ኢንዱስትሪ እንዳይሰማሩ መንግሥት የጣለውን ክልከላ አነሳ፡፡

የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሃላላ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ከፍላጎት በላይ ኢንቨስትመንት ተፈጥሯል በሚል ዕሳቤ የውጪ ኢንቨስትመንት መቀበል ቆሞ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በተካሄደው ጥናት ግን የሲሚንቶ ምርት እጥረት እንዳለና ዋጋውም በከፍተኛ መጠን በማሻቀቡ፣ የኮንስትራክሽን ዘርፉን እየጎዳው እንደሆነ ታይቷል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ኢንስቲትዩቱና የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጉዳዩን በዝርዝር ለመንግሥት በማቅረብ፣ በውጭ ኢንቨስትመንት ላይ የተጣለው ክልከላ እንዲነሳ ተወስኗል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

ውሳኔው የተላለፈው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሲሆን፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ በፀደቀው የተሻሻለው የኢንቨስትመንት አዋጅ እንዲካተት ተደርጓል፡፡

አጠቃላይ የአገሪቱ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የማምረት አቅም በዓመት 17.1 ሚሊዮን ቶን ሲሆን፣ ዓመታዊ የሲሚንቶ ምርት ፍላጎት 12 ሚሊዮን ቶን ደርሷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ በዓመት 8.9 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ በማምረት ላይ ይገኛሉ፡፡

አቶ ሳሙኤል 17.1 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም የተፈጠረ ቢሆንም፣ ፋብሪካዎቹ በተለያዩ ምክንያቶች የማምረት አቅማቸውን ከ50 በመቶ በላይ መጠቀም ተስኗቸዋል ብለዋል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረትና መዋዠቅ፣ የውጭ ምንዛሪና የመለዋወጫ እጥረት፣ በፀጥታ ችግር ምክንያት የማዕድን ግብዓትና የተመረተውን ምርት የማጓጓዝ ችግር በዋናነት ተጠቃሽ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ሐሙስ የካቲት 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ለባለድርሻ አካላት ባቀረበው የስድስት ወራት ቅድ አፈጻጸም ሪፖርት፣ ከዘርፉ ወጪ ንግድ ከቅዱ ማሳካት የቻለው 25 በመቶ ብቻ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ከዘርፉ ወጪ ንግድ በስድስት ወራት ውስጥ 23.4 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ቢያቅድም፣ ሊገኝ የቻለው 5.6 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደሆነ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

ለታየው ዝቅተኛ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ምክንያቱን ያስረዱት አቶ ሳሙኤል፣ በዋናነት ወደ ውጭ የሚላከው የሲሚንቶ ምርት መሆኑን ጠቁመው፣ በአገር ውስጥ ገበያ በተፈጠረው የሲሚንቶ እጥረትና የዋጋ ንረት ምክንያት ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ምርታቸውን ኤክስፖርት ከማድረግ ይልቅ፣ በአገር ውስጥ ገበያ በመሸጥ ላይ በመሆናቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በኬሚካልና የግንባታ ግብዓቶች ምርት ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች በውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ በጉምሩክ አሠራር በምርት ጥራት ደረጃ ማረጋገጫ አሰጣጥ ዙሪያ የሚያጋጥማቸውን ችግሮች ለኢንስቲትዩቱ አመራር አቅርበዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች