ለስድስት አሠርታት ያህል በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ ተቋማት በኢኮኖሚ (ምጣኔ ሀብት) ባለሙያነታቸው ከፍ ያለ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ በተለይ ከ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ በኋላ፣ ከሩብ ምዕት ዓመት በላይ የኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥትንና ተከታዩን ፌዴራላዊ ሪፐብሊክን በከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪነት ያገለገሉት አቶ ነዋየ ክርስቶስ ገብረአብ ናቸው፡፡ በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ መጀመርያ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን (1923-1967) በኢትዮጵያ ልማት ባንክና በፕላን ኮሚሽን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሠርተዋል፡፡
በ1960ዎቹ አጋማሽ ባህር ማዶ በመዝለቅም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድ ኢንቨስትመንትና የልማት ጉዳዮች ኮንፈረንስ በኢኮኖሚክስ ኦፊሰርነት፣ በዩኔስኮ ሥር በሌሴቶ የትምህርት ዕቅድ አማካሪ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በመቀጠልም በተመድ የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) አማካሪ፣ በዓለም ምግብ ድርጅት (ፋኦ) እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ ሠርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ለውጥን ተከትሎ አዲስ አበባ የተመለሱት አቶ ነዋይ፣ ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ በጡረታ እስከ ተሰናበቱበት ጊዜ ድረስ በተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነቶች አገልግለዋል፡፡ በሽግግር መንግሥት የፕሬዚዳንቱ የኢኮኖሚ አማካሪ፣ ፌዴራላዊ ሪፐብሊኩ ሲመሠረትም ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋና የኢኮኖሚ አማካሪና የአማካሪዎቹ ቡድን መሪ በመሆን፣ ሁለቱን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች አቶ መለስ ዜናዊና አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን አማክረዋል፡፡ በዚሁ ረዥም የአገልግሎት ዘመናቸው ከሽግግሩ ጊዜ ጀምሮ በአገሪቱ ሥራ ላይ የዋሉት ተከታታይ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ የልማት ስትራቴጂዎች ቀረፃ፣ ግምገማና ምዘና ሒደት ላይ ጉልህ ሚና ነበራቸው፡፡ የተከማቸ ብድር ጫና የነበረባቸውን ደሃ አገሮች ለማገዝ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ እ.ኤ.አ. በ1996 የጀመሩት “Heavily Indebted Poor Countries Initiative” በተባለ ፕሮግራም መሠረት ከአበዳሪ ተቋማትና አገሮች ጋር ተደራድሮ ኢትዮጵያ የዕዳ ስረዛ ዕድሉ ተጠቃሚ እንድትሆን ለማድረግ ኃላፊነት የተሰጠው ቡድን አባል በመሆን ባደረጉት ጥረት፣ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዕዳ ስረዛ ተጠቃሚ እንድትሆን አድርገዋል፡፡
በወሳኝ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ለመምከርና ለመወሰን የተቋቋመው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት የሚመራው የማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ማገልገላቸው ይወሳል፡፡
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ስትራተጂ በምርምርና ጥናት የታገዘ እንዲሆን ለማድረግ የኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ሲቋቋም፣ በሚኒስትር ማዕረግ በዋና ዳይሬክተርነት በማደራጀትና በመምራት በአፍሪካ አሉ ከሚባሉ ቀዳሚ የምርምር ተቋማት አንዱ እንዲሆን በማድረግ፣ በተለይም በሰው ኃይል ግንባታ ያደረጉት ጥረት በአገሪቱ ከነበሩት ጥቂት ዩኒቨርሲቲዎች የላቀ ውጤት አምጥተው የጨረሱ ወጣት ምሩቃንን አወዳድሮ በመምረጥ፣ በአውሮፓና እስያ ዕውቅ ዩኒቨርሲቲዎች እስከ ፒኤችዲ በማስተማር በአገሪቱ እያገለገሉ የሚገኙ በርካታ ወጣት ተመራማሪዎችን ለማፍራት አስችለዋል፡፡
ከ1996 እስከ 2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንግሥትን በመወከል የአፍሪካ ልማት አዲስ አጋርነት (ኔፓድ) አስተባባሪ ኮሚቴ አባል፣ ቀጥሎም ሊቀመንበር በመሆን ሠርተዋል፡፡ በተጨማሪም በዚሁ ዘመን የአፍሪካ የጋራ ግምገማ መድረክ (ኤፒአርኤም) አባል በኋላም ሊቀመንበር በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከ2001 እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ በአፍሪካ ኅብረት በኩል በቡድን 20 ስብሰባዎች አፍሪካን ወክለው በመገኘት ሲሳተፉ፣ የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚችል የረዥም ጊዜ የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ቀረፃ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ሰብሳቢ ነበሩ፡፡ ከ2002 እስከ 2003 ዓ.ም. የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ በሰየሙትና የኖርዌይና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በጋራ ይሰበስቡት በነበረው የፋይናንስ አማካሪ ቡድን አባል ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከ1995 እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ የመንግሥትና የለጋሽ ድርጅቶች ኮሚቴ የዕርዳታ አፈጻጸም የቁጥጥርና የአስተዳደር ማሻሻያ ሥራ ውስጥ ሰብሳቢ ሆነው ሠርተዋል፡፡ ከ1996 እስከ 2001 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የንግድ ውድድር ኮሚሽን አባል በመሆን ያገለገሉት አቶ ነዋየ ክርስቶስ፣ የትግራይ ልማት ማኅበር የቦርድ አባልም ነበሩ፡፡
ከአባታቸው ከአቶ ገብረአብ ቢያድግልኝ፣ ከእናታቸው ወ/ሮ እሌኒ መንገሻ ጥቅምት 17 ቀን 1934 ዓ.ም. በድሮ አጠራር በትግራይ ጠቅላይ ግዛት በዓድዋ አውራጃ ልዩ ስሙ ማይምሻም በተባለ ቦታ የተወለዱት አቶ ነዋየ ክርስቶስ፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ካዛንችስ አስፋ ወሰን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በኮተቤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በከፍተኛ ማዕረግ አጠናቀዋል፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ይባል በነበረው (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) በመግባት በ1954 ዓ.ም. በኢኮኖሚክስ የመጀመርያ ዲግሪ ካገኙት ጥቂት ኢትዮጵያውያን አንዱ ነበሩ፡፡ በ1958 ዓ.ም. እንግሊዝ ከሚገኘው የማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ድኅረ ምረቃ ዲፕሎማ፣ በመቀጠልም በ1975 ዓ.ም. ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የማስተርስ ዲግሪ ተቀብለዋል፡፡
ባለትዳር የነበሩት አቶ ነዋየ ክርስቶስ፣ ለኢትዮጵያና ጃፓን ግንኙነት መጠናከር ላበረከቱት አስተዋፅኦ ‹‹Order of the Rising Sun Gold and Silver Star›› የተባለው በጃፓን ለአንድ ሲቪል ሊሰጥ የሚገባው ከፍተኛው ሽልማት ከጃፓን ንጉሥ ተበርክቶላቸዋል፡፡
አቶ ነዋየ ክርስቶስ በ1960ዎቹ የመጀመርያ ዓመታት በአዲስ አበባ ይታተም በነበረው ሳምንታዊው ‹‹አዲስ ሪፖርተር›› (Addis Reporter) የእንግሊዝኛ መጽሔት በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ይጽፉ ነበር፡፡ የመካከለኛው ምሥራቅ የገበያና የውል ጉዳዮችን የሚተነትን በለንደን የሚታተም ወርኃዊ መጽሔት (Middle East Economic Digest MEED) የዝግጅት አማካሪ በመሆንም ሠርተዋል፡፡
አቶ ነዋየ ክርስቶስ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚን በሚመለከት በርካታ ጽሑፎችን አዘጋጅተው ለንባብ ከማብቃታቸውም በላይ፣ የታዳጊ አገሮችን ኢኮኖሚ በሚመለከት አራት ጽሑፎችን አዘጋጅተዋል፡፡ ጡረታ ከወጡ በኋላም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አፈጻጸምና የልማት አቅጣጫዎች በሚመለከት ያዘጋጁትን መጽሐፍ ለማሳተም፣ በዓለም ከታወቁ አሳታሚዎች ጋር እየተነጋገሩ እንደነበር ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
አቶ ነዋየ ክርስቶስ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው የካቲት 16 ቀን 2012 ዓ.ም. በ78 ዓመታቸው አርፈው፣ ሥርዓተ ቀብራቸው የካቲት 18 ቀን በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡
አቶ ነዋየ ክርስቶስ በአማካሪነት በሠሩባቸው ጊዜያት በሁለቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ውስጥና ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ባወጣው ፖሊሲ ሥር በሚቀረጹ ዕቅዶች ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው የሚነገርላቸው ሲሆን፣ የኢኮኖሚ ዕድገትና ለአየር ንብረት ለውጥ አይበገሬነት እጅ ለእጅ መሄድ አለባቸው የሚል እምነት ስላላቸው፣ በሁሉም ተግባሮቻቸው ውስጥ ከግንዛቤ የሚከቱት ዕሳቤ መሆኑ ይወሳል፡፡
አቶ ነዋየ ክርስቶስ በአማካሪነት ባገለገሉባቸው ዘመኖች ማብቂያ ገደማ በኢትዮጵያ መንግሥት በይፋ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኮሚሽነር ለመሆን እንዲወዳደሩ፣ እ.ኤ.አ. በ2017 ዕጩ ተደርገው ቀርበውም ነበር፡፡
የእሳቸውን ዕጩነት ያወጁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሒሩት ዘመነ፣ ‹‹የተሳካላቸውና የአሠርታትን ልምድ ያካበቱት አቶ ነዋይ አፍሪካን ወደ ዕመርታ ይመሯታል፤›› በማለት፣ በኢኮኖሚ ዘርፉ ያላቸውን ልምድ ያሞገሱ ሲሆን፣ ‹‹በኢትዮጵያ የመጣውን የኢኮኖሚ ተዓምር ለአፍሪካም ይደግሙታል፤›› ብለው ነበር፡፡
አቶ ነዋይ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኮሚሽን በአፍሪካ አገሮች የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂዎችና ዕቅዶች ውስጥ ተገቢውን ሥፍራ ሊይዝ ይገባል ያሉ ሲሆን፣ በዚህም ለአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063፣ ለኢኮኖሚ ትስስር፣ ለነፃ ገበያ፣ እንዲሁም ለኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ቃል ገብተው ነበር፡፡
(ለዚህ ጽሑፍ ብሩክ አብዱ አስተዋጽኦ አድርጓል)