ሰሌዳ በሌላቸው ተሽከርካሪዎች የሚፈጸመው ዝርፊያ ከፍተኛ መሆኑ ተጠቁሟል
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እጅግ በሚያስፈራና ግራ በሚያጋባ ሁኔታ በጠራራ ፀሐይና በውድቅት ሌሊት እየተፈጸመ ያለው የዘረፋ ወንጀል፣ ሥጋት ውስጥ እንደከተታቸው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
ዘረፋው የሚፈጸመው በተለያዩ መንገዶች መሆኑን የሚናገሩ የከተማው ነዋሪዎች፣ በመተላለፊያ መንገዶች ላይ ከሆነ አራትና ከዚያም በላይ የሆኑ ወጣቶች በተንተን ብለው በመቆም፣ አንዱ ቀምቶ ሲሮጥ ሌሎቹ ግራና ቀኝ በማቋረጥና አብረው በመሮጥ ያስመልጣሉ፡፡ በውድቅት ሌሊት ከሆነ ደግሞ በደንብ ተደራጅተውና ተሽከርካሪ በመያዝ ያለ ምንም ፍርኃት የፈለጉትን ዝርፊያ እየፈጸሙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለገሃር ቅርንጫፍ ገንዘብ አውጥተው ሲወጡ ከቢሮአቸው ስልክ ተደውሎ እያናገሩ እንደነበር የሚናገሩት ወ/ሮ ስንቅነሽ ተሊላ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከጆሯቸው ላይ ስልካቸውን ሌባ በቀላሉ ቀምቷቸው ሲሮጥ በርካታ ሰዎች የነበሩ ቢሆንም፣ በወቅቱ ግብረ አበሮቹ የፈጠሩት ማተረማመስ ያስፈራ ስለነበር ማንም ምንም ሊላቸው እንዳልቻለና ስልካቸውን ተነጥቀው መመለሳቸውን አስረድተዋል፡፡
እንደ ወ/ሮ ስንቅነሽ የተለያዩ ንብረቶቻቸውን መዘረፋችን ለሪፖርተር የገለጹት አቶ በቀለ ስንሻው፣ ወጣት ይፍሩ ተሰማ፣ አቶ ሞቱማ ጉርሜሳና ወ/ሪት ትዕግሥት በፈቃዱ፣ አሁን አሁን እያስፈራቸው የመጣው በጠራራ ፀሐይ እየተወሰደባቸው ያለው ሞባይልና ቦርሳ ብቻ ሳይሆን፣ በእኩለ ሌሊት የሚፈጸመው በደንብ በተደራጀና በመሣሪያ የተደገፈው የዘረፋ ወንጀል መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ወ/ሪት ትዕግሥት ሰሞኑን በቅርብ ጓደኛዋ ላይ በውድቅት ሌሊት የተፈጸመውን የዘረፋ ወንጀል ስታስረዳ፣ ‹‹ጓደኛዋ የሚኖረው የካ ክፍለ ከተማ ቀበና አካባቢ ነው፡፡ ሙያው መሐንዲስ ነው፡፡ ባለፉት ሳምንታት ውስጥ አንዱን ቀን ሥራ አመሻሽቶ እንደገባ፣ ከልጆቹና ባለቤቱ ጋር ስለውሏቸው ሲጫወቱ አምሽተው ይተኛሉ፡፡ ጓደኛዬ ከሁሉም ቤተሰቦቹ ቀድሞ ጠዋት ሲነሳ ቴሌቪዥኑ፣ ላፕቶፖችና በየመሳቢያዎቹ የተቀመጡ ዕቃዎች ተወሰደዋል፡፡ የሳሎን በሩን እንዴት እንደከፈቱት ባይታወቅም ገርበብ አድርገው እጅግ በጣም ብዙ የኮብል ድንጋይና የዛጉ ስለቶች አስደግፈውት ሄደዋል፤›› ስትል ገልጻለች፡፡
ወ/ሪት ትዕግሥት እንዳብራራችው፣ የጓደኛዋ ልጆች ሌሊት ድንገት ነቅተው ወይም ጓደኛዋ ኮሽታ ሰምቶ ተነስቶ ቢሆን ኖሮ፣ ያ በር ላይ ያስደገፉበት ኮብል ድንጋይና የዛጉ ስለቶች ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ ግልጽ መሆኑን ተናግራለች፡፡
ከመቶ ሺሕ ብር በላይ ግምት ያላቸው ንብረቶቹ የተሰረቁበት የትዕግሥት ጓደኛ፣ በአካባቢው ለሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ሪፖርት ሲያደርግ፣ ከፖሊሶቹ የተሰጠው ምላሽ አስገራሚ ብቻ ሳይሆን አስደንጋጭም እንደነበረም ወ/ሪት ትዕግሥት ገልጻለች፡፡ ዝም ብለው ለማስረጃ ያህል እንደሚመዘግቡት እንጂ ምንም ፋይዳ እንደሌለው ነግረውት እንደተመለሰ እንደነገራት ገልጻ፣ ሁኔታው እጅግ በጣም አሳሳቢ እየሆነ እንደመጣ አስረድታለች፡፡
ቀን ቀን ተኝተው ሲቅሙና ሲዶልቱ የሚቆዩ በርካታ ጉልበተኛ ወጣቶች፣ ሌሊት የፈለጉት ቤት እየሰበሩ ገብተው ዘረፋ እየፈጸሙ እንደሚገኙም የከተማው ነዋሪዎች እየተናገሩ ነው፡፡
ሰሌዳ በሌላቸው ሚኒባሶችና ቪትስ ተሽከርካሪዎች በመታገዝ፣ በተለይ ሌሊት ሌሊት የሚፈጸመው ዝርፊያ ተባብሶ መቀጠሉን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ የሰሌዳ ቁጥር የሌላቸው ተሽከርካሪዎችን የመቆጣጠር ሥልጣን የትራንስፖርት ባለሥልጣን ቢሆንም፣ የተፈቀደላቸውን ያህል ሲንቀሳቀሱ ዝም በመባሉ ግራ እያጋባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የሰሌዳ ቁጥር ተሰጥቷቸው በመሥራት ላይ ያሉ ሚኒባሶች የሰሌዳ ቁጥራቸውን ወደ ንግድ እንዲቀየሩ እያስገደደ የሚገኘው ትራንስፖርት ባለሥልጣንና የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ ያለ ሰሌዳ እየተዘዋወሩ መዝረፊያ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን ዝም ብለው ማየታቸው ተገቢ ባለመሆኑ፣ ትኩረት ሰጥተው ማንኛውም ተሽከርካሪ ያለ ሰሌዳ ቁጥር እንይንቀሳቀስ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለይ የጎዳና ተዳዳሪዎችን በመሰብሰብ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመመለስና የሚቋቋሙብትን ሁኔታ በመፍጠሩ በተለይ የከተማው ነዋሪዎች ደስተኛ ሆነው እንደነበር የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመታት በላይ የሆኑ ወጣቶች ግን አሁንም ከተማውን እየሞሉትና በቅሚያና በዘረፋ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ ስልክና ቦርሳ እየቀሙ ከመሮጥም ባለፈ በቡድን ሆነው በመቀማት ኅብረተሰቡ መንግሥትን እንዲያማርር እያደረጉ በመሆኑ፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ አፋጣኝ ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የተሽከርካሪዎችን መስታወት በብረትና ድንጋይ እየሰበሩ የመኪና ቴፕና ያገኙትን ነገር ከመውሰድ አልፈው፣ ተሽከርካሪውን ከእነ ነፍሱ ይዘው መሰወር በመጀመራቸው፣ ይህ አካሄድ ወዴት እያመራ እንደሆነ ሕዝብ ለመንግሥት ማስረዳት እንደማይጠበቅበትም አክለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽን ከአቅሙ በላይ ከሆነበት የፌዴራል ወይም ሌላ የፀጥታ አካላትን ድጋፍ በመጠየቅ፣ ወንጀለኞችን ከድርጊታቸው ማስቆምና ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
በከተማው ውስጥ በከተፍኛ ሁኔታ ተበራክቷል ስለተባለው የቀንና የሌሊት የዝርፊያ ወንጀል ጉዳይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ፣ ድርጊቱ ሊኖር ቢችልም መረጃውን ለመስጠት በደንብ አደራጅተውና ተዘጋጅተው ካልሆነ በስተቀር ምላሽ መስጠት እንደማይችሉ በመግለጻቸው፣ ማብራሪያውን ማካተት አልተቻለም፡፡