ቤጂንግ ያለወትሮዋ ዝምታ ውጧታል፡፡ ለቤጂንግ ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት መጓጓዧ የሆኑት አያሌ ብስክሌቶች ያለወትሯቸው በየመንገዱ ዳር በረዶ ተጋግሮባቸው ጫፍ እስከ ጫፍ ተሰድረዋል፡፡ በየመንገዱ ተፍተፍ የሚለው ልጅ አዋቂ ሁሉ በቤጂንግ ጎዳናዎች እንደቀድሞው አይታይም፡፡
በሰውና በተሽከርካሪ ብዛት የደመቀችው የወትሮዋን ሽቅርቅር ከተማ የሚያውቅ ሰው፣ ኦናነቷን መቀበል ይከብደዋል፡፡ በእርግጥም የቤጂንግ ውበቷ፣ ትርምሷ ነው፡፡ ብስክሌቶቹ፣ አውቶብሶቹ፣ ታክሲዎቹ፣ ነዋሪዎቿ በየቅርብ ርቀት የሚገኙት ሱፐር ማርኬቶች፣ ሬስቶራንቶች፣ ቤጂንግ ውበቷ ግርግሯ ስለመሆኑ ይህ የሰሞንኛ ክስተት ይመሰክራል፡፡
በጥርና የካቲት ወራት የቤጂንግ ከተማ ሕዝብ በከፍተኛ ደረጃ ለቋት የሚወጣበት ወቅት እንደሆነ አዋቂ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ የቤጂንግን ቅዝቃዜ ሽሽት ነዋሪው እነዚህን ወራት ከቤጂንግ ራቅ ብሎ ያሳልፋቸዋል፡፡ በከተማዋ የሚቀረው ጥቂት ሰው መሆኑን ከተማዋ ላይ በርከት ያሉ ዓመታትን ያሳለፉ ሰዎች አጫውተውኛል፡፡ በተለይ የቤጂንግ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኦና የሚሆኑበት ወቅት ነው፡፡ አንዳንድ ቤተሰቦቻቸው ራቅ ባሉ የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ፣ አልያም እንደ እኛ በትምህርት ወደ ከተማ ገብተው ክረምቱን የመመለስ ዕቅድ የሌለው ብቻ ነው የሚታየው፡፡
እኛም ከቤጂንግ፣ ከባድ ንፋስ ከተቀላቀለበት ብርዳማ አየር ጋር የዕረፍት ጊዜያችንን እንዴት እንደምናሳልፍ መመካከር ጀመርን፡፡ በዚህ ጊዜ እዚህ ቦታ እያልን ፕሮግራም ማውጣት፣ ቦታ ማጥናት ጀመርን፡፡ ለአራት ወራት በትምህርት የተወጠረ አዕምሯችንን ፈታ የምናደርግበት ብሎም በቤጂንግ ከተማ ዞር ዞር እያልን የምንጎበኝበት ጊዜ እንደሆነ ተነጋገርን፡፡ የቤጂንግን ብርድ በአብሮነት ጨዋታ እንደምናሳልፈው አቀድን፡፡ በተለይ እኔ የእስኬቲንግ ትዕይንቶችን ለማየት ጓጉቼ ስለነበር ቦታ በማጣራት ተጠምጄ ነበር፡፡ የተለያዩ የዓለም አቀፍ ተማሪዎች ኅብረት ይኼን ክረምት የተለያዩ ዝግጅቶችን በማቀድ የቤጂንግ ሰዎችን ዘና ለማድረግ ዕቅድ ይዘዋል፡፡ እኛም ተዘጋጅተናል፡፡
እንዲህ ባለ ስሜት ውስጥ ሆነን የዕረፍት ጊዜያችንን ማጣጣም ከመጀመራችን፣ ቤጂንግ በዝምታዋና በቀዝቃዛው አየሯ ላይ ሌላ ከባድ በረዶ ዘነበባት፡፡ ሚዲያዎች፣ ለነዋሪዎች የሚያስተጋቧቸው ማስጠንቀቂያዎች መዥጎድጎድ ጀመሩ፡፡ ውሃን በተባለችው ግዛቷ መነሻው በቅጡ ያልታወቀ፣ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ኮሮና የተባለ አደገኛ ቫይረስ በመከሰቱ፣ በሰዎች ላይ የሞት አደጋ እየተፈጠረ መሆኑ ተሰማ፡፡
በውሃን ከተማ ያልተገታው የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ወደ ከተማችን ቤጂንግ መግባቱም ተሰማ፡፡ ይህ ዜና እየሰፋና ሥርጭቱም እየቀጠለ የዕለት ተዕለት ዜና ሆነ፡፡ ከዚያ ባለፈ ደግሞ እኛ የምንኖርበት ዲስትሪክት ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዝ ሰማን፡፡ አሁን ግን እንኳንስ ወጥቶ መዝናናት ይቅርና ከቤት መውጣት ጭምር ከባድ ፍርኃትን ይፈጥራል፡፡ ይህ ወር ለቻይናውያን ታላቅ ወር ነበር፡፡
አዲስ ዓመታቸው ነው፡፡ የዕረፍት ጊዜያቸው ነው፡፡ ታታሪው የቻይና ሕዝብ አዲስ ዓመትን ለማክበር የዕረፍት ጊዜውንም ለማጣጣም በየሄደበት ወዴትም እንዳይንቀሳቀስ ታገደ፡፡ በያለበት ተቆለፈ፡፡ ዘመድ ከዘመድ፣ ወንድም ከወንድም፣ ጓደኛ ከጓደኛ መገናኘት ህልም ሆነ፡፡ ሁላችንም የዚህ ዜና መጨረሻ አጭር እንዲሆን ተመኘን፡፡
የቻይናዋ ውሃን ግዛት የጦርነት አውድማ ሆነች፡፡ ከኮሮና ቫይረስ ጋር የሚደረገው ውጊያ ተቀጣጠለ፡፡ ከጫፍ እስከ ጫፍ የሕክምና ባለሙያዎቿ ወደዚች ግዛት መትመም ጀመሩ፡፡ ውሃን ሆይ በርቺ፣ ይህ ፈተና ይታለፋል እያለች እናት ልጇን ትታ፣ ሌላውም ቤተሰቡን ተሰናብቶ የሕክምና ባለሙያውም ድጋፍ መስጠት የሚችለው ሁሉም ዜጋ ወደ ውሃን ተመመ፡፡ መነሻው አሁን ድረስ በግልጽ ያልታወቀው የኮሮና ቫይረስ በሺዎች የሚቆጠሩትን ሕይወት ቀጠፈ፡፡ ጦርነቱ አሁንም ቀጥሏል፡፡ መከራ የማይበግረው ሕዝብ ዛሬም ፈተናውን ላለመሸነፍ ወገቡን አጥብቆ ከልጅ እስከ አዋቂ ውሃን ታሸንፋለች እያለ ይዘምራል፡፡ ከመንግሥት የሚሰጠውን የቅድመ ጥንቃቄ መመርያ በመተግበር በሌላ በኩልም ድጋፍ ማድረግ የሚገባውን ከሁሉም የዓለም ጫፍ ዓይኑም ልቡን ውሃን ላይ በማድረግ የመጣበትን ለመመከት ደፋ ቀና እያለ ነው፡፡
በዚህ ከባድ ፈተና ውስጥ ቻይናውያን ፅናታቸው ዛሬም ከብረት የጠነከረ ነው፡፡ አንዳንድ አገሮች በሺዎች የሚቆጠሩ ሕዝቦቻቸውን ማነቃነቅ አቅቷቸው ዕለት ተዕለት በራሳቸው ዜጎች በሚፈጠሩ ችግሮች ሲታመሱ ይስተዋላል፡፡ እዚህ ነገሩ ለየት ይላል፡፡ ለቻይናውያን ቃል የማይሰበር ክቡር ነገር ነው፡፡ ሕግ ክቡር ነው፡፡ አድርግ ከተባልክ ታደርጋለህ፡፡ ምክንያቱም ለራስህ ስትል ነው፡፡ በቻይኖች ቤት መንግሥትና ሕዝብ አንድ ናቸው፡፡ መንግሥት ሕዝቡን፣ ሕዝቡም መንግሥትን ያደምጣል፤ ያከብራል፡፡
አሁን ከክልል ክልል እንደ ልብ መዘዋወር አይቻልም፡፡ ይህን ሁሉም ተቀብሎ እየተገበረው ነው፡፡ ከተማ ውስጥ ሕዝብ ወደ ሚበዛበት ቦታ መንቀሳቀስ ተከልክሏል፡፡ የአፍ መሸፈኛ ማስክ ሳያደርጉ መንቀሳቀስ አይቻልም፡፡ በቢሊዮን የሚቆጠረው የቻይና ሕዝብ በአንድ ጀምበር በቃል ብቻ የሚፈለገውን ማድረግ የሚቻለው እዚህ አገር ብቻ ይመስለኛል፡፡ ሥልጣኔ ለእኔ ይህ ነው፡፡
ይህ ሕዝብ አጀንዳው በኢኮኖሚ የፈረጠመች አገር ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት መደገፍ ብቻ ነው፡፡ ሌላው ትርፍ ነው፡፡ ሕዝቡ መሪውን መስማት ብቻ ሳይሆን፣ ማዳመጥ አዳምጦም መተግበር ይችልበታል፡፡ እኛም ቻይናውያን ዓለም እንደ ተዓምር ሲዘግበው የነበረውን ዕድገት ያስመዘገቡበት ሚስጥር በዚህ ክስተት በግልጽ መረዳት ቻልን፡፡ በእርግጥም ሕዝብ ከመሪ ጋር ሲዋሃድ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ይሆናል፡፡ ኮሮና ቫይረስ እያደረሰ ያለው ኪሳራ አንድ መነጋገሪያ አጀንዳ መሆኑ እንዳለ ሆኖ የሕዝቡ አንድ መሆን የመንግሥት ርብርብ የዕለት ተዕለት መነጋገሪያ አጀንዳችን ሆኗል፡፡ ይህች አገር በብዙ መልኩ ኃያል ናት፡፡ እንደው ሌላው እንደሚመኘው በቀላሉ የምትንበረከክ አገር አይደለችም፡፡ በተለይ ሕዝብና መንግሥት ያላቸውን ቁርኝት ላየ በእርግጥም ብዙ ከመናገር ብዙ ማዳመጥ የሚሻ ታጋሽና የማይደነግጥ ሕዝብና መንግሥት ያለበት አገር ነው ለችግር መንበር ከእዚህ የማይታሰብ ነው፡፡
በዚህ ከባድ ጊዜ ውስጥ ከሚለቀቁ ምሥሎች ልቤን ያሸነፈውን አንዱን ላካፍላችሁና ጽሑፌን ልቋጭ፡፡ የሕክምና ባለሙያ የሆነችው አንድ እናትና ልጅ ትዕይንት ነው፡፡ ምናልባት ሁላችሁም ዓይታችሁት ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ አናት ሁሉም ነገር ነች፣ የቤት ምሰሶ ነች ሁሉም ነገር ነች፡፡ እናትን ውሀን ጦርነት ውስጥ ነች፡፡ ኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን በማከም ላይ ናት፡፡ ልጅ ወደ እናት በእጇ ምግብ አንጠልጥላ ከፊት ለፊቷ ከእናቷ ጋር ዕንባዋን እያዘራች እናቷን ትጣራለች፡፡ ልብ ይሰብራል፡፡ እናት ሕይወት ትታ ሕይወት ልታተርፍ ሆስፒታል ውስጥ ከትማለች፡፡
ልጅ እማዬ እያለች ዕንባዋና ታዘራለች፡፡ እናትነትም፣ ሐዘንም፣ ወኔም፣ በተሞላበት አንደበት ልጄ እናትሽ ሞንሰተር እየተዋጋች ነው ብላ መለሰችላች፡፡ ሰዎችን የሚገድል ሞንሰተር እየተዋጋች ነው አለቻት፡፡ በእርግጥም በእዚያ የጦርነት ቤት ውስጥ ሆናችሁ ይህንን ሞንሰተር የምትዋጉ፣ ሕይወት እናትርፍ ብላችሁ ሕይወት የሰጣችሁ በሁሉም ልብ ውስጥ ዘለዓለም ከብራችሁ ትኖራላችሁ፡፡
ቻይናም ይህን ጦርነት በቅርቡ ድል ነስታ ወደ አዲስ ሰላማዊ ሁኔታ ሁሉም ነገር እንደሚመለስ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን በዚህች አገር የሚደረግ ማናቸውም እንቅስቃሴ፣ የሚተነፈሰው አየር ጭምር የሰበር ዜናቸው ማሞቂያ አድርገው የሚጠቀሙና የሚያሳስባቸው፣ አገሪቱ ወደ ፊት እየተምዘገዘገች እየሄደችበት ያለበት ፍጥነት ያሠጋቸው አካላት በሞራልም በአቅምም አገሪቱን ለማዳከም የሚምሱትን ጉድጓድ ላየ በእርግጥም ይህ ከባድ ሁኔታ የእነሱ ሠርግና ምላሽ ቢሆንም አገሪቱ አሁን ካላት ጥንካሬ አንፃር ግን ማገገሙ የገብስ ያህል ቀላል ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
በእርግጥም አገሪቱ ታስፈራለች፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2004 ጀምሮ አገሪቱ እየተምዘገዘገችበት ያለው የዕድገት ፍጥነት በእርግጥም ሁሌም ገናና ሆኖ እኔ ብቻ ልሰማ ለሚል አገር የጨዋታውን ሕግ የቀየረ ነውና በእርግጥም ለእንደዚህ ዓይነት አካል ይህች አገር ታስፈራለች፡፡ እኔ መፅናታችሁ ለዓለም ትምህርት ነው እያልኩኝ በእርግጥም ይህንን ፈተና እንደምታልፉት በመተማመን ውሀን ታሸንፋለች፣ ቻይናም ወደ ፊት መገስገሷን ትቀጥላለች እላለሁ ሰላም፡፡
(ሲና ሙሴ፤ ከቻይና)