Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በሕግ አምላክፍትሕ ፍለጋ ከሕግ እስከ ሕገ መንግሥት ተርጓሚ የተደረገ ተስፋ አስቆራጭ ጉዞ

ፍትሕ ፍለጋ ከሕግ እስከ ሕገ መንግሥት ተርጓሚ የተደረገ ተስፋ አስቆራጭ ጉዞ

ቀን:

በአሳዬ ቀፀላ

የአንድ አገር ዜጎች በሚኖሯቸው የዕለት ተዕለት የእርስ በርስ መስተጋብሮች፣ አለመግባባት፣ አለመስማማትና ወደ ፀብና ግጭት ሊያመሩ ወይም ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ ወደ ግጭት የሚያደርሷቸው አለመግባባቶች ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ግጭቶች በንግግር፣ በሥራ አጋጣሚ፣ የተስማሙባቸውንና ውል በቋጠሩባቸው የሰነድ ላይ ስምምነቶችን ባለማክበር ወይም በይሆናል ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ በማኅበረሰብ ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች እንደ ደረጃቸውና የአገሪቱ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች መፍትሔ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡

ከአገር ሽማግሌዎች እስከ ፍትሕ አደባባይ ባሉ የማስማሚያ መንገዶች በመጓዝ፣ የተፈጠሩ ግጭቶችን መፍታት የተለመደና ቀጥሎ የሚገኝ ነው፡፡ ከጎረቤት ሽምግልናና በተቋም ደረጃ ተቋቁሞ የማሸማገል ሥራ ከሚሠራው የግልግል ዳኝነት (Aritration) ያለፈ መካረር ሲኖር፣ ወደ መጨረሻው ሕግ ተርጓሚው የመንግሥት አካል (Judicial) ፍርድ ቤት ይሄዳል፡፡ ፍርድ ቤቱ አለመግባባት የፈጠረውን ጉዳይ ከመረመረና በሕግ አግባብ ትርጉም ከሰጠ በኋላ የመጨረሻውን ውሳኔ ይሰጣል፡፡ ፍርድ ቤት ሕግ ጠቅሶ በሰጠው ውሳኔ ቅር የተሰኘው ወገን፣ ‹‹የተሰጠው ውሳኔ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ የሚቃረን የሕግ አንቀጽ ተጠቅሶ በመሆኑ፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል፤›› በማለት፣ የመጨረሻውንና ተስፋ ያደረገበትን እውነተኛ ፍትሕ ለማግኘት ጉዳዩን ሥልጣን ወዳለው ፌዴሬሽን ምክር ቤት ይወስዳል፡፡ የዚህ መጣጥፍ ርዕሰ ጉዳይም የተጠቀሰውን ሒደት (Procedure) ተከትሎ፣ ከኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤት እስከ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ድረስ የተጓዘና እውነተኛ ፍትሕን ለማግኘት ያደረገው ጉዞ ተስፋ አስቆራጭ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ምናልባትም የጉዳዩን ሁኔታና እውነተኛነት ተመልክተው ‹‹የሚሉት ካለ›› በሚል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለኦሮሚያ ክልል መንግሥት ፕሬዚዳንትና ለፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቤቱታ የቀረበበት ጉዳይም ነው፡፡

- Advertisement -

ጉዳዩ የተጀመረው የኢትዮጵያ ፍትሐ ብሔር ሕግ ድንጋጌዎችን መሠረት አድርጎ በተፈጸመ የንግድ ድርጅት ግዥና ሽያጭ ውል ተዋዋዮች (ፈጻሚዎች) መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ወይም መካካድ ነው፡፡ ውሉ የተፈጸመው በኦሮሚያ ክልል በቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ከተማ ተገንብቶ የሚገኘውን ‹‹ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ኃላፊነቱ የተወሰነ ግል ማኅበርን›› በሸጡት በእነ ጌታቸው እሸቴ (ኢንጂነር) እና ድርጅቱን በገዙት በእነ በዕውቀቱ ታደሰ (ዶ/ር) መካከል ነው፡፡ የፋብሪካው ሽያጭና ግዥ ውል የተፈጸመው ኅዳር 18 ቀን 2005 ዓ.ም. ከሰባት ዓመታት በፊት ነው፡፡ ገዥና ሻጭ አስፈላጊውን የአገሪቱ ሕጎች የሚፈቅዱትን ፎርማሊቲዎች ካሟሉ በኋላ፣ ለመሸጥና ለመግዛት ስምምነት ላይ የደረሱበትን የፋብሪካውን አጠቃላይ ዋጋ 22,500,000 ብር እንዴት መክፈል እንደሚችሉ ዝርዝር ሒደቶችን በማስቀመጥ፣ እማኝና የፋብሪካው ባለድርሻዎች (ከሁለቱም በኩል) ጥምር ፊርማቸውን በስምምነት ሰነዱ ላይ በማስፈር፣ ውል መቋጠራቸውን ሰነዶች ያሳያሉ፡፡ የፋብሪካው ገዥ ባለሀብት በገቡት ውል መሠረት፣ ለሻጭ ባለሀብት የመጀመርያውን ክፍያ ሁለት ሚሊዮን ብር ወዲያውኑ ከፍለው ቀሪውን ክፍያ በአራት ዓመታት ውስጥ ለመክፈል መስማማታቸውንም ሰነዱ ይገልጻል፡፡ ገዥ ውል ሲፈጽሙ ከፋብሪካው ጋር አብረው የወሰዱት ግዴታም አለ፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ያበደረውን ሰባት ሚሊዮን ብር ቀሪ ክፍያ ለመክፈል፣ ገዥ ለሻጭ የሚከፍሉትን ሁለት ሚሊዮን ብር ቅድመ ክፍያና ለልማት ባንክ ለመክፈል የተስማሙበት ሰባት ሚሊዮን ብር ተቀንሶ የሚቀረውን 13,500,000 ብር በአራት ዓመታት ለመክፈል ከተስማሙ በኋላ፣ ፋብሪካውን ተረካክበው ገዥ ወደ ሥራ መግባታቸውን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

ለፍትሕ ተቋማት የቀረቡ ሰነዶች እንደሚያስረዱት፣ ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ፋብሪካ አጠቃላይ ይዞታው 11,305 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ ነው፡፡ ቦታው ሁለት የይዞታ ማረጋገጫ ያለው ሲሆን፣ ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ያረፈበት የቦታ ስፋት 3,015 ሜትር ካሬ ላይ ሆኖ፣ የይዞታ ማረጋገጫው ሰነድ (ካርታ) የተሠራው ግን በሻጭ ጌታቸው እሸቴ (ኢንጂነር) ስም የተመዘገበ ነው፡፡ ቀሪው 8,290 ካሬ ሜትር ቦታ ጅምር ግንባታ ያለበት ሆኖ፣ የይዞታ ማረጋገጫው ሰነድ (ካርታ) የተመዘገበው በጌት እሽት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ኃላፊነቱ የተወሰነ ግል ማኅበር ነው፡፡ ገዥ እነ በዕውቀቱ ታደሰ (ዶ/ር) ግዥ የፈጸሙት ሁለቱ በተለያየ ስም ተመዝግበው የሚገኙ ካርታ ያላቸውን ይዞታዎች አጠቃለው መሆኑንም ውል የፈጸሙባቸው ሰነዶች ያብራራሉ፡፡ ገዥና ሻጭ በገቡት ውል መሠረት ፋብሪካውን ተረካክበው ጥቂት ወራት ከቆዩ በኋላ፣ ገዥ በውሉ መሠረት ካለባቸው ቀሪ ክፍያ ላይ በመጀመርው ዓመት መክፈል ያለባቸውን 3,375,000 ብር ለመክፈል፣ ሻጭ ፋብሪካውን በገዥ ስም በማዘዋወር የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ (ካርታ) እንዲያስረክቧቸው ይጠይቋቸዋል፡፡ የሻጭ ምላሽ ግን የሸጥኩት በስሜ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የወጣበትን 3,015 ካሬ ሜትር አይመለከትም፣ ከእሱ ውጪ ያለውን 8,290 ካሬ ሜትር ጅምር ሕንፃ ያለበትንና በጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ኃላፊነቱ የተወሰነ ግል ማኅበር በሚል የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የተሠራለትን ብቻ ነው፤›› በማለታቸው፣ በገዥና በሻጭ መካከል አለመግባባት መፈጠሩን ለፍርድ ቤቶችና ለተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የተጻጻፏቸው ሰነዶች ያመለክታል፡፡

ሻጭ እነ ጌታቸው እሸቱ (ኢንጂነር) ለእነ ዶ/ር በዕውቀቱ ታደሰ የሸጡት ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ፋብሪካ ስም፣ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የተሠራለትን 8,290 ካሬ ሜትር ብቻ እንደሆነ ቢናገሩም፣ ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ፋብሪካ የተገነባው በስማቸው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በተሠራበት 3,015 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ መሆኑም ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ፋብሪካ በጻፈው ደብዳቤ፣ በፋብሪካው ስም የተመዘገበው 8,290 ካሬ ሜትር በጌታቸው እሸቱ (ኢንጂነር) ስም የተመዘገበው ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ፋብሪካ ሙሉ በሙሉ ያረፈበት 3,015 ካሬ ሜትር ቦታን ጨምሮ፣ በአጠቃላይ 11,305 ካሬ ሜትር ቦታ በመያዣነት ይዞ ብድር መስጠቱን ሰነዶች ይገልጻሉ፡፡

ሁለቱ ባለሀብቶች በተገበያዩት የቦታ ስፋት፣ የተለያዩ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነዶች (ካርታዎች) እና ፋብሪካው ስለተገነባበት ሁኔታ በቃል ንግግር ሊግባቡ ስላልቻሉ፣ ገዥ እነ በዕውቀቱ (ዶ/ር) ግዥውን በፈጸሙ በዓመቱ፣ ፋብሪካውን ከእነ ሙሉ ይዞታው ስመ ሀብቱን እንዲያዘዋውሩላቸው ለሻጭ እነ ጌታቸው እሸቴ (ኢንጂነር) በጽሑፍ መጠየቃቸውንም ኅዳር 11 ቀን 2006 ዓ.ም. የተጻፈው ደብዳቤ ያስረዳል፡፡

በጽሑፍ ‹‹የገዛሁትን ፋብሪካ በስሜ አዛውርልኝ፤›› የሚል ደብዳቤ የደረሳቸው ሻጭ፣ ስመ ሀብቱን ከማዛወር ይልቅ ፋብሪካው ያረፈበት 3,015 ካሬ ሜትር ቦታ የእሳቸው መሆኑን በመግለጽ፣ ገዥ በፋብሪካው ውስጥ አሰማርተዋቸው የነበሩ ሠራተኞችንና የጥበቃ ሠራተኞችን ጥር 26 ቀን 2006 ዓ.ም. ከፋብሪካው ያስወጣሉ፡፡ የሻጭ አካሄድን የተቃወሙት ገዥ ‹‹ሁከት ይወገድልኝ፤›› በማለት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰዳቸው፣ ሁከት መሆኑን የተረዳው ፍርድ ቤት ‹‹ድርጊቱ ሁከት ነው፤›› በማለት፣ የሻጭን የጥበቃ ሠራተኞች ከፋብሪካው እንዲወጡና የተባረሩት የግዥ ሠራተኞች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማድረጉንም ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡ የሻጭ አካሄድ ያስፈራቸው ገዥ፣ በፍትሐ ብሔር ሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሻጊያ ፋብሪካን መግዛታቸውን በመጥቀስ፣ ከሻጭ ጋር በገቡት ውል መሠረት ክፍያ ለመፈጸም ስመ ሀብቱ በስማቸው እንዲዞርላቸው በገቡት ውል መሠረት የሻጭንም ሆነ የመንግሥት ዕዳ (የልማት ባንክ ብድር) መክፈል እንዲችሉ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው፣ ለኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ክስ መመሥረታቸውንም የክስ ሰነዶች ይገልጻሉ፡፡ የቀረበለትን ክስ የመረመረው የምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ሁለቱንም ወገኖች አከራክሮ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ሻጭ ለፍርድ ቤቱ በስማቸው ተመዝግቦ የሚገኘው 3,015 ካሬ ሜትር ቦታ በሽያጭ ውሉ ውስጥ አለመካተቱንና ሌሎች የመከራከሪያ ነጥቦችን አንስተው መከራከራቸውን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይገልጻል፡፡ ገዥ በበኩላቸው ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ያረፈው በ3,015 ካሬ ሜትር ላይ መሆኑን፣ ስመ ሀብቱ በገዥ ስም አይዘዋወር እንጂ በፋብሪካው ውስጥ ሠራተኞች አሰማርተው ለአንድ ዓመት ያህል ምርት ሲያመርቱ መቆየታቸውንና ይህም ዕውቅና ባላቸው የኦዲት ድርጅቶች ጭምር ተመርምሮና ስለፋብሪካው አጠቃላይ ሁኔታ የሚያሳይ ማስረጃ በማቅረብ መከራከራቸውንም ውሳኔው ያብራራል፡፡ የግራ ቀኙን ክርክር የሰማውና በገዥና በሻጭ መካከል የተደረገውን ሕጋዊ ውል የተመለከተው ፍርድ ቤት፣ ሻጭ እነ ጌታቸው እሸቴ (ኢንጂነር)፣ ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ኃላፊነቱ የተወሰነ ግል ማኅበርን ለገዥ እነ በዕውቀቱ ታደሰ (ዶ/ር) መሸጣቸውን ማረጋገጡን በመግለጽ ሻጭ የፋብሪካውን ስመ ሀብት ለገዥ እንዲያዛወሩ ፍርድ መስጠቱን ሰነዶች ያብራራሉ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰጠው ፍርድ ያልተስማሙት እነ ጌታቸው እሸቴ (ኢንጂነር)፣ ፍርዱን በመቃወም ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብለዋል፡፡ ጎን ለጎን ደግሞ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሌላ ክስ መመሥረታቸውንም የፍርድ ሰነዶቹ ያብራራሉ፡፡ የምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠባቸው ፍርድ ከሥልጣኑ ውጪ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ለገዥ በውል ያልሸጡላቸውን 3,015 ሜትር ካሬ ቦታ ይገባኛል የሚሉት ከውል ውጪ መሆኑን በመጥቀስ፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ማቅረባቸውንም በይግባኛቸው አካተው አቅርበዋል፡፡ የይግባኝ አቤቱታውን የተመለከተው ኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሻጭ ያቀረቡትን የይግባኝ አቤቱታ ተቀብሎ፣ የምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ እንደሻረው የውሳኔ ሰነዱ ይገልጻል፡፡

የጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መሥራች እነ ጌታቸው (ኢንጂነር)፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመሠረቱትን ክስ በመቀጠል ሲከራከሩ ቆይተዋል፡፡ ሻጭ እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባቀረቡት ክስ፣ ከገዥ እነ በዕውቀቱ (ዶ/ር) ጋር ያደረጉት ውል በሕግ ፊት ተቀባይነት እንደሌለው፣ የፋብሪካውን ሽያጭ ዋጋ 13,500,000 ብር በአራት ዓመታት ውስጥ ለመክፈል ኅዳር 18 ቀን 2005 ዓ.ም. በውልና ማስረጃ የተዋዋሉትን የብድር ውል መሠረት አድርገው፣ የቅድሚያ ክፍያ መክፈል የነበረባቸውን ሁለት ሚሊዮን ብር አለመክፈላቸውን፣ የሻጭ የግል ንብረት የሆነ 3,015 ካሬ ሜትር ቦታ በሕገወጥ መንገድ ጠቅልለው መያዛቸውን፣ ሌሎችንም አቤቱታዎች በክሳቸው ጠቅሰዋል፡፡፡ ሻጭ በክሳቸው ጨምረው እንዳስረዱት፣ የግል ይዞታቸው በሆነው 3,015 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ የሚገኙትና ግምታቸው 20 ሚሊዮን ብር የሚሆኑ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ማሽኖች በገዥ ቁጥጥር ሥር በመውደቃቸው፣ ሻጭ ማሽኖቹን ቢያከራዩ ሊያገኙ ይችሉ የነበረውን 3.5 ሚሊዮን ብር ማጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ ገዥ፣ ሻጭ ሊያገኙ ይችሉ የነበሩትን 5,020,000 ብር ከእነ ወለዱ እንዲከፍሉ ጠይቀው ነበር፡፡

ተከሳሽ የነበሩት የፋብሪካው ገዥ እነ በዕውቀቱ (ዶ/ር) ለፍርድ ቤቱ በሰጡት ምላሽ፣ ሻጭ (ከሳሽ) ኅዳር 18 ቀን 2005 ዓ.ም. በጋራ የፈጸሙት ውል በሕግ ፊት አይፀናም ከማለት ባለፈ፣ ያቀረቡትና የጠቀሱት የሕግ አንቀጽ የለም፡፡ ቅድመ ክፍያ 2,000,000 ብር መፈጸማቸውን፣ ፋብሪካውን በ22,500,000 ብር ሲገዙ 7,000,000 ብር የልማት ባንክ ዕዳ መሆኑን ጠቁመው፣ ቅድሚያ ከከፈሉት 2,000,000 ብር ጋር ተደምሮ ከጠቅላላ ዋጋው ላይ ሲቀነስ የቀረውን 13,500,000 ብር በአራት ዓመት ለመክፈል የተዋዋሉት ውል ሕጋዊ ውል መሆኑን በክርክራቸው አስታውቃል፡፡ የባንከ ወለድን ጨምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መክፈላቸውንም በሰነድ አስደግፈው ማቅረባቸውን ፍርዱ ያሳያል፡፡ ከሳሽ 3,015 ካሬ ሜትር የግል ይዞታ መሆኑን ጠቅሰው፣ ተከሳሽ በጉልበት አጠቃለው እንደያዙ መገለጹ ከእውነት የራቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ፋብሪካውን ለመግዛት ውል ሲፈራረሙ ከሳሽ በውል ሰነዶች ላይ ያሰፈሩት ይዞታ 11,305 ካሬ ሜትር መሆኑንና ጌት እሸት ዲተርጅት ማምረቻና ማሸጊያ ፋብሪካ ያረፈውም በ3,015 ካሬ ሜትር ላይ መሆኑን በሰነድ ጭምር አስረድተዋል፡፡ ተከሳሾች (ገዥዎች) ሌሎች ክርክሮችን በሰነድ አስደግፈው በማቅረብ ተከራክረዋል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም አምስት ጭብጦችን ለይቶ በማውጣት የግራ ቀኙን ክርክር ከመረመረና ከተገቢ የሕግ ድንጋጌዎች ጋር ካገናዘበ በኋላ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ በፍርዱም ሻጭ እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) የግል ይዞታቸው መሆኑን ገልጸው የተከራከሩበት 3,015 ካሬ ሜትር ቦታና ማሽኖች፣ ከጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ጋር ተያይዘውና የፋብሪካው አካል ሆነው መሸጣቸውን በቀረቡት ማስረጃዎች ማረጋገጡን ፍርዱ ያስረዳል፡፡ በሻጭና በገዥ መካከል የተደረጉ ውሎች በሕግ ፊት የፀኑ ሊሆኑ አይችሉም የሚያስብል ነገር እንደሌለም ገልጾ፣ ነገር ግን ተከሳሾች ወይም ገዥ ያልከፈሉትን 17,699,952 ብር ውሉ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ ከሚታሰብ ወለድ ጋር እንዲከፍሉ የሚል ውሳኔ ማስተላለፉን ሰነዶቹ ያስረዳሉ፡፡

ቅድሚያ ክፍያ ሁለት ሚሊዮን ብርና የልማት ባንክ የብድር ዕዳ ሰባት ሚሊዮን ብር ተቀንሶ ገዥ ሊከፍሉ የሚገባው 13,500,000 ብር ሆኖ ሳለ፣ ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲከፍሉ ውሳኔ የተላለፈባቸው እነ በዕውቀቱ (ዶ/ር)፣ እላፊ ከ4.1 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲከፍሉ የተላለፈውን ውሳኔ በመቃወም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ አቅርበዋል፡፡ ገዥዎች ያቀረቡትን የይግባኝ አቤቱታ የተመለከተው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ‹‹ያላግባብ ተጨምሮ እንድንከፍል ተደርገናል፤›› ያሉትን ክፍያ አፅንቶታል፡፡ በተጨማሪም ሻጭ እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ፋብሪካ ያረፈበት ቦታ 3,015 ካሬ ሜትር የግል ይዞታቸው መሆኑን ገልጸው ያቀረቡትን የይግባኝ አቤቱታ በመቀበልና በማረጋገጥ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ውሳኔ ሽሮታል፡፡ ያላግባብ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ እንዲፈጽሙ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያስተላለፈባቸውን ውሳኔ ለማሻር ይግባኝ ያሉት እነ በዕውቀቱ (ዶ/ር)፣ ውሳኔው ከመፅናቱም በተጨማሪ ያልጠበቁትና ይሆናል ብለው ያልገመቱት ተጨማሪ ውሳኔ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት እንደተሰጠባቸው ተናግረዋል፡፡

ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ውሳኔውን የሰጠው የገዥን የይግባኝ አቤቱታ የተቃወሙት ሻጭ እነ ጌታቸው (ኢንጂነር)፣ በስማቸው የሚገኝ የግል ይዞታቸው የሆነ 3,015 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ፣ ከፋብሪካው ጋር ተጠቃሎ በሕገወጥ መንገድ ለገዥ መሰጠቱ አግባብ አለመሆኑን ተቃውመው ያቀረቡት የይግባኝ አቤቱታ ይገልጻል፡፡ የሁለቱንም ወገኖች ይግባኝ አጣምሮ የተመለከተው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የእነ  በዕውቀቱን (ዶ/ር) ይግባኝ ውድቅ በማድረግ፣ ሻጭ ጌታቸው (ኢንጂነር) ያቀረቡን አቤቱታ በመቀበል፣ የጠየቁት 3,015 ካሬ ሜትር ቦታ ለገዥ መሰጠቱ አግባብ ባለመሆኑ፣ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ መሻሩንና ለሻጭ ይዞታው እንዲሰጥ ውሳኔ መስጠቱን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ተስፋ ያልቆረጡት የፋብሪካው ገዥ እነ በዕውቀቱ (ዶ/ር)፣ የመጨረሻው የፍርድ ቤት አካል ለሆነው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የመጨረሻውን፣ ‹‹የተፈጸመብኝ የሕግ ስህተት ይታረምልኝ፤›› አቤቱታቸውን እንዳቀረቡ የውሳኔው ሰነድ ያብራራል፡፡ ሰበር ችሎቱም አቤቱታውን ተቀብሎ ሻጭ ወይም ተጠሪዎች እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) መልስ እንዲሰጡ ማድረጉንና ገዥ እነ በዕውቀቱም (ዶ/ር) የመልስ መልስ እንዲሰጡ ካደረገ በኋላ፣ ይግባኝ ሰሚው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባሳለፈው ውሳኔ ላይ የፈጸመው መሠረታዊ የሕግ ስህተት መኖር አለመኖሩን መመርመሩን ሰበር ችሎቱ በውሳኔው ገልጿል፡፡

ለሰበር ችሎት የመጨረሻውን አቤቱታ ያቀረቡት እነ በዕውቀቱ (ዶ/ር) የጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ፋብሪካን በ22,500,000 ብር ገዝተው፣ ለሻጭ እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ወዲያውኑ ሁለት ሚሊዮን ብር መክፈላቸውንና እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከተበደሩት ውስጥ የቀረባቸውን ሰባት ሚሊዮን ብር ዕዳ በማቀናነስ፣ የቀረውን 13,500,000 ብር በአራት ዓመት ውስጥ ለመክፈል ሕጋዊ ውል በማድረግ መስማማታቸውን ለፍርድ ቤቱ አሳውቀዋል፡፡ በወቅቱ የፋብሪካው ሻጭ እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ውሉን አሜን ብለው ከመቀበል ባለፈ ያነሱት ምንም ዓይነት ተቃውሞ እንዳልነበረ ጠቁመው፣ ነገር ግን እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) የሽያጭ ውሉ ላይ ተቃውሞ ወይም ክህደት በማቅረባቸው፣ ጉዳዩ ከክልል ፍርድ ቤት እስከ ፌዴራል ፍርድ ቤቶች መድረሱን  በዕውቀቱ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰጠው ውሳኔ፣ በውሉ ላይ ያልተጠቀሰና መክፈል ከሚገባቸው 13,500,000 ብር ላይ ከ4.1 ሚሊዮን ብር በላይ በመጨመር 17,699,952 ብር እንዲከፍሉ የተወሰነውን ውሳኔ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማፅደቁ ‹‹መሠረታዊ የሕግ ስህተት መሆኑን›› ለሰበር ችሎቱ የቀረበው አቤቱታ ይገልጻል፡፡ የቀረበውን አቤቱታ የተመለከተው ሰበር ችሎት፣ የፋብሪካው ሻጮች እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ለሥር ፍርድ ቤት ያቀረቡት የክፍያ ጥያቄ ተገቢ መሆኑን በመጠቆም፣ የፋብሪካው ገዥዎች እነ በዕውቀቱ (ዶ/ር) የሚከፍሉትን የገንዘብ መጠን ወቅቱ  ሳይከፍሉ ጊዜው ማለፉን በማረጋገጥ፣ የተጠየቀውን 17,699,952 ብር ከወለድ ጋር እንዲከፍሉ የሥር ፍርድ ቤቶች ያስተላለፉት ውሳኔ ‹‹የሕግ ስህተት ፈጽመዋል›› ሊያስብላቸው እንደማይቻል በውሳኔው አሳውቋል፡፡ ነገር ግን እነ  በዕውቀቱ (ዶ/ር) የሰበር ችሎቱን ውሳኔ ይቃወማሉ፡፡ ምክንያቱም እነሱ ለሰበር ችሎቱ ያቀረቡት አቤቱታ፣ የሥር ፍርድ ቤቶች ሁሉቱ ተከራካሪ ወገኖች በሕጋዊ ውል ላይ ካሰፈሩት የገንዘብ መጠን በላይ ጨምረው፣ በአንድ ጊዜ እንዲከፍሉ የሰጡት ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ሰበር ችሎቱ የሕግ ስህተት መፈጸም አለመፈጸሙን ማረጋገጥ የሚልባቸውን የሕግ ድንጋጌዎችን እንኳን አለመመርመሩ ይናገራሉ፡፡ የሥር ፍርድ ቤቶች የሠሩትን ስህተት ቢገነዘቡም፣ ራሳቸው ማስተካከል ስለማይችሉ በደንብ መርምሮ ስህተቱን ማረም የነበረበት ሰበር ሰሚው ችሎት ቢሆንም፣ እውነታውን ትቶ በሕጋዊ መንገድ የተፈጸመን በውል የታሰረ ግብይት፣ ‹‹የሕግ ስህተት የለውም፤›› ብሎ ማለፍ፣ ተገቢ አለመሆኑንና ውሳኔውንም ለማስፈጸም እንደማይቻል ገዥዎች እየገለጹ ነው፡፡

ሌላው ለሰበር ችሎት የቀረበው አቤቱታ እነ በዕውቀቱ (ዶ/ር) የገዙት ፋብሪካ ጠቅላላ ስፋት 11,305 ካሬ ሜትር ሆኖ ሳለ፣ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነዱ (ካርታው) በሁለት አካላት የተመዘገበ መሆኑን በተለያዩ ሰነዶች ላይ በመግለጽ፣ ለክርክር ማስረጃነት ያቀረቧቸው ሰነዶች ያሳያሉ፡፡ ነገር ግን በገዥና በሻጭ መካከል አለመግባባት ሲፈጠር ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ፋብሪካ፣ ሙሉ በሙሉ ያረፈበት 3,015 ካሬ ሜትር ቦታ የግል ይዞታቸው መሆኑንና በስማቸው የተመዘገበ የሰነድ ማስረጃ እንዳለቸው በመግለጽ ያቀረቡት የይግባኝ አቤቱታ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተቀብሎ ውሳኔ መስጠቱን፣ መሠረታዊ የሕግ ስህተት መሆኑን በመግለጽ እንዲታረም መጠየቃቸውንም ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡ ቦታው ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ፋብሪካ ሙሉ በሙሉ እንዳረፈበት ገዥ የገለጹ ቢሆንም፣ ሻጭ እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ግን በቦታው ላይ ያለው የፍራፍሬ ማሸጊያ አገልግሎት የዋለ መሆኑን ሲገልጹ፣ ሰበር ችሎቱ በአካል ተገኝቶና የፋብሪካውን ሁኔታ ተመልክቶ ትክክኛ ውሳኔ ሳይመለከት፣ ‹‹ሰበር ችሎት የሕግ ስህተት ካለ ከማየት በስተቀር፣ የፍሬ ነገር ክርክርን መርምሮና ማስረጃ መዝኖ ውሳኔ መስጠት አይችልም፤›› በማለት፣ ገዥ ያቀረቡትን አቤቱታ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ በመጨረሻም የሥር ፍርድ ቤት ማለትም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ማፅናቱን የውሳኔው ሰነድ ያስረዳል፡፡

በሰበር ችሎት የመጨረሻ ውሳኔ ተስፋ የቆረጡትና መራራ ፍርድ እንደሆነባቸው የሚናገሩት የፋብሪካው ገዥ እነ በዕውቀቱ (ዶ/ር)፣ ውሳኔ የሰጡትን የሰበር ዳኛ ከችሎት ውጪ በመሳደብ ለድብድብ ተጋብዘዋል በሚል ከእነ ባለቤታቸውና ቤተሰቦቻቸው ችሎት በመድፈር ወንጀል ታስረው፣ ከአንድ ወር እስከ ስድስት ወራት የሚደርስ የእስራት ቅጣት ተወስኖባቸዋል፡፡ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ በሕጋዊ ውል የገዙት ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ፋብሪካ ያረፈበት 3,015 ካሬ ሜትር ቦታ ለሻጭ እንዲሰጥ ውሳኔ ተሰጥቶ፣ እሳቸውና ቤተሰቦቻቸው ወደ ማረሚያ ቤት መወርወራቸውን ሰነዶች ከማረጋገጣቸውም በተጨማሪ እነ  በዕውቀቱም (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

ምንም እንኳን የመጨረሻው የፍርድ ቤት አካል የሆነው ሰበር ሰሚ ችሎት እስር ቢወሰንባቸውም፣ ተስፋ ያልቆረጡት እነ በዕውቀቱ (ዶ/ር)፣ በጠበቆቻቸው አማካይነት ችሎት በመድፈር ወንጀል የተጣለባቸው የቅጣት ውሳኔ፣ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 20፣ 25፣ 40፣ 9፣ 13 እና 79(3) ድንጋጌዎችን የሚቃረን መሆኑን ጠቁመው፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥላቸው አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ለዚህ የዳረጋቸውም በሕጋዊ ውል የገዙት ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ፋብሪካ ግዥ ጋር የተያያዘ መሆኑን፣ ከፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ የደረሰ ክርከር ቢያደርጉም፣ ሕጉን ያልተከተለና ዜጎች በሕገ መንግሥቱ ያገኙትን መብት የሚያሳጣና የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች የሚቃረን ውሳኔ መሆኑን በመጥቀስ፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥላቸው ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የመጨረሻ አቤቱታቸውን ማቅረባቸውን የውሳኔ ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

ጉባዔው የቀረበለትን አቤቱ ከተቀበለ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን ውሳኔ በማገድ ምርመራውን እንደ ጀመረም ሰነዶች ያሳያሉ፡፡ ጉባዔው ባለሙያዎችን ወደ ፋብሪካው በመላክና በአካል በማስጎብኘት፣ ፋብሪካው የሻጭ ይዞታ ነው በተባለው 3,015 ካሬ ሜትር ላይ እንደተገነባ ማረጋገጡን፣ እነ በዕውቀቱ (ዶ/ር) የምግብ ማቀነባበሪያ እንደሆነ ተደርጎ ለፍርድ ቤቶች መከራከሪያነት የቀረበው ሁሉ ሐሰት መሆኑ በቪዲዮ ካሜራ ጭምር በመቅረፅ መመለሱን የቀረበው ሪፖርት ያስረዳል፡፡

ነገር ግን ጉባዔው የላካቸው ባለሙያዎች የቀረፁትንና የተመለከቱትን ሪፖርት ያላካተተ ውሳኔ መስጠቱን ባለሀብቱ በዕውቀቱ ታደሰ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሰጠው ውሳኔ የገለጸው በአካል ተገኝቶ ያረጋገጠውንና ለማስረጃ በቪዲዮ ጭምር ቀርፆ ያስቀረውን ማሰረጃ ያካተተ ሳይሆን፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ሰበር ሰሚ ችሎች የሰጡትን ውሳኔ ቃል በቃል በመገልበጥ መሆኑን የውሳኔ ሰነዱ ያስረዳል፡፡ በመሆኑም ፋብሪካውን የገዙት እነ በዕውቀቱ (ዶ/ር) ከሕግ ተርጓሚ እስከ ሕገ መንግሥት ተርጓሚ ድረስ ያደረጉት እውነትና ፍትሕ ፍለጋ ከንቱ ልፋት መሆኑንና ከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንዳስገባቸው እየገለጹ ነው፡፡

የተፈጸመባቸው በደል እውነት መሆኑን የሚያረጋግጠው፣ እነ ጌታቸው እሸቱ (ኢንጂነር) በመጨረሻዎቹ የፍርድ ቤት ችሎቶች ያገኙትን ፍትሕ ለማረጋገጥ ንብረታቸውን ለማስረከብ የፌዴራል ፍርድ ቤቶቸ ፍርድ አፈጻጸም ቡድን ፋብሪካው ባለበት ቦታ መገኘቱን ሰነዶች ያሳያሉ፡፡ ነገር ግን የግል ይዞታ ነው በተባለው 3,015 ካሬ ሜትር ቦታ ነፃ ሳይሆን ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማከፋፈያ ፋብሪካ የተገነባበት ሆኖ ስላገኘው፣ ቡድኑ ማስፈጸም እንደማይቻል ለተቋሙ ሪፖርት አቅርቦ እስካሁን ማስፈጸም እንዳልተቻለም የተጻፉ ሰነዶች ያሳያሉ፡፡ 

ምናልባትም ሕግ የነፈጋቸውን እውነታ የአገር መሪዎች ተመልክተው ‹‹ዕንባችንን ሊያብሱልን ይችላሉ፤›› የሚል ተስፋ በመሰነቅ፣ በስምምነት ከፈጸሙት የፋብሪካው ግዥ ሕጋዊ ውል፣ ባለመስማማት ወደ ፍትሕ አደባባይ ሄደው እስከ ሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ድረስ ያደረሳቸውን የክርክር ሒደቶች የሚገልጹ የማስረጃ ሰነዶችን አባሪ በማድረግ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ለኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር፣ ለፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ እንዲሁም ለሌሎች ተቋማትም ‹‹የፍትሕ ያለህ›› ደብዳቤ ጽፈው ምላሽ እየተጠባበቁ መሆኑን ከሰነዶች ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...