በዓሊ ኩራ
- ከጅምር እስከ ጉዞ
የተከበርከው የኦሮሞ ሕዝብና ብሔር ብሔረሰቦች እንደምን ከረማችሁ? እነሆ የዛሬ ዓመት የተፈጸመን ጉዳይ ግልጽ ለማድረግ ወስኛለሁ፡፡ ይህንን የምጽፈው እውነታውን ይፋ ለማውጣት እንጂ፣ ማንንም ለማሳጣት ዓላማ በማድረግ አይደለም፡፡ ጉዳዩን በጽሑፍ ለማቅረብ የፈለግሁት ባለፈው አንድ ዓመት ስለጉዳዩ የተነገረውና የተጻፈው ትክክለኛነቱ ከግማሽ የማያልፍ በመሆኑ ነው፡፡ ሁሉም በሚባል ደረጃ ስለጉዳዩ ሲጽፉና ሲተቹ ከሌሎች በመጠየቅና በግምት እንጂ፣ የዕርቅ ኮሚቴው አባል የሆነ አንድም ሰው ሚዛናዊ ሆኖ አለመጻፉ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ መንገድ ጽፌያለሁ፡፡
እኔ በኦሮሞ ኅብረተሰብ ባህልና ሥርዓት መሠረት አባ ገዳ የሆንኩ፣ ባለፈው ዓመት የመንግሥትና የኦነግ አስታራቂ ኮሚቴ አባል ለመሆን የበቃሁ ሰው ነኝ፡፡ በተፈጥሮዬ በአዕምሮም በጽሑፍም ማስታወሻ የመያዝ ልማድ ስላለኝ ከሞላ ጎደል ይህንን ጽሑፍ ለማቅረብ ሞክሬያለሁ፡፡ ስለዚህ መጀመርያ ጉዳዩን ሳልቀንስ ሳልጨምር ከመጀመርያ እስከ መጨረሻ ድርጊቶቹን አቀርባለሁ፡፡ በመጨረሻ አስተውሎቴን መሠረት አድርጌ የራሴን ትዝብት አቀርባለሁ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የሰዎችን ስም የጠቀስኩት ሳላስፈቅድ ቢሆንም፣ ታሪክ ስለሆነ የሰዎችን ማንነት መደበቅ ታሪኩን ጎዶሎ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ስም መጥቀስ ግዴታ ሆኗል፡፡
ባለፈው ዓመት ማለትም በ2011 ዓ.ም. በመጀመርያዎቹ ወራት በኦነግ ታጣቂዎችና በመንግሥት ሠራዊት መካከል ግጭት ስለተፈጠረና በዚህ መሀል ንፁኃን ወገኖች እየተጎዱ ስለሆነ፣ አባ ገዳዎች ምን ትጠብቃላችሁ? ዕርቅ ለምን አታወርዱም? የሚል ጫና ከተለያየ አቅጣጫ መጉረፍ ጀመረ፡፡ ጥሪው ወደ አባ ገዳዎች ከመምጣቱ በፊት ዳያስፖራዎቹ የኦሮሞ ምሁራን ለኢትዮጵያ መንግሥት የተማፅኖ ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡ እንዲሁም እንደ እነ ኃይሌ ገብሬ፣ አዴ ጠይባና ሌሎች ግለሰቦች በግል ተነሳሽነት ይሁን በመንግሥት ቀስቃሽነት የኦነግ ታጣቂዎችን ለማነጋገር ወደዚያው አቅንተው ነበር፡፡ ነገር ግን ተጨባጭ ውጤት አልተገኘም፡፡
ከዚህ በኋላ አባ ገዳዎች ላይ ጫና እየበረታ ሲመጣ በየአካባቢው ያለን አባ ገዳዎች በስልክ ተነጋግረን፣ በአቶ በየነ ሰንበቶ የሚመራው የኦሮሞ አባ ገዳዎች ጉባዔ እንዲጠራ ተስማማን፡፡ ጉባዔው ተጠርቶ ጥር 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ፊንፊኔ በኦሮሞ ባህል ማዕከል ተሰበሰብን፡፡ የተሰበሰብነው 50 ያህል የምንሆን ሲሆን፣ ከጥቂት ወጣቶች በስተቀር ሁሉም አባ ገዳዎችና ሃደሲቄዎች ነበሩ፡፡ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች የሚባሉት አልነበሩብንም፡፡ ስለዚህ በእርጥብ ሳር እግዚአብሔርን ከተማፀንን በኋላ በበየነ ሰንበቶና በጫላ ሶሪ መድረክ መሪነት ከረፋድ እስከ ምሽት ውይይታችን የተካሄደው በፍፁም ቅንነትና መተማመን ነበር፡፡ ሆኖም በግለሰቦች ግንዛቤ ጉድለት አንድ የአካሄድ ስህተት ተፈጸመ፡፡ እንዲህ ነው፡፡
ከየዞኑ የመጣን ሰዎች ስለወቅታዊ ችግሩ የምናውቀውን በመናገር ቤቱ ግንዛቤ እንዲያገኝ አደረግን፡፡ በተፈጠሩት ችግሮች ላይ በሰፊው ስንወያይ ከዋልን በኋላ፣ ባለጉዳዮቹን እንዴት ወደ ዕርቅ መድረክ እናምጣ የሚል ወሳኝ ጥያቄ ተነሳ፡፡ በገዳ ውስጥ አልፈው ዩባ የሆኑት ቀነዓ ለሚ (ዶ/ር) የተባሉ ሰው እጅ አውጥተው፣ መቼም ይህ ሁሉ ሰው ባለጉዳዮቹን ማነጋገር አይችልም፡፡ ስለዚህ ከመካከላችን ጥቂት ሰዎችን መርጠን መንግሥትንም፣ ኦነግንም ያነጋግሩና ሁለቱም ወገኖች ዕርቅ የሚፈልጉ መሆናቸው ይረጋገጥ፡፡ ከዚያ በኋላ ቀጣዩ አካሄድ ይወሰናል አሉ፡፡
አንድ ከምሥራቅ ሐረርጌ የመጡ ሰው ሐሳቡን ደግፈው ተናገሩ፡፡ እኔም ይህንኑ ሐሳብ ደግፌ ተናገርኩ፡፡ አባ ገዳ ባይሆኑም በአገር ሽማግሌነት በአቶ ሆርዶፋ ዴቲ ጥሪ የመጡት፣ ነፍሳቸውን ይማርና አሁን በሕይወት የሌሉት አቶ ዓለማየሁ እሬሶ የተባሉ ሰው እጅ አውጥተው፣ ሰው ከመሀላችን አንመርጥም ሁላችንም አንድ ነን፣ አንድ ላይ ሆነን ነው የምናነጋግራቸው፣ እነሱ ጋ መሄድም አያስፈልግም፣ ጥሪውን ማሳወቅ ነው፡፡ መንግሥትም ኦነግም እዚሁ የኦሮሞ ባህል አዳራሽ መጥተው መነጋገር አለብን፡፡ ደግሞ ከሁለቱም ወገን ቁንጮዎቹን እንጂ ተወካዮችን አንፈልግም ብለው በስሜት ተናገሩ፡፡
ሰዎችም በስሜት ተንጠው “ኤዬን. . . ኤዬን. . . ኤዬን. . .” አሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሽምግልና የት አገር ነው የታየው ካልመጡስ ምንድነው የሚደረገው ብለን ብንከራከርም፣ ለሕዝብ ተናግረን ሕዝብ እናዘምትባቸዋለን ብለው ጥቂቶች ተመፃደቁ፡፡ ጥቂቶች ቢሆኑም ስሜታዊነትን ፈጥረው ሐሳባቸው እንዲያልፍ አደረጉ፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ዕርቁ የተፀነሰ ዕለት ምች መታው፡፡
ሙሉ ቀን ስንወያይ ውለን ምሽት ላይ በኦቦ ጫላ ሶሪና ቀነዓ ለሚ (ዶ/ር) የተዘጋጀ ዘጠኝ ነጥብ ያለው የአቋም መግለጫ በዶ/ሩ ተነቦልን አፀደቅነው፡፡ መግለጫው በየነ ሰንበቶ ከሚጽፉት ደብዳቤ ጋር አባሪ ሆኖ ለመንግሥትና ለኦነግ እንዲደርስ ተወሰነ፡፡ ጥር 14 ቀን 2011 ዓ.ም. በኦሮሞ ባህል አዳራሽ አባ ገዳዎች፣ ሃደሲቄዎች፣ ወጣቶች፣ የኦሮሞ ፖሊቲካ ፓርቲ ተወካዮችና አክቲቪስቶች አሸብርቀው ተገኙ፡፡ ከተገኙት አካላት ውስጥ የተለያዩ የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችና የአክቲቪስቶች መገኘት አብዛኛዎቻችንን ግር አሰኘን፡፡ በኋላ እንደ ደረስንበት ኦቦ ጀዋርና ኦቦ በቀለ ገርባ እንዲሁም ኦቦ ኃይሌ ገብሬ፣ አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ መክረው እንዳደረጉት አውቀናል፡፡
የጥር 14 መድረክ በአባ ገዳዎቹ ምርቃት ከተከፈተ በኋላ የዕለቱን አጀንዳዎች ያስተዋወቁት ቀነዓ ለሚ (ዶ/ር) ውይይቱ በኦሮሞ ባህልና ወግ መሠረት በሰላምና በረጋ መንፈስ እንዲካሄድ አሳስበው፣ መድረኩን ኦቦ በየነ ሰንበቶና ኦቦ ጫላ ሶሪ መምራት ጀመሩ፡፡ መንግሥትና ኦነግ ዕርቁን እንዲቀበሉ ኦቦ በየነና ኦቦ ጫላ አንድ ሰዓት ሙሉ ቆመው ተማፀኑ፡፡ ከሁለቱ ሰዎች ተማፅኖ በኋላ የኦነግ መሪ ኦቦ ዳውድ ኢብሳና የኦዴፓ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በየተራ ባደረጉት ንግግር ዕርቅን የሚጠላ እንደሌለ ገለጹ፡፡ እዚህ ላይ የኦቦ ዳውድ ውክልና የማያሻማ ሲሆን፣ የዶ/ር ዓለሙ ስሜ አሻሚ ነበር፡፡ የኦሮሚያ ክልል መንግሥትን ይሁን ወይም የፌዴራል የትኛውን እንደወከሉ በግልጽ አልታወቀም፡፡
እንዲሁ የመንግሥት ተወካይ ተብሎ ተያዘና ውይይቱ ቀጠለ፡፡ የሁለቱም ኃላፊዎች ንግግር በሚዲያ ተሠራጭቶ ሁሉም የሚያስታውሰው ስለሆነ እዚህ መዘርዘር አያስፈልግም፡፡ ከሁለቱ ኃላፊዎች ንግግር በኋላ ወደ ተሳታፊዎች ውይይት ተገባ፡፡ በተሳታፊዎች ውይይት ላይ ከተናገሩት ውስጥ የኦቦ ጀዋር መሐመድ መጠቀስ ያለበት ነው፡፡ ኦቦ ጀዋር፣ ‹‹እነዚህ ሰዎች ይዋሹናል፣ ግልጽ እንነጋገር ከተባለ ኦዴፓም ኦነግም ይዋሻሉ፣ አባ ገዳዎች ደግሞ ታባብላላችሁ፣ የምትዋሹም ውሸቱን ተውት፣ የምታባብሉም ማባበሉን ተውት. . .›› ካለ በኋላ፣ ‹‹እንዲያውም ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ለምን እዚህ እንደ መጣ አይገባኝም?›› አለና ሳይቆይ ተነስቶ ወጣ፡፡ በጀዋር ንግግር ከእነ ዓለሙ ስሜ የበለጠ እኛ አባ ገዳዎች ተሸማቀቅን፡፡
በሽምግልና ሥነ ምግባር መሠረት የጀዋር አነጋገር ተገቢ ስላልሆነ ብዙ አባ ገዳዎች ቅር አለን፡፡ ጀዋር ባህላዊ የዕርቅ ሥርዓትን እንደማያውቅና ችኩል መሆኑንም ተረዳን፡፡ ስሜታቸው የተቀሰቀሰ ወጣቶች ግን አጨበጨቡ፡፡ አባ ገዳ በየነ፣ ‹‹. . . ለምነን አባብለን፣ ሃቁን በአግባቡ አስረድተን እንጂ ሰድበናቸው እንዴት እናስታርቃለን?›› በማለት በጀዋር አባባል ቅሬታቸውን ገልጸው ነበር፡፡ ኦቦ በየነ ይህንን የተናገሩት ጀዋር እያለ ይሁን ወይም ከወጣ በኋላ ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
ኦቦ ኃይሌ ገብሬ ደግሞ ኦነግና መንግሥትን ‹‹ከብት ካስፈለገ ከብት አርደን እናስታርቅ፣ ሰው ካስፈለገ እኔን አርዳችሁ አስታርቁ፤›› ብለው ሕዝቡን አስለቀሱ፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ መናገር የሚፈልግ ሁሉ እጁን እያወጣ የተሰማውንና መሆን አለበት የሚለውን፣ በተለይም ስለሰላም አበክሮ ከተናገረ በኋላ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በሰጡት አስተያየት ውስጥ አንድ የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲቋቋም ሐሳብ አቀረቡ፡፡ ሐሳቡ ተቀባይነት ስላገኘ ተሳታፊው ዕረፍት እንዲወስድና የተወሰኑ አባ ገዳዎች (እነ ኦቦ በየነ ሰንበቶ፣ ኦቦ ጫላ ሶሪ፣ ኦቦ ሆርዶፋ ዴቲና ሌሎችም ነበሩበት) ዕጩ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላትንና በተጨማሪ የዕርቅ ኮሚቴ አባላት የሚሆኑትን መርጠው እንዲያቀርቡ ተደረገ፡፡
በዚሁ መሠረት የተወሰነ አባ ገዳዎች የአዳራሹ ግራ ረድፍ ላይ ተቀምጠን የዕጩ ተመራጮችን ስም ስናጽፍ ስናሰርዝ ጊዜ ፈጀን፡፡ አንዳንዱ ሰው አክቲቪስት መግባት የለበትም ይላል፣ ሌላው ሊረዱን ስለሚችሉ ይግቡ ይላል፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትም መግባት የለባቸውም የሚል ብዙ ተቃውሞ ነበር፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አክቲቪስቶች ከገቡበት ይኼ ዕርቅ፣ ዕርቅ ከሆነ ከምላሳችን ፀጉር ይነቀል ብለው የማሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ በዚህ ክርክር ምክንያት ኦቦ ጀዋር ሦስት ጊዜ ተጽፎ ሦስት ጊዜ ተሰርዞ በአራተኛው ተወሰደ፡፡ ኦቦ በቀለ ገርባና ብርሃነ መስቀል አበበ (ዶ/ር) ሁለት ጊዜ ተጽፈው ሁለት ጊዜ ተሰርዘው በሦስተኛ ተወሰዱ፡፡ የተወሰኑ ወጣቶች በመዝጋቢዎቹ ላይ ጫና በማድረግ ጀዋርና በቀለ እንዳይቀሩ አድርገዋል፡፡ ጭቅጭቁ ስለበዛ እኔና የተወሰነ አባ ገዳዎች በመሀል ላይ ትተን ውኃ መጠጣት ሄድን፡፡ ኦቦ በየነ፣ ኦቦ ጫላ፣ ኦቦ ሆርዶፋ ዴቲና ሌሎችም ተስፋ ሳይቆርጡ በመጨረሻ ላይ 11 ዕጩ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላትና 54 የዕርቅ ኮሚቴ አባላት መርጠው መድረክ ላይ ወጥተው ለቤቱ አሳወቁ፡፡
ዕጩ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት
- ጃፈር ዓሊ
- ጀዋር መሐመድ
- በቀለ ገርባ
- ታደሰ በሪሶ (ዶ/ር)
- ቀነዓ ለሚ (ዶ/ር)
- ብርሃነ መስቀል አበበ (ዶ/ር)
- ኃይሌ ገብሬ
- ጌታቸው ድብሳ
- ሌንጮ ቀነዓ
- ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ
- ካብር ሁሴን መሆናቸው ተገለጸ
በቀረቡት ዕጩዎች ላይ አስተያየት እንዲሰጥ መድረክ መሪዎቹ (ኦቦ በየነና ኦቦ ጫላ) ጠየቁ፡፡ ከዚህ በፊት በተናገሯቸው ንግግሮችና በጻፏቸው ጽሑፎች ምክንያት ገለልተኞች አይደሉም የሚል ተቃውሞ በኦቦ ጃፈር ዓሊና በዶ/ር ብርሃነ መስቀል ላይ በብዛት ቀረበ፡፡ የቀረበው ተቃውሞ ጠንካራ ስለሆነ አባ ገዳዎቹ በቸልታ ሊያልፉ አልቻሉም፡፡ ተቃውሞ በተነሳባቸው ሰዎች ምትክ ሌላ ጥቆማ እንዲደረግ ተጠየቀና ተጠቆመ፡፡ በዚሁ መሠረት አንድ የማላውቀው ሰው ወ/ሮ መኪያ የሚባሉትን ሲጠቁም፣ ኦቦ ድርቢ ደምሴ ግርማ ባልቻ (ዶ/ር) ጠቁመው ይሁኑ ተባለ፡፡ ከዶ/ር ግርማ በፊት ፕሮፌሰር መረራ ተጠቁመው ነበር፡፡
ኦቦ በየነ የፓርቲ አባል ናቸው ብለው አለፉ፡፡ ቤቱ ሳቀ፡፡ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ምን እየተሠራ ነው በቀለ የፓርቲ አባል አይደለም እንዴ? ምን ማለት ነው? ብለው አጉረመረሙ፡፡ በነገራችን ላይ ከቪዲዮውም እንደሚታየው አብዛኞቹ አባ ገዳዎች ከእነ ዶ/ር ዓለሙ ስሜ፣ ኦቦ ሞገስ ኢደኤና አርቲስት እልፍነሽ ቀኖ ጀርባ ስለተቀመጥን እነ ዶ/ር ዓለሙ በቀስታ የሚናገሩትን እንሰማ ነበር፡፡ እውነቱን ለመናገር የመንግሥት ተወካዮች የተባሉት በኮሚቴዎቹ ላይ ቅሬታ አለን ብለው በተለይም ኦቦ በቀለንና ኦቦ ጀዋርን ለመቃወም ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን እነ ኦቦ በየነም ዕድል ስላልሰጧቸውም፣ እነሱም እዚያ ያለው ሕዝብ ይጮህብናል ብለው በመፍራት (ይመስለኛል) ድምፃቸው ለሁሉም እንዲሰማ አድርገው አልተናገሩም፡፡
እነዚህ የቴክኒክ ኮሚቴ ሲሆኑ አባ ገዳዎችና ሃደ ሲቄዎች የዕርቅ ኮሚቴ ተባሉ፡፡ የዕርቅ ኮሚቴው በዕለቱ በቦታው የተገኙትን ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ዕርቅ ሥፍራው ሲኬድ ሊያግዙ የሚችሉ በየገዳ ማዕከላት ያሉ አባ ገዳዎችንና ሃደ ሲቄዎችን የሚጨምር ነበር፡፡ ከየገዳ ማዕከላቱ ሦስት ሃደ ሲቄና ሦስት አባ ገዳዎች ተብሎ 54 አባላት ያሉት የዕርቅ ኮሚቴ ተመሠረተ፡፡ ከዕርቅ ኮሚቴ አባላት በዕለቱ በቦታው ያሉት ከ40 የሚበልጡ አይመስለኝም፡፡ የቴክኒክ ኮሚቴና የዕርቅ ኮሚቴ በዚህ መልኩ ከተደራጀ በኋላ፣ ከሚታረቁት ወገኖች ሦስት ሦስት ተወካዮች እንዲኖሩ ተወሰነ፡፡ በዚህ መሠረት ከኦነግ ኦቦ አብዲ ረጋሳ፣ ኦቦ ዱጋሳ በከኮና ኦቦ ሚካኤል ቦረና ተወከሉ፡፡ በኦዴፓ በኩል ኦቦ ሞገስ ኢደኤ፣ ኦቦ ዓለማየሁ እጅጉና ኦቦ ኢተፋ ቶላ ተወከሉ፡፡ ከፌዴራል መንግሥት የተወከለ አልነበረም፡፡
በሒሳብ ደረጃ ሲሰላ 54 የዕርቅ ኮሚቴ፣ 11 የቴክኒክ ኮሚቴ፣ ከመንግሥትና ከኦነግ ስድስት ተወካዮች፣ በጠቅላላው የዕርቅ ሒደቱን የሚያመቻቹና ተግባራዊ የሚያደርጉ 71 አባላት ተብሎ ተገለጸ፡፡ ሚዲያ ግን በሰነፍ ጋዜጠኞች ወይም መግለጫ በሰጧቸው ሰዎች ስህተት ሁሉንም አንድ ላይ የቴክኒክ ኮሚቴ ብለው ከማስተላለፋቸውም በላይ ቁጥሩን 72 ብለው አወጁ፡፡ በዚህ ምክንያት እስከ ዛሬ 72 የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ተብሎ ይታወቃል፡፡ ይህ ስህተት በዕርቅ ሒደቱ ላይ ተፅዕኖ ባይኖረውም፣ ለታሪክ ምንጭ ከመሆን አንፃር ቀላል የማይባል ስህተት ነው፡፡
የተመረጡት የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት 11 ነበሩ፡፡ ለዚያውም ግርማ ባልቻ (ዶ/ር) ተጀምሮ እስኪያልቅ አንድም ቀን ያልተሳተፉ በመሆኑ፣ በተጨባጭ ሥራ ላይ የነበሩት አሥር የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ብቻ ነበሩ፡፡ ስብሰባው በዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲካሄድ ውሎ ወደየማደሪያችን ከገባን በኋላ ምሽቱን የእኛ ዜና ሚዲያውን አጣበበ፡፡ ኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሰው ዜናውን እየተቀባበለ ገዳ ይመራል ብሎ አወደሰ፡፡ ዕርቁ እንደሚሳካ ተስፋ አደረገ፡፡ ይህንን ስናይ እኛ አባ ገዳዎች ጭንቅ ውስጥ ገባን፡፡ ካልተሳካስ ለሚለው መልስ ስላላገኘን፡፡ ብቻ ተሰብስበን በምናድርበት ቦታ ፀሎታችንን አፀናን፡፡ በስልክ እየተደዋወልን በፀሎት እንድንተጋ ተነጋገርን፡፡
በማግሥቱ ጥር 15 ቀን 2011 ዓ.ም. የቴክኒክ ኮሚቴው እዚያው ኦሮሞ ባህል ማዕከል በጧት ተሰበሰበ፡፡ ከአባ ገዳዎችም የተወሰንነው እኛንም የሚመለከተን መስሎን ገባን፡፡ የቴክኒክ ኮሚቴዎች እስኪሟሉ ተብሎ እስከ ረፋዱ አራት ሰዓት ተጠበቀ፡፡ ከ11 ስምንት አባላት ተገኙ፡፡ ከአሥራ አንዱ ዶ/ር ግርማ፣ ኦቦ ካብርና ኣዴ መኪያ አልተገኙም፡፡ አራት ሰዓት ሲሆን ኦቦ ኃይሌ ወደ መድረክ ሄደው መሀል ባለው ወንበር ላይ ተቀመጡ፡፡ ቀጥለው ኦቦ በቀለን ጠሩና በቀኛቸው አስቀመጡ፡፡ ቀጥለው ጀዋርን ጠርተው በግራቸው አስቀመጡ፡፡ ከዚያ እኔ የቴክኒክ ኮሚቴውን እመራለሁ፣ በቀለ የእኔ ምክትል ይሆናል፣ ጀዋር ደግሞ ጸሐፊያችን ይሆናል ብለው ነገሩን፡፡ አካሄዱ ግር ስላለኝ በእኔ ረድፍ ከተቀመጡት የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት አንዱን መቼ ተመራረጣችሁ ብዬ ጠየኩዋቸው፡፡ ይኼ በራስ ተነሳሽነት ኃላፊነት መውሰድ ስለሆነ ባንመራረጥም ችግር የለውም አሉኝ፡፡ ለአካሄዱና ለመተማመን ብዬ እንጂ እሱስ ችግር አለው ብዬ አይደለም እንዳልኩኝ ኦቦ ኃይሌ፣ ‹‹እናንተ አባ ገዳዎች ከሰዓት ነው የምንገናኘው፣ አሁን ቦታ ልቀቁልን፤›› አሉ፡፡ እኛም ወጣን፡፡
ከሰዓት በኋላ አባ ገዳዎችና ሃደ ሲቄዎች በአንዱ አዳራሽ ውስጥ ሆነን ቴክኒክ ኮሚቴውን ስንጠብቅ ነበር፡፡ መጠበቁ እጅግ አሰልቺ ነበር፡፡ አመሻሽ ላይ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ስምንት ሆነው መጡ፡፡ በማግሥቱ አምቦ ላይ ሊቀርብ የተዘጋጀውን መግለጫ ረቂቁን አቀረቡልን፡፡ ጀዋር አምስት ዋና ዋና ነጥቦች ያሉት ረቂቅ አንብቦልን ይሆናል ያልነውን ጨማምረንበትና ይኸው በደንብ ተጽፎ ይቅረብ ካልን በኋላ፣ ቀነዓ ለሚ (ዶ/ር) እጅ አውጥተው ‹‹ከጧት ጀምሮ ባደረግነው ውይይ ላይ የሚገባው ሠራዊት ከወንጀል ነፃ የመሆን መብት እንዲኖረውና በይቅርታ እንዲታለፍ የሚለው ስድስተኛ አንቀጽ ይኑር የሚል ሐሳብ አቅርቤ በሐሳቡ ላይም የዕርቅ ጎዶሎ የለውም በሚል መነሻ ማብራሪያ ሰጥቼ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር፣ አሁን አላቀረብከውም፤›› ሲሉ፣ ‹‹አዎን እውነት ነው፣ ዘልየው ነው ይቅርታ፤›› ብሎ ጀዋር ከወንጀል ነፃ የመባል መብት ምን ማለት እንደሆነ ኮሚቴው የተነጋገረበትን ከገለጸልን በኋላ ጻፈው፡፡ ሁላችንም በአንቀጹ መኖር ደስታችን ገለጽን፡፡
በማግሥቱ ጥር 16 ቀን 2011 ዓ.ም. አምቦ ከተማ በተካሄደው ጉባዔ ላይ የውሳኔ ሐሳብና የአተገባበር መርሐ ግብር የያዘው መግለጫ በጀዋር ተነበበ፡፡ መግለጫው በጀዋር በመነበቡ ደስ ቢለንም በጀዋር ድምፅ ብዙዎቻችን አልተደሰትንም፡፡ ሌሎች ጥሩ ድምፅ ያላቸው ማንበብ ይችሉ ነበር፡፡ የአምቦውን ሥነ ሥርዓት በሚዲያ ተላልፎ አብዛኛው የሰማውና ያየው ስለሆነ እሱን ለማብራራት አልለፋም፡፡ ነገር ግን ሰዎች ልብ ያላሉት ወይም ጥቂቶች ብቻ በጨረፍታ ሰምተው ሙሉ ማብራሪያ ሊሰጡበት ያልቻሉት አንድ ነገር ነበር፡፡ እሱም ኦቦ ኃይሌ ገብሬ፣ ‹‹የኦሮሞን ትግል ማነው በቀዌ (ጠመንጃ) የጀመረው? ኤሌሞ ነው ወይስ ታደሰ ነው? ብቻ የጠመንጃ ትግል ማብቃት አለበት፤›› ብለው በአምቦው መድረክ ላይ የተናገሩት ነው፡፡ ይህንን አባባል ብዙ ሰው የወሰደው መዋጋት ይቁም ለማለት ተፈልጎ ይሆናል በሚለው አጠቃላይ አንድምታ ነበር፡፡ ሆኖም በዚያኑ ቀን በሌላ ቦታ በጥቂት ሰዎች ፊት፣ ‹‹ይህ “አባቦ” የሚያካሄደውን ጦርነት ማስቆም አለብኝ፣ ኤሌሞ ነው ወይስ ታደሰ ነው? ይህን በጠመንጃ ትግል የጀመረው? የጀመረውን አስተካክላችሁ ንገሩኝ፣ ለማንኛውም በሆነው ሰው የተጀመረውን የትጥቅ ትግል ኃይሌ ወደ ሰላም ቀይሮ አስቆመው መባሉ አይቀርም፣ አስቆማለሁ፣ ደግሞ እግዚአብሔርን ብቻ ለምኑልኝ፤›› ብለው መናገራቸው ተሰምቷል፡፡ በነገራችን ላይ ኦቦ ኃይሌ አባኦን (ኦነግን) “አባቦ” ብለው ነው የሚጠሩት፡፡
ከአምቦ መድረክ ቀጥሎ ዓርብ ጥር 17 ቀን 2011 ዓ.ም. የቴክኒክ ኮሚቴውና የዕርቅ ኮሚቴ ከረፋዱ በአራት ሰዓት ላይ በተለመደው ቦታ ስብሰባ ተቀመጥን፡፡ መድረኩን ለመምራት የተቀመጡት አሁንም ኃይሌ፣ በቀለና ጀዋር ነበሩ፡፡ ሰው ሁሉ ግራ ገባው፡፡ እኔንም እንደዚያው፡፡ ያወጣነው የተለየ ሕግ ባይኖርም ዕርቁን በባለቤትነት የሚመራው የኦሮሚያ አባ ገዳዎች ጉባዔ ስለሆነ፣ የጋራ ስብሰባውን ኦቦ በየነና ኦቦ ጫላ ሶሪ መምራት ነበረባቸው፡፡ ለማንኛውም ስብሰባው ቀጠለ፡፡
ከስብሰባው አጀንዳዎች ሁለቱ የፌዴራል መንግሥትን እንዴት እናናግር የሚልና የኮሚቴዎቹን ቃል አቀባይ መምረጥን የሚመለከት ነበር፡፡ የፌዴራል መንግሥትን ለማነጋገር በሚመለከት የመንግሥት ተወካዮች ከእነ ኦቦ በየነ፣ ጀዋርና በቀለ ጋር ሆነው ለሚቀጥለው ቀን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ቀጠሮ እንዲያሲዙ ተወሰነ፡፡ ለዚህ ዕርቅ መሳካት ጠቅላይ ሚኒስትሩንና በወቅቱ የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት (ኦቦ ለማ) ማነጋገር ወሳኝ መሆኑ ላይ ውይይት በምናደርግበት ጊዜ ዛሬም ኦቦ ዓለማየሁ እሬሶ ብድግ ብለው፣ ‹‹ዕርቁ እንዲሳካ ከተፈለገ ዋና ቁልፍ ያዥ መምጣት አለበት፣ እሱም ለማ መገርሳ ነው፡፡ እሱ ካልሆነ እኛ ምስለኔ አንፈልግም፤›› አሉ፡፡ አባባላቸው የመንግሥት ተወካዮችን አስቆጣ፡፡ ሁላችንም ተናደድን፡፡ እኔ በግሌ ከወጣን በኋላ እርስዎ ዕርቁ እንዳይሳካ ይፈልጋሉ እንዴ? ምንድነው መሳደብ ብዬ ተቆጣሁኋቸው፡፡ ይኼ ዛሬ ገና ወደ ኋላ ተመልሰን ባለሥልጣናትን እናናግር የሚባለው ከሁሉ በፊት መሆን የነበረበት ነበር፡፡ በዚያን ጊዜም እርስዎ ነዎት ያሰናከሉት ብሎ ብዙ ሰው ወረደባቸው፡፡ ኦቦ ዓለማየሁ ከዚያን ቀን ጀምረው መምጣት አቆሙ፡፡
የቃል አቀባይ ጉዳይ አጀንዳው ሲነሳ ወደ ውይይት ሳይገባ ኦቦ ኃይሌ ቀደም ብለው፣ ‹‹ያው እንግዲህ ጸሐፊያችን ጀዋር ቃል አቀባይነቱን ደርቦ ይሥራ፣ አጋዥ ሰው ያስፈልገኛል ካላ እሱ ራሱ የመረጠውን ይጨምር፤›› አሉ፡፡ በዚህን ጊዜ ኦቦ በየነ እጅ ሳያወጡ ቀጥታ በኃይለ ቃል መናገር ጀመሩ፡፡ ‹‹እንዴ ምን ማለታችሁ ነው? ምን እያላችሁ ነው? እዚህ ጋቢ ለብሰን ስንቀመጥ አላዋቂ መሰልናችሁ እንዴ? ስንት ምሁራን በመሀከላችን አሉ፤›› በማለት ወዲያ ወዲህ እያዩ ሰው ለመጠቆም ሲሉ ከግራና ቀኛቸው ከተቀመጡት ውስጥ አንዱ በጋቢ ሥር እጁን ሰድዶ ጎንትሏቸው ጉዳዩን እንዲዘሉ አደረገ፡፡ እኔ ኦቦ ጫላ ሶሪ ናቸው እንዲተው የነኳቸው ብዬ ነው የምገምተው፡፡
በመሠረቱ ቃል አቀባይ እኛ አባ ገዳዎች ከውስጣችን መምረጥ ነበረብን፡፡ ይህ ሁኔታ ከተከሰተ በኋላ ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች የዕርቁን መድረክና ሒደት ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ሥር ለማዋል ለምን ፈለጉ የሚለው ጥያቄ በሁሉም አዕምሮ መመላለስ ጀመረ፡፡ ከመድረክ ውጪ መነጋገሪያ ማድረግ ጀመርን፡፡ ይህንን ጉሩምሩምታ ሰምተው መሰለኝ በቀጣዩ ቀናት የቴክኒክ ኮሚቴና የዕርቅ ኮሚቴ አንድ ላይ ሲሰበሰቡ ኦቦ በየነና ኦቦ ጫላ ሲመሩ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ጉዳዩ ግራ ገብቶን ብዙ ብናወራም፣ እነ ጀዋርንና ኦቦ በየነን መጠርጠር ኃጢያት መስሎ ይታየን ነበር፡፡
ጥር 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ጧት በኦሮሞ ባህል ማዕከል፣ አባ ገዳዎችም ቴክኒክ ኮሚቴውም ተገናኘን፡፡ ግን ከአባ ገዳዎችና ከሃደ ሲቄዎች ግማሽ ያል የምንሆን ብቻ ነን የተገኘነው፡፡ የቴክኒክ ኮሚቴውም ግማሽ ያህሉ ነው የተገኘው፡፡ እስከ ረፋዱ 5፡45 ሰዓት እነ ጀዋር፣ ኦቦ በየነ፣ ኦቦ ኃይሌ ለተለያዩ መሥሪያ ቤቶችና ባለሥልጣናት ሲደውሉ ቆዩ፡፡ በመጨረሻ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማግኘት አትችሉም አሉን አሉ፡፡ ስለዚህ ምን ይሻላል ሲባል ጀዋርና ኦቦ ኃይሌ ተያይዘን ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መሄድ አለብን አሉ፡፡ ለምን መሄድ አስፈለገ ሲባል ከሥር ያሉት ባለሥልጣናት ዕርቁን የማይፈልጉ አሉ፣ ትናንት ምሽት የኦፒዲኦ ካድሬዎች ተሰብስበው የአባ ገዳዎችን (የእኛን) መግለጫ ተችተው አንቀበልም ብለዋል በማለት ጀዋር ከውስጥ አዋቂ መረጃ ማግኘቱን ነገረን፡፡
ታዲያ ምን አለፋን እምቢ ብለዋል ብለን ለሕዝብ አሳውቀን መተው ነው እንጂ የሚል ሐሳብ አነሳን፡፡ እንደዚሁ ከምንተው ዓብይን ለማግኘት እንሞክር እሱን ማግኘት ካልተሳካ ለሕዝብ አሳውቀን እንተዋለን ተባለ፡፡ እንደሱ ከሚሆን በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ደጋግመን በትዕግሥት ብንሞክር ይሻላል የሚል ሐሳብ ከአባ ገዳዎቹም ከቴክኒክ ኮሚቴ አባላትም ቀረበ፡፡ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ጀዋር በአማርኛ ‹‹የፈራ ይመለስ›› ብሎ ተናገረ፡፡ ዞሮ ዞሮ አብዛኞቻችን ሳናምንበት በጠቅላላው ከሃያ በላይ የምንሆን ሰዎች ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሄደን፣ በአዋሬ በኩል ባለው በር ላይ ሠፈርን፡፡ ጠባቂዎቹ ለምን በቀጠሮ አትመጡም ብለው ከቦታው እንድንነሳ ለማስገደድ ሞከሩ፡፡ ኦቦ ኃይሌ ገብሬና ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ጀለቢያዎቻቸውን አንጥፈው ተኙ፣ ሁላችንም ተቀመጥን፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ግቢ የጥበቃ አባላት ጠመንጃዎቻቸውን አቀባብለው እኛን በር ላይ ትተው ወደ ኋላችን አለፉ፡፡ ሁለት ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ቦታ ቦታ አስያዙ፡፡ በርካታ ወታደሮችም ቦታ ያዙ፡፡ እንደ ገመትኩት ተጨማሪ የሰው ኃይል እኛን ተከትሎ ይመጣል ብለው በመሥጋት ድንገት ከመጣ ከእኛ እንዳይቀላቀል አስበው ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እኛ ቦታውን ለቅቀን እንድንሄድ በልመናም በቁጣም ይጠይቁን ነበር፡፡ እኛም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኛን ለማናገር ለምን ከበደው? ሰላም እንዲወርድ ነው እንጂ የተለየ ዓላማ ኖሮን አይደለም እየተባባልን ቆየን፡፡ ጥበቃዎቹም ለኃላፊዎቻቸው በማሳወቅ ኃላፊዎቹም እየደወሉ በተለይም ከኦቦ ጀዋርና ከኦቦ በየነ፣ እንዲሁም ከኦቦ ኃይሌ ጋር ይነጋገሩ ነበር፡፡ በዚህ መሀል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ውስጥ የሚሠራ ሰው ለምሳ ሲወጣ ጀዋር ያውቀው ኖሮ አነጋገረው፡፡ ሰውየው በፈገግታ የጀዋርን ቃል ሰማ፡፡ ከዚያም በፈጣን ዕርምጃ ወደ ግቢ ተመለሰ፡፡ ሰውየው ተመልሶ ሲመጣ ግን እንደ በፊቱ ፊቱ ፈገግታ አልነበረውም፡፡ ጀዋርን ጠርቶ ከእኛ ለይቶ አነጋገረው፡፡
ጀዋር ሰውየውን አሰናብቶ ወደ እኛ መጣና ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኛን ማናገር አለመፈለጉን ገለጸ፡፡ ቁረጡ እንግዲህ እዚሁ ማደር ነው ተባብለን ተቀመጥን፡፡ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ሳይሆን የመጣው የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር መላኩ፣ ፋንታም ከእኛው ጋር አዋራ ላይ ተቀምጦ በፀሐይ ይቃጠል ነበር፡፡ መላኩ ‹‹ወይ ወደ እኔ ቢሮ፣ ወይ ወደ ጄኔራል ብርሃኑ ቢሮ ሄደን እንወያይ?›› ብሎ ያቀረበውን ሐሳብ እነ ጀዋር አልተቀበሉም ነበር፡፡
እዚያ ቦታ ላይ ፈገግ የሚያሰኙ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ የመንግሥት የፀጥታ አባላት ጀዋር እኛን አስከትሎ ወደ ግቢ እንዳይገባ ይከለክላሉ፡፡ የእነሱ ጓደኞች የሆኑት የጀዋር ጠባቂዎች ደግሞ የግቢው የፀጥታ አባላት ወደ ጀዋር እዳይጠጉ ይከለክላሉ፡፡ ሁኔታው ረጋ ብሎ ጀዋር በሄድነው ሰዎች መሀል ተቀምጦ ሲወያይ፣ የጀዋርና የግቢው የፀጥታ ኃይሎች ተጠጋግተው ያወራሉ፡፡ በፊት አብረው የነበሩ ናቸውና፡፡
እንዲሁ ውለን አመሻሽ ላይ አሁንም ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ከእነ ጄኔራል ብርሃኑ ጋር እንደ ገና ተነጋግሮ ብርሃኑ ጁላና ደምመላሽ ገብረ ሚካኤል ወደ እኛ ቢሮ መጥተው ያነጋግሩን ማለታቸውን ነገረን፡፡ ታዲያ ምን ችግር አለ ሄደን እናነጋግርና በዚያው ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንድናገኝ ያመቻቹልን ይሆናል ብለን ሁላችንም ሐሳብ አቀረብን፡፡ ተበታትነን ከተቀመጥንበት ጀዋርና ኃይሌ ሰበሰቡንና ከዚህ ንቅንቅ አንልም፣ ከዚህ ጉዞ ከጀመርን እነሱ ጋ ሳንደርስ ወታደር ልከው በመንገድ ላይ አግተው ወደመጣንበት እድንመለስ ያስገድዱናል፡፡ ስለዚህ ከፈለጉ እነሱ ራሳቸው ይምጡና እንነጋገር አሉ፡፡ ይህንኑ አጠገባችን ላለው የፖሊስ ኃላፊ ተናገሩ፡፡ ኃላፊውም ለእነ ደምመላሽ ደውሎ ሲነግራቸው ሜዳ ላይ ምንድነው የምንነጋገረው በቃ መተው ይችላሉ ብለው መናገራቸውን የፖሊስ ኃላፊው ነገረን፡፡ ሁኔታው ግራ ገብቶን ዝም ብለን ከራሳችን ጋር ማውራት ስንጀምር እስካሁን በዝምታ ሁኔታውን ሲከታተሉ የቆዩት ቀነዓ ለሚ (ዶ/ር)፣ ‹‹እንደዚህ እልህ መያያዝ ሳይሆን እነ ደምመላሽ ይምጡና ከእነሱ ጋር ወደ ቢሮአቸው እንሂድ፣ ይህንን ንገራቸው፤›› አሉ፡፡ በዚህ ሐሳብ ሁላችን ተስማማን ጀዋርም ሳይቃወም ዝም አለ፡፡
የፖሊስ ኃላፊው እነ ደምመላሽ እንዲመጡ በስልክ ነገራቸው፡፡ በ15 ደቂቃ ውስጥ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላና ደምመላሽ በየራሳቸው መኪና በአጀብ መጡ፡፡ ጀዋርና ኦቦ ኃይሌ በዚችው ቅፅበት ከመቼው እንደተወያዩ ሳይታወቅ ጄኔራሉና ደምመላሽ እንደመጡ፣ ‹‹አሁን ጊዜው መሽቷል፣ ሰዓቱ 11፡30 ሆኗል፣ ከአሁን በኋላ ከእናንተም ጋር መወያየት አንችልም፣ ዓብይ ነገ እንዲያነጋግረን ይህንን አደራ ስጡልን፤›› ብለው ኦቦ ኃይሌ እርጥብ ሳር ለጄኔራሉ ሰጡ፡፡ በእዚሁ ተሰነባብተን ወደ ቤታችን ገባን፡፡
ከዚያን ቀን ጀምሮ ኦቦ ጀዋር መሐመድ፣ ኦቦ በቀላ ገርባ፣ ኦቦ ኃይሌ ገብሬ፣ ኦቦ በየነ ሰንበቶ፣ ኦቦ ጫላ ሶሪና ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ አንዳንዴ ስልክ እየዘጉ፣ አንዳንዴ የመንግሥት አካላትን እያነጋገርን ስለሆነ በትዕግሥት ጠብቁን እያሉ ጠፉብን፡፡ የምንሰማው ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማነጋገር ሳይቻል ቀርቶ ወደ ኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ቢሮ መመላለስ መጀመራቸውን ሰማን፡፡ እኛ ግን ከመጣን ሁለት ሳምንት ስላለፈን፣ ገንዘብና ስንቅ አልቆ እዚያው የኦሮሞ ባህል ማዕከል በፀሐይና በረሃብ እየተጠበስን ነበር፡፡
ጥር 20 ቀን 2011 ዓ.ም. እዚህ ከእኛ ራሳቸውን ያገለሉ ሰዎች ኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ቢሮ ሄደው ኦቦ ለማን አላገኙም ነበር፡፡ ለእኛ ግን አግኝተናል ቀጠሮ ላይ ነን ጥሩ እየሄደ ነው፣ ይሉናል፡፡ ጥር 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ሰዎቻችን ኦቦ ለማን አግኝተው ቀጠሮ ተቀብለው መጥተው ኦሮሞ ባህል ማዕከል መጥተው ሁላችንም ቆመን ለሚዲያ መግለጫ ሰጡ፡፡ በዚያን ቀን በሰጡት መግላጫ ኦቦ በቀለ ገርባ፣ ‹‹ኦቦ ለማ ታመው ውጭ አገር ነበሩና አሁን መጥተው ዛሬ አነጋግረውናል፤›› በማለታቸው በመንግሥት ባለሥልጣናት ዘንድ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር፡፡ ከእኛ ጋር የሚሳተፉት የመንግሥት ተወካዮች፣ ‹‹እሱ ሐኪም ነው? ወይስ አሳክሟቸው ነው እንዲህ የሚያወራው?›› ብለው ቅር አላቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ኦቦ ለማ መገርሳ ኦቦ በቀለን ክፉኛ ተቆጥቶት በቀለ ይቅርታ መጠየቁን ሰምተናል፡፡
እነ ኦቦ ኃይሌ ስንት ቀን ኦቦ ለማ ቢሮ እንደተመላለሱ ቁጥሩን በትክክል ባይገልጹም፣ ከኦቦ ለማ ጋር ካደረጓቸው ውይይቶች ውስጥ በአንዱ ላይ የመሳተፍ ዕድል የነበራቸው ታደሰ በሪሶ (ዶ/ር) የዕርቁን አንቀጽ ስድስት ሁሉም በቸልታ ሲያልፉ እሳቸው ውይይት እንዲደረግበት ጥያቄ አንስተው ኦቦ ለማ፣ ‹‹ይህማ በተዓምር አይሆንም፣ ባንክ ለዘረፈና ሰው ለገደለ እኛ ምሕረት አናደርግም፤›› ብሎ በቁጣ በመናገሩ የአንቀጹ ጉዳይ በዚሁ አበቃ፡፡
የካቲት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ስብሰባ ተደረገ፡፡ በስብሰባው ላይ የመንግሥት ተወካዮች የነበሩት ዓለማየሁ እጅጉና ኢተፋ ቶላ አልተገኙም፡፡ በእነሱ ምትክ ታዬ ደንደአና ሌላ አንድ ሰው ተገኙ፡፡ ስለመተካካታቸውና ምክንያቱ ያሳወቀን ሰው የለም፡፡ በስብሰባው ላይ ሁሉን ነገር ጨርሰናል፣ የኦነግ ሠራዊት ለማስገባት ነገ ወይም ተነገ ወዲያ ስለምንቀሰቀስ ዝግጅት አድርጉ አሉን፡፡ የነገሩን ዝግጅት አንድ ዘማች ወታደር ወደ በረሃ ሲዘምት የሚያደርገውን ዝግጅት ነው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጋር እንዴት ሳይገናኙ እንደቀሩ (እንዳልቻሉ)፣ ከኦሮሚያው ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ ጋር ምን እንደተነጋገሩና ምን እንደተባባሉ ምንም ሪፖርት አላቀረቡልንም፡፡ ሰው ግን ዝም ብሎ ማለፍ አልቻለም፡፡ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተን ጠየቅን፡፡ እኔ የኦነግ ሠራዊት ጋ የምንደርሰው እንዴት ነው? የት ነው የምናውቀው? ወይስ ማነው የሚወስደን? ብዬ ጠየቅሁ፡፡ ሌንጮ ቀነዓ የተባለ የቴክኒክ ኮሚቴ አባል ከኅብረተሰቡ ጋር ምንድነው የምንወያየው? የኦነግ ሠራዊት ጥያቄ ቢጠይቀን እንዴት ነው የምንመልሰው? በማለት ጠየቀ፡፡ ሌሎችም ከትራንስፖርት፣ ከጉዞ ደኅንነት ጋር ተያይዞ በርካታ ጥያቄዎችን ጠየቁ፡፡
ብዙውን ጊዜ በማዳመጥ የሚያሳልፉት ቀነዓ ለሚ (ዶ/ር)፣ ‹‹ለመሆኑ የዕርቅ ኮሚቴና የቴክኒክ ኮሚቴ በጋራ ያስተላለፍነውን መግለጫ እያንዳንዱን ነጥብ ሳይሸራረፍ የመንግሥት አካላት ተቀብለዋል ወይ ወይስ ያልተቀበሏቸው ነጥቦች አሉ? ያልተቀበሏቸው ነጥቦች ካሉ በምን መልኩ ተስማማችሁ? ሌላው ደግሞ አሁን የያዝነው የመጀመርያው ዕቅድ ፕላን ኤ የሚባለው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ዕቅድ ካልተሳካ ፕላን ቢ የሚባለውን ምን አማራጭ አስቀመጣችሁ? በማለት ጠየቁ፡፡
በነገራችን ላይ ታደሰ በሪሶ (ዶ/ር)፣ ቀነዓ ለሚ (ዶ/ር) ብዙውን ጊዜ አይናገሩም፣ ሲናገሩ ግን መሠረታዊ ነገር ይናገራሉ፡፡ በተለይ ዶ/ር ቀነዓ ላለፉት ሁለት ሳምንታት እነ በየነና ኃይሌ ኦቦ ለማ ዘንድ ሲመላለሱ ምን እንደሚባሉ፣ በምን ጉዳዮች ላይ እንደሚነጋገሩ ከኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ዕለት በዕለት ሙሉ መረጃ እንደሚያገኙ ዘግይቼ ነበር የተረዳሁት፡፡ ነገር ግን የሚያውቁትን አይናገሩም፡፡ ብዙ ጊዜ ደውዬ ስጠይቃቸው መጀመርያ እኔ ምን አውቃለሁ እንዳንተው ነኝ ብለው ቆጣ ብለው፣ ምናልባት እንዲህ ሊሆን ይችላል ብለው ቆንጥረው ይነግሩኝና ጥያቄ እንዳላከታትል ቶሎ ስልክ ይዘጉብኛል፡፡ ኋላ ላይ ሲታይ ከነገሩኝ ነገር አንዳችም ስህተት ሆኖ አልተገኘም፡፡
እንግዲህ ጥያቄ የመመለሱን ጉዳይ ኦቦ ጀዋር የመጀመርያውን ዕድል ወስዶ፣ ‹‹እዚያ ሄደን ሕዝብን የምናወያየው ነገር የለም፣ የኦነግ ሠራዊትም ቢሆን መግባት የሚፈልገውን ይዞ መምጣት እንጂ እዚያ የምትደራደሩት ነገር የለም፤›› ካለ በኋላ፣ ዶ/ሩ ለጠየቁት ለአንዱ ጥያቄ፣ ‹‹አዎን መንግሥት የኮሚቴዎቹን ውሳኔ ተቀብሏል (Wanni Sharafame Hinjiru)›› (የተሸራረፈ የለም) አለ፡፡ (ክፍል ሁለት ሳምንት ይቀጥላል)
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡