Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ኮሮና ቫይረስን በተመለከተ ያልተገቡና ሥጋት ላይ የሚመሠረቱ ውዥንብሮችን ለማስቀረት ብቸኛው መንገድ ግልጽነት ማስፈን ነው›› ጆን ንኬንጋሶንግ (ዶ/ር)፣ የአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ዳይሬክተር

ጆን ንኬንጋሶንግ (ዶ/ር) በአፍሪካ ኅብረት ሥር ለሚተዳደረው የአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ተቋሙን እንዲመሩ ከመሾማቸው ቀድሞ፣ በአሜሪካ ሲዲሲ ሥር ሴንተር ፎር ግሎባል ሔልዝ የተሰኘውን የጤና ተቋም በተጠባባቂ ምክትል ዋና ኃላፊነት መርተዋል፡፡ በዚያው በአሜሪካ ሲዲሲ ሥር የኢንተርናሽናል ላቦራቶሪ ቅርንጫፍ በሆነውና የኤችአይቪ/ኤድስ፣ እንዲሁም የሳንባ በሽታን በሚመለከተው ክፍል ውስጥ በዋና ኃላፊነት ሠርተዋል፡፡ ትሮፒካል ባዮሜዲካል ሰርቪስ፣ እንዲሁም ሜዲካል ኤንድ ፋርማሲውቲካል ሳይንስስ በተሰኙ የትምህርት መስኮች ሁለት የማስትሬት ዲግሪዎችን ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ብራስልስ አግኝተዋል፡፡ የሕክምና ዶክትሬታቸውን በሜዲካል ሳይንስስ (ቫይሮሎጂ) መስክ በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ሠርተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1993 እስከ 1995 ባለው ጊዜ በቤልጂም ኢንስቲትዩት ኦፍ ትሮፒካል ሜዲስን በተሰኘ ተቋም የሕክምና ዘርፍ ኃላፊ በመሆንና የዓለም ጤና ድርጅት ተባባሪ በሆነው የኤችአይቪ ምርመራ ማዕከል አገልግለዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1995 የአሜሪካ ሲዲሲን ሲቀላቀሉ በተለይ የላቦራቶሪ ዘርፉን በኃላፊነት ለመምራት፣ የኮትዲቯር የሲዲሲ አቢጃን ማዕከል ዋና ኃላፊ ሆነው ነበር፡፡ በሙያቸውና በኃላፊነት ከሠሩባቸው ትልልቅ ተቋማት ባሻገር በአሜሪካ የጤና ሚኒስቴር ለኅብረተሰብ ጤና ጥበቃ ምርምር ሥራዎች የሚበረከተውንና ‹‹ሼፐርድ አዋርድ›› የተሰኘውን ሽልማት አግኝተዋል፡፡ ዩኤስ ዳይሬክተርስ ሪኮግኒሽን አዋርድ፣ እንዲሁም በቅርቡ ዊሊያም ዋትሰን የተሰኘውና ለላቀ አስተዋጽኦ የሚሰጠውን ሜዳይ በማግኘት በሲዲሲ ማዕከል የሚሰጠውን ይህንን ከፍተኛ የዕውቅና ሽልማት የተጎናፀፉ አፍሪካዊ መሪ ናቸው፡፡ ሽልማቱ በተለይ በላቦራቶሪ ምርምር መስክ አስተዋጽኦ ላደረጉና በመሪነት ሚናቸው ለተመሰከረላቸው የሚሰጥ ከመሆኑም ባሻገር፣ በአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ‹‹ፕሬዚዳንትስ ኢመርጀንሲ ፕላን ፎር ኤድስ ሪሊፍ›› የተሰኘውን ፕሮግራም በመደገፍ ሚናቸው ልቆ ለሚገኙ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች የሚሰጥ ነው፡፡ በኮትዲቯር መንግሥት የሚሰጠውን ‹‹ናይት ኦነር›› የተሰኘ የመስፍናውያን የክብር ሜዳልያ ተቀብለዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 በሴኔጋል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል ‹‹ኦፊሰር ኦፍ ላየን›› የተሰኘውን ሽልማት በኅብረሰብ ጤና ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ መታሰቢያ ይሆናቸው ዘንድ ተበርክቶላቸዋል፡፡ በበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በልዩ ልዩ የአማካሪነት ሥራዎች የሚሳተፉት ዶ/ር ንኬንጋሶንግ፣ የዓለም አቀፉ የፀረ ኤችአይቪ ክትባት ተቋምን፣ እንዲሁም የበሽታ ወረርሽኝን ለመከላከል በተዘረጋው ዓለም አቀፍ የዝግጁነት ጥምረት ውስጥ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ በአካዴሚውም ቢሆን በርካታ ጆርናሎችንና መጻሕፍትን በመጻፍና በማበርከት፣ እንዲሁም በመገምገም እንደሚሳተፉ ግለ ታሪካቸው ይመሰክራል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ኅብረት ከሁለት ዓመታት በፊት በመሪዎች ውሳኔ ያቋቋመውን አፍሪካ ሲዲሲ በመምራት ላይ የሚገኙትን ጆን ንኬንጋሶንግ (ዶ/ር)፣ አሳሳቢውንና እንደ ሰደድ እየተዛመተ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ በተመለከተ ብርሃኑ ፈቃደ፣ የአፍሪካን ሥጋቶችና የዝግጁነት ሥራዎች በሚመለከት ኃላፊውን አነጋግሮ የሚከተለውን አጠናቅሯል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ስለኮሮና ቫይረስ ከመነጋገራችን በፊት የአፍሪካ ሲዲሲ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ምን ሲያከናውን እንደቆየ ቢገልጹልን?

ዶ/ር ንኬንጋሶንግ፡- አፍሪካ ሲዲሲ የተቋቋመው በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ውሳኔ መሠረት እ.ኤ.አ. ጃኑዋሪ 31 ቀን 2018 ነበር፡፡ ወቅቱ የኢቦላ በሽታ ወረርሽኝ የተከሰተበትና በምዕራብ አፍሪካ በተለይም በሴራሊዮን፣ በላይቤሪያና በጊኒ 11 ሺሕ በበሽታው የተያዙ ሰዎች የሞቱበት ነበር፡፡ ከዚህ በመነሳት የአፍሪካ መሪዎች ትልቅ ትርጉም ያለው ውሳኔ በማሳለፍ፣ የአፍሪካ ሲዲሲ እንዲቋቋም የሚጠይቀውን የትግበራ ሒደት እንዲፋጠን አድርገዋል፡፡ ተቋሙ እንዲመሠረት በተወሰነው መሠረት በሁሉም ቀጣናዎች የየራሱ አደረጃጀቶችን ይዞ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ በመሆኑም አምስት ቀጣናዎችን ይዞ ለምዕራብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያን፣ ለማዕከላዊ አፍሪካ ክፍል ጋቦንን፣ ለደቡባዊ አፍሪካ ዛምቢያን፣ ለሰሜን አፍሪካ ግብፅን፣ እንዲሁም ለምሥራቅ አፍሪካ ኬንያን የየቅርንጫፎቹ ማዕከላት ዋና መገኛ በማድረግ ሥራ ጀምሯል፡፡ በኅብረተሰብ ጤና አገልግሎት መስክ የሚንቀሳቀስ አኅጉራዊ ተቋም ሲሆን፣ የተሰጠው ተልዕኮም አፍሪካን ከማንኛውን ዓይነት በሽታ የመጠበቅ፣ ከተላላፊ ብቻም ሳይሆን ከማይተላለፉ በሽታዎችና በየጊዜው እየተከሰቱ ከሚገኙ አዳዲስ በሽዎችም ጭምር አኅጉሪቱን የመከላከል፣ እንደ ኤችአይቪ፣ ሳንባና ወባ ያሉ ወረርሽኞችንም የመከላከል የዕለት ተዕለት ተግባሮቹ ናቸው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ኮሮና ቫይረስን ጨምሮ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በርካታ በሽታዎች ተከስተዋል፡፡ ይሁንና አፍሪካ እንዲህ ካሉ ተላላፊ በሽታዎችም ሆነ ከሌሎቹ የበሸታ ዓይነቶች ሊደርስባት የሚችለውን ጉዳት ለመቋቋም ያላት ብቃት ምን ያህል ነው?

ዶ/ር ንኬንጋሶንግ፡ራዕዩ፣ ዕውቀቱና ፖለቲካዊ ተነሳሽነቱን ያሳዩ የአፍሪካ መሪዎች ምንጊዜም መመሥገን አለባቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ራሳችንን አስገራሚ ሁኔታ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ በበርካታ ምክንያቶች አዳዲስ በሽታዎች እየተከሰቱ፣ ፀባያቸውንም በዚያው ልክ እየቀያየሩ በመምጣት ላይ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል እያደገ የመጣው የአኅጉሪቱ የሕዝብ ቁጥር አንዱ ነው፡፡ ዕድገቱ በከፍተኛ ፍጥነት እየተወነፈጨ ነው፡፡ አፍሪካ ከቅኝ ግዛት ነፃ በወጣችበት ወቅት የነበራት የሕዝብ ቁጥር 300 ሚሊዮን ነበር፡፡ ይህ አኃዝ ከግብፅ እስከ ደቡብ አፍሪካ፣ ከላይቤሪያ እስከ ሶማሊያ የነበረው የወቅቱ አጠቅላይ የሕዝብ ብዛት ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ወደ 1.2 ቢሊዮን አሻቅቧል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2050 ወደ 2.4 ቢሊዮን እንደሚያድግ ይጠበቃል፡፡ በዚህ ደረጃ በፍጥነት በሚያድገው የሕዝብ ብዛት የተነሳ ከዚህ ቀደም ሰው ያልደረሰባቸው፣ ለግብርና፣ ለምግብ እንዲሁም ለመጠለያና ለመሠረተ ልማቶች ያልዋሉ አካባቢዎችን ሁሉ ማዳረስና ለኑሮ ማዋል እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ በዚህ ምክያትም ከዚህ ቀደም ምን ዓይነት ንክኪ ወዳልነበረው ሥነ ምኅዳራዊ ሥርዓት ውስጥ እየገባን ተጋላጭነታችንን እያባባስነው መጥተናል፡፡ ለአብዛኛው የቫይረስ በሽታ ምንጮቹ እንስሳት ናቸው፡፡ ከ70 በመቶ ያላነሰውን ቫይረስ የምናገኘው ከእንስሳት ሲሆን፣ ተለዋዋጭ የሆነው ሥነ ምኅዳርም እንደ አዲስ ለሚከሰቱ በሽታዎች ምቹ የመራቢያ መንገድ እየሆናቸው ነው፡፡

የሕዝብ ብዛት በፍጥነት ሲጨምር፣ ሰዎች ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ይገደዳሉ፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀን ከአምስት እስከ ስድስት ጊዜ ያህል ወደ ቻይና ይበራል፡፡ ኤምሬትስም በሁሉም የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የበረራ መስመሮች አሉት፡፡ የቱርክ አየር መንገድም እንዲሁ ነው፡፡ በዚህ ሳቢያ ሰዎች በአኅጉሪቱ ውስጥ ከአንዱ ሥፍራ ወደ ሌላው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ይበልጥ እየተስፋፋና እየጨመረ መጥቷል፡፡ የሕዝብ ብዛትና ከቦታ ቦታ የሚደረገው እንቅስቃሴ መጨመር የበሽታ አምጪ ተዋህስያን እንቅስቃሴም በዚያው ልክ እየጨመረ ይመጣል፡፡ ይህ በጣም ወሳኙ ነገር ነው፡፡ በዚህ መሰሉ ለውጥ ሳቢያ፣ ሰዎች ከገጠራማ አካባቢዎች ወደ ከተሞች ይፈልሳሉ፡፡ በዚህ ሳቢያም በከተሞች አካባቢ በርካታ ለኑሮ የማይመቹ መንደሮች እየተፈጠሩ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ አካባቢዎችን  በኬንያና በኢትዮጵያ በብዛት እናገኛለን፡፡ ከዚህ ባሻገር የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተፅዕኖም እያየን ነው፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ በእርግጥም ተፅዕኖ እንዳለው በተጨባጭ እየታየ ነው፡፡ ሁላችንንም እየጎዳን ነው፡፡ በአፍሪካ የሚከሰቱ ግጭቶች ለበሽታ መዛመት የሚያድርጉትን አስተዋጽኦም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ያሉ ምክንያቶች ለአዳዲስ በሽታዎች መፈጠርና ለወረርሽኝ መከሰት ትልቅ አስዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል አፍሪካ ምን ያህል ዝግጁ ነች?

ዶ/ር ንኬንጋሶንግ፡- እ.ኤ.አ. እስከ ፌብሩዋሪ 18 ቀን 2020 ዓ.ም. ድረስ በግብፅ አንድ የኮሮና ቫይረስ ተሸካሚ መገኘቱ ተጋግጧል [ቃለ ምልልሱ ከተደረገ ከአንድ ሳምንት ወዲህ አልጄሪያ ሌላኛዋ የኮሮና ቫይረስን ሪፖርት ያደረገች አገር ሆናለች]፡፡ እስካሁን በአኅጉር ደረጃ ከዚህ ውጪ ሪፖርት የተደረገበት ክስተት አልተሰማም፡፡ ይህ ጥሩ ዜና ነው፡፡ ይሁን እንጂ በቻይና እየሆነ ያለውን በንቃት እየተከታተልን እንገኛለን፡፡ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል፡፡ በርካቶች ለሞት ተዳርገዋል፡፡ በርካታ አገሮች በሽታው ተዛምቷል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ጥሩ ዕድል ያገኘንበት አጋጣሚ ነበረን፡፡ እ.ኤ.አ. ከዲሴምበር ጀምሮ የመዘጋጀት ዕድል ማግኘታችን ትልቅ ዕድል ስለነበር በመላው አፍሪካ ስንዘጋጅ ቆይተናል፡፡ በበርካታ አካባቢዎች በሰፊው ተዘጋጅተናል፡፡ አንደኛው ዝግጅታችን የምርመራ ዝግጅትን የሚመለከት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ለ16 አገሮች ያሠራጨናቸው የምርመራ መሣሪዎች ነበሩ፡፡ በወዲያኛው ሳምንት ለ20 ተጨማሪ አገሮች አዳርሰናል፡፡

ከአሥር ሺሕ በላይ ለኮሮና ቫይረስ ምርመራ የሚውሉ መርማሪያዎችን አከማችተናል፡፡ ይህንን ክምችት ባለስፈለገ ጊዜ ለየትኛውም ከአገር ወዲያኑ ማዳረስ እንችላለን፡፡ ከኤርፖርቶችና አየር መንገዶች ጋር አብረን እየሠራን ነው፡፡ ሥልጠናዎችንም ሰጥተናል፡፡ ግባችን በወሩ መጨረሻ የተሟላ የላቦራቶር ዝግጅትን ጨምሮ በኤርፖርቶች የሚደረገውን የልየታ ሥራ፣ በበሽታ የመያዝ ዕድል እንዳይኖር ከፍተኛ ቁጥጥር ማድረግና የሥጋት ሁኔታዎች ሲከሰቱ በአፋጣኝ መረጃ መለዋወጥ የሚቻልባቸውን መንገዶች በሚገባ በመዘርጋት ዝግጁ ሆነን መጠበቅ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር ራሳችንን በበቂ ሁኔታ በመዘጋጀትና ቫይረሱ ቢያጋጥም እንኳ በፍጥነት በመለየት ምላሽ መስጠት የምንችልበትን መንገድ መከተል ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- በትክክል ካስታወስኩ ለኢቦላ በሽታ በፍጥነት መዛመትና ለበርካቶች ሞት መንስዔው በሽታው በተከሰተባቸው አገሮች ውስጥ የነበረው ደካማ የምርመራና የሕክምና ዝግጅት ችግር ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ታዲያ አፍሪካ ከኢቦላ በኋላ ለኮሮና ቫይረስ ያደረገችው ዝግጅት ምን ያህል አስተማማኝ ነው?

ዶ/ር ንኬንጋሶንግ፡- ልንዘጋጅ የምንችለው በመላው አፍሪካ ያለው የጤና ሥርዓት በሚችለውና በሚፈቅደው አቅም ልክ ነው፡፡ እንደማስበው በምዕራብ አፍሪካ ተከስቶ ለነበረው የኢቦላ ወረርሽኝ ለምን መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ግንዛቤ የተገኘበት መሆኑ አዎንታዊ ጎኑ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1976 መከሰቱ ይፋ የተደረገ በሽታ፣ በተለየ የሕዝብ አሠፋፈር ሥርዓት ውስጥ ድንገት በመግባት ጉዳት ሲያስከትል ያየንበት የመጀመርያ ክስተት ሆኖ ነበር፡፡ በሽታው በከተሞች አካባቢ ሲከሰት የመጀመርያው ከመሆኑም ባሻገር፣ በከተሞች ከነበረው የጤና ክብካቤ ሥርዓት በላይ በመሆን አስከፊ ጉዳት አድርሷል፡፡ አገሮች ለበሽታው ተገቢውን ትኩረት መስጠት የጀመሩትም ነገሩ ከቁጥጥር ውጭ መሆን ሲጀምር ነበር፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት የጋራ ውጫዊ የቁጥጥር ሥልት በመዘርጋት፣ የእያንዳንዱን አገር ሁኔታ ለመገምገም ተጠቅሞበታል፡፡ የአገሮች የዝግጁነት ደረጃ ተመዝኖበታል፡፡ ይህ ሥርዓት የጋራ ሥልት በመጠቀም ከግባችን አኳያ እንድንንቀሳቀስ አስችሎናል፡፡

ከአፍሪካ ውጪ የሚገኙ ባለሙያዎች እየመጡ የዝግጁነት ሥርዓታችንንና የመሠረተ ልማት አውታሮቻችንን ይገመግማሉ፡፡ ቁጥጥር ያደርጉባቸዋል፡፡ እነዚህ ነገሮች መኖራቸው ከተረጋገጠ በኋላ የድጋፍ አሰጣጥ ሒደቱ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፡፡ የዓለም የጤና ደኅንነት ሥርዓት የምንለው ተዘርግቶ ድጋፎችም በሰፊው እየተደረጉለት ይገኛል፡፡ ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዘረጋ ሲሆን፣ የአገሮችን የጤና ሥርዓት ለማጠናከር ሲባል የተጀመረ ነው፡፡ ከኢቦላ ወረርሽኝ ክስተት በላይ ለውጦችና መሻሻሎች እየታዩ ነው፡፡ ይህ ግን በቂ አይደለም፡፡ አስፈላጊውን ሀብት በማንቀሳቀስና የጤና ዘርፉን በማጠናከር ረገድ ቁርጠኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡ በአፍሪካ የጤና ደኅንነት እንዲረጋገጥ ይህንን ተግባር በሚገባ ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መስክ ውይይት መደረግ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታን ጨምሮ በርካቶች ሥጋተቸውን ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ እንዲያቋርጥ ተጠይቆ ነበር፡፡ በሽታው አንዴ ከገባ መከላከል የሚቻልበት አቅም በአፍሪካ እንደሌለ የሚያሳስቡ ሥጋቶች እየተስተጋቡ ነው፡፡ በመሪዎች ደረጃ እንዲህ ያለው ሥጋት ጎልቶ ሲወጣ ሲታይ ምን ማለት ነው? በጤናው አጠባበቅ መስክ ላይስ ምን ዓይነት መተማመን ሊኖረን ይችላል? 

ዶ/ር ንኬንጋሶንግ፡እንዲህ ያለው አሳሳቢ ወረረሽኝ በሚያጋጥም ጊዜ፣ ልንገዘባቸው የሚገቡን ቁምነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው ከክስተቱ ጀርባ ስላለው ሳይንስ ነው፡፡ ሳይንስን በመተግበር ሁሉንም ዕርምጃዎቻችንን ማስተባበር መፍትሔ መፈለግ እንጂ በየቦታው የሚነገረውን ሁሉ መቀበል አይጠቅመንም፡፡ ሁለተኛው የተሳሳተ መረጃን በንቃት መዋጋት መቻል ይኖርብናል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ እውነታን እንጂ ፍርኃትና ሥጋትን ማስተጋባት የለብንም፡፡ እነዚህን ሦስት ጉዳዮች በመተግበር፣ ራሳችንን በሥነ ልቦና አዘጋጅተን በተገቢው መንገድ በሽታውን ለመቋቋም መዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡ ይህን ካልኩ በኋላ በመላው ዓለም ተቀባይነት የተቸረውና ሁሉም የተስማማበት ዓለም አቀፍ የጤና ቁጥጥር ሥርዓት አለ፡፡ የዓለም ጤና ድርጅትም ይህን በሚመለከት መመርያዎች አሉት፡፡ በአጠቃላይ መመርያው ከሚያስቀምጣቸው ጉዳዮች መካከል የንግድ፣ የሰዎችንና የአየር መንገዶችን እንቅስቃሴ አለመገደብ ይገኝበታል፡፡ ይህ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ መላምት ማስቀመጥ እፈልጋለሁ፡፡ ወደ ቻይና የሚደረገውን በረራ በማስቆማችን ብቻ ከቻይና ወደ አፍሪካ የሚመጡትን ልንገታቸው አንችልም፡፡ እኔ ቻይናዊ ብሆን፣ ወደ አፍሪካ ለመምጣት የሚያስችሉኝ በርካታ መንገዶች ይኖሩኛል፡፡ ወደ ሞስኮ በመሄድ ወደ ቱርክ የሚያቀና አውሮፕላን ተሳፍሬ፣ ከዚያም ወደ ዱባይ በማቅናት ወደ አፍሪካ መግባት እችላለሁ፡፡ ይህንን መቆጣጠር በጣም ከባድና ውስብስብ ይሆናል፡፡

ይሁንና ወደ ቻይና መብረራችንን ካላቆምንና ግልጽነት የሰፈነበት አሠራር ከተከተልን፣ ማን ከየት እንደሚመጣ ለመቆጣጠርና ለመከታተል የሚያስችል የተሻለ ዕድል ይኖረናል፡፡ ነገር ግን ከሁዋን ግዛት በሞስኮ በኩል ወደ አፍሪካ ለመምጣት የሚያስችሉ በርካታ አየር መንገዶች ስላሉ፣ በትክክለኛው መንገድ ጉዟቸውን ለመቆጣጠርና ለመከታተል የሚደረገውን ጥረት ከባድ ያደርጉታል፡፡ ኮሮና ቫይረስን በተመለከተ ያልተገቡና ሥጋት ላይ የሚመሠረቱ ውዥንብሮችን ለማስቀረት ብቸኛው መንገድ ግልጽነት ማስፈን ነው፡፡ በረራዎችን አናቁም፡፡ ነገር ግን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ሳናወላዳ መከተልና መተግበር ይጠበቅብናል፡፡ አፍሪካ በፍጥነት ምላሽ የሚሰጥበት አቅም እንዲኖራት ለማስቻል መፍትሔው፣ የኮሮና ቫይረስን በፍጥነት በመለየት አፋጣኝ ዕርምጃ መውሰድ መቻል ነው፡፡ ከሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሁለት ሺሕ አልጋዎች የሚይዝ ሆስፒታል ለመገንባት አቅሙ አይኖረን ይሆናል፡፡ ነገር ግን በፍጥነት ለይተን ምላሽ መስጠት የምንችልበት አቅም አለን፡፡ በመላው አፍሪካ የሚገኙ ሁሉም የጤና ተቋሞቻችን በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህም ብርታት ይሰጠናል፡፡

ሪፖርተር፡- በኤርፖርቶች አካባቢ ስለሚደረገው ፍተሻ ገልጸዋል፡፡ ሥልጠና መሰጠቱንም አውስተዋል፡፡ መሣሪያዎች ስለመተከላቸውም ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ኤርፖርቶች በምን አግባብ ፍተሻ ይደረግባቸዋል? ማንስ ነው የሚከታተላቸውና ከሚያቀርቡት ሪፖርት ባሻገር ቁጥጥር የሚያደርግባቸው?

ዶ/ር ንኬንጋሶንግ፡- በየጊዜው ቁጥጥርና ክትትል ይደረግባቸዋል፡፡ እንደ ምሳሌ የምጠቅስልህ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ያለውን አሠራር ነው፡፡ አዲስ አበባ ወደ ቻይና የሚሄደውና የሚመጣው ተጓዥ በከፍተኛ መጠን የሚስተናገድባት ከተማ ነች፡፡ በመሆኑም ከጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታዋ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከተወከሉ ሚኒስትርና ከዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ጋር፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን በቅርቡ በኤርፖርት ላይ ፍተሻ አድርገን ነበር፡፡ ባየሁት ነገር በጣም ተደስቻለሁ፡፡ ከኤርፖርቱ ወጪ በሚገኝ አካባቢ የለይቶ ማቆያ ሥፍራ አዘጋጅተዋል፡፡ ይህ ላልተጠበቁ አጋጣሚዎች በጣም ወሳኝ ዝግጅት ነው፡፡ ዝግጅቱ ሁሉ አንድን ተጠርጣሪ ለመለየት ይረዳህ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ቫይረሱ ሳይታወቅ እስከ ሁለት ሳምንት የመቆየት ተፈጥሮ ያለው በመሆኑ ዝግጅቱ ሙሉ በሙሉ ዋስትና ሊሰጥ አይችልም፡፡

በበሽታው የተያዘ ሰው በኤርፖርት ውስጥ ተመርምሮ ሲያልፍ ምንም ዓይነት የበሽታ ምልክት ላይገኝበት ይችላል፡፡ ነገር ግን ቢያንስ ሰዎች ኤርፖርት በሚደርሱበት ጊዜ መመርመርና ክትትል ማድረግ የምንችልበትን ሥርዓት ዘርግተናል፡፡ ምንም ዓይነት የበሽታው ምልክት ሳይታይብህ ልታልፍ ትችል ይሆናል፡፡ እኛ ግን ዝርዝር የጉዞ መረጃዎችህን ስለምንይዝ የምትጓዝበትን ቦታ ሁሉ ማወቅ እንችላለን፡፡ ለ14 ቀናት ያህል እነዚህን ሰዎች እንከታተላለን፡፡ ይህ እንግዲህ በሽታው ራሱን የሚገልጽባቸው ቀናት በመሆናቸው ነው፡፡ ማድረግ የምንችለውን ሁሉ እያደረግን ነው፡፡ ሁሉንም ነገር መቆጣጠር ግን አንችልም፡፡ አንድ በቫይረሱ የተያዘ ሰው ሳይታወቅ ድንገት ቢያልፍ፣ በዚያ ሰው ምክንያት ወረርሽኝ ሊከሰት የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ በተቻለን መጠን የሚጠረጠሩትን ሁሉ ለይተን ለማውጣት እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርት አካባቢ ተግባራዊ የሚደረጉ የቁጥጥር ሥልቶችና የትግበራ ሒደቶች ከሌሎች ከተሞች አኳያ የበለጠ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው መሆን እንደሚጠበቅባቸው ከሚያመላክቱ ጉዳዮች መካከል፣ ቢያንስ ከተማዋ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ማዕከልና በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚገኙባት መሆኗ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ተጨማሪ ጥንቃቄዎች መደረግ አያስፈልጋቸውም ይላሉ? 

ዶ/ር ንኬንጋሶንግ፡- ላረጋግጥልህ የምችለው ነገር ቢኖር፣ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በከፍተኛ ተጠንቀቅ እየሠራ እንደሚገኝ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋና ማዕከል ከመሆኗ በተጨማሪ፣ ከኒውዮርክና ከጄኔቫ በመከተል ሦስተኛዋ የዲፕሎማቲክ ከተማ ነች፡፡ ይህ በመሆኑ ፈተናው ምን ያህል እንደሚሆን እንገነዘባለን፡፡ ዝም ብለን እንደማንመለከት ማመን ያስፈልጋል፡፡ ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በቅርበት እየሠራን ነው፡፡ በምንችለው ሁሉ ከፍተኛ ድጋፍ እያቀርብን ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅትም እየደገፋቸው ነው፡፡ ሁሉንም ነገር በሚገባ እየተወጣን ስለመሆናችን እርግጠኛ መሆን ትችላለህ፡፡ የዲፕሎማቶችን ብቻም ሳይሆን የማንኛውንም የአዲስ አበባ ነዋሪ የጤና ደኅንነት ማስጠበቅ ኃላፊነታችን ነው፡፡ በሽታው በአዲስ አበባ ቢከሰት በቀላሉ ወደ ተቀረው አፍሪካ የመዛመት ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በተካሄደው የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ወቅት የበሽታው ክስተት አለማጋጠሙ አስገራሚ ነበር፡፡

ዶ/ር ንኬንጋሶንግ፡- በከፍተኛ የጥንቃቄ እንቅስቃሴ ውስጥ ሆነን ሁሉንም ስንፈትሽ ነበር፡፡ መሪዎችንም ጭምር ፈትሸናል፡፡ ለስብሰባ ሲገቡ ተመርምረዋል፡፡ ሥራችንን በህቡዕ ስናከናውን ቆይተናል፡፡ በሳይንሱ በውጤታማ መንገድ በሽታን ለመቆጣጠር መፍትሔው ሕዝብን ከሥጋት ነፃ ማድረግ መቻል ነው፡፡ ሥራችን ልክ እንደ ወታደር ነው፡፡ ወታደሮችን በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ብታፈሳቸው ፀጥታን ልታሰፍን ትችላለህ፡፡ ነገር ግን ፍርኃትና ሥጋትን ትፈጥራለህ፡፡ እኛ  ምንም ማንም ሳያውቅ ክትትል እያደረግን ነው፡፡ በሽታን የመለየት ሥራ ከወታደራዊ ተልዕኮ ጋር ይቀራረባል፡፡ በወታደራዊ ሥልት ጠላት ከማወቁ በፊት የሚገኝበትን ሥፍራ ታውቅበታለህ፡፡ በሽታንም እንዲሁ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቻይና የኮሮና ቫይረስ የወረርሽኝ ሥርጭት እየቀነሰ ስለመሆኑ አስታውቃ ነበር፡፡ ይሁንና ለበሽታው መፍትሔ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ስለበሽታው ሥርጭት በቻይና ሪፖርት የተደረገው ጉዳይ ለአፍሪካ ምን አንድምታ ይኖረዋል?

ዶ/ር ንኬንጋሶንግ፡- በሥርጭት ረገድ በሽታው ወደ መቀነሱ እየመጣ ነው መባሉ ለአፍሪካ ብቻም ሳይሆን ለመላው ዓለም ጥሩ ዜና ነው፡፡ በሽታውን በቻይና ለመቆጣጠር ወደሚቻልበት ደረጃ የሚወስደው ፍንጭ መገኘቱ፣ ኮሮና ወደ አፍሪካ የሚመጣበትን ዕድል አነስተኛ ሊያደርገው ይችላል፡፡ እስካሁን ለበሽታው ፈዋሽ መድኃኒት እንደሌለ መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡ ምናልባትም ከአንድ ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ ለቫይረሱ ማርከሻ ክትባት ላይገኝ ይችላል፡፡ ክትባት ማዘጋጀት ብዙ ጊዜ ይወስዳል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው ብቸኛ መፍትሔ በሕይወት የመቆያ ጊዜን ለማራዘም የሚያግዙ ድጋፎችን መስጠት ብቻ ነው፡፡ ይህም ለአፍሪካ የማይታሰብ ነገር ነው፡፡ ቻይና ያጋጠማትን ወረርሽኝ እንዴት መቋቋም እንደምትችል አሳይታለች፡፡ በከፍተኛ ፍጥነት ሆስፒታል ገንብታለች፡፡ የሕይወት ማቆያ ድጋፍ መስጫዎች በገፍ አሏት፡፡ በአፍሪካ ይህ አይታሰብም፡፡ አዳዲስ የበሽታው የመከሰቻ ፍጥነት የመቀነስ አዝማሚያ ማሳየቱ ጥሩ ዜና ነው (ከሳምንት በፊት ከነበረው ሁኔታ አኳያ ነው)፡፡ በሽታን ለመዋጋት ተመራጩ መንገድ ከምንጩ መዋጋት መቻል ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማስተላልፈው መልዕክት የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ያለበቂ ምክክርና ውይይት እንዳይፀድቅ ነው›› አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም፣  የሕግ ባለሙያ

አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም በዳኝነትና በጥብቅና ሙያ ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ በሕገ መንግሥትና አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ  ጠበቆች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ...

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...