Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ልማት ባንክ አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ትርፍ አስመዘገበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የተበላሸ ብድር ክምችቱ ወደ 34 በመቶ ዝቅ ብሏል

የተበላሸ ብድር ክምችቱ ወደ 40 በመቶ አሻቅቦ የቆየው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ህልውናውን አደጋ ላይ ስለመውደቁ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

ሊመለስ የማይችለው ወይም የተበላሸው የብድር ክምችቱ መጠን ከሌሎች በርካታ ችግሮች ጋር ተዳምረውና ባንኩን ከማንገዳገድ አልፈው ለፋይናንስ ኢንዱስትሪውም ዳፋቸው እንዳይተርፍ ሥጋት ሲያጭሩ ከርመዋል፡፡ ያለፈውን በጀት ዓመት በኪሳራ ማጠናቀቁ የባንኩን የወደፊት ጉዞ ይበልጥ ሥጋት ያሳድራል የሚሉ አመለካከቶች እንዲጎለብቱ አስገደድዶ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ከነባራዊ ሁኔታዎች በመነሳት፣ የልማት ባንክ የወደፊት ዕጣ ፈንታን የተመለከተ ጥናት እንዲሠራ እስከማዘዝ ደርሷል፡፡ በዚህ ደረጃ ሲገለጽ የሰነበተው የልማት ባንክ የተበላሸ ብድር ክምችትና ዓምና የ740 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ማስመዝገቡ፣ ዘንድሮ 2012 ዓ.ም. ዕጣ ፈንታው አጣብቂኝ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ሥጋቶች ነበሩ፡፡  

ባንኩ ይህ ሥጋት ከሥጋት እንዳልዘለለ የሚያመላክት መረጃ ይፋ በማድረግ በባንኩ ላይ የተንሰራፉትን አሉታዊ አመለካከቶች በተወሰነ ደረጃ የቀለበሰ አፈጻጸም እንዳስመዘገበ አስታውቋል፡፡ የተበላሸ የብድር መጠኑን እየቀነሰ መምጣቱን፣ የኪሳራ ጉዞውንም በመዝጋት፣ በግማሽ ዓመቱ በባንኩ ታሪክ ከፍተኛ ትርፍ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡ ባንኩ ትርፋማ መሆን የቻለው፣ የሪፎርም ዕርምጃዎችን በመውሰዱ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ በመሆኑም የተበላሸ የብድር መጠኑ 40 በመቶ ገደማ ከነበረበት  ወደ 34 በመቶ ሊወርድ መቻሉን አመላክቷል፡፡

የግማሽ ዓመቱን አፈጻጸም በተመለከተ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለኢየሱስ በቀለ በሰጡት መግለጫ፣ ከታክስ በፊት 951.6 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡን አስታውቀዋል፡፡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ228 በመቶ ብልጫ ያለው ውጤት እንደሆነ ሲጠቀስ፣ የባንኩ ጠቅላላ ሀብትም 83.4 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ ተጠቅሷል፡፡

በግማሽ ዓመቱ 6.27 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር መፍቀዱና ከዕቅዱም 83 በመቶ ማሳካቱን ገልጿል፡፡ ከዚህ ውስጥ 4.4 ቢሊዮን ብሩ ለተበዳሪዎች መልቀቁን ይህም በስድስት ወራት ውስጥ ለማሳካት ካቀደው ውስጥ የዕቅዱን 77 በመቶ ማሳካት እንደቻለ የሚሳይ ነው፡፡ ከሰጠው ብድር ውስጥ 4.51 ብር መሰብሰብ እንደቻለ ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል፡፡ የብድር ማስመለስ እንቅስቃሴውም የዕቅዱን 118 በመቶ ያሳካበት ነበር፡፡ በብድር መፍቀድ የ4 በመቶ ጭማሪ በብድር መልቀቅ፣ የሰባት በመቶ ማነስና በብድር መሰብሰብ ደግሞ የ125 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አኳያ አፈጻጸሙን ውጤታማ አሰኝቶታል፡፡

በዘንድሮ በጀት ዓመት የ13.76 ቢሊዮን ብር ብድር በማፅደቅና 11.96 ብር ለመልቀቅ አቅዶ ወደ ሥራ የገባው ልማት ባንክ፣ 7.88 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ፣ 4.3 ቢሊዮን ገቢ ለማግኘትና የባንኩን አጠቃላይ ሀብት 96.18 ቢሊዮን ለማድረስ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

በ2011 ዓ.ም. 740 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ቢያስመዘግብም፣ በዘንድሮ ግማሽ ዓመት ትርፋማ የመሆኑ ሚስጥር መላው የባንኩ ሠራተኞች ተረባርበው በመሥራታቸውና አዲሱ የባንኩ ሥራ አመራር ቦርድም ከሥራ አስፈጻሚው ጋር በጥምረትና በመተጋገዝ በመሥራታቸው የተገኘ ለውጥ ነው ተብሏል፡፡ በመሆኑም የተበላሸ ብድር መጠኑን በመቀነስና አዳዲስ ፕሮጀክቶች ወደ ተበላሸ ብድር ዝርዝር እንዳይገቡ ክትትል ማድረጉ ውጤታማ እንዳደረገው ተጠቅሷል፡፡

በዚሁ ጉዳይ ላይ የባንኩ ፕሬዚዳንት እንደገለጹት፣ ለተመዘገበው ትርፍ አንዱ ምክንያት ተጨማሪ የተበላሸ ብድር እንዳይሰከትና ከዕቅድ በላይ መጠባበቂያ እንዳይዝ በመደረጉና ይህም ዕቅድ በመሳካቱ ነው፡፡ የተበላሸ ብድር ክምችት የነበረባቸው 57 ፕሮጀክቶችን ወደ ጤናማ መስመር ማስገባቱና ለፕሮጀክቶቹ የሚውለው መጠባበቂያ በመቀነሱ በወጪ መደብ የተያዘው ገንዘብ በገቢ ዝርዝር ውስጥ ሊወድቅ በመቻሉ ውጤት መታየቱን አብራርተዋል፡፡

በ2012 ዓ.ም. ባንኩ ለማትረፍ ያቀደው 200 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በግማሽ ዓመቱ መጨረሻ የተገኘው ግን ከዕቅዱ እጅጉን ያሻቀበና ከ950 ሚሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ በተበላሸ ብድር ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱ ፕሮጀክቶች መካከል 202 ሚሊዮን ብር ማሰባሰብ መቻሉም ተገልጿል፡፡

የተበላሸ ብድር መጠኑ ወደ 34 በመቶ ዝቅ ቢልም፣ ይህ አኃዝ በገንዘብ ሲተመን 16 ቢሊዮን ብር በመሆኑ፣ የተበላሸ ብድር መጠኑን ለመቀነስ አሁንም ብዙ የሚቀረው መሆኑ ነው፡፡ አቶ ኃይለ የሱስም፣ ከዚህ ለመውጣትና ብዙ ላለመክሰር የተበላሸ ብድር ማስቆም አማራጭ የሌለው በመሆኑ ባንኩ በከተፍኛ ሁኔታ የሚሠራበት መሆኑንና የሪፎርሙም አካል እንዲሆን ተደርጓል፡፡

በዚህ ምክንያት በባንኩ ካፒታል ላይ የደረሰውን ጉድለት ለመሙላት ዝርዝር የካፒታል ማሻሻያ ጥናት ተጠንቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለመንግሥት ቀርቧል፡፡

ከብድር አሰጣጥና አስተዳደር ጋር በተያያዘ ትልቅ ችግር የነበረው ብድሮች ከዚህ ቀደም የሚሰጡበት የብድር ፖሊሲ ነው፡፡ ይህ ፖሊሲ አሁን ተሻሽሏል፡፡ እንዲህ ባለው ምክንያት እየተበራከተ የመጣውን የተበላሸ ብድር ለመግታት፣ በዝናብ ለሚለማ እርሻ አዲስ ብድር መስጠት ለማቆም ወስኗል፡፡ ይህም ሆኖ በአሁኑ ወቅት ባንኩ ብድር የሰጠባቸው 462 በዝናብ የሚለሙ ፕሮጀክቶች ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን 171 ተበዳሪዎች  እርሻዎቻቸውን ጥለው መሄዳቸው ታውቋል፡፡ እርሻዎቹን ለመረከብ ንብረቶቹን በማስያዝ የተበደሩትን አካላት በሕግ የማፈላለግ ሥራ ተጀምሯል፡፡ 71 ፕሮጀክቶች በልዩ ምርመራ በመለየታቸው ለሕግ እንዲቀርቡ ይደረጋል ተብላል፡፡

ከባንኩ የተበላሸ ብድር ጋር በተያያዘ ሌላው ተጠቃሽ ጉዳይ፣ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ያለው ጉዳይ ነው፡፡ በርካታ የውጭ ኩባንያዎች የተበላሸ ብድር አስመዝግበዋል፡፡ የቱርኩ አይካ አዲስ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በዋቢነት ይጠቀሳል፡፡ ኩባንያው ያለባቸውን ዕዳ ባለመክፈላቸው ባንኩ ንብረቶቻቸውን ቢረከብም፣ በሐራጅ ለመሸጥ የገጠመው ፈተና ቀላል እንዳልነበር አስታውቋል፡፡

በአይካ አዲስ ዙሪያ የባንኩ ፕሬዚዳንት በሰጡት ማብራሪያ ይህ ፈተና ምን ያህል እንደሆነ ያሳያል፡፡ አይካ አዲስ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያስገባ የነበረ ትልቅ አምራች ድርጅት እንደነበር በማስታወስ፣ አሁን ላይ ግን ያስገባ የነበረው የውጭ ምንዛሪ በምን ያህል ወጪ ብድሩን ሊከፍል ያስችለው ነበር? ትርፋማስ ነበር ወይ? ሌሎች የሚጠበቁበትን እንደ ግብር የመሳሰሉትን ግዴታዎች ይወጣ ነበር ወይ? ተብሎ ሲጠየቅ፣ በርካታ ችግሮች እንደነበሩበት አሳይቷል፡፡ እንዲህ ካሉ ችግሮቹ ጋር ባንኩ አይካ አዲስን እንደተረከበው ጠቅሰዋል፡፡

በርካቶቹ የውጭ ኩባንያዎች ላይ ይህ ችግር እንደሚታይ ገልጸው፣ ‹‹በተለይ የውጭ ባለሀብቶች ፕሮጀክቱን ጥለው ከሄዱና ባንኩ ከተረከባቸው በኋላ አሠራራችን ሲፈትሽ ያልተከፈሉ የተለያዩ የግብር ዕዳዎች ተገኝተዋል፡፡ ላስገቡት ዕቃ ለጉምሩክ መክፈል ሲገባቸው ያልከፈሉ ነበሩ፡፡ ሌላው ቀርቶ ከሠተራኞች ደመወዝ ላይ የጡረታ ተቀማጭ ሰብስበው ለጡረታ ዋስትና መሥሪያ ቤት ያልከፈሉ መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህ ብቻም ሳይሆን ከሦስተኛ ወገን በዱቤ ለወሰዱት ንብረት ክፍያ ያልፈጸሙም ተገኝተዋል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ሳቢያ አብዛኞቹ ጥለው ሄደዋል፡፡ እንደ ምሳሌ የተጠቀሰው አይካ አዲስ ሲሆን፣ ባንኩ ከመረከቡ በፊት ከባለሀብቶቹ ጋር በመሆን ፋብሪካው ከገባበት ችግር ወጥቶ እንዴት ውጤታማ እንደሚሆን በጋራ ታቅዶ የተወሰነ ጊዜ ቢተገበርም፣ ዕቅዱን ለማሳካት ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንዲደረግ በተደረገው ጥናት መሠረት ባንኩ ግማሹን ባለሀብቶቹም ግማሽ ድርሻ አዋጥተው ዘመናዊ ማኔጅመንት የሚመራው አሠራር ለመፍጠር ስምምነት ተደርጎ ሥራው ከተጀመረ በኋላ በመሀሉ ላይ ጥለው መጥፋታቸውን ፕሬዚዳንቱ አስታውሰዋል፡፡

ብድሩ ባለመከፈሉም ድርጅቱን በውርስ ተርክቦታል፡፡ ፋብሪካው ከ4,500 በላይ ሠራተኞች ያሉት በመሆኑ ሥራውን ላለማቋረጥ በነበረው ማኔጅመንት እንዲቀጥል ከተደረገ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ለሠራተኛውም ደመወዝ እየከፈለ ይገኛል፡፡ እንዲህ ባለ መንገድ ከተረከባቸው ኩባንያዎች አብዛኛዎቹ ግን ለመዘጋት ተገደዋል፡፡ አብዛኞቹ በባንኩ እየተዳደሩም ወጪያቸውን መሸፈን ባለመቻላቸው እንደሚዘጉ ገልጸዋል፡፡

ለሠራተኞች በሕግ የሚገባቸውን መብት አክብረን አሰናብተናል ያሉት አቶ ኃይለየሱስ፣ የአይካ አዲስ ጉዳይ ግን በተቻለ መጠን ሠራተኛው ሳይበተን ማስቀጠል የሚቻልበት አሠራር እየተተገበረ ጎን ለጎን እንዲሸጥ እየተሞከረ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ ፋብሪካውን ለመግዛት ፍላጎት ያሳዩ አካላት በመኖራቸው በቅርብ ጊዜ ውስጥ በሽያጭ አለያም ጥናት ተካሂዶና ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ተደርጎ ፋብሪካው ውጤታማ የሚሆንበትን አካሄድ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረበት እንደሚገኝ ባንኩ አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ አይካ አዲስን ለመሸጥ ሁለት ጊዜ ጨረታ ቢወጣም ገዥ አልተገኝም ነበር፡፡

እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች በአጠቃላይ የባንኩ የፋይናንስ ቁመና ላይ ያለችውን ኢንፕሌኬሽኖች አጥንቶ በውጪው ዓለም እንደሚደረገው እነዚህ እሴቶቸ ተለይተው ለብቻቸው የሚተዳደሩበትን ዓመት ማኔጅመንት ኩባንያ ማቋቋም ይጠይቃል፡፡ ለዚህ በተወሰነ ደረጃ ዝርዝር ጥናት ተጠንቷል፡፡ ይህንን ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በጋራ እንሠራን ብለዋል፡፡ የባንኩን ወደፊት ለማራመድ ደግሞ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ቀርፆ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ያሳወቀው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ባንኩ ራሱን ችሎ በአዲስ አሠራር እንዲራመድ ሊያግዘው የሚችል መሆኑን የሚጠቅም ነው፡፡ ለዚህ ግን አሁንም የመንግሥትን ዕገዛ ይሻል ተብሏል፡፡ ሌላው መንግሥት በአገር በቀል ኢኮኖሚ ፕሮግራም መሠረት እንዲህ ያለው ባንክ ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ባንክ ከውጭ ድጋፍ እያገኘ ቁመናው ተስተካክሎ ልማቱን ለመደገፍ የሚችልበት ደረጃ እስኪደርስ አሁንም ለአጭር ጊዜ የመንግሥትን ድጋፍ የሚፈልግ እንዲሁም አቶ ኃይለየሱስ ገልጸዋል፡፡   

በዚህም ባንኩ የአምስት ዓመታት የሪፎርም ዕቅድ ነድፎና አዲስ ራዕይ ቀርፆ ወደ ትግበራ ገብቷል፡፡ የሪፎርም ዕቅዱ የተዘጋጀው በአገር በቀሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም መሠረት ሲሆን፣ የባንኩን ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎች በማጣጣም እንደተዘጋጀ ተወስቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች