Thursday, June 13, 2024

በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ቀልድ የለም!

ኢትዮጵያውያን መቼም ሆነ የትም በአገራቸው ሉዓላዊነት ላይ ተደራድረው አያውቁም፡፡ ኢትዮጵያውያን የሚለያዩባቸው የተለያዩ ጉዳዮች ቢኖሯቸው እንኳ፣ በአገር ሉዓላዊነት ላይ ግን መቼም ቢሆን ተለያይተው አያውቁም፡፡ የውስጥ ጉዳያቸው ተካሮ ወደ ግጭት ቢያመራም፣ የአገር ሉዓላዊነትን የሚደፍር የውጭ ጠላት ሲነሳ ግን በአንድነት ለመቆም ተወዳዳሪ የላቸውም፡፡ በታሪክ የሚታወቁትም ለአገራቸው ባላቸው ወሰን የሌለው ጥልቅ ፍቅር ነው፡፡ በጊዜያዊ ጠብ ሲኮራረፉ እንኳ ወሳኙ ጊዜ ሲመጣ ስምምነት ፈጥረው አንድ ላይ እንደሚቆሙ ታሪክ ህያው ምስክር ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በአገር ሉዓላዊነት ቀልድ የለም ሲሉ መልዕክቱ ግልጽ ነው፡፡ ለእነሱ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ማለት ብሔራዊ ጥቅም፣ ደኅንነት፣ ነፃነት፣ መብትና ክብር ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ማንም ጣልቃ መግባትም ሆነ መወሰን አይችልም፡፡ ኢትዮጵያውያን ከታላቁ የዓድዋ የጀግንነት ድል ታሪክ የቀሰሙት፣ ሉዓላዊነትን በአንድነት ቆሞ ማስከበር ነው፡፡ ሰሞኑን በ124ኛው የዓድዋ ድል ክብረ በዓል ላይ በኢትዮጵያዊያን ሲተላለፉ የነበሩ መልዕክቶች በግልጽ ያመላከቱት፣ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ፈፅሞ መደራደር እንደማይቻል ነው፡፡ በተለይ ሰሞኑን የአሜሪካ መንግሥት የታላቁን የህዳሴ ግድብ አስመልክቶ ያወጣው ሉዓላዊነትን የሚጋፋ አሳፋሪ መግለጫ፣ የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ቁጣ የቀሰቀሰ ከመሆኑም በላይ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸውን ወገኖች በአንድነት ያሠለፈ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በገዛ ጉልበታቸውና ገንዘባቸው ያለ ማንም አጋዥ በሚገነቡት ታላቁ የህዳሴ ብሔራዊ ፕሮጀክታቸው ላይ የተቃጣው ጣልቃ ገብነት፣ መቼም ቢሆን የማይታገሱትና የማይደራደሩበት እንደሆነ በግልጽ አቋማቸውን እየገለጹ ነው፡፡ በሉዓላዊነት ቀልድ የለም ብለዋል፡፡

እዚህ ላይ አንድ የታሪክ ሰበዝ በመምዘዝ የጥንቶቹን ኢትዮጵያውያን ገድል ከዚህ ትውልድ ጋር ማያያዝ አስፈላጊ ነው፡፡ በ17ኛው ክፍለ ዘመን የዓባይን ወንዝ መነሻ ለማወቅ፣ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ስኮትላንዳዊ አሳሽ ጀምስ ብሩስ የሰጠውን ምስክርነት ማውሳት ጠቃሚ ነው፡፡ እ.አ.ኤ. ከ1769 እስከ 1774 በኢትዮጵያ ቆይታ ያደረገው ጀምስ ብሩስ በወቅቱ የታዘበውን ባሰፈረበት ጽሑፍ፣ ‹‹ኢትዮጵያዊያን በሰላም ጊዜ እርስ በርሳቸው ቢዋጉም፣ የውጭ ጠላት ሲመጣ ግን ግማሽ ጨረቃ ቅርፅ ሠርተው ድምጥማጡን ያጠፉታል፤›› ብሎ ነበር፡፡ እንደ ጀምስ ብሩስ በርካታ የውጭ ጸሐፍት ይህንን አኩሪ ታሪክ የዘገቡ ሲሆን፣ ከታላቁ የዓድዋ ጦርነት በፊትም ሆነ በኋላ ይህ የኢትዮጵያዊያን ጀግንነት ለመቀጠሉ በርካታ መረጃዎችን ማጣቀስ ይቻላል፡፡ የዓባይ ወንዝ መነሻን ለማወቅ በኢትዮጵያ የተዘዋወረው ጀምስ ብሩስ ኢትዮጵያዊያንን በዚህ ደረጃ ሲገልጻቸው የወቅቱ የምዕራባውያን ሐያሲዎች በማጋነን ልቦለድ የጻፈ ያህል ቢያብጠለጥሉትም፣ ኢትዮጵያውያን በተደጋጋሚ በተለያዩ የጦር ግንባሮች ወራሪዎችንና ተስፋፊዎችን በጀግንነት መክተው እንዳባረሩዋቸው፣ ኢትዮጵያም በአፍሪካ አኅጉር ብቸኛዋ እስካሁን ቅኝ ያልተገዛች አገር ለመሆኗ በዚህ ዘመን ምስክር ማፈላለግ አያሻም፡፡ ዓለም የሚያውቀው ሀቅ ነውና፡፡ ኢትዮጵያዊያን በሉዓላዊነታቸው የማይደራደሩና ለማንም እጅ ጥምዘዛ የማይንበረከኩ መሆናቸውን ደግሞ፣ ታላቁ የዓድዋ ድል ህያው ምስክር ነው፡፡ አሁንም ይህ ገድል አሸብርቆ እንደሚቀጥል ተስፋ አለ፡፡

በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ በሚደረገው ድርድር አሜሪካ ጣልቃ በመግባት ለግብፅ ያሳየቸው አሳፋሪ ድጋፍ መና መቅረት የሚችለው፣ አሁንም ኢትዮጵያውያን የውስጥ ሽኩቻቸውን አቁመውና ተጠናክረው አንድነታቸውን በተግባር ሲያሳዩ ብቻ ነው፡፡ ለፖለቲካ ሥልጣንም ሆነ ለማንኛውም ጉዳይ የሚደረገው ፉክክርም ሆነ ትንቅንቅ፣ ከኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ህልውና በታች መሆን አለበት፡፡ በዚህ ወሳኝና ታሪካዊ ወቅት የዓድዋ ጀግኖችን አርዓያነት በመከተል፣ በፍፁም ጨዋነትና ትዕግሥት ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ማሳየት ተገቢ ነው፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የጋራ ሀብትና የአንድነት ተምሳሌት ስለሆነ፣ ይህ የጋራ ፕሮጀክት የውጭ ኃይሎች አደጋ ሲደቀንበት ማፈግፈግ አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሲቆሙ የሚበግራቸው እንደሌለ ስለሚታወቅ፣ በመከፋፈል ለጠላት ዒላማ ተጋላጭ መሆን አይታሰብም፡፡ ኢትዮጵያ ለዓባይ ተፋሰስ 86 በመቶ የውኃ ሀብት እያበረከተች፣ በፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህ በመገዛት ማንንም ለመጉዳት እንደማትፈልግ በተደጋጋሚ ቃል ገብታለች፡፡ እግረ መንገዷንም ከዚህ የውኃ ሀብቷ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለመጠቀም ግድብ ስትገነባ ግን፣ በተለይ ከግብፅ በኩል በተደጋጋሚ የሚፈጸምባት በደል ከሚታገሡት በላይ ነው፡፡ እዚህ ድርድር ውስጥ የተገባው ከፍተኛ ትዕግሥት በመላበስ ጭምር ስለሆነ፣ በታዛቢነት ስም ገብታ እንደለመደችው የሸፍጥ ድርጊት ውስጥ በገባችው አሜሪካ ሌላ ተጨማሪ በደል ሲፈጸምባት ኢትዮጵያውያን አይታገሡም፡፡ ግብፅንም ሆነ አሜሪካን ከዚህ ድርጊታችሁ ታቀቡ መባል አለበት፡፡ ኢትዮጵያውያን የማንንም ጣልቃ ገብነት የማይፈልጉና ክብር ያላቸው መሆናቸውን ማስገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ አፍሪካውያን ወንድሞቿና እህቶቿ ማዞር አለባት፡፡ በወታደራዊ የበላይነቷና በታላቁ አሜሪካ አይዞሽ ባይነት በመተማመን ሰላማዊውን ድርድር ወደ ጦር ሜዳ ፍልሚያ ለመቀየር የምታስበውን ግብፅ ተንኳሽነት፣ በደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት በሚመራው የአፍሪካ ኅብረት አማካይነት በመግታት ወደ ድርድር ማምጣት የግድ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በዚህ ጉዳይ ላይ ገለልተኛ ሆኖ የቆየው የአፍሪካ ኅብረት አሁን ጥንካሬውን ማሳየት አለበት፡፡ ይህ እንዲሆንም የኢትዮጵያ መንግሥት ጫና ማሳደር ይጠበቅበታል፡፡ ኢትዮጵያ ለሰላም ስትል ይህንን ዕድል መጠቀም ሲኖርባት፣ የከፋ ነገር ከመጣ ደግሞ እንዴት ማስተናገድ እንደሚቻል ይታወቃል፡፡ ግብፅ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት የአስዋን ግድብን ስትገነባ ኢትዮጵያን እንዳላማካረች እየታወቀ፣ ነገር ግን ኢትዮጵያ በምትገነባው ግድብ እንድትደራደር ዕድል ተሰጥቷት በደል ስትፈጽም የአፍሪካ ኅብረት የሩቅ ታዛቢ መሆን የለበትም፡፡ ከኅብረቱ በተጨማሪ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ‹ነግ በእኔ› ብለው፣ ከዓመታት በፊት ያፀደቁትን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እንዲከበር እንዲታገሉ ማነሳሳት ይገባል፡፡ ውኃውን በፍትሐዊ ተጠቃሚነት የጎረቤታሞች የጋራ ሀብት እናድርገው ሲባል፣ በቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነት መሠረት ግብፅ የበላይ እንድትሆን መፈቀድ የለበትም፡፡ ይህንን ዕብሪት ሲቻል በሰላም ካልሆነም በአርበኝነት መንፈስ ማስተንፈስ እንደሚቻል ማሳወቅ የግድ ይሆናል፡፡ ይህ የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ ሳይሆን የሉዓላዊነት ማስከበሪያ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በታሪካቸው የሚታወቁት የዘመቱባቸውን ተከላክለው ድባቅ ሲመቱ እንጂ፣ በሌሎች ላይ ሲዘምቱ አለመሆኑን ታሪክ ከበቂ በላይ ይመሰክራል፡፡ አሁንም በሰላም የመጣውን በዘንባባ ዝንጣፊ፣ አሻፈረኝ ብሎ የሚዳፈረውን ደግሞ በሚገባው ቋንቋ ማነጋገር ይቻላል፡፡ አማራጭ ሲጠፋ ሉዓላዊነት የሚከበረው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡

ሰሞኑን አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ሌላ ክህደት ፈጽማለች፡፡ ከዚህ በፊት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ገንዘብ የተከፈለበትን የጦር መሣሪያ አልሰጥ በማለቷ፣ የዚያድ ባሬ ሶማሊያ ወረራ ፈጽማ ከባድ ጉዳት ደርሶብናል፡፡ የደርግ መንግሥት በዚህ
ምክንያት ወደ ምሥራቁ ጎራ በመቀላቀሉ ኢትዮጵያ ለዓመታት ጦርነት ውስጥ ተዘፍቃ ነበር፡፡ ምንም እንኳ አሜሪካ ለጥቅሟ ስትል በዓለም ላይ በርካታ ችግሮች መፍጠሯ ቢታወቅም፣ ካሁን በኋላ በኢትዮጵያ ላይ ሌላ መከራ እንዲመጣ ማድረግ የለባትም፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን ችግር በፍጥነት በዲፕሎማሲ በመፍታት የተጣመመውን የአሜሪካ ፖሊሲ እንዲቃና መሥራት አለባት፡፡ የአሜሪካ የተጣመመ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በአፍሪካ ምድር ታላቁን የውኃ ጦርነት እንዳያስነሳ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲረባረብ ማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡  በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያን፣ በሰከነ መንገድ አሜሪካ እየተከተለች ያለውን አደገኛ ፖሊሲ እንድትቀለብስ ሌት ተቀን መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚገዳደር ማናለብኝነት መቆም አለበት፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን ዋነኛው ብሔራዊ ጥቅም ስለሆነ፣ ለሌሎች ኃይሎች ጥቅም ማስፈጸሚያ የመስዋዕትነት ጠቦት መሆን የለበትም፡፡ ኢትዮጵያዊያን በኃይለኞች ማስፈራሪያ ወይም ጫና እንደማይንበረከኩ ማሳየት የግድ ነው፡፡ ታላቁ የዓድዋ ድል ተጋድሎና የአርበኝነት ስሜት ዛሬም ህያው መሆኑን ለዓለም ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ከዳር እስከ ዳር በአንድነት ተሠልፈው፣ ይህንን ዘመን የማይሽረውንና የማይበርድ የጀግንነት ወኔ ለጉልበተኞች ጭምር በማሳየት ማስገንዘብ አለባቸው፡፡ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ቀልድ የለም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...

የ‹‹ክብር ዶክትሬት›› ዲግሪ ጉዳይ

በንጉሥ ወዳጅነው ‹‹የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ግልጽ የሆነ መመርያ እስኪወጣ ድረስ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...

ከግጭት አዙሪት ውስጥ የሚወጣው በሰጥቶ መቀበል መርህ ነው!

የኢትዮጵያን ሰላም፣ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች ማዕከል በማድረግ መነጋገር ሲቻል ለጠብ የሚጋብዙ ምክንያቶች አይኖሩም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚደረጉ ክንውኖች በሙሉ ከጥፋት የዘለለ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ዘርፈ...