Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሦስት ስኳር ፋብሪካዎች በመንግሥት ይዞታ ሥር እንዲቆዩ ተወሰነ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በፕራይቬታይዜሽን ዕቅዱ መሠረት በሽያጭ ወደ ግል እንዲዛወሩ ከተባሉት ስኳር ፋብሪካዎች ውስጥ፣ ሦስት በማምረት ሒደት ላይ የሚገኙ ስኳር ፋብሪካዎች በመንግሥት ይዞታ ሥር እንዲቆዩና የተቀሩት ከመጪው ሰኔ ወር ጀምሮ የሽያጭ ጨረታ እንዲወጣባቸው ተወሰነ።

መንግሥት በተወሰኑ የልማት ድርጅቶች ላይ የወሰነውን ፕራይቬታይዜሽን እንዲያከናውን ኃላፊነት በተሰጠው ገንዘብ ሚኒስቴር ሥር የተቋቋመው የፕራይቬታይዜሽን ኮሚቴ፣ የስኳር ፋብሪካዎችን ሽያጭ በተመለከተ ያሳለፈው ውሳኔና ዝርዝር መርሐ ግብር እንደሚያስረዳው፣ በሽያጭ ወደ ግሉ ዘርፍ እንዲዘዋወሩ ከተባሉት 13 የመንግሥት ስኳር ፋብሪካዎች ውስጥ ሦስቱ መሸጥ እንደሌለባቸው ተወስኗል።

ስኳር ፋብሪካዎቹን በሙሉና በከፊል በመሸጥ ወደ ግሉ ዘርፍ እንዲያዘዋውሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው ገንዘብ ሚኒስቴር፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ የስኳር ኮርፖሬሽን ሥራ አመራር ቦርድና ሥራ አመራር በኩል የቴክኒክ ዳሰሳ ጥናት፣ የሀብት ግመታ፣ የፕራይቬታይዚሽንና የማርኬቲንግ ጥናት በውጭ ገለልተኛ አካል ተጠንቶ የፕራይቬታይዜሽን ሒደቱን በተመለከተ በመንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤት ውሳኔ መተላለፉን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በዚህ መሠረት ካሉት የስኳር ፋብሪካዎችና ካልተጠናቀቁ የስኳር ፕሮጀክቶች መካከል መንግሥት በስኳር ኮርፖሬሽን ሥር ሦስት ፋብሪካዎችን ይዞ እንዲቀጥል ተወስኗል። ከፕራይቬታይዜሽን ሒደቱ እንዲወጡና በመንግሥት ይዞታ ሥር እንዳሉ እንዲቀጥሉ የተባሉት ፋብሪካዎች ነባሮቹ ፊንጫ ስኳር ፋብሪካና መተሐራ ስኳር ፋብሪካ ሲሆኑ፣ ከኦሞ ኩራዝ ቀጥር ሁለት ወይም ቁጥር ሦስት አንዱ እንደ አመቺነቱ ተመርጦ በመንግሥት ይዞታ ሥር እንዲቀጥል ተወስኗል።

እነዚህ የስኳር ፋብሪካዎች ለማስፋፋትም ሆነ ቀሪ ሥራዎቻቸውን ለማጠናቀቅ፣ ምንም ተጨማሪ ኢንቨስትመንት የማይፈልጉና የተሻለ ምርት እየሰጡ በመሆኑ ነው በመንግሥት ይዞታ ሥር እንዲቀጥሉ የተወሰነው። ሪፖርተር ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ቀሪዎቹ አሥር ስኳር ፋብሪካዎችና ያልተጠናቀቁ የስኳር ፕሮጀክቶች፣ ከመጪው ሰኔ ወር 2012 ጀምሮ የሽያጭ ጨረታ እንዲወጣባቸው ተወስኗል።

በተቀሩት ፋብሪካዎች ላይ የሚወጣው ጨረታ ፋብሪካዎቹን ሙሉ በመሉ ወደ ግል ለማዘዋወር ሲሆን፣ ከመንግሥት ጋር በሽርክና ለማልማት ከፊል ጨረታ ማውጣት ደግሞ በአማራጭነት ተቀምጧል።

መንግሥት ከ2003 ዓ.ም. አንስቶ ተግባራዊ ማድረግ የጀመራቸው እነዚህ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ወለድን ሳይጨምር 149 ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥና የውጭ ዕዳ እንዳለባቸው፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት መዘገባችን ይታወሳል። መንግሥት ለስኳር ፋብሪካዎቹ የይዞታ ማረጋገጫ ማግኘት ባለመቻሉም፣ ፋብሪካዎቹን ወደ ግል ለማዘዋወር የሚደረገውን ጥረት እንዳይስተጓጎል ሥጋት ፈጥሯል፡፡

ወደ ግል እንዲዘዋወሩ የተባሉትን ስኳር ፋብሪካዎች በከፊልም ሆነ በሙሉ የመግዛት ፍላጎት ያላቸው የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን በሰነድ እንዲገልጹ መንግሥት ባቀረበው ጥሪ መሠረት፣ በርካታ ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን ለገንዘብ ሚኒስቴር ማሳወቃቸውን እንዲሁ መዘገባችን አይዘነጋም።

ፍላጎቶቻቸውን ካስታወቁ ኩባንያዎች መካከል ከኬንያ፣ ከአልጄሪያ፣ ከሞሪሸየስ፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ከኳታር፣ ከናይጄሪያና ከሌሎችም የተውጣጡ ኩባንያዎች ጨረታው የሚከፈትበትን ቀን እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡ ከአገር ውስጥም የቢራ ፋብሪካዎችን ጨምሮ በመጠጥ ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚንቀሳቀሱና በምግብ ማቀነባበር መስክ የተሰማሩ፣ የሸንኮራ አገዳ አምራቾችና ሌሎችም ጨረታው ይፋ የሚወጣበትን ጊዜ ከሚጠባበቁት መካከል ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ በሲሚንቶ ምርቶቹ የሚታወቀው ዳንጎቴ ኢንዱስትሪስ፣ መንግሥት ለሽያጭ ካቀረባቸው የስኳር ፋብሪካዎች መካከል ቢያንስ ሁለቱን ለመግዛት ፍላጎት እንዳለው የዳንጎቴ ግሩፕ ወኪል አቶ አዲስ ዓለማየሁ ለሪፖርተር መግለጻቸው ይታወሳል። እንደ አቶ አዲስ ገለጻ፣ ዳንጎቴ ግሩፕ ጨረታው ይፋ የሚደረግበት ትክክለኛ ጊዜ መቼ እንደሆነ ብቻ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች