ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ባቋቋሙት ካቢኔ ውስጥ ከተካተቱት የመጀመርያዎቹ የካቢኔ አባላት ውስጥ አንዱ የነበሩት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊኒን ጨምሮ 15 በተለያዩ ኃላፊነት ሲሠሩ የነበሩ ግለሰቦች፣ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርና አምባሳደር ሆነው ተሾሙ፡፡
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ማክሰኞ የካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት ሹመት ዘጠኝ ባለሥልጣናት ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሲሆኑ፣ ስድስት ግለሰቦች ደግሞ በአምባሳደርነት ሥልጣን ተሹመዋል፡፡
አምባሳደሮቹ በተለያዩ አገሮች እንደሚመደቡ ከመግለጽ ባለፈ ማን በየትኛው አገር እንደሚመደብ ባይገለጽም፣ ዋና ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ፣ የሕፃናት፣ ወጣቶችና ሴቶች ሚኒስትር ወ/ሮ የዓለም ፀጋዬ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሒሩት ዘመነ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ማርቆስ ተክሌ (አምባሳደር)፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊና፣ አቶ ይበልጣል አዕምሮ፣ አቶ ምሕረት አብ ሙሉጌታ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸውና አቶ ተፈሪ መለስ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ተሹመዋል፡፡
አቶ አድጎ አምሳያ፣ አቶ ጀማል በከር፣ አቶ አብዱ ያሲን፣ አቶ ለገሠ ገረመው፣ ወ/ሮ እየሩሳሌም ዓምደ ማርያምና አቶ ሽብሩ ማሞ ደግሞ በአምባሳደርነት መሾማቸው ተገልጿል፡፡
የአምባሳደርነት ሹመት የተሰጣቸው ግለሰቦች በተለያዩ ተቋማት በከፍተኛ ሥልጣንና ኃላፊነት ላይ ተሹመው በመሥራት ላይ ያሉ ቢሆንም፣ ማርቆስ ተክሌ (አምባሳደር) በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር በነበሩት በሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) ከመተካታቸው በስተቀር፣ ሌሎቹን ማን እንደሚተካቸው ወይም ከሥልጣናቸው ተነስተው ለአምባሳደርነት ሹመት ያበቃቸውም ምክንያት አልተገለጸም፡፡