Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኢትዮጵያ አንድነት የተቀነቀነበት የታላቁ ዓድዋ ድል 124ኛ ዓመት ክብረ በዓል

የኢትዮጵያ አንድነት የተቀነቀነበት የታላቁ ዓድዋ ድል 124ኛ ዓመት ክብረ በዓል

ቀን:

ሰኞ የካቲት 23 ቀን 2012 ዓ.ም. 124ኛው የታላቁ ዓድዋ ድል በዓል በዓድዋ ተራሮች ሥርና በአዲስ አበባ ከተማ በታላቅ ሥነ ሥርዓት ሲከበር፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ሉዓላዊነት በአንድነት የመቆም አስፈላጊነትን አስረግጠው አስታውቀዋል፡፡ በበዓሉ ዋዜማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ‹‹ዓድዋ አንድም ብዙም መሆናችንን ያሳየንበት ታሪክ ነው…›› ብለው፣ ‹‹… ጣሊያኖች ወደ ዓድዋ ሲመጡ የታያቸው ልዩነታችን ነው፡፡ በልዩነታችን ላይ ሠርተው ኢትዮጵያዊያንን በማዳከም ቅኝ ግዛትን ሊጭኑብን አስበው ነበር… ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ግን ያሰቡትን አላገኙም፡፡ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ጉዳይ፣ በሉዓላዊነታቸው ጉዳይ፣ በነፃነታቸው ጉዳይ የማይደራደሩ መሆናቸውን አሳዩ … ኢትዮጵያዊያን ኅብራዊ አንድነት እንዳላቸው ዓድዋ መሰከረ፤›› ብለዋል፡፡ በዓድዋ ከተማ ታላቁ ጀግንነት በተፈጸመባቸው ተራሮች ሥር በነበረው ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ ‹‹የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን በየትኛውም ወቅት በአገር ልዕልና፣ መብትና ነፃነት ላይ እንደማይደራደሩ ያሳየ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የዓድዋ ድል ከማንኛውም የውስጥ ችግር በላይ ለአገር ነፃነት ትኩረት በመስጠት ነፃ አገር ማቆየት መቻሉንም አስረድተዋል፡፡ ‹‹የዓድዋ ድል ስንነጋገርና ስንደማመጥ የማንወጣው አረንቋ እንደሌለ ማሳያ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ ‹‹የዓድዋ ድል አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን የአገራቸውን ነፃነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር በየጊዜው ከወራሪዎች ጋር ሲያካሂዱ የነበረውን ጦርነት ማጠቃለያ በዓድዋ በመግጠም፣ ሊገመትና ሊተነበይ የማይችል ድል ያስመዘገቡበት ነው፤›› ብለዋል፡፡ በተጨማሪም፣ ‹‹ሰሞኑን የህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ የቀረበውን የውል ሰነድ ቆም ብለን ከውጫሌ ውል በመማር የሠፈሩ ሐሳቦችና ቃላት፣ በሉዓላዊነታችን ላይ የመጡና ከዚያም አልፎ የሌላ ጂኦ ፖለቲካዊ ዓላማ ማስፈጸሚያ ገፀ በረከትና እጅ መንሻ ሆነው እንዳያገለግሉ በከፍተኛ ጥንቃቄና ኃላፊነት መፈጸም ይገባናል፤›› በማለት አሳስበዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በተደረገው ክብረ በዓል የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች ማኅበር ሊቀመንበር ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፣ ኢትዮጵያ በዓድዋ የከፈለችው መስዋዕትነት ለአፍሪካውያን መትረፉን አስታውሰዋል፡፡ ‹‹አገራችን ኢትዮጵያ አሁን እጅግ ፈታኝ ጊዜ ላይ ትገኛለች፤›› ብለው፣ ‹‹ኢትዮጵያዊያን ከልዩነት ይልቅ አንድነትን፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን በማስተጋባት ለአገራቸው ዘብ መቆም አለባቸው፤›› በማለት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በዓድዋ የድል በዓል በተለያዩ አልባሳት በመድመቅ አደባባይ የወጡ ኢትዮጵያውን፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደ ዓድዋ ጀግኖች ለአገር በአንድነት መቆም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በመስዋዕትነት ተከብሮ የኖረውን የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ለማጠናከር፣ የዓድዋ ድል የአንድነት ዓርማ መሆን እንዳለበት በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች አስተጋብተዋል፡፡ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር አሜሪካ ለግብፅ የሚወግን መግለጫ ማውጣቷን በመቃወም፣ መንግሥት በሉዓላዊነት ላይ የተዶለተውን ሴራ በማክሸፍ የኢትዮጵያን ጥቅም እንዲያስከብር ጠይቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...