Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየሰሜን ኮሪያ ሚሳይል ማስወንጨፍ

የሰሜን ኮሪያ ሚሳይል ማስወንጨፍ

ቀን:

ዓለም በኮሮና ቫይረስ ሥጋት ውስጥ ወድቋል፡፡ መነሻውን ከቻይና አድርጎ አሁን ላይ 37 አገሮችን ያጠቃው ይህ ቫይረስ፣ ለዓለም ሥጋት በተለይም ለእስያ ቀዳሚ አጀንዳ ነው፡፡

ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓንና ሌሎችም የቀጣናው አገሮች ወጋቸው ሁሉ ኮሮና ቫይረስን መቆጣጠር፣ ብሎም ማጥፋት ላይ ሆኗል፡፡ የአንዳንድ ኩባንያ ሠራተኞች ሥራቸውን ቤት እንዲያከናውኑ፣ በአንዳንድ ሥፍራ ደግሞ ትምህርት ቤት ጭምር እንዲዘጋ እየተደረገም ይገኛል፡፡

አሜሪካ ስድስት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ እንደሞቱባት ስታስታውቅ፣ በአፍሪካም በስድስት አገሮች ኮሮና ቫይረስ መግባቱ ተነግሯል፡፡

አሜሪካ ከዚህ ቀደም ካገደቻቸው የውጭ አገር ዜጎች በተጨማሪ ኮሮና ቫይረስን ለመግታት ስትል ተጨማሪ ገደብ እንደምትጥል ስታስታውቅ፣ በዓለም በቫይረሱ ተጠቅተዋል ከተባሉት ከ90,000 በላይ ሰዎች መካከል ከ90 በመቶ በላዩ የሚገኙባት ቻይና ደግሞ ትኩረቷ ሁሉ ኮሮና ቫይረስ ላይ ከሆነ ወር ሞልቷል፡፡  

ጉዳዩ እ.ኤ.አ. በ2008 እንደተከሰተው የዓለም ኢኮኖሚ ያሽቆለቁላል፣ የየኩባንያዎችን አቅም ያሽመደምዳል የተባለው ኮሮና ቫይረስ ለዓለም አጀንዳና ሥጋት በሆነበት በዚህ ወቅት፣ ለሰሜን ኮሪያ አጀንዳ አልሆነም፡፡ ይልቁንም እ.ኤ.አ. 2020 ከገባ ወዲህ የመጀመርያዋ ነው የተባሉትን ሁለት ሚሳይሎች ለሙከራ በማስወንጨፍ ትኩረት ስባለች፡፡

የሰሜን ኮሪያ ሚሳይል ማስወንጨፍ

 

ሰኞ የካቲት 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ሰሜን ኮሪያ ሁለት ሚሳይል ማስወንጨፏን ቢቢሲ ሲዘግብ፣ ለዚህ ምክንያቱ ሰሜን ኮሪያ ፍፁም እንዳይደረግ የምፈልገው ደቡብ ኮሪያና አሜሪካ በየዓመቱ የሚያደርጉት ጥምር ወታደራዊ ልምምድ በኮሮና ቫይረስ ሥጋት ምክንያት መራዘሙ መገለጹን ተከትሎ ነው፡፡

ደቡብ ኮሪያና አሜሪካ በየዓመቱ የሚያደርጉትን ጥምር ወታደራዊ ልምምድ ሰሜን ኮሪያ ሁሌም እንደነቀፈች ሲሆን፣ ልምምድ ሲያደርጉም ሆነ ካደረጉ በኋላ ወይም ሊያደርጉ ሲሉ ሚሳል የማስወንጨፍ ልማድ እንዳላትም ይታወቃል፡፡ አገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የምታነሳው አጀንዳ ቢኖርም፣ ‹‹ወታደራዊ ልምምዱ ሰሜን ኮሪያን ለማጥፋት ስለሆነ ይቁም፤›› የሚል ነው፡፡ ይህ ባለመሆኑ ደግሞ ወቅቱን ጠብቆ የአፀፋ ምላሽ የምትሰጠው የሚሳይል ሙከራ በማድረግ ነው፡፡  

የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ተቋምን ዋቢ አድርጎ ቢቢሲ እንዳሰፈረው፣ ሁለቱ ሚሳይሎች የተወነጨፉት ከሰሜን ምሥራቅ የባህር ዳርቻ በደቡብ ኮሪያና ጃፓን መካከል ነው፡፡ የተተኮሱት ሚሳይሎችም አጭር ርቀት ተወንጫፊ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል እምነት እንዳላት ደቡብ ኮሪያ ገልጻለች፡፡

ሰሜን ኮሪያ እ.ኤ.አ. 2019 ግንቦት ላይ ለ18 ወራት አቋርጣ የነበረውን የሚሳይል ሙከራ ዳግም ማድረጓ፣ በኋላም ጥቅምት ላይ መድገሟ የሚታወስ ሲሆን፣ የአሁኑ በሦስት ወራት ልዩነት የተሞከረ ነው፡፡

ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ፕሮግራሟን ታቋርጥ ዘንድ፣ እ.ኤ.አ. በ2018 የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና የሰሜን ኮሪያ አቻቸው ኪም ጁን ኡንግ ታሪካዊ የተባለውን ውይይት በሲንጋፖር አድርገው የነበረ ቢሆንም፣ ሰሜን ኮሪያን ከኑክሌር ነፃ ማድረግ ላይ ከመግባባት አልደረሱም፡፡

ሁለቱ መሪዎች እ.ኤ.አ. በ2019 ዳግም በቬይትናም ቢገናኙም፣ ውይይታቸው ያለ ስምምነት ነበር የተጠናቀቀው፡፡ ሰሜን ኮሪያን ከኑክሌር ነፃ የማድረግ ውይይቱ በእንጥልጥል ባለበት ወቅት፣ ሚሳይል መሞከር ምናልባትም በአገሪቱ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ በመቃወምም ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል፡፡

ሰሜን ኮሪያ በ2019 ማብቂያ ላይ ያደረገችው ተመሳሳይ ሙከራ አሜሪካ ላይ ውጥረት ለመፍጠር እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ሆኖም አሜሪካ ሰሜን ኮሪያ ሙሉ ለሙሉ የኑክሌር ፕሮግራሟን ካልዘጋች፣ ምንም ዓይነት ማዕቀብ እንደማይነሳ አስታውቃ ነበር፡፡

ሰሜን ኮሪያ ከ450 ኪሎ ሜትር እስከ 13 ሺሕ ኪሎ ሜትር ሊወነጨፉ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ሚሳይሎች ባለቤት መሆኗንም ቢቢሲ አስፍሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...