Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየዓድዋ ድል ሥነ በዓል ድባብ

የዓድዋ ድል ሥነ በዓል ድባብ

ቀን:

በሔለን ተስፋዬ

‹‹ዘራፍ አካኪ ዘራፍ

ዘራፍ አካኪ ዘራፍ

- Advertisement -

ጠብመንጃ አንግቶ ከነጥይቱ

ጎራዴ መዞ ሲሄድ ከቤቱ

ወየውለት ጠላት አለች እናቱ

እንኳን እናቱ የወለደችው

ኮራች አማቹ የተጋባችው››

ይህ ፉከራ በታዳጊዎች የተስተጋባው የካቲት 23 ቀን 2012 ዓ.ም. የዓድዋ ድል 124ኛ ዓመት በተከበረበት የአዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ ነው፡፡

ታዳጊዎቹ ጋሻና ጦር መሰል ነገር ይዘው ጎርደድ እያሉ አንዳንዴም በጉልበታቸው በርከክ እያሉ ‹‹ዘራፍ…ዘራፍ›› እያሉ ትርኢቱን ሲያቀርቡ ለተመለከተ የመንፈስ እርካታን ይለግሳል፡፡

አፄ ምኒልክ  ሐውልት ዘሪያ ያለው ሕዝብ እጅግ ብዙ ነው፡፡ ከሁሉም ሰዎች ገጽ የሚነበበው ደስታና የድል በዓሉን ለማክበር ቀደምት አባቶችንና እናቶች ይለብሱት የነበረውን ዓይነት በመልበስ ይበልጥ ድምቀት እንዲፈጠር አድርጎታል፡፡ የአፄ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱ አለባበስን ተላብሰው እነሱን አክለው፣ ጎርደድ እያሉ ለታዳሚው ከሚያቀርቡት ትዕይንት በተጨማሪ እነሱን የከበቡት አገልጋዮች፣ ፈረሶች፣ ጥሩንባ፣ ነጋሪትን ላየ ቀደምት የነበረውን በዓይን ማየት ባይቻልም በሐሳብ ወደ ኋላ የነበሩትን ትዕይንቶች እንዲታወስ ዕድል የሰጠ በዓል ነው፡፡

የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. የሰው ልጅ እኩል መሆኑን ኢትዮጵያውያን ለዓለም ሕዝብ ያሳወቁበት የድል ቀን ያሰኘው፣ ወራሪውን የጣሊያን ጦር ዓድዋ ላይ ድል የመቱበት ስለሆነ ነው፡፡ በዚህ የድል ቀን ከኢትዮጵያውያን አልፎ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች አንገታቸውን ቀና ያደረጉበትም ጭምር ነው፡፡

የዓድዋ የድል በዓልን በአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች ሲያከብሩ ማየት የተለመደ ቢሆንም የዘንድሮው አከባበር እጅግ ያማረና በዛ ያለ ተሳታፊ የነበረበት መሆኑ ታይቷል፡፡

በአዲስ አበባው አከባበር ሁሉም በየቡድኑ ሆኖ ፉከራውና ሽለላውን ያቀልጠዋል፡፡ ከመሀል ፒያሳ እስከ የዓድዋ ዘመቻ መታሰቢያ ድልድይ በተደረገው የእግር ጉዞ አንዳንዶች በፉከራና በቀረርቶ ሌሎች ደግሞ ኢትዮጵያን የሚያሞግሱ ዜማዎችን እያዜሙ ጉዞውን ቀጥለዋል፡፡ በተለይ ለዚህ የድል በዓል የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ቀድመው ከመሰናዳታቸው በበለጠ አባቶች ይታወሱ ዘንድ በባዶ እግራቸው ሲፎክሩና ሲሸልሉ ላየ ደስታን አጭሯል፡፡

ዕለቱ የድል በዓል ሊባል የቻለው የቀደሙት አባቶች ለአገራቸው በአንድነት ሆነው በመታገላቸውና መስዋዕት በመሆናቸው ጭምር ነው ሲሉም ተሰምተዋል፡፡

የዓድዋ የድል በዓል አከባበር ከተንፀባረቁባቸው መልዕክቶች ብዙዎች አንድነትንና ሰዋዊነትን የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡

ወጣቶች ካንፀባረቋቸው ሐሳቦች መካከል ‹‹እንነጋገር ያገሬን ነገር››፣ ‹‹እንነጋገር የዓባይን ነገር›› ጎልተው ተሰምተዋል፡፡ በተለይም የህዳሴ ግድብ ዙሪያ የበዓሉ ተሳታፊዎች ይበልጥ አንድ መሆናቸውን አሳይተውበታል፡፡

በዋዜማው የካቲት 22 ቀን በሰውኛ ፕሮዳክሽን ኢንተርቴይመንት አማካይነት የተዘጋጀው ‹‹ምሕረት ዋዜማ›› ቴአትር የበዓሉ መንደርደርያ ሆኗል፡፡

በሚካኤል ሚሊዮን፣ ምንተስኖትና መዓዛ ታከለ የተደረሰውና 150 ተዋንያን የተሳተፉበት ‹‹ምሕረት ዋዜማ›› ቴአትር የአፄ ምኒልክ ሩህሩህነት ብሎም ቀደምት የነበረውን የሰዎች መደመማጥና የሃይማኖት አባቶች ተሰሚነት በከፊል ያንፀባረቀ ነው፡፡ የዘንድሮ የዓድዋ ድል በዓል አብዛኛው ሐሳብ በይበልጥ አገራዊ አንድነት ላይ ያንፀባረቀ ነው፡፡

በሌላ በኩል ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› ዝክረ ዓድዋ ልዩ የኪነ ጥበብ ምሽት ሌላኛው የዓድዋ ድል በዓል የተከበረበት ነው፡፡ በምሽቱ አጭር የመድረክ ቴአትር፣ ግጥም፣ ፉከራ ሽለላና ቀረርቶ የቀረበ ሲሆን ተጋባዥ እንግዶች በዓሉን በማስመልከት የተለያዩ መልዕክቶችን ለታዳሚያን አቅርበዋል፡፡

ከመልዕክቶቹ መካከል የዓድዋ ድል በዓል የጥቂት ወይም የአንድ ጎራ ተደርጎ ብቻ የሚወሰደው አካሄድ መቅረት እንዳለበትና በዓሉ የጥቁር ሕዝብ ድልነት በተጨማሪ የሰው ልጅ እኩልነት የተረጋገጠበት መሆኑ ይገኙበታል፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ኢትዮጵያዊ በሙሉ ባለው አቅምና ችሎታ ግድቡን ከማጠናቀቅ ባሻገር ከግድቡ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ለሚፈጥረው ነገር በሙሉ ኢትዮጵያውያን ዕገዛ ማድረግ እንደሚገባቸው ተንፀባርቋል፡፡

የዓድዋ ድል ቀደምት አባቶችና እናቶች የእርስ በእርስ ሽኩቻዎችን ወደ ጎን ትተው ለአገራቸው አንድ በመሆናቸው የመጣ ድል በመሆኑ አሁንም በአገር ህልውና በሚመጣ ጉዳይ አንድ መሆን ይጠይቃል የሚሉ ሐሳቦች በምሽቱ በይበልጥ ተደምጠዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...