Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገር‹‹ግመል ሰርቆ አጎንብሶ››

‹‹ግመል ሰርቆ አጎንብሶ››

ቀን:

በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እንደተለመደው የተመሠረተበትን 45ኛ ዓመት የልደት በዓሉን የካቲት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. መቀሌ ከተማ ውስጥ እስከ መቶ ሺሕ ይደርሳል የተባለለት ሕዝብ በታደመበት አደባባይ በደማቅ ሁኔታ እንዳከበረ፣ ከርቀትም ቢሆን ተከታትለናል፡፡ በዚህ ጸሐፊ አስተያየት ዓላማው ገብቷቸውም ይሁን ሳይገባቸው በመሪዎቻቸው ሸር እየተሰበኩ በትግራይ ሕዝብ ሓርነት ስም ደማቸውን በከንቱ ያፈሰሱና አጥንታቸውን የከሰከሱ ወንድና ሴት ወጣቶች፣ ዛሬም ሆነ ለዝንታለሙ ክብርና ሞገስ ይገባቸዋል፡፡

እንግዲህ የወቅቱ የሕወሓት መሪና የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በዚያ ደማቅ ትዕይንተ ሕዝብ ላይ በአካል ተገኝተው በነቂስ አደባባይ ለተሰበሰበው ታዳሚ ያደረጉት ንግግር፣ የዚህ አነስተኛ መጣጥፍ ዓይነተኛ ማጠንጠኛ ነው፡፡

ሰውየው ድሮም ቢሆን የጤንነታቸው ሁኔታ ያን ያህል አስተማማኝ እንዳልሆነ አስቀድመን እናውቃለን፡፡ በዕለቱ ግን ከናካቴው “የዕብድ ገላጋይ ድንጋይ ያቀብላል” ዓይነት ሆነው እንዳረፉ ነበር በመደመም የተመለከትናቸው፡፡

ትግራይ የሪፐብሊኩ ክፍልና አካል እንዳልሆነች ቆጥረው፣ “ኢትዮጵያ ያላግባብ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ እየገባችብን ነው፤” ሲሉ የደበዘዘ ቀልድ ቢጤ የተጣባውን ምሬታቸውን በማሰማት ንግግራቸውን የጀመሩት ታጋይ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ የትግራይን ማኅበረሰብ አምርሮ እንደሚጠላ በከፍተኛ ድፍረት ያስደመጡት ረብ የለሽ ዲስኩር አስተዛዛቢ ነበር፡፡ ሆኖም ትግርኛ ተናጋሪው ወገናችን የሚኖረው በትግራይ ክልል ብቻ አይደለም፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ትግሬን በጅምላ የሚጠላ ሕዝብም ፈጽሞ የለም፡፡

በእርግጥ ‘ሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ናቸው’ የሚለው የዘልማድ አባዜ አብዛኞቹን የሕወሓት መሪዎች የተጠናወታቸው ክፉና ፈውስ ያልተገኘለት ደዌ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ይህ ዓይነቱ ኃላፊነት የጎደለው ድምዳሜ የትግራይን ሕዝብ አንጀት ለመብላት የተወጠነ ነው ከሚባልና በቀላሉ ከሚጣጣል በስተቀር፣ ከቁም ነገር የሚቆጠር እንዳልሆነ የብዙዎች እምነት ነው፡፡

በዚህስ ቢወሰኑ ምን ነበረበት? የርዕዮተ ዓለም ሐረጋቸው ከታላቁ መሪ ከአቶ መለስ ዜናዊ የሚመዘዘው እኝህ ግለሰብ፣ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የሚገኙት በጣት የሚቆጠሩ ተወካዮቻቸው የአገልግሎት ዘመናቸው ከማብቃቱ በፊት እሳቸው አለ የሚሉትን የአንድ ብሔር ጥላቻ በመቀልበስ በኩል ከመቸውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ተግተው እንዲሠሩ፣ ይህ ካልተሳካላቸው ግን ትግራይ ራሷን የቻለች አገር እንደሆነች ለዓለም በይፋ እንዲያውጁላቸው አበክረው ሲማፀኑ ተሰምተዋል፡፡ በተለይ ይኼኛው ያልታረመ አነጋገራቸውማ የሕወሓት አመራር ከረዥሙ ዕድሜው እንኳ ጨርሶ የማይማርና ‘አድሮ ቃሪያ’ መሆኑ ይበልጥ የተጋለጠበት ሳይሆን አልቀረም፡፡

ለመሆኑ በቁጥር ከ38 የማይበልጡት አባላቱ ይቅርና መላው የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ራሱስ ቢሆን፣ ‘ትግራይ ከፌዴሬሽኑ ተገንጥላ ነፃና ሉዓላዊት አገር ትሁን’ ብሎ የማወጅ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ተሰጥቶታል እንዴ?

እንዲያ ከሆነ እኮ ለ‹ትንታጉ› ብሔርተኛ ማለፊያ ምሥጋና ይግባቸውና በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የሥልጣን አካላት አወቃቀርና የኃላፊነት ድልድል ረገድ ሳናስበው አዲስና ተጨማሪ ዕውቀት ገበየን ማለት ነው፡፡

ከዚህ በተረፈ የአገር ውስጥ ፖለቲካው ክፉኛ የተመሰቃቀለበትና በፍፁም ቀቢፀ ተስፋ ላይ የወደቀው ድርጅት፣ ድንበር ተሻግሮ የትናንት ጌቶቹ የነበሩትን የሻዕቢያን መሪዎች በሰላ ሂስ እስከ ማብጠልጠል የተዳፈረበትንና በተቃራኒው የጎረቤት ኤርትራን ሕዝብ አብዝቶ የተለማመጠበትን ሚስጥር ለአንዳፍታ መመርመር ተገቢ ይሆናል፡፡

አዛውንቶቹ የሕወሓት መሪዎች በተናጠል እየወጡ ሰሞኑን በሰጧቸው ቃለ ምልልሶች የኤርትራ መንግሥት፣ በተለይም ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገብተው እየፈተፈቱ ነው በማለት ሲያማርሩ ሰምተናቸዋል፡፡ ከልባቸው ስለመሆኑ አብዝተን ብንጠራጠርም ከመካከላቸው በዚህ ልክ እጃቸው መርዘሙን እንደሚቀጥል ከታወቀ፣ ሊቆረጥ እንደሚችል ግልጽ ዛቻ እስከ መሰንዘር የደረሱም ይገኙባቸዋል፡፡

በመሠረቱ ሕወሓትን በፀረ ኢትዮጵያዊነት ጠፍጥፎ የሠራውና ያሠለጠነው ሻዕቢያ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የሁለቱን ድርጅቶች ግንኙነት በቅርበት ለተከታተለ ሰው ሻዕቢያ ለሕወሓት የልብ ወዳጁ ባይሆን እንኳ የዘወትር አስጎብዳጁ እንደሆነ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ከዚህ የተነሳ ይህንን አልኩ በማለት ለማስመሰል ካልሆነ በስተቀር፣ ቁንጮውን ኢሳያስ አፈወርቂን ይቅርና በየትኛውም እርከን ላይ የሚገኙ የሻዕቢያ መሪዎችን ያን ያህል ተጋፍቶ የማንጓጠጥ ሀሞት የለውም፡፡

ሕወሓት ከፍጥረቱ ጀምሮ ያደገውና ሽበት እስኪወርሰው ድረስ የጎለመሰው በሻዕቢያ ጉያ ውስጥ ተወሽቆ ነው፡፡ መላውን የመሀል አገር ወገን ከጎኑ አሠልፎ ድባቅ እንደሚመታው እያወቀ እንኳ፣ በኢትዮ ኤርትራ የጦር ሜዳ ፍልሚያ እሱን ፊት ለፊት የመገዳደር አቅምም ሆነ የሥነ ልቦና ጥንካሬ እንደሌለውና እንዳልነበረው፣ በብዙ አጋጣሚዎች አስተውለናል፡፡ በዚያ አሰቃቂና ዓላማ ቢስ ጦርነት ያለ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ትብብርና ድጋፍ ሕወሓት የሻዕቢያን የግፍ ጥቃት በብቃት የመከላከልና የመመከት አቅም እንዳልነበረው ታይቷል፡፡

የዛሬውን አያድርገውና “አማራ አለ በሎ፣ አፋር አለ በሎ፣ ጋምቤላ አለ በሎ …” በማሰኘት እነ እያሱ በርሄን ወደ መድረክ እያወጣ በትግርኛ ቋንቋ ያስጨፍር የነበረበት ኩነት አሁን የሚንቀውና እነጠለዋለሁ የሚለው ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በፍልሚያው አብሮት እንዲሠለፍና የሻዕቢያ ጦር በባድመና በሽራሮ ግንባሮች በኩል ያካሂደው የነበረውን ያንን መጠነ ሰፊ ወረራ ለመቀልበስ ምን ያህል ይለማመጥ እንደነበር ያስታውሰናል፡፡

አምባገነኑ የአገረ ኤርትራ መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ከሁለት አሠርተ ዓመታት በኋላ  በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ አስተዳደር ጋባዥነት አዲስ አበባን በጎበኙበት ወቅት፣ በዕለቱ መድረኩን የተረከበው አሽቃባጭ አስተዋዋቂ ከመደበኛው መስመር ወጥቶ ‘አንዴ ለኢሱ’ እያለ ላንቃው እስኪሰነጠቅ ድረስ እሳቸውን ለመቀበል በሚሊኒየም አዳራሽ የታደመው ኅብረተሰብ ሞቅ ያለ ጭብጨባውን ከዕልልታ ጋር እንዲያስተጋባላቸው አጥብቆ ሲማፀን ይህ ጸሐፊ ታዝቧል፡፡

እንዲህ ያሉትንና ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሳይቀሩ ሰማይ የሰቀሏቸውን ጉልበተኛ መሪ ነው እንግዲህ የቀድሞው የትግራይ አገረ ገዥ በቆየው የትግል ወኔ፣ “በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባታቸውን ከቀጠሉ እጃቸውን እቆርጠዋለሁ፤” ሲሉ የሚዝቱባቸው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1981 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የሕግ ፋኩልቲ ያገኙ ሲሆን፣ በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ ከነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...