Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለአገር የሚሆን ወኔ የት ጠፍቶ?

እነሆ መንገድ። ከሜክሲኮ ወደ ቄራ፡፡ ጎዳናው እያደር ይጠባል። ተጓዥ እርስ በርሱ እየተጠላለፈ ይራኮታል። ባለማወቅ ማፈር ተረስቷል። በጡንቻ መወጠር፣ በትከሻ ስፋት ካልሆነ በቀር ለመከባበር ያለው ፍላጎት ቀዝቅዟል። ለመሆኑ ይኼ መንገድ ትናንት የሄድኩበት ነው ብለው ዘወር ሲሉ የሚያዩት የሚተን ትዝታ ነው። ትናንትና እዚያ ጥግ ቆመን እውነት አውርተናል ብለው የመተከዝ ዕድል ሳይኖርዎ በትንሹ ሦስት አልፎ ሂያጅ ይገጭዎታል። በሐሳቡ ነገር እየበላ የሚራመደው ለይቅርታ ጊዜ ለስሌለው ዘወር ብሎ የሚያይዎት የለም። ባለበት የሚቀጥል ነገር የለም። መንገድ ይሰፋል፣ ይጠባል። ትውልድ ይመጣል፣ ይሄዳል። ገዥ ይወጣል፣ በሌላ ይተካል። ተገዥ አጨብጭቦ የሰቀለውን አሯሩጦ ለማውረድ ፋታ ያለው አይመስልም። ሁሉም ነገር በቅፅበት ይቀያየራል። አገር ግን ያው ባለበት ይኖራል። ከዚህ ቢሸሹ እዚያ መጠጊያ አይጠፋም። ነገር ግን የሚጠጋውም የሚያስጠጋውም ተመሳሳይነትን ዓርማ ለማድረግ ሲሻኮቱ፣ አገር እየተረሳች መንገዱም ይሰለቻል፡፡ ሲሰለች ደግሞ ተስፋ ያስቆርጣል!

በአገር ይሁን እንጂ አልቃሽም ስም አለው። ባይመስልም ልቦና የማይስተው ሀቅ ነው። ባይዋጥልንም ነገር ዓለሙ በለውጥ ጎዳና እያቀዣበረ በትናንት፣ በዛሬና በነገ መሀል ቢያመዳድበንም፣ ባንግባባና ልዩነቶቻችን እያደር ቢሰፉም አገር ዓይንሽ ለአፈር አትባልም። ለዚህም ነው ከትናንት የተራረፈ ተስፋና ሥጋት ይዘን ዛሬም ለብክነት የምንራወጠው። ከመራወጡ መልስ የገባን መስለን እንመሰጣለን። በየፈፋው ቆም እያልን ሐሳብ እናዋጣለን። ያልጠገበ ሆድ እያሸን የእግዜር ሰላምታ በፈገግታ እንለዋወጣለን። ባይዋጥልንም የሚጠላንን ለመውደድ እንጥራለን። ባንጥርም የማንኖረውን ለመስበክ እንሻለን። ምክንያቱም ይህ የእኛ ጎዳና ነው። መገኛውም አገር ነው። መንገድ ጠበበኝ ተብሎ፣ መንገድ ተለወጠብኝ ተብሎ፣ ፀባይና አመል ከፋ ተብሎ አገር አይሸሽም። የማይስማማ ካለ ሌላ ታክሲ መያዝ መብቱ ነው! 

“ታክሲ!” እጮሃለሁ። ወያላው “አስገባው!” ብሎ በሩን ከፈተ። ምናለበት ሌላ ሌላውም እንዲህ ስንጠራው አቤት ቢለን? ምናለበት ብዙ ሳናንኳኳ የተዘጋብን በር ሁሉ እንደዚህ ሚኒባስ በር አሸርግዶ ቢበረገድ? ከዚያ እስከዚህ ድረስ ይኼን ያህል ‹እ. . .ህ. . .ህ. . .› ያሳቀፈን ጥፋት ምንድነው? መንገዱን ጋሬጣ ሞልቶት ለጥሬ ለቀማ ስንቸኩልና ስንደማ መኖራችን ለምንድነው? እዚህ ጎዳና ላይ ሲሆን እግዜር እንደ ፈጠረው ሰው፣ ካልሆነ ደግሞ እንደ ምድር ፍጥረት ለሚኖር ጥያቄው ብዙ ነው። ይኼ መንገድ ይኼ ጎዳና ላይ እንደ ጥሬ የፈሰሰው ጥያቄ የተመለሰ ቀን ነው የዕፎይታ ዲግሪያችንን የምንጭነው። ‹‹አይደለም እንዴ?›› ሲል አንዱ፣ ‹‹አትሄድም? ወይ ግባ ወይ . . .››  ወያላው ተነጫነጨ። ለምን ከጥጋብ በላይ መነጫነጭ ተትረፈረፈ? የሚያውቅ አለ? ‹ዘመኑ የመቃናት ነው› ሲሉን አብረን በአንድ ልብ ‹አዎ ነው!› የማንለው ምን እየታየን ነው? ይኼ መነጫነጭ ነው ወይስ ሀቅ ላይ አተኩሮ ተስፋና እምነትን የመካድ ደካማነት? መንገዱ እንዲህ ያሳስባል። የፀሐዩ ንዳድ የልጅነት ሩጫን አያስታውስም። የጉልምስና ድካምን የሕይወትን ሠልፍ ብዛት የሚጠቁም ቀስት አለው። ከላይ ፀሐዩ እንደ ቀስት ወበቅ ሆኖ ይወርዳል። ከታች እኛ አለን። ሁሌም ሥፍራችን ታች መሆኑ እርግጥ ነው!

ውሉን በማናውቀው የኑሯችን እንቆቅልሽ ብዛት ወደ ላይ ስንጠቁም፣ የላይኛው ደግሞ እየተጠቃቀሰ እርስ በርሱ ይጠቋቆማል። ይህንን እያየን በመጠቋቆም መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮችን አልፈው ወደ ባለፀጋነት የተሸጋገሩ አገሮች ያሉ ይመስሉናል። ወያላው እኔን ይጠቁማል፣ ሾፌሩ ወያላውን፡፡ በዚህ መሀል፣ ‹‹አቦ ዝጋውና እንሂድ በቃ!›› ብሎ ይነጫነጫል። ተሳፋሪዎች ሾፌሩን፣ ‹ለምን አትነዳውም ግን? እናንተም በሥልጣን እንደሚባልግ ሹም ለሕዝብ ግድ የላችሁም። ምን ቢያደርጉዋችሁ ይሻል ይሆን?› ይሉታል። ትዕግሥት እዚች ምድር ተፀንሳ ገና ያልተገላገልናት የስለት ልጃችን ሳትሆን አትቀርም። ተሳፍሬ ወያላው በሩን ሲከረችም ታክሲያችን ከቆመችበት ተንቀሳቀሰች። የሚራመድ እግር ይዘን ስናበቃ መጠባበቅ እያቃተንና መማማር እያቃተን፣ ያለፉን ትርጉም አልባ ዓመታት ነገም ይደገሙ ይሆን? የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና!

 ጨዋታው መሀል ከረፈደ ደርሰናል። ከሾፌሩ ጀርባ አጠገብ ለአጠገብ የተቀመጡ ወጣቶች ያወራሉ። ‹‹ያ ባለፈው ያስተዋወቅኩህ ልጅ እኮ በሜክሲኮ አድርጎ አሜሪካ ገባ!›› ይላል አንደኛው። ‹‹ተው እባክህ? ከሳዑዲ ተመለሰ አላልከኝም እንዴ በቅርቡ? ወይ የሰው ፍጥነት? እንዴት ደስ ይላል በእናትህ!›› ብሥራቱን የሰማው ሲያዳንቅ ‹ነግ በእኔ›  ይመስልበታል። ‹ነገ እኔስ እሱ ማለት አይደለሁ?› ይሉት ዕሳቤ የሚያስጨንቀው ይመስላል። ‹‹እንዴት ያለ ቅን ልጅ መሰለህ በቃ ይኼ አገር አይሆነውም፤›› ሲለው ደግሞ፣ ‹‹አገሩ ለማን ይሆናል? እኛም እኮ እስኪቆርጥልን ነው። በተለይ እኔ ይኼ አሁን የጀመርኩት ሥራ ካልሆነልኝ ጥዬ ስጠፋ ታያለህ እንጂ፣ ዝም ብዬ በጥጋብ የሚንፈላሰሱት ላይ ለማፍጠጥ እጄን አጣጥፌ ችጋር አፍሶ ሲውጠኝ አላይም። ዳናዬም አይገኝ . . .›› ይላል የወዲያኛው። ‹‹ስደት ውሎ ይግባ እንጂ ከድህነት ጋር መርመጥመጥ ታሪክ ይሆናል፤›› ይላል አንዱ። ከጎኔ የተቀመጠ ጎልማሳ፣ ‹‹ጀግኖቹ እናቶቻችንና አባቶቻችን የአውሮፓ ቅኝ ገዥን  ያንበረከኩበትን 124ኛ የዓድዋ ድል እያከበርን እንዲህ ያለ የተስፋ ቢሶች ጉድ እንስማ?›› ሲል እሰማዋለሁ፡፡ እውነቱን እኮ ነው!

በተለይ የሁለቱ ወጣቶች ፊት ላይ የሚታይ ‹አትፍራ!› የሚል ቃል ተጽፎ ተለጥፏል። እነሱ ብቻም አይደሉም አብዛኞቻችን መውደቅ እየፈራን፣ መክሰር እየፈራን፣ መጣር እየፈራን በተቀመጥንበት ቃሉን እያየን እንዳላየን እናልፋለን። ‹‹እኔ የምለው ግን ስንት ከፍሎ ነው የሄደው?›› ያጣራል የነገው የስደት ተስፈኛ። ‹‹ከጀመረው ቢዝነስ ይልቅ ስደቱ ላይ ቢያተኩር አይሻለውም ይኼ ሰውዬ? አስቀድሞ እኮ ሥራው እንደማይሳካ አምኗል፤›› ትለናለች አጠገባችን የተቀመጠች ሽሙንሙን። ‹‹ከሦስት መቶ ሺሕ ብር በላይ ሳይፈጅበት ቀረ?›› ይመልሳል የውስጥ አዋቂው። ‹‹ፓ! አሁን እዚያ ድረስ በሦስት መቶ ሺሕ ብር ከመንጋተት እዚህ ጨመር አድርጎ አንድ ቪትዝ ገዝቶ ራይድ እየሠራ አይኖርም?›› ትላለች አሁንም። ሁሉም ራሱ በቆመበት ማዕዘን ላይ ሌላውን እያቆመ መፍትሔ ላይ መረባረብ ሲገባን፣ ከማቀናጀት መሸሽ ግንባር ቀደም ዕሳቤያችን የሆነ ይመስላል። በአንድነት ተባብረው ዓድዋ ላይ ለማመን ያዳገተ ገድል ያከናወኑ ጀግኖች አፅም የሚፋረደን እየመሰለኝ ነው!

ወያላው ሒሳቡን እንደተቀበለ ወዲያው መልስ እያስረከበ፣ ‹‹ሕግ አልከበር ብሎ ፍትሕ ሲዘገይ አስተማሪነቱና ማስፈራሪያ መሆኑ ያጠራጥራል። ደግሞም ለተመጣጣኝ ጥፋት ተመጣጣኝ ፍርድ ስለማንሰማ ነው እንዲህ የሚዘገንን ወንጀል ሲደጋገም የምናደምጠው። በአጥፊዎች ላይ ለምን አስተማሪ የሚሆን ፍርድ በቶሎ አይሰጥም?›› አላት በየዋህነት የዘመናችን ነገር አብሰልስሎት ይመስላል። ‹‹አትፍረድ ይፈረድብሃል ብያለሁ ዛሬ!›› ሲል ጎልማሳው ጣልቃ ገብቶ ይሰማል። ‹‹መንግሥት እኮ ዳኛ አይደለም፤›› አለው ሾፌሩ ዞሮ ሳያይ። ‹‹እሱን እንኳን ተወው፣ ዳኛ በዕጩነት አቅርቦ የሚያፀድቀው ማን ሆነና?›› ሲሉ ሁለቱ ከፊት የተቀመጡ ወጣቶች ጎልማሳው፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱን አክብራችሁ ተጫወቱ እንጂ?›› ብሎ ለብቻው ሳቀ። ‹‹እሱን ትተን መጀመርያ እንደ ሰው ለመኖር ለምን አንሞክርም?›› ሲለው አንዱ፣ ‹‹ሰው ለመሆን እኮ አገርን ማክበርና መውደድ፣ ለአገራቸው ክብር የተሰውትን ማክበርና መዘከር. . .›› እያለ ሲዘረዝር ዝምታ ሰፈነ፡፡ እውነቱ ሲነገረን ጭጭ ማለትም እኮ ትልቅ ነገር ነው!

ወያላው ይኼኔ አንድ ጥቅስ ጠቆመን። ‹‹አገሩን የሚወድ ወገኑን አያጠቃም›› የሚል። ‹‹አይ እናንተ! አሁን በዚህ ዘመን የምናየው ክፋትና ጭካኔ እውነት ከሰው ይመስላችኋል? አይደለም። ሰው እንዲህ አይጨክንም፣ እርኩስ መንፈስ ካልተዳበለው በቀር፤›› ብለው አዛውንቱ መንፈሳዊ ዕሳቤያቸውን እያብራሩ ካሰጋን ጨዋታ ጎትተው አወጡን። ረዘም ቀጠን የሚል እስካሁን ትንፋሹን ያልሰማነው ሌላ ወጣት፣ ‹‹እውነታቸውን ነው። ዕውን ከሰው ቢሆንማ የገዛ ወገንን መግደል፣ ማሳደድ፣ መዝረፍ፣ ማፈናቀል፣ ኢትዮጵያዊነትን ማጣጣል፣ የጀግንነት ታሪክን ማበሻቀጥ፣ አገር ሰላም መንሳትና የጠላት ተላላኪ መሆን የዘወትር ሥራ ይሆን ነበር?›› አለ ሁላችንንም ከግራ ቀኝ እየቃኘ። አንዳንዱ እኮ መድረክ አጣ እንጂ ይናገረዋል! ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹ኧረ ዘንድሮስ ማፈሪያው በዛ፤›› ይላል ከመጨረሻ ወንበር። ‹‹አንተ ደግሞ ደግመህ እንዳታወራ። ቀፎውን ሳይነኩ ማር ቆረጣ ማን ያቅተዋል ዕድሜ ለጭሱ፤›› ትላለች ወይዘሮዋ። ‹‹ምን ማለት ነው?›› ሲላት ጎልማሳው፣ ‹‹አይ በቃ። እናንተ ደግሞ እንግሊዝኛ ካልተቀላቀለ ቅኔ መፍታት ያቅታችኋል፤›› ትላለች። ‹‹ኧረ ያፈረበትን ይናገር ልጁ። ምንድነው የሰው ማይክ መንጠቅ? ስንቱን ተነጣጥቀን እንችለዋለን? ምናለበት ብንሰማማ?›› ብላ አንዷ ጮኸች። ሰሚ በሌለበት ጩኸት በርክቶ ስንቱ ድምፁ በምድረ በዳ ቀርቷል፡፡

ማፈሪያው በዛ ያለው ነገሩን ቀጠለ፣ ‹‹አማረልኝ ብለው በፌስቡክ ዕርቃናቸውን እየደነሱ ቪዲዮ የሚለቁትን አላያችሁም? ኮሜንቱ ሁሉ ድሮ ሰው ሲያብድ ወደ አማኑኤል ነበር። አሁን ወደ ፌስቡክ ሆኗል እያለ ፕሮፋይሉን ለመክፈት እስኪሳቀቅ ድረስ አፈረ እኮ። ምንድነው ግን እንዲህ እኛና ፌስቡክ ደማችን አልዋሀድ ያለው? በዚያ ስድብ ነው። በዚህ ዕርቃን ነው። ወዲህ በሃይማኖት ወዲያ ለአቅመ ፖለቲካ በማይበቃ ገለባ ሐሳብ ተበጠበጥን እኮ?›› ሲል ጎልማሳው፣ ‹‹እንደ እኔ አካውንትህን ዘግተህ አትገላገልም?›› አለው። ‹‹ተዘግቶስ የት ይኬዳል? በዚያ ሲዘጋ በዚህ የማይዘጉት መስኮት ይከፈታል። እዚያ ዕርቃናቸውን የሚደንሱ አውቆ አበዶች ጉድ ሲያሰኙህ፣ ቢቢሲና ሲኤንኤን ደግሞ ሱፍና ክራቫት የለበሰ ዘናጭ የአሜሪካ ዕብድ ትናንት የሾመውን ዛሬ ሲሽር ያሳዩሃል። የዛሬ ዘመን ዕብዶች ልዩነት በአለባበስና በፖዚሽን ካልሆነ በስተቀር በምን ትለያቸዋህ?›› ብላ ያበጠውን አፍርጣው አረፈች። ዛሬም እንደ አዲስ የጦር ነጋሪት በሚጎሰምባት ዓለም፣ ቀልበ የጠፋው ቀልበ ቢስ መልክ እየቀያየረ ሲያብድ እንዴት ግራ አይገባን? በዚህ መሀል ወያላው ‹መጨረሻ› ብሎን ተራ በተራ ስንወርድ አንዱ፣ ‹‹እኔን ግራ እየገባኝ ያለው ይህ ወፈፍ የሚያደርገው ትውልድ አገሩ ችግር ገጥሟት ድረስልኝ ብትለው፣ ጀርባውን ሰጥቶ ተኝቶ ሊማረክ ነው? ወይስ በአላየሁም በአልሰማሁም እግሩ በመራው ልቡን ጥሎ ሊሰደድ ነው?›› ሲል፣ ያችው ተናጋሪ ደፋር፣ ‹‹አብደሃል እንዴ? ግፋ ወደ ፊት እያለ እንደ ጀግኖቹ ይፋለማል፣ ጀግንነት እኮ ደሙ ውስጥ ነው ያለው፣ ጎራው ና. . . ጎራው ና. . . ›› ስትል ፉከራና ቀረርቶው ቀለጠ፡፡ ምንስ ቢሆን ለአገር የሚሆን ወኔ ይጠፋል እንዴ? መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት