Thursday, July 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ባንክ ለሴቶች ብቻ ከሚሰጠው የቁጠባ አገልግሎት የ47 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ሰበሰበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠቀም ያለ ወለድ እንደሚያስብበት ካስታወቀው የሴቶች የቁጠባ ሒሳብ ከ47 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ማሰባሰቡን ገለጸ፡፡ በሴቶች ሠራተኞች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ሁለተኛውን ቅርንጫ ከፍቷል፡፡

ተሰናባቹ የንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊና በሴቶች ሠራተኞች ብቻ አገልግሎት እንዲሰጥ የተከፈውን ቅርንጫፍ አስመልክተው እንደተናገሩት፣ ሴቶች የተሻለ ወለድ የሚያገኙበትን የቁጠባ አገልግሎት ካስጀመረበት እ.ኤ.አ. ከማርች 2014 ጀምሮ 4.3 ሚሊዮን ሴቶች በቁጠባ አገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ከእነዚህ ተጠቃሚዎች የተሰባሰበው ገንዘብ ከ47 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡

የሴቶችን የፋይናንስና ኢኮኖሚ አቅም ለማጎልበት ታስቦ ለቆጣቢ ሴቶች ከመደበኛው የቁጠባ ሒሳብ ብልጫ ያለው ወለድ የሚያገኙበትና ከባንኩ ጋር ከሚሠሩ አቅራቢዎችና አገልግሎት ሰጪዎች ግብይት ሲፈጽሙም ቅናሽ የሚያገኙበት አገልግሎት እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ሴቶችን ወደ አመራርነትና ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ለማምጣት ባከናወናቸው ሥራዎች አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን አቶ ባጫ ጠቅሰው፣ ንግድ ባንክም የሴቶችን አቅም ለማጎልበት በሚል መነሻ ለሴቶች ብቻ የሚውሉ የፋይናንስ አገልግሎቶችን እያቀረበ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

ባንኩ ለሴቶች የሚያቀርባቸውን የፋይናንስ አገልግሎቶችን ለማስፋፋት ሁለተኛውንና በሴቶች ሠራተኞች ብቻ አገልግሎት የሚሰጠውን ቅርንጫፍ ሥራ አስጀምሯል፡፡ ይህም ለሴቶች ታስበው እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ማሳያ ነው ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም ቦሌ፣ አትላስ ሆቴል አካባቢ የመጀመርያውን የሴቶች ቅርንጫፍ ከፍቶ አገልግሎት በማቅረብ ላይ ሲሆን፣ በልደታ አካባቢ የተከፈተው ቅርንጫፍም ሙሉ ሠራተኞቹ ሴቶች ብቻ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡

አንድ ዓመት በፊት የተከፈተው የቦሌው ቅርንጫፍ ሴቶች ሠራተኞች ብቻ የሚያስተዳድሩት ሲሆን፣ በአንጋፋው የባንክ ባለሙያ አቶ ለይኩን ብርሃኑ መሰየሙ ይታወቃል፡፡

በሴቶች ሠራተኞች ብቻ አገልግሎት የሚሰጠው የባንክ ቅርንጫፉ ደንበኞቹ የሚፈልጉትን አገልግሎት በተቀላጠፈና ምቾታቸው በጠበቀ አኳኋን እንዲያገኙ ከማስቻሉም ባሻገር፣ በተከፈተ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሻለ አፈጻጸም የታየበት ስለመሆኑ ተነግሮታል፡፡ ይህም ሴቶች ለውጥ የማምጣትና የውጤታማነት ብቃታቸው ማሳያ ተደርጓል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች