Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ልማት ባንክ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ያበደረበት የሊዝ ፋይናንስ ችግር ገጥሞታል

ተዛማጅ ፅሁፎች

በርካታ የሊዝ ቅርንጫፎችን ለመዝጋት እንደተገደደ አስታውቋል

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ስለወደፊት ጉዞው ከወዲሁ እያከናወነ ስለሚገኘው እንቅስቃሴና በዓመቱ ስድስት ወራት ውስጥ ስላስመዘገበው ውጤት ከሰሞኑ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ባንኩ ጥያቄ ሲነሳበትና ሲወቀስበት ከነበረው የተበላሸ ብድር ክምችት አዘቅት ውስጥ ለመወጣት እያደረገ ስላለው ጥረት የተብራራበት አግባብ የፕሬዚዳንቱ አቶ ኃይለየሱስ በቀለ መግለጫ አካል ነበር፡፡

በመጪዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ ልማት ባንክ የተበላሸ ብድር ክምችቱን ከ40 በመቶ ወደ 10 በመቶ ዝቅ ለማድረግ እየሠራ ስለመሆኑ ፕሬዚዳንቱ አስታውቋል፡፡ በዘንድሮው  ግማሽ ዓመት የ40 በመቶውን ክምችት ወደ 34 በመቶ ዝቅ ማድረጉ የአራት ዓመታት ጉዞው ማሳያ ሆኗል፡፡

የተበላሸ ብድር ክምችቱ ከፍተኛ ከሆነባቸው ምክንያቶች መካከል ባንኩ ሲከተለው የቆየው የብድር አሰጣጥና አስተዳደር ሥርዓት አንዱ እንደነበር የባንኩ ፕሬዚዳንት ገልጸው ነበር፡፡ የባለሥልጣናት ጣልቃ ገብነትና የሠራተኞች የሥነ ምግባር ችግር ለከፍተኛ የተበላሸ ብድር ክምችት እንደዳረገው ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል፡፡

ባንኩ የተበላሸ ብድር ክምችቱን ለማውረድ በሚያከናውናቸው ሥራዎቹ አማካይነት ውጤት እንደሚያስመዝግብ ገልጾ፣ ጤናማ የሆኑና ዕዳቸውን በአግባቡ ከሚከፍሉ ፕሮጀክቶች የሚሰበስበው ተመላሽ ብድርም እየጨመረ መምጣቱ ተገልጿል፡፡ ወደ ተበላሸ የብድር ዕዳ ማዕቀፍ ውስጥ ገብተው ከነበሩ መካከል እንዲያገግሙ የተደረጉ ፕሮጀክቶች የብድር ዕዳቸውን መመለስ ወደሚችሉበት አቅም እንዲመለሱ እየተደረገ ስለመሆኑም አቶ ኃይለየሱስ ተቅሰዋል፡፡

በአንፃሩ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለእርሻ ሥራ ተበድረው ባለመክፈላቸውና ዕዳቸውን ለማስመለስ ሲሞከር ባስመዘገቧቸው የእርሻ መሬቶች አካባቢ ያልተገኙ ወይም የጠፉ 171 ተበዳሪዎችን፣ በሕግ ለማስጠየቅ እንቅስቃሴ እንደጀመረ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ከዚህ ባሻገር ግን ከሁለት ዓመታት በፊት በልማት ባንክ የተጀመረው የሊዝ ፋይናንስ አገልግሎት ፈተና እንደሆነበት ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሊዝ ፋይናንስ ዙሪያ ፕሬዚዳንቱ በሰጡት ማብራሪያ፣ በብድር መልክ የማሽነሪ ግዥዎችን በመፈጸም በሊዝ ለተጠቃሚዎች የማስተላለፍ አገልግሎት በባንኩ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ የዚህ አገልግሎት ተጠቃዎች በሚገቡት የውል ስምምነት መሠረት ባንኩ ገዝቶ ለሚያቀርብላቸው የማሽን ወጪ፣ በማሽኑ ሠርተው ከሚያገኙት ገቢ ለባንኩ ተመላሽ የሚያደርጉበት አሠራር ነው፡፡

ይህ አገልግሎት ከተጀመረ ሁለት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ እስከ ዘንድሮ ግማሽ ዓመት ድረስም ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ማሽኖች ተገዝተው ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል፡፡ የብድር ማስያዣ ሳይጠየቁ ለተጠቃሚዎች በረዥም ጊዜ የሚከፈል የብድር ስምምነት መሠረት በየጊዜው ክፍያ እንዲፈጸምባቸው ታስበው ማሽሪዎች ሲገዙ ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ አብዛኛዎቹ የሊዝ ፋይናንስ ተበዳሪዎች በአግባቡ ክፍያ እንደማይፈጽሙ ታውቋል፡፡

ልማት ባንክ በሊዝ ፋይናንስ አቅርቦት ለ155 የግብርና ሜካናይዜሽን ድርጅቶች 355 ሚሊዮን ብር፣ በማኑፋክቸሪንግ መስክ ለተሠማሩ 553 ኢንተርፕራይዞች 2.5 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ለሌሎች 97 ተበዳሪዎች 670 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ማሽኖችን ገዝቶ አቅርቧል፡፡

የሊዝ ፋይናንስ ተጠቃሚዎች ዕዳቸውን በአግባቡ መክፈል ባለመቻላቸው ሳቢያ  አገልግሎቱ ወደፊት እንዴት ይቀጥል የሚለው ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ ከጅምሩም ቢሆን አገልግሎቱ ተገቢው ጥናት እንዳልተደረገበት ጠቅሰዋል፡፡ ባንኩ መሸከም ከሚችለው አቅም በላይ እንደሆነበትም አስታውቀዋል፡፡ ይህ በመሆኑ ለሊዝ ፋይናንስ አገልግሎት ተብለው በመላ አገሪቱ ከተከፈቱት ቅርንጫፎች ውስጥ በአብዛኞቹ መዘጋታቸውን አቶ ኃይለየሱስ ተናግረዋል፡፡

በሊዝ ፋይናንስ አማካይነት የማሽን አቅርቦት ሥራ ለመሥራት ባንኩ የገባው ከጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ወደ መካከለኛ ደረጃ ያደጉትን አካላት ለማገዝ ነበር፡፡ ይኸውም የብድር ዋስትና ማቅረብ ለማይችሉ ነገር ግን የተወሰነ የካፒታል አቅም ላላቸው አካላት የማምረቻ መሣሪያዎችን በብድር እየገዛ ባንኩ ቢያቀርብለቸው ውጤታማ ይሆናሉ ከሚል መነሻ ብድር መስጠት ጀምሮ ነበር፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ አምራቾች ለውጭ ገበያ የሚውል ምርት ማቅረብ እንደሚችሉ በመታሰቡ ጭምር በነፃ ማሽን እንዲያገኙና ሠርተው እንዲከፍሉ የሚያችለው የፋይናንስ አገልግሎት ብዙ ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡

‹‹ወደ ሥራው ሲገባና ዓላማው ለማስፈጸም የተቀመጠውን አሁን ላይ ሆነን ስናየው፣ በቂ ዝግጅት እንዳልነበር ማየት ችለናል፡፡ በባንኩ በኩል በቂ ዝግጅት አልተደረገም፡፡ በባለድርሻ አካላት በኩልም በቂ ዝግጅት አልተደረገም፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ እንደ ምሳሌ ያነሱትም የክልሎች የአነስተኛና ጥቃቅን አደረጃጀቶች የብድር አቅርቦት ለማግኘት የተቸገሩትን፣ በጥቃቅንና አነስተኛ መስክ የተሰማሩ ዜጎች አቅማቸውን ምን ያህል እንደሆነ በመፈተሽ የመመልመልና ቦታ የማዘጋጀት ሒደት ላይ በአግባቡ እንዳልሠሩ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ ለዚህ ሥራ ኃላፊነት የተሰጣቸው የክልል ቢሮዎችና የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን አልተወጡም ተብለው ተኮንነዋል፡፡

ይህ በመሆኑ በየክልሉ የተከፈቱ 80 ቅርንጫች ተገልጋይ ማስተናገድ እንዳልቻሉ ተጠቅሷል፡፡ ባንኩ በሁለት ዓመታት ውስጥ ከ80 በላይ ቅርንጫፎች እንዲከፍት ከመገደዱም ባሻገር፣ ልምድ ያላቸውና ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ  ባለሙያዎችን ቀጥሮ ቢያሰማራም ውጤቱ ሲታይ ግን አብዛኛዎቹ ቅርንጫፎች በተገቢው መንገድ ሥራ እየሠሩ እንዳልሆነ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ኃይለየሱስ ገለጻ፣ አንዳንዶቹ ቅርጫፎች ጭራሹኑ ተበዳሪ ባለማስተናገዳቸው በተከፈቱባቸው አካባቢዎች የሊዝ ብድር ፍላጎት እንዳልነበር ያሳያል፡፡ አሊያም ደግሞ ፍላጎቱ ኖሮ፣ ዝግጅቱ እንዳልነበር የሚጠቁም ነው ብለዋል፡፡ በእነዚህ ቅርንጫፎች ውስጥ ስድስት ወይም ሰባት ባለሙያዎችን አሰማርቶ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከሁለት የማይበልጥ ደንበኛ በማስተናገድ ከፍተኛ ወጪ እያወጡ መቆየቱ አዋጭ ስላልሆነ፣ አብዛኛዎቹ ቅርንጫፎች እንዲዘጉ መደረጋቸው ታውቋል፡፡ ‹‹ቅርንጫፎቹን የዘጋነው አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆናቸው ነው፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ወደፊት የሊዝ ብድር ፍላጎቱ ካለ ግን እየታየ እንደሚከፈቱ ጠቅሰዋል፡፡ በሊዝ ፋይናንስ ላይ የሚቀርቡ በርካታ ቅሬታዎች እንዳሉ ይነገራል፡፡ ፕሬዚዳንቱም ቅሬታዎች መኖራቸውን አምነው፣ ቅሬታዎች የሚመነጩት ግን አገልግሎቱን በአግባቡ ካለመረዳት ነው ብለዋል፡፡

ባንኩ የሊዝ ብድር አገልግሎት የሚሰጠው ደንበኛውን ለይቶና አጥንቶ፣ ፍላጎትን መሠረት ባደረገ መልኩ የማሽን ግዥ ይፈጽማል፡፡ ከውጭና ከአገር ውስጥ አምራቾች ወይም አቅራቢዎች ላይ ማሽን ገዝቶ፣ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓቱን ባንኩ ራሱ አጠናቆ፣ ትራንዚተር ቀጥሮና አጓጉዞ የሚያስገባው ልማት ባንክ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ማሽኑ ለደንበኛው ከደረሰ በኋላም ቢሆን ለሥራ የሚተክለውና የሚያዘጋጀውም ባንኩ ነው፡፡ ሥራው በዚህ አያበቃልም፡፡ ማሽኑ ከተተከለ በኋላ እንደገና የሥራ ማስኬጃ ብድር ጥያቄ ለባንኩ ስለሚቀርብለት የተወሳሰበ ሒደት እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ሁሉ ተከናውኖ የጥሬ ዕቃ አቅርቦትና መሰል ችግሮችም የባንኩ ፈተናዎች ናቸው፡፡ የገበያ ትስስር ሌሎችም በርካታ ጉዳዮች ወደ ባንኩ እየተወረወሩ፣ የሊዝ ብድር አገልግሎቱን ፈታኝ እንዳደረጉበት አቶ ኃይለየሱስ ጠቅሰዋል፡፡ በሊዝ ፋይናንንስ ፕሮግራም መሠረት የሥራ መስኬጃ ማቅረብ የሌሎች ባንኮች ኃላፊነት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኃይለየሱስ፣ በተግባር ግን ብድሩን ማቅረብ አልቻሉም ብለዋል፡፡ ባንኮች የሥራ ማስኬጃ ብድር የማቅረብ ፍላጎት የላቸውም፡፡ ለዚህ አገልግሎት ተብሎ የሚሰጡት ፋይናንስ ቢኖርም፣ የሚጠይቁት የብድር ወለድ ከፍተኛ በመሆኑ ልማት ባንክ በተወሰነ ደረጃ ቢሆን የሥራ ማስኬጃ አቅርቦት ላይ እንዲሠራ ተገዷል ይላሉ፡፡

በጠቅላላው በሊዝ ፋይናንስ አገልግሎት እስካሁን 780 ኢንተርፕራይዞች ብድር የወሰዱ ሲሆን፣ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎ ለልዩ ልዩ የማምረቻ መሣሪያዎች ግዥ ውሏል፡፡ የተገዙትን ማሽኖች የተረከቡት ኢንተርፕራይዞችን በሚመለከት ፕሬዚዳንቱ ሲገልጹ፣ ‹‹የተወሰኑት ውጤታማ ሆነው ሥራቸውን እየሠሩና ክፍያቸውን እየከፈሉ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ግን እየተንገዳገዱ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ለዚህ ምክንያት ከሆኑ መካከል የጥሬ ዕቃ አቅርቦት፣ የገበያ ትስስር ችግሮች እንደሚነሱ ገልጸው፣ እንዲህ ያሉትን ችግሮች ግን ባንኩ ብቻውን እየተጋፈጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ በሊዝ አገልግሎቱ ላይ ቅሬታ የሚቀርብበት ዋነኛው ምክንያትም ከአቅሙ በላይ ስለሆነበት በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ማሽን ገዝቶ፣ አጓጉዞ ተክሎና ሥራ አስጀምሮ ማስረከቡን ባለመረዳትና ነገሩን ቀላል ሥራ አድርጎ በማየት የሚቀርቡ አስተያየቶች ናቸው፤›› በማለት በባንኩ ላይ ለሚሰነዘሩ ቅሬታዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹በእኛ እምነት ይህ ሥራ የባንክ ሥራ አይደለም፡፡ ገንዘብ ለማስተዳደርና ገንዘብ ለማቅረብ ከአጋሮቻችን ጋር ልንሠራ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ሳንዘጋጅ መግባት ነበረብን ወይ? የሚለውን አሁን መጠየቅ አለብን፤›› ይላሉ፡፡ ማሽን ገዥ፣ ማሽን አቅራቢና ተካይ እንደገና ደግሞ ሳይከፍሉ ሲቀሩ ማሽኑን ነቅሎ መውሰድ፣ እንደገና ለሌላ ተበዳሪ ማስተላለፍን የሚጠይቅ ሥራ በመሆኑ ጉዳዩን በዝርዝር ተገምግሞ ከታየ በኋላ በባንኩ ድምዳሜ መሠረት ከአቅሙ በላይ ኃላፊነት መሸከሙ ተረጋግጧል፡፡ ‹‹ስለዚህ ይህንን ኃላፊነት የሚጋራ አካል እንዲቋቋም ወይም እኛ ለተወሰነ ጊዜ መቀጠል ካለብን በምን አግባብ እንቀጥል የሚለውን ከባለድርሻ አካላት ጋር ተስማምተን ግልጽ በሆነ ስምምነት እንቀጥል ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

ባንኩ በ2012 ግማሽ ዓመት በጠቅላላው ለ2,520 ፕሮጀክቶች 47.14 ቢሊዮን ብር ብድር ያቀረበ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 48ቱ የውጭ ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ባንኩ ካቀረበው አጠቃላይ ብድር ውስጥ ለውጭ ኩባንያዎች የሰጠው አሥር ቢሊዮን ብር ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች