በአፍሪካ ግዙፉ መስህብና ከዓለም አስደናቂ ፏፏቴዎች ከሚሠለፉት መካከል የሚጠቀሰው ቪክቶሪያ ፏፏቴ፣ ከአኅጉሩ በአራተኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው የዛምቤዚ ወንዝ ዳርቻ የሚገኝ ሲሆን፣ የዚምባቡዌና የዛምቢያ ድንበር መለያ ነው፡፡ አንድ መቶ ሜትር ከፍታና ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው በመሆኑ በዓለም ብቸኛው ግዙፍ ፏፏቴ ያደርገዋል፡፡ የፏፏቴው ድምፅም እስከ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ይሰማል፡፡ በ19ኛው ምዕት ዓመት በተጓዡ ዴቪድ ሌቪንግስተን በእንግሊዝ ንግሥት ቪክቶሪያ ስም የተሰየመ ቢሆንም፣ የአካባቢው ጎሳዎች የሚጠሩት ‹‹ሞሲ ኦ ቱንያ›› (ነጎድጓዳማው ጢስ) በማለት ነው፡፡ ከቪክቶሪያ ፏፏቴ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ሁዋንጌ ብሔራዊ ፓርክ ከዚምባቡዌ መስህቦች ትልቁ ነው፡፡ ፓርኩ በውስጡ ካቀፋቸው የዱር እንስሳት መካከል ‹‹ዘ ቢግ ፋይቭ›› ተብለው የሚታወቁት አንበሳ፣ ዝሆን፣ ቀጭኔ፣ አውራሪስና ጉማሬ ይገኙበታል፡፡ ፎቶዎቹ የፏፏቴውንና የፓርኩን ገጽታዎች ያሳያሉ፡፡