በአሸናፊ ዋቅቶላ (ዶ/ር)
የዓለም ጤና ድርጅት ለአዲሱ የ2019 ኮሮና ቫይረስ በሽታ የካቲት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋዊ ስም አውጥቷል። በዚህም መሠረት በሽታው ኮቪድ-19 ተብሎ ሲጠራ ታዋቂ የጤና ተቋማትና የሕክምና ጆርናሎች ስያሜውን በመቀበል ወዲያውኑ በሥራ ላይ አውለውታል። የቫይረሱ አዲስ ስም ሳርስ–ኮቭ-2 እንዲሆን ተወስኗል።
እንደሚታወቀው ዓለም ጤና ድርጅት ጥር 21 ቀን 2012 ዓ.ም. አዲሱ የ2019 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለም አቀፋዊ አሳሳቢነት ያለው አጣዳፊ የሕዝብ ጤና ሁኔታ እንደሆነ አውጇል። እንደተፈራው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ በሽታ በቻይና ውስጥ ከመስፋፋቱም ሌላ ወደሌሎች የዓለም ክፍሎች በከፍተኛ በፍጥነት ተበትኗል።
በአሁኑ ወቅት የኮቪድ–19 በሽታ ዓለም አቀፍ ወረርሽ ሆኖ ከፍተኛ ሥርጭት እንዳያሳይ ያለው ሥጋት እየጨመረ ነው። ሁኔታውን ለመቆጣጠር ያለው ክፍተት “ጠባብ” እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት ሥራ አስኪያጆች በይፋ እየተናገሩ ነው። ባለፉት ጥቂት ቀናት እንደ አዲስ በሽታው የተረጋገጠባቸው አገሮች ቁጥርና በአንዳንድ ቀድሞ በተዘገበባቸው አገሮች ደግሞ የመስፋፋትና የሞት መጠን በፍጥነት እያደገ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት በፌብሯሪ 28 ቀን 2020 ዓለም አቀፍ የበሽታው መሠራጨት ሥጋት ምደባን ከከፍተኛ ወደ በጣም ከፍተኛ አሳድጎታል።
አንዳንድ በጣም የበለፀጉ አገሮች በሽታው እጅግ የከፋ ለመሆን ከቻለ ለሚያስፈልጋቸው ምላሽ መዘጋጀት መጀመራቸውን በየዜና ማሠራጫው እየለፈፉ ነው። ምንም እንኳን አሜሪካን የመሰሉ ጥቂት አገሮች ለእንደዚህ ዓይነት በሽታዎች ምላሽ ለመስጠት ሲዘጋጁ የቆዩበት ጊዜ በአሠርታት ቢቆጠርም በውስጣቸው በሽታው ቢስፋፋ የመቆጣጠር ችሎታቸው ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሰዎች የሚስማሙበት ጉዳይ አይደለም። ይህን ነገር የጤና መዋቅሮቻቸው ጠንካራ ባልሆኑ በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮች አንፃር ሲታይ ሁኔታው እጅግ በጣም አሳሳቢ እንደሆነ መገመት አያስቸግርም።
በሌላ በኩል ደግሞ በፍጥነት የሚጨምረውን ስለበሽታው ያለውን ዕውቀት የዓለም ጤና ድርጅት፣ የቻይና የበሽታዎች መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል (ሲሲዲሲ)፣ የአውሮፓ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል (ኢሲዲሲ) እና የአሜሪካ የበሽታዎች ቁጥጥርና መከላከያ ማዕከሎች (ሲዲሲ)፣ እንዲሁም ታዋቂ የሕክምና ጆርናሎች መዘገብና ማሠራጨት ላይ እየተረባረቡ ናቸው። በተጨማሪም የበሽታውን ሥርጭት ለመቀነስና ራስን ለመጠበቅ ምክሮች በስፋት እየተሰጡ ነው።
በዚህ እጀግ አሳሳቢና ፈጣን በሆነው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ማናቸውም አገር ሊጠቃ እንደሚችል በማሰብ የሚታወቁትን ዋና ዋና ግኝቶች በድረ ገጻችን አማካይነት ከማድረስ ባሻገር በአማርኛ ቋንቋ መጽሐፎችን አለፍ አለፍ እያልን እናቀርባለን። በዚህ ጽሑፍ ላይ የሚቀርበው ለአጠቃላይ አንባቢና ለጤና ባለሙያዎችም ይጠቅማሉ የተባሉትን ጭምር ነው። ወረርሽኙ እየተስፋፋ ያለው በከፍተኛ ፍጥነት እንደመሆኑ የሚገኘውም መረጃ እንደዚያው በፍጥነት እያደገ መሆኑን መገንዘብ ያሻል። በመሆኑም መረጃዎች በጊዜም እንደሚወሰኑ መታወቅ አለበት።
ስለ ቫይረሱ ምንጭ
የኮሮና ቫይረሶች ብዙ ዓይነቶች ናቸው። ሰዎችንና የተለያዩ እንሰሳትን እንደሚይዙ ይታወቃል። የሰው ልጆች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በጨመሩ ቁጥር በሽታ አምጪ ቫይረሶችን ብዙ ሳይታመሙ ከሚሸከሙ እንስሳት ጋር ይበልጥ ያገናኛቸውና አንዳንዴ ሰዎች በአጋጣሚ ቫይረሶቹን ወስደው ለበሽታዎች ይዳረጋሉ። በተለይ የሌሊት ወፎች በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የኮሮና ቫይረስ ዓይነቶችን ይይዛሉ። ሌሎች የኮሮና ቫይረስ ተሸካሚዎች አሳማዎች፣ ግመሎችና ድመቶችን ሲሆኑ እነኚህ የመሀል ተቀብሎ አስተላላፊ ሚና ይጫወታሉ። በተጨማሪም እንደ ኮሮና ቫይረስ ያሉ አርኤንኤ ቫይረሶች እጅግ በጣም ፈጥነው የሚራቡና በመራባት ራስ ቀጂነት ጊዜ ስህተቶችን እየፈጠሩ በፍጥነት ስለሚለወጡ የበሽታ አምጭነት ፀባዮች በየጊዜው ይፈጥራሉ።
በሰው ልጆች ላይ ጥቃትን የሚያደርሱ የኮሮና ቫይረሶች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ስድስት ብቻ ነበሩ። አራቱ ጉንፋን መሰል ያልጠና የላይኛው ትንፋሻዊ መንገድ የሚያሳምሙ ሲሆኑ፣ በቅርቡ የተነሱት የጠና አጣዳፊ ትንፋሻዊ ቅምረ ሕመም (ሳርስ) እና የመካከለኛ ምሥራቅ ትንፋሻዊ ቅምረ ሕመም (መርስ) የታችኛውን ትንፋሻዊ ክፍል አጥቅተው የሳምባ ምችና አጣዳፊ ትንፋሻዊ መታወክ ቅምረ ሕመም በማድረስ የሞት አደጋ ያስከተሉ ናቸው። ኮቪድ-19 በዲሴምበር 2019 በቻይና ውኃን ከተማ ተቀስቅሶ በዚያው አገር ውስጥ በጥቂት ሳምንታት ከመሠራጨቱ ባሻገር አሁን ከአንታርቲካ በስተቀር በሁሉም ክፍለ ዓለማት ውስጥ ደርሷል። የኮቪድ-19 አስተላላፊ ቫይረስ (ሳርስ–ኮቭ-2) ዋናው ተሸካሚ እንስሳ የሌሊት ወፍ እንደሆነ ይታመናል። ነገር ግን የመሀል ተቀብሎ አስተላላፊ እንሰሳ የትኛው እንደሆነ ገና አይታወቅም።
የኮቪድ-19 ሥርጭት
ዓለም ጤና ድርጅት በኮቪድ-19 ምክንያት በየአገሩ የታመሙ ሰዎችና የሞቱትን ቁጥር ሁኔታ ዘገባዎች ድረ ገጹ ላይ ያሠፍራል።
እስከ ፌብሯሪ 29 ቀን 2020 ድረስ የታማሚ ብዛት በዓለም 85403፣ ቻይና 79394፣ ከቻይና ውጪ 6009 ሲሆን፣ የሞቱ ቁጥር በቻይና 2838፣ ከቻይና ውጪ 86 ናቸው፡፡
በሽታውን መለየት
ሕመሙን በፍጥነት ማወቅ እንዳይዛመት ከመርዳቱ በተጨማሪ ታማሚው ጊዜውን በጠበቀ ሁኔታ የድጋፍ ሕክምናውን እንዲያገኝ ያስችላል። ሁሉንም ታማሚዎች እንደሕመማቸው ዓይነትና ጥናት መመደብና ሕመሙ የተረጋገጠባቸው ወይም የተጠረጠረባቸውን ሰዎች ከሌሎች ታማሚዎች መለየት ያስፈልጋል። በተጨማሪም ተገቢውን የበሽታ ትልልፍ መከላከያና ቁጥጥር መንገዶችን መጠቀም የግድ ነው። የአሜሪካ በሽታዎች መቆጣጠርና መከላከል ማዕከሎች በድረ ገጹ እንዳስቀመጠው የአዲሱ 2019 ኮሮና ቫይረስ ሕመም ዝርዝር የሕክምና መገለጫዎች ገና ስላላዳበሩ ለጊዜው በበሽታው በመያዝ የተጠረጠሩ ሰዎች የሚመረመሩት ለሳርስ ኮሮና ቫይረስና ለመርስ ኮሮና ቫይረስ የወጡትን መስፈርቶች አክሎ በመጠቀም ነው። ትኩሳት አጣዳፊ ትንፋሻዊ ሕመም ያላቸው ሰዎች ሲያጋጥሙ ዝርዝር የጉዞ ታሪክ መወሰድ ይኖርበታል።
ትኩሳት ታማሚው የተሰማው ወይም በምርመራ የተገኘ ሊሆን ይችላል።
የቅርብ ንክኪ የሚባለው ከኮሮና ቫይረስ በሽተኛ ጋር በሁለት ሜትር ርቀት ውስጥ ለረዥም ጊዜ መቆየት፣ ወይም ይረስ ሕመምተኛ በሽታ አስተላላፊ ፈሳሾች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ማድረግ (ለምሳሌ ለታማሚው ሳል መጋለጥ) ሲኖር ነው፡፡
የሕመሙ መገለጫዎች
ስለበሽታው መገለጫዎች እስካሁን ያለው መረጃ ውሱን ሲሆን በአብዛኛው የተገኘው ከጥቂት አነስተኛ የታማሚዎች ቁጥር ካላቸው ጥናቶች ነው።
ሕመም አካሄድ
በሽታው ምንም የሕመም ስሜት የማያሳይ፣ ገራገር ወይም የጠና ሊሆን ይችላል። በዚህም መሠረት የኮቪድ-19 በሽታ መንስዔ ቫይረስ ማለትም ሳርስ–ኮቭ-2 ሰውነታቸው ውስጥ ገብቶ ምንም የሕመም ስሜቶች የማያሳዩ ሰዎች ይኖራሉ ማለት ነው። አብዛኛዎቹ ታማሚዎች የሚኖራቸው በሽታ ገራገር ወይም ያልጠና ነው። የትኞቹ በሽተኞች የጠና ሕመም ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ማወቅ ይጠቅማል።
ላይ በተጠቀሱት ጥናቶች ውስጥ በኮቪድ-19 ሳምባ ምች ሆስፒታል ከተኙት ውስጥ ለሞት የበቁት ቁጥር ከ4 እስከ 15 በመቶ ነበር። በታማሚ ቁጥራቸው ዝቅተኛ በሆኑት በእነዚህ ጥናቶች ውስጥ የሞት አደጋ ከፍ ያለ ሆኖ ቢገኝም በኋላ በቻይና በተለቀቀው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጥናት ውስጥ የሞት አደጋ በመቶ ላይ ከተጠቀሰው ዝቅተኛ ሆኖ ተዘግቧል።
በፌብሯሪ 28 ቀን 2020 በኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦፍ መዲሲን በወጣው ጥናት፣ በሽታው የተረጋገጠባቸው ታማሚዎቹ ቁጥር 1099 ሲሆን የተገኙት ደግሞ ከ552 ሆስፒታሎች ነበር። የጥናቱ ዋነኛ መድረሻ ነጥብ የፅኑ ሕሙማን መቆያ መድረስ፣ በመኪና መተንፈስ ወይም ሞት ነበር። መካከለኛ ዕድሜ 47 ዓመት ሴቶች 41.8 በመቶ፣ ዋነኛ መድረሻ ነጥብ የደረሱ 67 (6.1 በመቶ)፣ ፅኑ ሕሙማን መቆያ የገቡ 5 በመቶ፣ በመኪና መተንፈስ የደረሰባቸው 2 በመቶ የሞቱ 1.4 በመቶ ከጠቅላላው ታማሚዎች ከዱር እንስሳት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የነበራቸው 1.9 በመቶ ሲሆኑ፣ ትኩሳት ወደ ሆስፒታል ሲመጡ 43.8 በመቶ፣ ሆስፒታል ውስጥ ተኝተው 87.7 በመቶ፣ ሳል 67.8 በመቶ፣ ተቅማጥ 3.7 በመቶ፣ ሆስፒታል ሲመጡ የሊምፍ ህዋስ መቀነስ 83.2 በመቶ
ፅኑ ሕሙማን ማቆያ ውስጥ
በውሀን ጂን ዪን ታን ሆስፒታል ውስጥ በኮቪድ-19 ሳምባ ምች ምክንያት ፅኑ ሕሙማን ማቆያ ውስጥ የገቡ ሰዎች ሕክምና አካሄድ ዝርዝር በፌብሯሪ 21 ቀን 2020 በላንሴት ጆርናል ውስጥ ታትሟል። የጥናቱ ጊዜ ከዲሴምበር መጨረሻ ግድም እስከ ጃኗሪ 26 ሲሆን የጠቅላላው ታማሚዎች ቁጥር ታማሚዎች ቁጥር 710 ነበር።
ፅኑ ታማሚዎች 52፣ የፅኑ ታማሚዎች አማካይ ዕድሜ 59.7 ዓመት ወንዶች 35 (67 በመቶ)፣ ሥር ሰደድ በሽታዎች ያሏቸው 21 (40 በመቶ)፣ ትኩሳት 51 (98 በመቶ)፣ አጣዳፊ ትንፋሻዊ መታወክ ቅምረ ሕመም 35 (67 በመቶ) ናቸው፡፡
የላቦራቶሪ ግኝቶች
በኮቪድ-19 የሳምባ ምች ታማሚዎች ሆስፒታል በሚገቡበት ጊዜ የሚታዩ ዋና ዋና የላቦራቶሪ ግኝቶች የነጭ የደም ሕዋሶች ቁጥር ማነስ፣ የነጭ የደም ሕዋሶች ቁጥር መጨመር፣ የሊይምፍ ሕዋሳት ቁጥር መቀነስ፣ የትራንሳሚኔዞች ከፍ ማለትን ይይዛሉ።
ሕክምና
የኮቪድ-19 ሕክምና በሆስፒታል ውስጥ መሰጠት ያለበት ባየር ተላላፊ በሽታ ማግለያ ክፍል ውስጥ ነው። ለታማሚዎች እንክብካቤ በሚደረግበት ወቅት መደበኛ ጥንቃቄዎች፣ የአየር ትልልፍ ጥንቃቄዎች፣ የንክኪ ጥንቃቄዎችና የዓይን ጥንቃቄዎች መደረግ አለባቸው። ዋናው ሕክምና ድጋፍ ሰጪ ሕክምና ሲሆን ኦክሲጅን፣ የፈሳሽና ኤሌክትሮላይት ማስተካከል፣ ለሕመምና ለትኩሳት መድኃኒት መስጠት፣ እንዳስፈላጊነቱ ቱቦ ማስገባትና የመኪና መተንፈሻን መጠቀም፣ ሴፕሲስ ከተጠረጠረ የፀረ ባክቴሪያ ሕክምና መስጠትን ይጨምራል። የተዘረዘሩት ቁሳቁሶችና የተግባራቱ ልምዶች ብዙ ታዳጊ አገሮች ውስጥ ውስን በመሆናቸው ምክንያት ሊመጣ የሚችለውን ነገር መገመት አይከብድም።
ኮርቲ ኮስቲሮይድስ
ምንም እንኳ የኮቪድ–19 በሽታ ሰውነትን ከሚጎዳበት ዋነኛ መንገዶች አንዱ ከቁጥጥር ያለፈ ብግነትን መፍጠር ቢሆንም ኮርቲኮስቲሮይድስ ፀረ ብግነቶች በኮቪድ-19 ራሱ በተያያዘ ሳምባ ምች ሕክምና ጥቅም አልተገኘባቸውም።
ፀረ ቫይረሶች
በአሁኑ ጊዜ ለኮቪድ-19 የሚሆኑ ፀረ ቫይረስ መድኃኒቶች የሉም። የአሜሪካ ብሔራዊ ጤና ተቋም ስለታቀዱት የመድኃኒት ጥናቶች ድረ ገጹ ላይ አሥፍሯል። በዚህም መሠረት ዕጩ መድኃኒቶች ረምደሰቪር (በእንሰሳት ማሳያ ላይ የፀረ ኮሮና ቫይረስ ተስፋ ያሳየ)፣ ሎፒናቪር ሪቶናቪር (ፀረ ኤች አይቪ) እና ሌሎች ሰፋ ያለ የድርጊት አቅም ያላቸውን መድኃኒቶች ለማጥናት ታቅዷል።
ለበሽታው ይበልጥ አስጊ ሁኔታዎች
በተለያዩ ጥናቶች የተዘገበው የዕድሜ መግፋትና የተጓዳኝ በሽታዎችና ሁኔታዎች መኖር ለበሽታው መጥናትና ሞት ይበልጥ እንደሚያጋልጡ ነው።
ልጆችና ኮቪድ-19
እስከ ጃንዋሪ 22 ቀን 2020 ክትትል በተደረገባቸው 425 ሕሙማን ውስጥ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት የሆኑ ልጆች አልነበሩም። በሌሎች ጥናቶች ውስጥ ኋላ እንደታየውም በልጆች ላይ የሚደርሰው የበሽታ መያዝ አነስተኛ ነው። ለዚህ ምክንያቱ በአሁኑ ጊዜ ግልጽ አይደለም።
በእርጉዝ ሴቶችና ኮቪድ–19
ላንሴት ፌብሯሪ 12 ቀን 2020 እትም ላይ በዘጠኝ እርጉዝ ሴቶች ላይ የተደረገውን ጥናት ውጤት አቅርቧል።
የጥናቱ ወቅት ከጃኗሪ 20 ቀን እስከ ጃኗሪ 31 ቀን 2020 ድረስ ሲሆን ዘጠኙም የወለዱት በቀዶ ሕክምና (ሲዘሪያን ሴክሽን) ነበር። የተገኙባቸው ትኩሳት 7፣ ሳል 4፣ ጡንቻ ሕመም 3፣ የሕመም ስሜት 2፣ የፅንስ መታወክ 2፣ የፅንስ መታወክ-2፣ የሊምፍ ሕዋስ መቀነስ 5፣ የትራንሳሚኔዝ መጨመር 3፣ የሳምባምች 0፣ ሞት 0፣ ሕያው አራስ ልጆች 9 ነበሩ። ከተለያዩ ቦታዎች ለሳርስ ኮቭ-2 የተደረጉ ምርመራዎች (አምኒዮታዊ ፈሳሽ፣ እምብርት ገመድ ደም፣ የአራስ ልጅ ጉሮሮ፣ የጡት ወተት) 6 (ሁሉም ነፃ) በዚህም መሠረት ይህ ትንሽ ጥናት የሚያሳየው በእርግዝናና በወሊድ ጊዜ ቫይረሱ ከእናት ወደ ፅንስና ልጅ እንዳልተላለፈ ነው።
የቻይና ግዙፍ መረጃ
በቅርቡ ከቻይና የተለቀቀው ግዙፍ መረጃ ስለበሽታው ያለውን ዕውቀት አዳብሮታል። በዚህም መሠረት በሽታው ከያዛቸው ላይ ምን ያህሉ የጠና እንደሚሆንባቸውና ልጆች በብዛት እንደማይጠቁ ታውቋል። በትናንሽ ጥናቶች እንደታየው በዕድሜ የገፉና ተጓዳኝ ሕመሞች ያላቸው ሰዎች ይበልጥ ለጠና በሽታ እንደሚዳረጉ ተደርሶበታል። ቢሆንም ስለበሽታው ገና ያልታወቁ ዝርዝሮች መኖራቸው ይታመናል።
በታማሚ ቁጥሩ መጠኑ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጥናት በቻይና የተለቀቀው በፌብሯሪ 11 ቀን 2020 ነበር። የተጠኑ የሕሙማን ሕክምና ዘገባዎች 72314፣ በሽታ የተረጋገጡባቸው 44672 (61.8 በመቶ)፣ የተጠረጠሩ 16186 (22.4 በመቶ) ሲሆን፣ ያለላቦራቶሪ ምርመራ የተገመቱ 10576 (14.6 በመቶ)፣ የሕመም ስሜትና ምልክት ያላሳዩ 889 (1.2 በመቶ)፣ በሽታው ከተረጋገጠባቸው ውስጥ 30 እስከ 79 ዓመት (86.6 በመቶ)፣ ሞቱ 1023 (2.3 በመቶ)፣ የታመሙ የጤና ባለሙያዎች 1716፣ የሞቱ የጤና ባለሙያዎች 5 (0.3 በመቶ)፣ ሲሆኑ፣ በበሽታው መያዝ በዕድሜ፣ 50 እና ከ50 በላይ (ከ50 በመቶ በላይ)፣ 30 እስከ 49፣ 15,000 ግድም (36 በመቶ)፣ 0-19 ከ1000 በታች (2 በመቶ) ናቸው፡፡ ፆታና ከጾታ አንፃር ሲታይ ወንዶች 51.4 በመቶ፣ ሴቶች 48.6 በመቶ፣ የሞት አደጋ ወንዶች 2.8 በመቶ ሴቶች 1.7 በመቶ አማካይ 2.3 በመቶ ሆኗል፡፡ የበሽታው መጥናት መጠን ገር 80 በመቶ፣ የጠና 14 በመቶ፣ የሞት ሽረት 5 በመቶ፡፡
የበሽታው ትልልፍ
የኮርቪድ-19 ትልልፍ እስካሁን በደምብ አልተጣራም። ስለጉዳዩ አብዛኛዎቹ ሐሳቦች የመነጩት ከሌሎቹ የጠኑ የኮሮና ቫይረስ ትልልፍ ዕውቀት ነው። ትልልፉ ሊመጣ የሚችልባቸው መንገዶች ብዙ ናቸው። የበሽታው መገለጫዎች ከመምጣታቸው በፊት፣ በሽታው ከሚታይባቸው፣ ከበሽታው ከዳኑ፣ የበሽታውን ምንም ምልክት ከማያሳዩ፣ በአጠቃላይ ሲታይ የቫይረስ ትልልፎች ይበልጥ የሚካሄዱት ይበልጥ ከታመሙ ሰዎች ነው። ከዚህ ውጪ ያሉትን መተላለፊያ መንገዶች ማወቅና መመጠን አስቸጋሪ ነው።
በቁሳቁስ ላይ የመቆየት ችሎታ ውሱን ስለሆነ ከቻይና ወይም ሌላ የተጠቃ አገር የመጣ ዕቃና ጥቅል በሽታውን ያስተላልፋል ተብሎ አይጠበቅም። ቢሆንም ቫይረሱ በዕቃዎች ላይ ከሰዓቶች እስከ ጥቂት ቀናት ሊቆይ ስለሚችል በቤት ውስጥና ከቤት ውጪ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
መከላከያ ጭንብል
የአሜሪካ በሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከሎች (ሲዲሲ) የትንፋሻዊ ሕመሞችን ለመከላከል ሁሉም ሰዎች ጭንብሎችን እንዲጠቀሙ አይመክርም። ጭምብሎችን መጠቀም ያለባቸው የትንፋሻዊ ሥርዓት ታማሚዎች፣ እነሱን የሚንከባከቡ ሰዎችና የጤና ባለሙያዎች ናቸው።
የዓለም ጤና ድርጅት ስለጭምብሎች አጠቃቀም ማስተማሪያ ገጽ አውጥቷል።
- ጤነኛ ሰው ጭንብል የሚያስፈልገው ታማሚ ሰውን የሚከባከብ ከሆነ ነው።
- በማሳልና በማስነጠስ ጊዜ ጭንብል መጠቀም ነው።
- ጭንብል ይበልጥ የሚጠቅመው ቶሎ ቶሎ እጆችን ከማፅዳት (አልኮል ላይ የተመሠረተ እጆች ማበሻ ወይም ውኃና ሳሙና) ጋር ነው።
- ጭንብሉን ከማሰር በፊት እጆችን መታጠብ ያስፈልጋል።
- አፍንጫና አፍ ሙሉ ለሙሉ መሸፈን አለባቸው።
- ጭንብሉን ጀመጠቀም ጊዜ በእጆች እንዳይነካ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ድንገት ከተነካ እጆችን ማፅዳት (አልኮል ላይ የተመሠረተ እጆች ማበሻ ወይም ውኃና ሳሙና) ነው።
ጭንብሉን ለማውለቅ የሚፈታው ከኋላ ነው። የፊት ለፊቱ ክፍል መነካት የለበትም። ወዲያውኑ በሚዘጋ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ተጥሎ እጆችን ማፅዳት (አልኮል ላይ የተመሠረተ እጆች ማበሻ ወይም ውኃና ሳሙና) ያስፈልጋል።
የአየር ጉዞ
የኮርቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ የአገሮቻቸው እንዳይገባ ወደ ቻይና የሚደርጉትን በረራዎች የገደቡ አገሮች አሉ። ሌሎች ደግሞ እስካሁን ድረስ ያለምንም ገደብ ወደ ቻይናና ከቻይና የአየር ትራንስፖርታቸውን ቀጥለዋል። በየአውሮፕላን ጣቢያ የሰውነት ሙቀት መለካት ጥቅሙ አከራካሪ ነው።
የክትባቶችና የፀረ ቫይረስ መድኃኒቶች ሙከራዎች
የአሜሪካ ብሔራዊ ጤና ተቋም ለኮቪድ-19 መከላከያ ክትባቶች ለማግኘት ሥራ እንደጀመረና ከጥቂት ወራት በኋላ ሙከራዎች እንደሚጀምር ገልጿል። ይኸው ስለታቀዱት የፀረ ቫይረስ መድኃኒት ጥናቶች ላይ በተጠቀሰው ድረ ገጹ ላይ አሥፍሯል። በዚህም መሠረት ዕጩ መድኃኒቶች ረምደሰቪር (በእንሰሳት ማሳያ ላይ የፀረ ኮሮናቫይረስ ተስፋ ያሳየ)፣ ሎፒናቪር ሪቶናቪር (ፀረ– ኤቻይቪ) እና ሌሎች ሰፋ ያለ የድርጊት አቅም ያላቸውን መድኃኒቶች ለማጥናት ታቅዷል።
የዓለም ዝግጅት
በአገሮች ውስጥ ሊደርሱ የሚችሉት የኮቪድ-19 ሥርጭት አደጋዎች ይገመታሉ። እነኚህ የሚደረጉት በማሳያ ጥናቶች ነው። ለምሳሌ በላንሴት የሕክምና ጆርናል ውስጥ በፌብሯሪ 20 ቀን 2020 በወጣው ጥናት ውስጥ በአፍሪካ አገሮች ያለውን ሁኔታ በሽታውን ከማስገባት ዕድልና ከመቆጣጠር ብቃት ጋር በማነፃፀር ምደባ አድርጓል። ወደ አገር የማስገባት ዕድሉ ከፍ ያለና የመቆጣጠር ብቃት ዝቅ ያለ ከሆነ የሥርጭት አደጋው ይበልጥ ከፍ ይላል ማለት ነው።
አሁንም ቢሆን መደረግ ያለበት ሁሉም አገሮች ተባብረው ይህንን ወረርሽኝ ማቆም ነው። ይህ ካልሆነ በዓለም ሰዎች ላይ በተለይም በደሃ አገሮች ሕዝቦች ላይ እጅግ የከፋ አደጋ ሊደርስ ይችላል። ከሁሉም አስፈሪው በሰዎች ላይ የሚደርስ የሕመምና የሞት አደጋ ሲሆን የሚከተሉት ሌሎች ውስብስቦች በሽታውን ይበልጥ እንዲስፋፋ ከማድረጋቸው በተጨማሪ የተዳከሙ የጤና መዋቅሮችን ይበልጥ መዳከም፣ ወትሮኑ የተዛቡና ያልተመጣጠኑ ኢኮኖሚዎችን ይበልጥ ማዳከምና ከዚህ ጋር የተያያዙ ሌሎች መዘዞች እንዲፈጠሩ ያደርጋል። የኑሮ ውድነት ይበልጥ ሲባባስ እጅግ ብዙ ሕዝቦች የባሰ ሁኔታ ውስጥ ይገባሉ።
ባለፉት ጥቂት አሠርታት ውስጥ አዲስ ብቅ እያሉ ወይም እንደገና እየተነሱ ከፍተኛ ክልላዊና ሉላዊ ሥርጭቶችን ያሳዩ በሽታዎችን ለመቆጣጠር የዓለም ጤና ድርጅት፣ ድንበር የለሽ የዶክተሮች ማኅበር (ኤምኤስኤፍ)፣ የበሽታዎች መመከላከያ ማዕከሎች (ሲዲሲ) እና ሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ከፍተኛ ሥራዎችን ሠርተዋል፣ አሁንም እየሠሩ ናቸው። እነኚህ ድርጅቶችና በየአገሩ ያሉ የጤና ባለሙያዎች አንዳንዴ ሕይወትን የሚያስከፍል እጅግ ከፍተኛ መስዋዕትነቶች ቢከፍሉና እየከፈሉ ቢሆንም በተደጋጋሚ ለሚከሰቱት በሽታዎች ዓለም ዝግጁ አለመሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ከዚህ በፊት ተደጋግሞ እንደሚሰማው፣ ነገር ግን በቂ ዕርምጃ የማይታይበት የዓለም ዝግጁነት ጉዳይ ሊተኮርበት ይገባል።
ያለንበት አጣዳፊ ሁኔታ የሚጠይቀው ሁሉም አገሮች ተባብረው የጊዜውን አደጋ ማቆም ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር ባይኖርም እያንዳንዱ አገር ለዘለቄታው ያለውን ዝግጁነት ማጠናከሩ ምርጫ የሌለው ጉዳይ ነው። ይህ ጉዳይ በጤና ዘርፈ ልማት የሚወሰን ስላልሆነ ሁሉም እንዲያነሳው ጊዜው ያሳስባል። በዚህ ጸሐፊ ግምት ዋናው ችግር የዕውቀትና የግንዛቤ አይደለም። ሁሉም ሰው የማያየው ግዙፉ ነገር በዓለም ላይ የተንሰራፋው በትርፍ ላይ የተመሠረተ የኢኮኖሚና ሶሻል ሥርዓት ነው። የአብዛኛው ዓለም የጤና መዋቅራዊ ብቃት ደካማ ሆኖ ዘላቂ የጤና ደኅንነት መጠበቅ የዋህነት ነው። አስቸኳይ ነገር በመጣ ጊዜ መጣደፍ ብቻ ያዘለው ከፍተኛ አደጋ በአንዱ ወረርሽኝ ጊዜ የነገሮች ከቁጥጥር ውጪ መውጣት መፈጠር መቻሉ ነው። ይህ እጅግ በጣም አሳሳቢ የኮቪድ–19 በሽታ የመጨረሻው አይሆንም። የሰው ልጅ ወደፊት በተሻለ መዘጋጀት ካልቻለ ቫይረሶችን ከመሰሉ ጠላቶች ጋር ያለውን ግብግብ በአሸናፊነት ላይወጣ ይችላል።
አዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡