Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለካስ በአካል ብንለያይም በመንፈስ አንድ ነን?

ሰላም! ሰላም! እንዴት ይዞናል? መቼም አንዴ ሲያመጣው አይጣል ነው? በዚህ በኩል ታላቁን የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ድል ለማክበርና በዓድዋ ተራሮች ክቡር ሕይወታቸውን በአገር ፍቅር ወኔ ለመስዋዕትነት የሰጡትን ለመዘከር ስንራወጥ፣ በሌላ በኩል ነፃነታችንንና ሰብዓዊ ክብራችንን የሚያዋርድ መግለጫ ከወደ አሜሪካ ሲሰማ ደማችን ምን ያህል በቁጣ እንደተንተከተከ ለእናንተ አልነግርም፡፡ መቼም ከራሳች አልፈን ለዓለም ጭቁን ሕዝቦች ጭምር ቤዛ የሆንበትን ታሪክ ስንዘክር ደስ ይላል። የዓድዋ ድል እኮ ራሱን የቻለ የሚሊኒየማችን ተዓምራዊ ድል ነው አትሉም እንዴ? ይህንን እንደ ፈርጥ የሚያበራ ድላችን ላይ ቀዝቃዛ ውኃ ሲቸለስበት ያበሳጨናል። በእውነቱ ልብ የሚያደማ ሐዘን ተሰምቶኛል። ነገር ግን ኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ ውስጣዊ መቃቃራቸውን ወደ ጎን ብለው፣ በአገራቸው መብትና ነፃነት ላይ አንደራደርም ሲሉ ስሰማቸው ውስጤ በሐሴት ተሞላ፡፡ ‹‹ድሮስ እርስ በርስ እንነጃጀስ እንደሆነ ነው እንጂ የቁርጡ ቀን ሲመጣ እኮ አንበሶች ነን. . .›› ሲሉኝ የነበሩት አዛውንቱ ባሻዬ ሲሆኑ ምሁሩ ልጃቸው ደግሞ፣ ‹‹ለጠላት ቀዳዳ እየከፈትን እንጂ ማን ደፍሮ ይህንን አድርጉ፣ ያንን አታድርጉ ይለን ነበር. . .›› እያለ ተንተከተከ፡፡ ለማንኛውም እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ኢትዮጵያዊያን ቅኔ ናቸው የሚባለው አባባል ይስማማኛል፡፡ ቅኔ ውስጡ በሰምና በወርቅ የተለበጠ እንደሆነ በደመነፍስ ስለሚገባኝ፡፡ ‹‹የምናውቀው ባይኖር የሚያውቁ እናውቃለን›› ነው ነገሩ!

ባሻዬ በወገናችን መተባበር ምክንያት ፍንደቃዬን ዓይተው፣ ‹‹ልጅ አንበርብር!›› ሲሉኝ ‹‹አቤት?›› ስላቸው፣ ‹‹እንዲያው የዘመኑ ነገር አንዱ ጥሬ ሌላው ብስል እየሆነ እንጂ፣ የአገር ጉዳይ ሲነሳ አመሥጋኝም ተመሥጋኝም መኖር አልነበረበትም. . .›› ሲሉኝ የመብሰል ፀጋ ታላቅ መሆኑ ገባኝ፡፡ መብሰል ማለት ማረር ወይም መንገርገብ ሳይሆን፣ ከደጅም ከውስጥም ተመጣጥኖ ማደግ መሆኑን የነገረኝ ምሁሩ ልጃቸው ነው፡፡ እኔም አካባቢዬን ሳስተውል በለብለብ ትምህርት ሳይሆን ዕድሜ የገራቸው ጭምቶችንና አስተዋዮችን የሚስተካከላቸው እንደሌለ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ‹‹ከአያያዝ ይቀደዳል ከአነጋገር ይፈረዳል›› እንዲሉ፣ ከባለ ዲግሪዎቹ ይልቅ ባለ ድግሮቹ በማስተዋል ውስጥ ያካበቱት ዕውቀት እንኳንስ ለኢትዮጵያ ለአፍሪካና ለተቀረው ዓለም እንደሚተርፍ ከሽምግልና ሥርዓቶቻችን እስከ የነገር ብልት አዋቂዎቻችን ድረስ ያለውን ብልኃትና ጥበብ ሳስብ እደመማለሁ፡፡ መማር በማስተዋል ካልታጀበ ፋይዳ ቢስ መሆኑን መቼም ለእናንተ ማስረዳት አይጠበቅብኝም፡፡ ያለ በለዚያማ እኔም ልሂቃኑ ከሚባሉት ተርታ ተሠልፌ ማወናበዴ ነው፡፡ ዞር አወናባጅ ማለትስ አሁን ነው!

እንግዲህ ማስተዋልን ምርኩዝ አድርጌ ስለዕውቀት ሳነሳ አካሄዴን መቼም መጠርጠር ትችላላችሁ። ጠርጥሩ ግድየለም። የዘመኑ ሰዎች እኮ ሲፈጥረን አነጣጥረን በመሳት፣ አጉል ጠርጥረን ከወዳጅ በመጣላት የተካንን ነን። አለ አይደል ስናነጣጥር አብዛኛውን ጊዜ ቀስታችን ዒላማውን ከመምታት ይልቅ እግራችን ሥር ይወድቃል። እስኪ ጎንበስ በሉና እግራችሁ ሥር ተመልከቱ። ይኼንን ሁሉ ጥልፍልፍ ጎዳና በምን የተነሳ ይመስላችኋል የቆምንበት? እግራችን ሥር በወደቁ ቀስቶች ምክንያት እኮ ነው። ይልቅ ቀስቶቹን ምን አከሸፋቸው በሉ። ለሦስት ሺሕ ዘመናት ተብሎ ተብሎ የጠነዛ ለጆሮ የሰለቸ ቃል ልደግምባችሁ ነው። ቃሉም ‘ምቀኝነት’ ይባላል። ለጠላቶቻችን በቀላሉ ዒላማ ሆነን እርስ በርስ ስንጠዛጠዝ፣ በነገር ፍላፃ ስንወጋጋ፣ አገራችንን ከማንም በላይ በሀብት ማማ ላይ ማቆም ሲገባን ድህነት ውስጥ ስንዘፍቃት፣ የኋላቀርነትና የማይምነት አረንቋ ውስጥ ስንከታት፣ ሕዝባችንን የአምባገነኖች መጫወቻ ስናደርግ፣ ዘለዓለም ለማንኖርበት ሥልጣን ስንገዳደልና ስንሳደድ፣ ይህም አልበቃ ብሎ የባዕዳን መሳቂያ መሆናችን ያሳፍራል፡፡ የቁርጡ ቀን አንድ መሆን እየቻልን ምን ይሆን የሚያባላን ልክፍት ከተባለ በጠላቶቻችን የተዘራብን መቅሰፍት ነው መልሱ፡፡ መልሱን ካወቅን እስኪ ልብ እንግዛ!  

ሌላው ችግራችን በቅጡ ያልተረዳነው የመርሳት በሽታ ይመስለኛል፡፡ ታሪካችን በብዙ መዛግብት ታጭቆ ሲነገረን ዛሬ ሰምተን ነገ እንረሳዋለን፡፡ ትናንት የተግባባንበትን መልሰን እንሽረዋለን፡፡ እስቲ እንደ ግለሰብ እሺ ይሁን ጠዋት ያቀድነው ግድየለም ሰው ነንና ከቀትር በኋላ ይረሳ እንበል። ኮሞዲኖ ላይ ያስቀመጥነውን ዕቃ ምናልባት የት እንዳስቀመጥነው ረስተን አልጋ ሥር እንፈልግ ይሆናል። ግን እንዴት አገራችንና ማንነታችን ይረሳል? እንዴት ተፈጥሯዊ ሰብዕናችን ይዘነጋል? እውነቱን እንነጋገርና አያት ቅድመ አያቶቻችን ተከባብረው እንዳልኖሩ፣ መሀላችን ምን ቢገባ ነው እንዲህ የምንሰዳደበው? የመከባበር ባህላችን እንዴት ቢረሳ ነው ኢትዮጵያዊ ወገናችንን ፍፁም ባልተገራ አንደበት እየተሳደብን ራሳችንን የምናዋርደው? መርሳት በሽታ እንደሆነ ያመንኩት የዘመናችን ሰዎች እንደ ዕብድ ሲሰዳደቡ ነው፡፡ ጠላቶቻችን ውስጣችን የቀበሩት የጊዜ ፈንጂ እንዳይፈነዳና አዘቅት ውስጥ እንዳንገባ፣ እኛ ኢትዮጵያዊያን የታሪክ አደራ እንዳለብን እናስታውስ፡፡ እኔ ደላላ እንጂ የሥነ ልቦና ባለሙያ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን አስተዋዮች የሚናገሩትን ቁምነገር ሳዳምጥ አንዱ ችግራችን ይኼ ስለመሰለኝ ነው፡፡ እኔም የአገሬ ጉዳይ ይዞኝ ሥራዬን ረስቼ ከደንበኛዬ ጋር የያዝኩት ቀጠሮ ሰዓቱ አለፈ። የኑሮ ዘመን ሰዓት እላፊ ቢጀመር እኮ፣ ከምቀኝነትና ከስም አጥፊነታችን ጋር ባለንበት ባትሪው እንዳለቀ ስልክ ሲጥ ብለን የምንቀረው እኛ ነበርን። ወይ ነዶ አለ የአገሬ ሰው!

ከመጪው ምርጫና ሒደቱ፣ ከአሠላለፋችንና ከድብቁ ፍላጎታችን በስተጀርባ በአገርኛነትና በዓለም አቀፋዊነት መሀል የጠፋብንን ነገር ደግሞ ላጫውታችሁ። በቅርቡ ከአንድ ዳያስፖራ ወዳጄ ጋር በጋራ የጀመርነውን ሥራ በተመለከተ ወደ ሆላንድ ተጉዤ ነበር። እናም ከዋና ከተማው አምስተርዳም እሱ ወደ ሚኖርበት ኡትረክት ወደሚባል ከተማ፣ ደግሞም ወደ አገር ቤት የሚጫነው ዕቃ ፈር ወደሚይዝበት ሮተርዳም ከተማ ለመመላለስ ባቡርና አውቶቡስ አላዋጣን አለ። መቼም ደቾች ነገረ ሥራቸው ሁሉ ሽክፍ ያለ ነው። ማንም ከየትም አገር ቢመጣ እዚህ አገራቸው እንደ አዲስ መንጃ ፈቃድ ካላወጣ መኪና አያስነዱም። ለአጭር ጊዜ የሄደ ጎብኚ ግን ምናልባት በድጋፍ ደብዳቤ መኪና ተከራይቶ ሳይቻል አይቀርም መባልን ስሰማ ወደ አንዱ ቀበሌ ሄድኩ። ስጠይቅ እስኪ መንጃ ፈቃድህን አምጣ አሉኝ። ጎሽ ብዬ በኩራት ላጥ አድርጌ አወጣሁት። ድንቄም ኩራት። የሚያስተናግደኝ ነጭ ትኩር ብሎ አንዴ እኔን አንዴ መንጃ ፈቃዱን እያየ፣ ‹‹ምንድነው?›› አለኝ። ‹‹ምኑ ነው ምንድን?›› ስለው ማንበብ እንዳልቻለ አሳየኝ። ተቀብዬ ሳየው ተውት ሌላውን ስሜ እንኳን በእንግሊዝኛ አልተጻፈም። የሚያበቃበት ጊዜ 2012 ዓ.ም. ይላል። በማርስ፣ በጁፒተር፣ በመሬት፣ በቻይና ወይም በአውሮፓ አቆጣጠር እንደሆነ የሚታወቅ ነገር የለም። ነገሩን ረጋ ብዬ ሳጤን ሌላ ጣጣ ራሴ ላይ ላመጣ እንደሆነ ገብቶኝ ግድ የለም ተወው ብዬ ወጥቼ ተፈተለኩ። ብቻ ከቀበሌያቸው ራቅ ማለቴን አስተውዬ የሆነ ሥፍራ አረፍ ስል መናደድም፣ ማዘንም፣ መናዘዝም አቃተኝ። የቸርቻሪ ሱቅ ሳይቀር በእንግሊዝኛ መጠሪያ የንግድ ፈቃድ በሚታደልባት አገሬ፣ መታወቂያና መንጃ ፈቃዳችን ላይ ግን አትዩን አትስሙን ዓይነት ቋንቋ አጠቃቀማችን አበሸቀኝ። ሥራችን ሁሉ ሱሪ በአንገት እየሆነ እግራችንን በየሄደበት ሁሉ የሚጠላለፈው እስከ መቼ ይሆን? ይህም ደረቅ ሀቅ ነውና እንዋጠው አይደል!

እንግዲህ የእኛን ነገር አስረግጦ ለሚያውቀው ከኑሮ ውድነት በላይ አላፈናፍን ያለን፣ ሙስና የሚባል ስም የተሰጠው የአገር ዘረፋ እንደሆነ ይታወቃል። እናም ሁሌም የሚያስገርመኝን ‘ለምን ቢያንስ በብዙ ጉዳዮች ሁላችንም እኩል ደስ አይለንም?’ ብዬ ያገኘሁትን አንድ ሰው ስጠይቅ፣ ‹‹ኧረ እባክህ ተወኝ። ዝም ብለህ ስታስበው ከመቼ ወዲህ ነው እንዲያ ያለ ነገር በእውነተኛና በሀቀኛ የአገር ባላደራነት ሠርተን የምናውቀው? ኧረ ተወኝ ሆድ ይፍጀው ነው የሚባል!›› እያለ ሰውየው ነገሩን ሲያወሳስብብኝ ዝም አልኩት። ታዲያ እኔን የማይገባኝ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ይኼ ውስብስብ ባህሪያችን ነው። ደስታችንና ሐዘናችን በየት፣ እንዴት እንደሆነ የማንታወቅ ማለት እኮ በቃ ምን አለፋችሁ እኛ ነን። ‹‹የእኛ ሰው ያለ ሰበብ እንዲህ ነገር አያላምጥም። ሞኝ አትሁን እባክህ?›› ስትለኝ ማንጠግቦሽ፣ ‹‹እንዴት?›› አልኳት። ‹‹ምን እንዴት አለው? እዚህ አገር ሁሉም ሥራ ሁሉም ጀብዱ ሰሞነኛ ነው። ዘመቻ! ዘመቻ! ዘመቻ! የአንድ ሰሞን የእናት አገር ጥሪ ነገ ካልቀጠለ ምን ዋጋ አለው አርባ ጊዜ ባያነበንቡ?›› አለችኝ። ታዲያ ነገሩ ሲበዛብኝ አቋሜ ሁሉ ላላ። በዚህ ቀውጢ ኑሮ ላይ ደግሞ አገር በነገር ተለውሳ ስትጨመርበት ማሰብ ይከብዳል። ለማንኛውም ‘የወሬ የለውም ፍሬ’ ስለሆነ ከአሉባልታው ፈቀቅ እንበል። በአሉባልታ ልማትና ብልፅግና የሚመጣ ቢሆን ኖሮ፣ ኢትዮጵያ አገራችን የኃያላን አውራ መባሏን የሚጠራጠር አይኖርም። አሁንም ‘ያልጠረጠረ ተመነጠረ’ ካላላችሁ በቀር!

በሉ እንሰነባበት። ወደ አገር ቤት ተመልሼ እዚህ የነበሩኝ ጉዳዮች ጨራርሼ ያልተቀበልኳቸውን ኮሚሽኖች ተቀባብዬ ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር አንድ አንድ ለማለት ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ተያይዘን ሄድን። ስለጉዞዬ እየጠየቀኝ ድንገት ያ የቋንቋና የመታወቂያ ነገር ትዝ ብሎኝ በትዝብት ነገርኩት። እሱም ነገሩ ደንቆት፣ ‹‹በእርግጥ ይኼን አስቦ ለመሥራት ይከብዳል፤›› አለኝና ትንሽ ቆይቶ ቀና ሲል የግሮሰሪያችን ስም ታየው። ‹‹ፈን ግሮሰሪ›› ጮክ ብሎ አነበበው። ‹‹አሁን ከእኔና ከአንተ መታወቂያና መንጃ ፈቃድ ወይም ከዚህ ግሮሰሪ ስያሜ የትኛው ነው ዓለም አቀፋዊ መሆን የነበረበት?›› እያለ መብከንከን ሲጀምር፣ የግሮሰሪያችን ታዳሚዎች በወሬያችን ጣልቃ እየገቡ አንድ አንድ ማለት ጀመሩ። ያው እንደምታውቁት ጣልቃ ገቦች በበዙበት በዚህ ዘመን የእኛም ጉዳይ ጣልቃ ገብ ቢጋብዝ አይደንቅም፡፡ እስኪ አስቡት በትዳራችን መሀል ቤተሰብ ጣልቃ ሲገባ፣ በጓደኛሞች መሀል ጣልቃ ገቢው ሲበራከት እያየን በአገራችን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብነት ያማራቸው ሲከቡን ደማችን ቢፈላም ብልኃት ሊኖረን ይገባል፡፡ ይህ ብልኃት ኅብረታችንን ስለሚጠይቅ ነቃ ብንል ምን ይለናል!

ግሮሰሪ እንደገባን አንዱ፣ ‹‹ለስሙ ነው እንጂ አገር አገር ብለን አክርረን የሞትነው፣ በሞታችን ማግሥት የሚፈነጭበት ያው ሥቃያችን ነው፤›› ብሎ ገጠመ። ‹‹ድንቄም ሥቃይ? አሁን ከዚህ ወዲያ ምን ትፈልጋለህ? ታሪክ የዓለም አውራ ብሎ ሲመሰክርልን በጎን የሚገዳደሩን አሉ፡፡ ይህ ዕድላችን ቢሆንም ተባብረን ከተጋፈጥነው የማይወጣ አቀበት የማይደረመስ ገደል የለም፤›› ይላል ሌላው። በዚህ መሀል ከዳር በኩል የሚያስገመግም ድምፅ ተሰማ፡፡ ተንጠራርተን ስናይ አንድ ትልቅ ሰው ጠረጴዛውን መታ መታ እያደረጉ፣ ‹‹እነሱም ይላሉ ተኩሰን አንስትም፣ እኛም እንላለን ቃታ አናስከፍትም፣ እንዲህ ተባብለን የተገናኘን ለት ተሰብሰብ አሞራ እንድትበላ ጉበት ተብሎ እንደሚፎከር የማያውቅ አለ እንዴ?›› ብለው ሲጠይቁ፣ አንዱ እመር ብሎ ተነስቶ፣ ‹‹ደረስንባቸው ሳይታጠቁ እንደ ዝንጀሮ ፀሐይ ሲሞቁ ሲባልም እናውቃለን፤›› አላቸው፡፡ ቀዩ፣ ጠይሙ፣ ጥቁሩ፣ ረጅሙ፣ አጭሩ፣ ከሲታው፣ ወዛሙ፣ ምስኪኑ፣ ደፋሩ፣ ሳቂታው፣ ኮስታራው፣ ሁሉም በየዓይነቱ ከዳር እስከ ዳር የሆዱን በሆዱ ይዞ በሰዎቹ ምልልስ ሲያውካካ ከጦርነት ድል አድርጎ የሚመለስ ዘማች ይመስል ነበር፡፡ በሐሳብ ብንለያይም በአገራችን ጉዳይ አንድ ነን የሚል መፈክር የሚያስተጋባ ድል አድራጊ ሠራዊት ይመስል፣ ግሮሰሪዋ ‹‹ጉሮ ወሸባዬ!›› ሲባልባት እኔና የባሻዬ ልጅ በስሜት ተውጠን ስናጨበጭብ ሰዓቱ ነጎደ፡፡ ለካ በአካል ብንለያይም በመንፈስ አንድ ነን? መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት