በየካ ተራራ ለዓመታት ተጠብቆ የኖረ የደን ይዞታ ውስጥ የሪል ስቴት ኩባንያ ግንባታ እንዲያካሂድ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፈቃድ ማግኘቱን በመግለጽ፣ በ40 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ደን ጭፍጨፋ እየተካሄደ እንደሚገኝ የአካባቢው ነዋሪዎች አቤቱታ አሰሙ፡፡
በየካ ተራራ ልዩ ቦታው ላምበረት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የወረዳ አምስትና ዘጠኝ ነዋሪ የሆኑ ግለሰቦች እንደገለጹት፣ ለሪል ስቴት ልማት ተብሎ የተሰጠው ቦታ ከዚህ ቀደም ለአረንጓዴ ሥፍራነት ተከልሎ ነበር፡፡ ከዚህ በፊት ጥያቄ ቀርቦ ቦታው ለሪል ስቴት መዋል እንደሌለበት በመታመኑ ግንባታ ሳይካሄድ መቆየቱን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ፡፡
የደኑ ይዞታ እስከ 40 ዓመታት ያስቆጠሩ እንደ አጋም ያሉ ዛፎች የሚገኙበት እንደሆነ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ሚዳቋን የመሳሰሉ እንስሳት ይታዩበት የነበረ ጫካ ነው ያሉት የአካባቢው ነዋሪ አቶ ሻምበል እዘዘው፣ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ ቦታው ለሪል ስቴት ሲጠየቅ እየተከለከለ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
ሆኖም ከጥቂት ቀናት ወዲህ በደኑ ይዞታ ውስጥ አጥር ማጠር እንደተጀመረና ከ17 ያላነሱ ሕጋዊ ይዞታ ያላቸው ነዋሪዎችም ከቦታቸው እንዲነሱ መጠየቃቸውን፣ አንዳንዶቹም በሕጋዊ መንገድ ከእነ ካርታው የገዙትን ይዞታ ቤት እንዳይገነቡበት ዕግድ እየወጣባቸው መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡ ካርታም ሆነ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ እያላቸው፣ በላያቸው ላይ ለሪል ስቴት ኩባንያው ተደራቢ ካርታ መሰጠቱ ግራ እንዳጋባቸው በመግለጽ ለመንግሥት አቤቱታ እያሰሙ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
በአካባቢው ከዚህ ቀደም ትልልቅ ሕንፃዎች መገንባት እንደማይቻል ተጠንቶ እንደነበር፣ ከተራራማነቱ የተነሳ የግል ቤት ለሚገነቡ ከሁለት ፎቅ በላይ እንዳይሠሩ ሲከለከል ቢቆይም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትልልቅ ከፍታ ያላቸው ሆቴሎች እየተገነቡ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ያስረዳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ደን እየተመነጠረ ግንባታ እንዲካሄድ የሚደረገው እንቅስቃሴ ወትሮውንም ለጎርፍ የተጋለጠውን አካባቢ ለአደጋ የሚዳርግ፣ በክረምት ወራትም በርካታ ነዋሪዎችን ሥጋት ላይ የሚጥል በመሆኑ መንግሥት በአጽንኦት እንዲመለከተው ነዋሪዎች ጠይቀዋል፡፡
ከይዞታቸው እንደሚነሱና በቤታቸው አጥር ላይም ቀይ ምልክት እየተደረገ መሆኑ አግባብ እንዳልሆነ የገለጹ ነዋሪዎች፣ መንግሥት የሚከተለው አሠራር ግራ እንዳጋባቸው ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በከተማ አስተዳደሩ እየተተገበረ ያለው የመሬት ልማት ፕላን አሠራር የተዘበራረቀ መሆኑንና ተራራ አናት ላይ ሪል ስቴት እንዲለማበት መፍቀዱ አንዱ ማሳያ ነው ያሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ ከ300 በላይ ነዋሪዎች የተፈራረሙበት ሰነድ ከሦስት ወራት በፊት ለመንግሥት በማስገባትና ለፍርድ ቤት በማቅረብ ጭምር በካርታ ላይ ካርታ ማውጣት ተገቢ እንዳልሆነ በማስዳኘት ዕግድ ቢያስወጡም፣ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተጥሶ ግንባታ እንዲካሄድ መፈቀዱን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም የከተማው ከንቲባ ጽሕፈት ቤትም ሆነ በተዋረድ የሚገኙ የከተማው አስተዳደር አካላት ችግሩን ተመልክተው እልባት እንዲሰጡበት አሳስበዋል፡፡
ነዋሪዎቹ እንዲህ ያሉትን አቤቱታዎች ቢያሰሙም የብርሃን ጎሕ ሪል ስቴት ባለንብረት የሆኑት ወ/ሮ ፀሐይ ቦጋለ በበኩላቸው፣ ቦታው ለልማት የተሰጣቸው ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሆነና ሕጋዊ ይዞታቸው በመሆኑ ለማልማት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተሰጣቸው 40 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የደን ጭፍጨፋ እንዳልፈጸሙ፣ ይልቁንም በአብዛኛው የባህር ዛፍ ብቻ እየመረጡ እንዳስነሱ ሞግተዋል፡፡ አብዛኞቹ ተከራካሪዎቻቸው ሕጋዊ እንዳልሆኑ፣ ይልቁንም አንዳንዶቹ ከጥቂት ቀናት በፊት ካርታ ሲሰጣቸው እንደታዘቡ ጠቁመዋል፡፡ ምንም እንኳ ነዋሪዎቹ ካርታ እንዳላቸው ቢገልጹም፣ በየካ ክፍለ ከተማ በኩል የሚደረግ አግባብነት የጎደለው አሠራር ነው ሲሉም ወቅሰዋል፡፡
ነዋሪዎቹ በበኩላቸው ከአካባቢው ማኅበሰረብ ጋር ተግባብቶና ተስማምቶ መሥራት ሲቻል፣ ደን መመንጠርና የዜጎችን የመኖር መብት መጋፋት አግባብ እንዳልሆነ ጠቁመው፣ ልማቱ ይፈለጋል ከተባለም የጥቂቶችን ህልውና ከመጋፋት ይልቅ በተሰጣቸው ቦታ ብቻ ተወስነው ሊሠሩ ይገባ ነበር ብለዋል፡፡ የሪል ስቴት ኩባንያው ከተሰጠው ወሰን አልፎ እንደመጣባቸው ቢገልጹም፣ ወ/ሮ ፀሐይ በበኩላቸው ነዋሪዎቹ በድርጅታቸው ይዞታ ውስጥ እንደገቡባቸውና አንዳንዶቹም ቦታውን በመሸጥ ጭምር ጣልቃ እንደገቡባቸው ተከራክረዋል፡፡ ለሪል ስቴት ልማቱ የከተማ አስተዳደሩ ሙሉ ድጋፍና ዕውቅና እንደሰጣቸው አስታውቀዋል፡፡
በሁለቱ ወገኖች መካከል የተነሳውን ውዝግብ ለማጣራት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ፣ በዚህ ተቋም ሥር ለሚገኘው የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ፣ ለከንቲባው ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት፣ እንዲሁም ለየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ጥያቄዎችን በማቅረብ የአስተዳደሩን አስተያየቶች ለማካተት የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ የተገኙት ምላሾችም ኃላፊዎች ሥልጠና ላይ ናቸው የሚሉ ሲሆኑ፣ አንዳንዶቹም በመጪው ሳምንት ከጽሕፈት ቤታቸው መረጃ ማግኘት እንደሚቻል የሚገልጽ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በስልክም ሆነ በአጭር ጽሑፍ ጥያቄ የቀረበላቸው ኃላፊዎች ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ12 ዓመታት በፊት የተመሠረተው የየካ ተራራ ጎረቤታሞች ማኅበር ራሱን እንደ አዲስ በማደራጀትና የየካ ተራራ ነዋሪዎች ማኅበር በሚል የተሻሻለ ስያሜ በመዋቀር፣ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን በጋራ ለመፍታትና በአካባቢው የልማት ሥራዎች ላይ መንቀሳቀስ ስለሚችልባቸው ጉዳዮች ስብሰባ በመጥራት ተወያይቷል፡፡
ማኅበሩን በቦርድ ሰብሳቢነት የሚመሩት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ሲሆኑ፣ ወ/ሮ መሠረት ዘውዱ ምክትል ሰብሳቢ ናቸው፡፡ ማኅበሩ በመንገድ ሥራ፣ በትምህርት ቤት ግንባታና በመሳሰሉት ማኅበራዊ ፋይዳ ባላቸው ተግባራት በመሳተፍ የአካባቢውን ነዋሪዎች ችግር ለመቅረፍ እንደሚንቀሳቀስ ወ/ሮ መሠረት አስረድተዋል፡፡