Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየግብፅ ድብቅ ፍላጎት የዓባይ ውኃን መቆጣጠር እንደሆነ የመንግሥት ግምገማ አመለከተ

የግብፅ ድብቅ ፍላጎት የዓባይ ውኃን መቆጣጠር እንደሆነ የመንግሥት ግምገማ አመለከተ

ቀን:

ግብፅ በህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቅ ላይ የሚደረገውን ድርድር አስታካ፣ የዓባይ ውኃን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር እያሴረች መሆኑን መንግሥት ያደረገው ግምገማ አመለከተ፡፡

የግድቡን ውኃ አሞላልና አለቃቅን በተመለከተ የግድቡ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በምታቀርበው የሙሌት ስትራቴጂ ላይ ተመሥርቶ የታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች ከሆኑት ከግብፅና ከሱዳን ጋር በትብብርና በጋራ ተጠቃሚነት መንፈስ በመደራደር ስምምነት ላይ መድረስ ሲገባ፣ ግብፅ በኢትዮጵያ የቀረበውን የሙሌትና የአለቃቀቅ ፕሮፖዛል ሙሉ በሙሉ ሊቀይሩ የሚችሉና በዓባይ ውኃ ላይ ለዘመናት የቆየውን የበላይነት ለማስቀጠል ጥረት እያደረገች መሆኑን መንግሥት በግምገማው አመልክቷል፡፡

ግምገማውን አስመልክቶ ለሪፖርተር መረጃ የሰጡ አንድ ከፍተኛ ባለሙያ፣ ግብፅ የህዳሴ ግድቡ የመጀመርያ ምዕራፍ የውኃ ሙሌት ከተካሄደ በኋላ ሁለተኛውና ዋናው የውኃ ሙሌት ሊከናወን የሚገባው፣ በጥቁር ዓባይ የውኃ ተፋሰስ ላይ የሚኖሩ ኃይድሮሎጂካዊ ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ ተጠንተው መሆን አለበት የሚል ሐሳብ ማቅረቧን ጠቁመዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በተጨማሪም ከመጀመርያው ሙሌት በኋላ የሚቀጥለው ምዕራፍ ሙሌት መከናወን የሚገባው ኢትዮጵያ የጥቁር ዓባይን አማካይ ተፈጥሯዊ የውኃ ፍሰት ለታችኞቹ አገሮች እየለቀቀች መሆን እንደሚገባው ሐሳብ ማቅረቧን፣ ይህም አንዱ የልዩነት ምንጭ መሆኑን ባለሙያው አስረድተዋል፡፡

 ከላይ የተነሱትን የግብፅ ሐሳቦች አስመልክቶ በኢትዮጵያ በኩል በተደረገው ግምገማ፣ የግድቡ የውኃ ሙሌት ግብፅን እያስፈቀዱ እንዲከናወን የሚያስገድድ ነው፡፡ የጥቁር ዓባይ ውኃ ተፈጥሯዊ ፍሰት የሚባል ነገር በአሁኑ ወቅት እንደሌለ የገለጹት ባለሙያው፣ በጥቁር ዓባይ ተፋሰስ ላይ የፊንጫና የጣና በለስ ኃይል ማመንጫ ግድቦች መገንባታቸውን፣ እንዲሁም ህዳሴ ግድብ ደግሞ በዚሁ ተፋሰስ ላይ እየተገነባ የሚገኝ መሆኑን በምክንያትነት ያወሳሉ፡፡

በመሆኑም የጥቁር ዓባይ ተፈጥሯዊ ፍሰትን እንዲጠበቅ መጠየቅ ማለት፣ ግብፅ ለእነዚህ ግድቦች ዕውቅና እንደማትሰጥ አመላካች መሆኑ እንደ ተገመገመ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ሁለተኛው ምዕራፍ ሙሌት ከመጀመሩ አስቀድሞ የጥቁር ዓባይ ኃይድሮሎጂካዊ ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ መጠናት እንዳለባቸው፣ በየሦስት ዓመቱም በጥቁር ዓባይ ውኃ ፍሰት ላይ ኦዲት መደረግ እንዳለበት በግብፅ መነሳቱን የተናገሩት ባለሙያው፣ ይህ ማለት ኢትዮጵያ በራሷ ሉዓላዊ ግዛት ላይ ለምታከናውነው ፕሮጀክት የግብፅን ይሁንታ እንድትጠይቅ የሚያስገድድ ነጥብ በመሆኑ ተቀባይነት እንደማይኖረው መገምገሙን ገልጸዋል፡፡

 በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና የግብፅ የአስዋን ግድብ የውኃ መጠናቸው በከፍተኛ ደረጃ ከቀነሰ፣ አንደኛው ግድብ ሌላኛውን ግድብ መደገፍ እንዳለበት ግብፅ መጠየቋን የጠቆሙት ባለሙያው ይህ አገላለጽ ግልጽ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

‹‹የግብፅ አስዋን ግድብ በከፍተኛ ደረጃ ከቀነሰ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ውኃ በመልቀቅ ድጋፍ እንዲያደርግ ከሆነ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ግድቦች የውኃ መጠናቸው በቀነሰበት ሁኔታ አንደኛው ግድብ ሌላኛውን ያግዛል ማለት ግልጽ እንዳልሆነና ሆን ተብሎ ለማደናገር እንዲቀመጥ ግብፆች መፈለጋቸውን ያሳያል፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ነጥብ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ እንደሆነ ያነሱት ባለሙያው፣ በጥንቃቄ ጉድለት ይህንን የግብፅ ሐሳብ መቀበል ግብፅ ከህዳሴ ግድቡ በላይ ያሉ የኢትዮጵያ ግድቦችም በድርቅ ወቅት ውኃ እንዲለቁ መብት የሚሰጣት ሊሆን እንደሚችል ከግንዛቤ ውስጥ መግባቱን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የህዳሴ ግድቡ የረዥም ጊዜ የውኃ አስተዳደርን (Long-Term Operation) የተመለከተ ድርድር እንዲደረግ በግብፅ በኩል የቀረበው ሐሳብ፣ ሌሎቹን የዓባይ ተፋሰስ አገሮችን በማግለል የዓባይ ውኃ ክፍፍል በሦስቱ አገሮች መካከል እንዲደረግ ውጤት የሚኖረውና ኢትዮጵያ በሌሎቹ አገሮች ላይ ክህደት እንድትፈጽም የሚያደርግ በመሆኑ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በአጠቃላይ የግብፅ ፍላጎት ሲታይ በዓባይ ውኃ ላይ የያዘችውን የበላይነት ማጠናከር፣ ኢትዮጵያን ስምምነት ውስጥ በማስገባት በጥቁር ዓባይ ላይ የተሠሩትንም ሆነ ወደፊት የሚሠሩትን ፕሮጀክቶች በግብፅ ፈቃድ እንዲከናወኑ የማድረግና የኢትዮጵያን ወንዝ የመቆጣጠር ውጤት እንደሚያስከትል በመንግሥት መገምገሙን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ የራሷን ፕሮፖዛል (ምክረ ሐሳብ) ይዛ ከታችኞቹ አገሮች ጋር በትክክለኛ ሉዓላዊነት መርህ ድርድር እንምታደርግ ገልጸዋል፡፡ የአሜሪካ የገንዘብ ተቋም ኃላፊ በቅርቡ በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ ስምምነት እንዳይደረስ እንቅፋት እንደሆነች አድርገው የወቀሱ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሜሪካ ሦስቱ አገሮች ስምምነት ላይ እንዲደረስ ድጋፍ ማድረግ ላይ ብቻ እንድትወስንና ይህንንም በገለልተኝነት መርህ እንድትፈጽም ጠይቋል፡፡

በተመሳሳይ የዓረብ ሊግ አገሮች በዚህ ሳምንት የግብፅን ፍላጎት በመደገፍ ያወጡትን መግለጫ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማውገዝ፣ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ሉዓላዊ ህልውና ያላቸው በመሆኑ የዓረብ ሊግ ይህንን መብታቸውን ማክበርና በእነሱ በኩል ያለውን ምክንያታዊ እውነታዎች ማገናዘብ ሲገባው፣ የያዘው አቋም ተገቢና የሊጉ አባል አገሮች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያላገናዘበ መሆኑን አስታውቋል፡፡

አሜሪካም ሆነች የዓረብ ሊግ አባል አገሮች ለኢትዮጵያ የልማት ሥራዎች የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ አጋሮች በመሆናቸው የህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ ከግብፅ ጋር የተፈጠረው ውጥረት ኢትዮጵያ ከእነሱ ድጋፍ እንዳታገኝ ወደ መከልከል ሊያደርሳቸው እንደሚችል በኢትዮጵያ ልሂቃን በኩል በሥጋት ደረጃ ይነሳል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ሰሞኑን የገዥው ፓርቲ (ብልፅግና) አመራሮች በፓርቲያቸው ፕሮግራምና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሲያደርጉት የነበረውን ውይይት ባለፈው ሳምንት ሲያጠናቅቁ የተገኙት የፓርቲው ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ ካነሷቸው ጉዳዮች አንዱ የህዳሴ ግድቡን የተመለከተ ነበር፡፡

 በዚህ ንግግራቸውም፣ ‹‹ከውጭ ለምናገኘው ሀብት ብለን አገራዊ ክብራችንን አሳልፈን አንሰጥም፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹ባለፈው ነገር ሳንቆጭና የያዝነውን ሳንለቅ ግድቡን አጠናቀን የሕዝባችንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንሠራለን፡፡ የሌሎች አገሮችን ጥቅም በማይጋፋ መንገድ ጥቅም ላይ እናውለዋለን፤›› ብለዋል፡፡

 አሜሪካ በኢትዮጵያ የተጀመሩ የኢኮኖሚ ሪፎርሞችን ለመደገፍ አምስት ቢሊዮን ዶላር ብድር ልታቀርብ እንደሆነ የውጭ ሚዲያዎች የገንዘብ ሚኒስትሩን አቶ አህመድ ሽዴን፣ እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ የተዘጋጀውንና ከወራት በፊት ሥራ የጀመረውን ፋይናንሺያል ዴቨሎፕመንት ኤጀንሲ ኃላፊ በመጥቀስ መዘገባቸው ይታወሳል፡፡

ይህ ኤጀንሲ ‹‹Build Act›› ተብሎ በሚታወቀው እ.ኤ.አ. በ2019 በወጣ የአሜሪካ ሕግ የተቋቋመ ሲሆን፣ የኤጀንሲው ማቋቋሚያ ምክንያት የአሜሪካን የውጭ ፖሊሲ ለማስፈጸም እንደሆነ የሕጉ ምዕራፍ ሁለት ላይ የተቀመጠው ዓላማ በግልጽ ያስረዳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...