Saturday, June 22, 2024

የውጭ ተፅዕኖን በብቃት መመከት የሚቻለው ውስጣዊ ስምምነት በመፍጠር ብቻ ነው!

ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ምክንያት ከመቼውም ጊዜ በላይ የውጭ ተፅዕኖ ተጋርጦባታል፡፡ ከአምስት ወራት በኋላ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ሊጋብዝ የሚችል ምርጫ ታካሂዳለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በኮረና ቫይረስ ምክንያት የዓለም ኢኮኖሚ እየተቀዛቀዘ በመሆኑ ግንባር ቀደም ተጠቂ ልትሆን ትችላለች፡፡ በውጭ ዕርዳታና ብድር ላይ የተንጠላጠለው ኢኮኖሚ በበቂ መጠን ሥራ መፍጠር ካልቻለ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች ዕጣ ፈንታ ያሳስባል፡፡ በአጠቃላይ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚስተዋሉ ችግሮች ላይ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጉልህ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ክስተቶች ቢያጋጥሙ በማለት በከፍተኛ ጥንቃቄ መራመድ ተገቢ ነው፡፡ በተለይ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ከአጉል ብሽሽቅ፣ ትችትና ከማይመስል የፖለቲካ ነጥብ አስቆጣሪነት በመውጣት የመርህ ሰው ቢሆኑ ይመረጣል፡፡ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር ገጽታውን ቀይሮ አደገኛ ምዕራፍ ውስጥ ሲገባ ለምን አሜሪካ ገባችበት ብሎ ከማላዘን፣ ከችግሩ ውስጥ እንዴት መውጣት እንደሚቻል መፍትሔ ማመላከት የተሻለ አቅም ይገነባል፡፡ የተሳሳተን መውቀስ ቀድሞ የነበረና ወደፊትም የሚቀጥል ቢሆንም፣ ከወዲያኛው ወገን በኩል ሊኖር የሚችል ምክንያትን አውቆ ስህተትን ለማረም መረባረብ ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ነገር ከሥልጣንና ከጥቅም የበላይነት ጋር ብቻ እየተቆራኘ የአገር ጉዳይ ሲዘነጋ፣ ለውጭ ተፅዕኖ በቀላሉ መንበርከክ ይከተላል፡፡ ለዚህም ሲባል ነው በጋራ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ልዩነትን ይዞ ስምምነት መፍጠር አስፈላጊ የሚሆነው፡፡

የዓለም የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች የሚዘወሩት ስትራቴጂካዊ ጥቅምን ታሳቢ በማድረግ መሆኑ ለማንም የሚሳት አይደለም፡፡ ከኃያላን አገሮች ጋር የሚደረግ ግንኙነት ከፍተኛ ብልኃትና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ስለሆነ፣ ችግር ማጋጠሙ እየታወቀም ቢሆን ሙከራ መደረጉ ግን አይቀርም፡፡ ከልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ጋር በህዳሴው ግድብ የገባንበት ሆድና ጀርባ የሚያደርግ ወቅታዊ ችግር፣ ትዕግሥትን የሚፈታተን ቢሆን እንኳ በዘዴ መቋጨት አለበት፡፡ ይህንን ከባድ ጊዜ በጥበብ በማለፍ ግብፅን ወደ ድርድር ጠረጴዛው ጎትቶ ለማምጣት፣ ኢትዮጵያዊያን በአርቆ አሳቢነትና በአስተዋይነት ልዩነቶቻቸውን ማጥበብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ግብፅ የዓረብ ሊግ አባል አገሮችን ከጎኗ እንዳሠለፈች፣ ኢትዮጵያም የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮችን ከጎኗ ለማሠለፍ ኢትዮጵያውያን መተባበር አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች በሚኖርባት አገር ውስጥ፣ መሠረታዊ የማይባሉ ቅራኔዎችን ማጦዝ ቅንጦት ነው፡፡ ሕዝብን በብሔርና በእምነት በመለያየት ማጋጨትም ሆነ የአገርን ሰላምና መረጋጋት መፈታተን፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የውጭ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ተላላኪ መሆን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በሰላምና በትብብር መፍታት የሚችሉትን መናኛ ቅራኔ፣ ላልተገባ ዓላማ በማዋል አገርን ቀውስ ውስጥ መክተት ለውጭ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ቀዳዳ መፍጠር ነው፡፡ የውጭ ኃይሎች ጥቅማቸውን ለማስከበር ሲሉ ኢትዮጵያን አተራምሰው፣ ኢትዮጵያውንን ደግሞ እንደ የመናውያንና ሶሪያውያን ለስደት ከመዳረግ አይመለሱም፡፡ ይህ ደግሞ ተራ አሉባልታ ሳይሆን እውነት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የዓባይን መነሻ ለመቆጣጠር የተፈጸሙ ወረራዎችና በጀግኖች ኢትዮጵያዊያን የከሸፉ ጥቃቶች ከበቂ በላይ ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያዊያን አንድ ሲሆኑ ማንም እንደማይችላቸው ግልጽ ነው፡፡ አንድነታቸው ሲላላ ግን ታሪካዊ ጠላቶች ጎራዴያቸውን ስለው ይነሳሉ፡፡

ኢትዮጵያዊያን ከዚህ ቀደም በጀግኖች አባቶቻቸውና እናቶቻቸው ተጋድሎ አገራቸው ታፍራና ተከብራ እዚህ መድረሷን ሲዘክሩ፣ እነሱም በተራቸው የተላለፈላቸውን አደራ የመወጣት ኃላፊነት እንዳለባቸው መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በጨቋኝ ገዥዎች ሥር ጭምር ሆነው አገራቸውን ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች ሲከላከሉ መኖራቸው የሚታወቅ ስለሆነ፣ በዚህ ዘመን ደግሞ በእኩልነትና በነፃነት የሚኖሩባት ጠንካራ አገር ለመገንባት መረባረብ ግድ ይላቸዋል፡፡ እዚህ ላይ ግን አንድ መራራ ሀቅ ማመን የግድ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያውያን ልሂቃን በታሪካቸው ላይ መግባባት አለመቻላቸው በጣም ያሳፍራል፣ ያሳዝናል፡፡ የጥንቶቹ ኢትዮጵያዊያንም ሆኑ የዛሬዎቹ በጉራዕ፣ በጉንደት፣ በሰሃጢ፣ በዓድዋ፣ በካራማራ፣ በባድመ፣ ወዘተ በተደረጉ ከባድ ጦርነቶች በተገኙ አንፀባራቂ ድሎች እኩል ሲኮሩና አርዓያነታቸውን ሲያንፀባርቁ አይታዩም፡፡ ከዘመነ መሣፍንት ወዲህ በተነሱት በአፄ ቴዎድሮስ፣ በአፄ ዮሐንስ፣ በአፄ ምኒልክ፣ በአፄ ኃይለ ሥላሴ፣ ወዘተ ላይ ያላቸው ምልከታ የፖለቲካ ወለምታ አለበት፡፡ በኢትዮጵያዊ ማንነትና በብሔርተኝነት ውዝግቦች ሚዛናቸውን ይስታሉ፡፡ አገርን ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች ለመከላከል የተደረጉ ተጋድሎዎችን በመግፋት፣ በእርስ በርስ ጦርነት የተገኘን ድል ማጀገን ምን ያህል አሳፋሪ እንደሆነ እንኳ መግባባት የለም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ልሂቃን በታሪክ ያጋጠሙ ዝንፈቶችን በመተማመን ለማስተካከል፣ አኩሪ ገድሎችን ደግሞ በመጪው ትውልድ ለማስቀጠል ቢተጉ ኖሮ ለአድፋጭ ጠላት በር አይከፍቱም ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ስትጎዳ የኖረችው በዚህ ምክንያት መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ከስህተቶች መማር የግድ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የታሪክ መስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች፡፡ ትክክለኛውን አቅጣጫ ይዛ እንድትጓዝ የማድረግ ኃላፊነት የኢትዮጵያውያን ብቻ ነው፡፡ ለፖለቲካ ሥልጣን የሚደረገው ፉክክር ሥልጡን ሆኖ የሁሉንም ተሳትፎ በእኩልነት እንዲያረጋግጥ ተባብሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ መጪው ምርጫ ከእንከን የፀዳ እንዲሆን አገር የሚያስተዳድረው መንግሥት፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችና ስብስቦች፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ አደረጃጀቶችና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በንቃት መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዘንድሮ ይደረጋል በሚባለው ምርጫ ዋዜማ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስር፣ ማስፈራራት፣ የቢሮ መዘጋት፣ የስብሰባዎች መከልከል፣ የሰነዶች መነጠቅ፣ ወዘተ እንደ ደረሱባቸው ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቤቱታ ማቅረባቸው ሲሰማ ያሳዝናል፣ ያሳፍራል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ በተሻለ ሁኔታ እየተከፈተ ነው ተብሎ በሚታሰብበት በዚህ ወቅት፣ ምርጫውን ለውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ሊያመቻች የሚችል አጋጣሚ መፈጠር የለበትም፡፡ በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት፣ ከእንዲህ ዓይነቱ ክስና ውንጀላ ራሱን ማፅዳት አለበት፡፡ ይህ ምርጫ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር አለበት ተብሎ ሲጠበቅ፣ ከዚህ በፊት የነበሩ አሳፋሪ ድርጊቶች እንዲደገሙ መፈቀድ የለበትም፡፡ አቤቱታ አቅራቢ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ስብስቦች ራሳቸውን በሚገባ መፈተሽ አለባቸው፡፡ በዚህ ዘመን ከመንግሥታት ባልተናነሰ የፖለቲካ ኃይሎችም ምርጫን የማበላሸትም ሆነ የማጭበርበር ድርጊት ውስጥ እየገቡ መሆኑን፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች ጭምር በስፋት እየተወሳ ነው፡፡ በተለይ ‹ሲሞቅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ› በሚባል አጉል ብሂል ትርምስ መፍጠር የሚፈልጉ ኃይሎች ይጠንቀቁ፡፡ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነው ሕዝብ ሁሉንም ነገር በትዕግሥትና በአንክሮ እየተከታተለ ነውና፡፡ ይህ ዓይነቱ ድርጊት ለጠላት አመቺ ሁኔታ ከመፍጠር በዘለለ ለኢትዮጵያ አይጠቅማትም፡፡

በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹አዲሱ ትውልድ በአሮጌ አስተሳሰብ አይመራም›› ማለታቸው አይዘነጋም፡፡ ስለአዲሱ ትውልድ ሲነገር ታዲያ ከመፈክር ተሸካሚነትና ከፕሮፓጋንዳ አስተጋቢነት እንዴት መላቀቅ እንዳለበት በግልጽ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ አዲሱ ትውልድ ጥራት ያለው ትምህርት፣ ሥነ ምግባርና ሞራላዊ እሴቶች እንዲላበስ ሲደረግ የአገር ፍቅር ስሜት ይሰርፅበታል፡፡ ልዩነቶችን በግጭት ሳይሆን በሰላማዊና በሠለጠነ መንገድ እንዴት መፍታት እንደሚችል ይረዳል፡፡ በስሜታዊነት ሳይሆን በምክንያታዊነት ይመራል፡፡ ታሪክን ሲመረምር የጎራ አሠላለፍ ውስጥ ሆኖ ሳይሆን ሳይንሳዊ ሥነ ዘዴዎችን ይከተላል፡፡ አገርን ከሚያጠፉ ይልቅ የሚያለሙ ተግባራት ውስጥ ይገኛል፡፡ ለሐሳብ ልዕልና እንጂ ለጉልበት ሥፍራ አይሰጥም፡፡ በሐሰተኛ ወሬ ሳይደናበር እውነትን ማረጋገጥ ላይ ያተኩራል፡፡ በተጣራ ማስረጃ እንጂ በግርድፍ መረጃ አይበይንም፡፡ በአጠቃላይ ለፍትሕ፣ ለነፃነትና ለእኩልነት እንጂ ለአምባገነንነት አያጎበድድም፡፡ ለአገር ታላላቅ ጉዳዮችና ለተቋማት ግንባታ ትኩረት ይሰጣል እንጂ ለግለሰቦች ተክለ ሰብዕና አይዋደቅም፡፡ ይህንን የመሰለ ብቁና ንቁ ትውልድ ማፍራት ይገባል፡፡ ሰብዕናው የተሞረደ ልሂቅ ትውልድ ሲፈጠር የአገር ገጽታ ይለወጣል፡፡ ለዚህ ዕውን መሆን ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሠረቱን መጣል አለባቸው፡፡ በውጭ ኃይሎች ተፅዕኖዎች ምክንያት ኢትዮጵያ ያለፈችባቸው የመከራ ዘመናት ያብቁ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ በላይ ይንቁ፡፡ የውጭ ተፅዕኖን በብቃት መመከት የሚቻለው ውስጣዊ ስምምነት በመፍጠር ብቻ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...