Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኦሊምፒክ ዝግጅት የአትሌቶችን ሐሳብ ያካተተ እንደሚሆን ተገለጸ

የኦሊምፒክ ዝግጅት የአትሌቶችን ሐሳብ ያካተተ እንደሚሆን ተገለጸ

ቀን:

ኢትዮጵያ የአበረታች ቅመሞች ሥጋት ካለባቸው አገሮች ተርታ ተካታለች

ከመጪው ሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ በጃፓን በተለያዩ ከተሞች እንደሚከናወን የሚጠበቀው የቶኪዮ ኦሊምፒክ በውድድሩ ወቅት በአገሪቱ የሚኖረው የአየር ፀባይ በራሱ ኢትዮጵያውያኑን ጨምሮ ለብዙ አትሌቶች አስቸጋሪ መሆኑ እንደማይቀር የዘርፉ ሙያተኞች ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያን ዝግጅት በሚመለከት ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በዝግ መወያየቱ ተሰምቷል፡፡

ኢትዮጵያ በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በአትሌቲክስ፣ በወርልድ ቴኳንዶና በብስክሌት እንደምትሳተፍ ሲረጋገጥ፣ በዓለም አቀፉ ተቋም ሁሉን አቀፍ ተደራሽነት (ዩኒቨርሳሊቲ) ፕሮግራም በዋና፣ በአንድ ወንድና በአንድ ሴት መሳተፍ የሚያስችል ዕድል ሊኖር  እንደሚችል የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡

ከሁሉን አቀፍ ፕሮግራም ውጭ ባሉት ስፖርቶች ለቶኪዮ ኦሊምፒክ በተለይ በአትሌቲክሱ ዘርፍ የተመረጡ ብሔራዊ አትሌቶች ዝርዝር ለብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ተላልፎ ዝግጅት ተጀምሯል፡፡ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በተለይ ውድድሩ ከሚደረግባቸው የጃፓን ከተሞች ወቅታዊ አየር ፀባይ ጋር ተያይዞ መደረግ ስለሚገባው ዝግጅትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከብሔራዊ ፌዴሬሽኖቹ አመራሮች፣ የቡድን መሪዎችና ዋና አሠልጣኞች ጋር ተወያይቶ መግባባት ላይ እንዳልደረሰ ግን የሚናገሩ አሉ፡፡

ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ምንጮች ለሪፖርተር እንደሚናገሩት ከሆነ፣ ውይይቱ የተደረገው ባለፈው ሐሙስ የካቲት 26 ቀን 2012 ዓ.ም. በብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው መሰብሰቢያ አዳራሽ ሲሆን፣ ዝግጅቱ ከአዲስ አበባ ውጭ ቢቻል የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ከሚካሄድባቸው የጃፓን ከተሞች አየር ፀባይ ጋር ተቀራራቢነት ወዳለው አካባቢ ተንቀሳቅሶ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ በኦሊምፒክ ኮሚቴ በኩል ዕቅድ መቅረቡ፣ ይሁንና ዕቅዱ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት መጀመርያ ጉዳዩ ለብሔራዊ አትሌቶች ቀርቦ እንዲወያዩበትና እንዲያምኑበት ማድረግ በሚለው ተስማምተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አድማሱ ሳጅን በቀረበው ሐሳብ እንደሚስማሙ፣ ሆኖም ግን ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚኖሩት በአዲስ አበባ ከተማ በመሆኑና በተሽከርካሪዎች ጢስ በተበከለ ከተማ ተቀምጦ መዘጋጀት ሊያስከትል የሚችለው ጥቅምና ጉዳት አትሌቶቹ በተገኙበት መተማመን ላይ ተደርሶ ከ2020 ኦሊምፒክ ተቀራራቢነት ወዳለው አካባቢ ተንቀሳቅሶ መዘጋጀት የግድ ስለመሆኑ ጭምር ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የአየር ፀባይ በሚመለከት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴን ጨምሮ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሙያተኞች፣ ‹‹የአዲስ አበባ አየር ፀባይ ለኦሊምፒክ ዝግጅት አይደለም በከተማው የዕለት ተዕለት ኑሮውን ለሚመራው ነዋሪ ሳይቀር ከባድ እየሆነ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴም ሆነ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የሚደረጉት ዝግጅት ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ አትሌቶቹም ለዚህ ተባባሪ የሚሆኑት ለማንም ብለው ሳይሆን፣ ለራሳቸው ጭምር እንደሆነ ሊያምኑ ይገባል፤›› በማለት ለቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ አዲስ አበባ ተቀምጦ በሚደረግ ዝግጅት ውጤት እንደማይታሰብ ያስጠነቅቃሉ፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በ2020 የውድድር ዓመት የስፖርት አበረታች ቅመሞች (ዶፒንግ) አጠቃቀምን በሚመለከት ከፍተኛ ሥጋት ካለባቸው ጥቂት የዓለም አገሮች አንዷ ሆና እንደምትቀጥል የሚያመላክቱ ዘገባዎች እየወጡ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት በበኩሉ፣ ወርልድ አትሌቲክስ፣ ኦሊምፒክን ጨምሮ ተቋሙ በሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ጠንካራ ተሳትፎ የሚያደርጉ አገሮችን በ“ኤ” ምድብ እንደሚመድባቸው በድረ ገጹ ባሰፈረው መረጃ ይገልጻል፡፡

አትሌቲክስ ኢንቴግሪቲ ዩኒት መረጃን በመጥቀስ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ፣ ኢትዮጵያ በሚቀጥለው የውድድር ዓመት በችግሩ ከሚጠረጠሩ ሰባት አገሮች አንዷ ትሆናለች፡፡ እንደ ብሔራዊ ጽሕፈት ቤቱ ከሆነ፣ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገው ምርመራና ቁጥጥር ተጠናክሮ የሚቀጥል ከመሆኑም በላይ የሕግ ጥሰት በሚፈጽሙ አካላት ላይም አስፈላጊውን የዕርምት ዕርምጃ ይወሰዳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...