አንዳንዴ ራሴን ያላሰብኩት አጋጣሚ ውስጥ አገኘዋለሁ፡፡ ማስታወሻ መያዝ እወዳለሁና ከማስታወሻዬ በረከት ትቋደሱ ዘንድ እንዲህ ከትቤዋለሁ፡፡ በቀደም ከደሴ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዘውን ‹‹ታታ›› አውቶቡስ የተሳፈርኩት ከጠዋቱ 12 ሰዓት ላይ ነው፡፡ ሁለት ሰዎች የሚያስቀምጠው ወንበር ላይ አረፍ ከማለቴ ከኋላዬ ተከትለውኝ የገቡ አዛውንት መነኩሴ አጠገቤ ተቀመጡ፡፡ የተለመደውን ሰላምታ ካቀረቡልኝ በኋላ በፀጥታ ውጭ ውጩን ማየት ጀመሩ፡፡ አውቶቡሱ ሞልቶ ጉዞ ስንጀምር ለፈጣሪ ፀሎት አድርሰው ጉዞው የተባረከ እንዲሆን ምልጃ አቀረቡ፡፡ ከዚያም ስለቤተሰብ፣ ሥራና መሰል ጉዳዮች እየጠየቁኝ ማውራት ጀመርን፡፡
አውቶቡሱ ኮምቦልቻን አልፎ መገስገስ ሲጀምር እንደ ወትሮዬ የያዝኩትን መጽሐፍ ከቦርሳዬ አውጥቼ ማንበብ ቀጠልኩ፡፡ የመጽሐፉን ርዕስ ካዩ በኋላ ፈገግ ብለው፣ ‹‹የዘመኑ ወጣት የሚያነብ አይመስለኝም፡፡ ቢያነብም ከልብ ወለድና ከቀልዳ ቀልድ የሚዘል እንዳልሆነ ባውቅም፣ አንተ ግን ትገርማለህ፤›› አሉኝ፡፡ እኝህን መነኩሴ ያስገረማቸው የእኔ ‹‹ዳስ ካፒታል›› መጽሐፍ ማንበብ ነው፡፡
አነጋገራቸው ስላስገረመኝ፣ ‹‹ለመሆኑ ይህንን መጽሐፍ ያውቁታል?›› ስላቸው ከት ብለው ሳቁ፡፡ ‹‹ወይ አለመተዋወቅ?›› ካሉኝ በኋላ፣ ‹‹የመጽሐፉ ደራሲ ጀርመናዊው ካርል ማርክስ መሆኑን አንተ ሳትወለድ በፊት ማወቅ ብቻ ሳይሆን፣ በሚገባ አንብቤዋለሁ ያውም ከበርካታ ዓመታት በፊት . . .›› ሲሉ የመነኩሴው አነጋገር ግራ አጋባኝ፡፡ መጽሐፉን አጠፍ አድርጌ ለሌላ ገለጻ ተመቻችቼ ተቀመጥኩ፡፡
መነኩሴው በመስኮት ወደ ውጭ እያዩ በሐሳብ ርቀው የተጓዙ ይመስላሉ፡፡ ገጽታቸውን ለማጤን ስሞክር ጠይም፣ ረጅም፣ ፅዱና ግርማ ሞገስ ያላቸው ሲሆኑ እርጋታ ይታይባቸዋል፡፡ ዕድሜያቸው በግምት 70 ይሆናል፡፡ አተኩሬ እያየኋቸው እንደሆነ የገባቸው መነኩሴው ደጅ ደጁን እያዩ፣ ‹‹የትምህርት ደረጃህ ምንድነው?›› ሲሉኝ፣ የመጀመርያ ዲግሪዬን በኢኮኖሚክስ ይዤ አሁን ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪዬን ለመያዝ እየተማርኩ መሆኔን ነገርኳቸው፡፡
ፈገግ እያሉ እያዩኝ፣ ‹‹ዕድሜህ ስንት ነው?›› በማለት ጠየቁኝ፡፡ ሰላሳ ዓመት ሊሞላኝ ስድስት ወራት ይቀሩኛል አልኳቸው፡፡ ‹‹በዚህ ዓለም ስትኖር በርካታ ውጣ ውረዶች ስለሚገጥሙህ ፅናት እንድታገኝ ፈጣሪህን ፈጽሞ እንዳትረሳ . . .›› በማለት ምክር ካቀረቡልኝ በኋላ ትምህርቴን በርትቼ እንድማርና ቤተሰብ እንድመሠርት አሳሰቡኝ፡፡ ከዚያም እኔም መጽሐፌን እንዳነብ እሳቸውም ትንሽ ማንቀላፋት እንደሚፈልጉ ነግረውኝ ለጊዜው ንግግራችን ተገታ፡፡
እሳቸው እያንቀላፉ እኔም መጽሐፌን እያነበብኩ ደብረሲና ደርሰን አውቶቡሱ ቆመ፡፡ ቁርሳችንን መቀማመስ ስለነበረብን ብቀሰቅሳቸው የኩዳዴ ፆም ላይ መሆናቸውን ነግረውኝ እኔ ልበላ ሄድኩ፡፡ ምግብ ቤቱ ውስጥ አጠገቤ ጠረጴዛ ከበው የተቀመጡ ሦስት ሴቶች እኔ አጠገብ ስለተቀመጡት መነኩሴ ያወራሉ፡፡ በከፍተኛ አድናቆት ስለሳቸው ይነጋገሩ ስለነበር ጆሮዬን ጥዬ ሰማሁዋቸው፡፡ አንዷ በከፍተኛ ስሜት ውስጥ ሆና፣ ‹‹እሳቸው እኮ የዶክትሬት ዲግሪ አላቸው፡፡ አሜሪካና አውሮፓን ተመላልሰውባቸዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን አኝከው ውጠውታል ማለት ብቻ ይቀላል…›› እያለች ስትናገር እሳቸው አጠገብ በመቀመጤ ዕድለኛ መሆኔ ተሰማኝ፡፡ ሴቶቹ ወሬያቸው ቢቀጥልም እኔ ወደ አውቶቡሱ በፍጥነት ተመለስኩ፡፡
የአውቶቡሱ በራፍ ሲከፈት ተንደርድሬ ገባሁ፡፡ መነኩሴው ነቅተው ነበር፡፡ የገዛሁላቸውን ውኃ እየሰጠኋቸው፣ ‹‹አባቴ የምጠይቅዎት ነገር ስላለኝ ፈቃደኛ ቢሆኑልኝ …›› ስላቸው፣ ‹‹ልጄ ከፀሐይ በታች ምን አዲስ ነገር አለና ነው የምትጠይቀኝ?›› ብለው ውይይታችንን ጀመርን፡፡ በእርግጥም እኚህ መነኩሴ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በ1950ዎቹ አጋማሽ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን፣ ከአሜሪካ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛና የዶክትሬት ዲግሪዎችን ማግኘታቸውን አረጋገጥኩ፡፡ በአገር ውስጥ በቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ በአየር መንገድና በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ውስጥ መሥራታቸውን፣ በአሜሪካ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ማስተማራቸውን፣ ከዚያም የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ሲገረሰስ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ነገሩኝ፡፡
በባላባታዊው ሥርዓት በአርሶ አደሩና በደሃው ሕዝብ ላይ የደረሰውን የመከራ ቀንበር ለማስወገድ በተደረገው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ንቁ ተሳታፊ እንደነበሩ ከነገሩኝ በኋላ፣ በሰፊው ሕዝብ መስዋዕትነት የተገኘው አብዮት በወታደራዊው ኃይል ሲቀለበስ በተቃውሞ የተነሳው የኢሕአፓ አባል በመሆን ትግል ውስጥ መግባታቸውን በሰፊው አብራሩልኝ፡፡ ወታደራዊው ደርግ የኢሕአፓ አባላት ላይ ቀይ ሽብር አውጆ የሰፊው ሕዝብ ልጆችን ሲጨፈጭፍ፣ በጅምላ እስር በሺዎች የሚቆጠሩትን ሲያሰቃይና አገሪቱን ማቅ ሲያለብሳት የነበረውን አሰቃቂ ትዕይንት አብራሩልኝ፡፡ እሳቸውም ከአሰቃቂው የማዕከላዊ ግርፊያና ስቃይ እስከ ከርቸሌ ድረስ ያሳለፉትን የዘጠኝ ዓመታት የመከራ ጊዜ ተነተኑልኝ፡፡
‹‹ይኼውልህ ሰፊውን ሕዝብ ከብዝበዛ፣ ከአፈናና ከድህነት ነፃ ለማውጣት የተነሳው ያ ትውልድ እንዳይሆኑ ሆኖ ሲቀር ዓለም አስጠላችኝ፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አርነት የተነሳው ያ ጀግና ትውልድ ረግፎ አገሪቱ ባዶዋን ስትቀር ሁሉም ነገር ኦና ሆነብኝ፡፡ ከእስራት ስፈታ ሁሉንም ነገር ትቼ ገዳም ገባሁ፡፡ ያንን ዘመን ሳስታውስ ባዶነት ይሰማኛል፡፡ ነገር ግን በፈጣሪ ታላቅ ተግባር ስለምፅናና እስካሁን አለሁ፡፡ ከገዳም ወደ ገዳም እየዞርኩ አለሁ እልሃለሁ፤›› ብለውኝ፣ ‹‹ሰማህ ልጄ! ኢትዮጵያ የፈጣሪ ጥበቃ ያላት አገር መሆኗን ዕወቅ፡፡ ነገር ግን የአንተም ሆነ የትውልዱ ንፁህ ህሊና፣ ቅንነትና ተቆርቋሪነት የተሞላበት ዕገዛ እንደሚያስፈልጋት መረዳት አስፈላጊ መሆኑን አስብ፡፡ አገር ከሌለች ምንም ነገር የለም ብቻ ሳይሆን፣ ተዋራጅነትና የማንም መጫወቻ መሆን መከተል እንዳለ ለራስህም ለቢጤዎችህም መልዕክቴን አስተላልፍ፡፡ በእኛ ትውልድ ምክንያት ኢትዮጵያ ብዙ መከራ አይታለች፡፡ ይህ መከራ በዚህ ትውልድ እንዲቆም ካልተደረገ መጪው ጊዜ የበለጠ ይከብዳል፡፡ የእኛን ስህተት እባካችህ እንዳትደግሙ…›› ብለውኝ አዲስ አበባ ስንደርስ ቀበና አካባቢ ወርደው ተለዩኝ፡፡
በዚህ ወርኃ የካቲት የ1966 ዓ.ም. ታላቁ ሕዝባዊ አብዮት 46 ዓመታት ሞሉት፡፡ ከአብዮቱ ዘመን ትዝታ ጋር ያገናኘኝ ገጠመኜ ከእኚህ አባት ጋር ሲያገናኘኝ አንድ ሐሳብ መጣልኝ፡፡ ለመሆኑ ስንቶች ይሆኑ በተለያዩ የአብዮቱ ትዝታዎች ውስጥ የሚኖሩት? አብዮቱን በአግባቡ መምራት ያቃተው ትውልድ እርስ በርሱ ተፋጅቶ ያተረፈው ምንድነው ሲባል መልሱ ፀፀት እንደሆነ ከበቂ በላይ እናውቃለን፡፡ የዚያን ዘመን ሰዎች በርካታ መጻሕፍት አስነብበውናል፡፡ ነገር ግን የዚህን ዘመን ሰዎች ከመምከርና ያንን ስህተት እንዳይደግሙ ከማሳሰብ ይልቅ፣ ያኔ አወራርደው ያልጨረሱትን በቀልና ቂም ለመወጣት ሲሉ ይዋሻሉ፡፡ እኚህ ምሁር አባት ግን አገራችሁን አስቡ ሲሉ ለእኔ የተሰማኝ፣ ‹ከእኛ የከፋ ስህተት ውስጥ ወድቃችሁ መመለሻ የሌለው ችግር ውስጥ እንዳትገቡ› የሚል መልዕክት ነው፡፡ እውነታቸውን ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በህዳሴ ግድቡ ምክንያት የግብፅ ፈተና አልላቀቀን ብሎ መከራ ስናይ፣ የአሜሪካ ድንገት ከግብፅ ጋር ተደርቦ ማበር እንደ በጋ መብረቅ የሚያስደነግጥ ነው፡፡ ለዚህም ነው በአገር ጉዳይ ቀልድ የለም ብለን ለአገራችን በአንድ መንፈስ ተባብረን መቆም ያለብን፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡
(መኰንን አበጋዝ፣ ከደሴ)