Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለምርጫ የሰነፈው ንግድ ምክር ቤት

በአገር አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ንግድ ማኅረሰቡን የሚወከለው የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ለመምራት በየሁለት ዓመቱ በሚደረጉ ምርጫዎች ወቅት አብዛኛውን ጊዜ ችግር ሲያጋጥም ይታያል፡፡

የንግድ ምክር ቤቱን አመራሮች ለመሰየም የሚደካሄደው የምርጫ እንቅስቀሴ በተቃረበ ቁጥር ቦታውን ለመያዝ የሚፈልጉ ወገኖች በተደጋጋሚ ሲያወዛግቡ ታይተዋል፡፡ ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትነት፣ በምክትል ፕሬዚዳንትነት እንዲሁም በቦርድ አባልነት ለማገልገል የሚመረጡ ኃላፊዎችን ለመሰየም የሚካሄዱ ምርጫዎች በመጡ ቁጥር በሚነሱት ፉክቻዎች ምክንያት ተቋሙ በተደጋጋሚ ስሙ ሲነሳ ሲጣል መክረሙ ይታወቃል፡፡ በዚሁ ችግሩ ሳቢያም በሚዲያ ሲተች እንደነበር አይዘነጋም፡፡

የምክር ቤቱ መለያ እስኪመስል ድረስ በየሁለት ዓመቱ የሚደረገው ምርጫ ዋዜማ ሰሞን የሚነሳው አቧራ በርካቶችን ከማስገረም አልፎ፣ ምን ቢገኝበት ነው የሚሉ ጥያቄዎችን ሲያስነሳ ነበር፡፡ በእርግጥ በዚህ ኃላፊነት ቦታ ላይ ለመቀመጥ የሚደረገው ትግል የተለያየ ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ በርካታ ለግል ጥቅም የሚውሉ አጋጣሚዎች እንደሚገኙበት መገለጹ አንዱ ነው፡፡ ተቋሙን በአግባቡ ከማገልገል ይልቅ የኃላፊነት ቦታውን ለግል ጥቅም ያደሉ ሰዎች የሚራወጡበት መድረክ መሆኑም ለወቀሳ አብቅቶታል፡፡ ተቧድነው ለራሳቸው የሚያደሉላቸውን ኃላፊዎች ለመምረጥ ግለሰቦች የሚያደርጉት ሸብረብ በአግባቡ የሚሠሩ ትጉኅና የግሉ ዘርፍ እውነተኛ ተቆርቋሪዎችን እንዲሸሹ ማስገደዱ አልቀረም፡፡  

እንዲህ ባለው ሁኔታ አካሄዱ ይገለጽ የነበረው ንግድ ምክር ቤት፣ ከሦስት ዓመታት በፊት እንዲህ ያሉ ሽኩቻዎችን ለማስቀረት መሥራት አለበት ተብሎ የተለያዩ ማሻሻያዎች ተደርገው ነበር፡፡ በሰበብ በአስባቡ ይዘገይ የነበረው ምርጫ እንደምንም ታካሂዶ አዳዲስ አመራሮች ተገኝተው ነበር፡፡ ተመራጮቹ የቀደመውን ስህተት እንደማይደግሙ ታምኖባቸው ነበር፡፡ የንግድ ምክር ቤቱን ሕገ ደንብ ጠብቀው በወቅቱ ጠቅላላ ጉባዔ ይጠራሉ፡፡ የሥልጣን ዘመናቸው ሲያበቃም ጊዜውን ጥብቀው ኃላፊነታቸውን ያስረክባሉ የሚል እምነት ተጥሎባቸው ነበር፡፡  

አሁን በኃላፊነት ላይ የሚገኘው አመራር ወደፊት ምርጫዎች እንደቀድሞው እንደማይታጎሉና አሠራሩም እንደማይዘበራረቅ ቃል ቢገባም፣ በተግባር ግን አሁንም የቀድሞው ሲደረግ እየታየ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የኃላፊነት ዘመኑን ያጠናቀቀው አመራር የቀደመውን ስህተት ደግሞታል፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ የኃላፊነት ጊዜው ያበቃው ጥቅምት 2012 ነበር፡፡ በዚሁ መሠረት ቢበዛ እስከ ኅዳር መጨረሻ ድረስ ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቶ ምርጫ በማካሄድ ኃላፊነቱን ማስረከብ ነበረበት፡፡ ይህ ግን አልሆነም፡፡ ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫው መካሄድ ከነበረበት ከአምስት ወራት በላይ ካላካሄደም እንዲያውም በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም እየተደረገ ያለ ጥረት እንደሌለም ይነገራል፡፡ በእርግጥ ለዚህ ምርጫ መራዘምና ሕገ ደንቡን ጠብቆ አለመካሄዱ ከወራት በፊት ይፋ ከወጣ መረጃ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ ንግድ ምክር ቤቱ በጥቅምት ወር ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ ተዘጋጅቶ እንደነበር ነው፡፡ ነገር ግን ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት 18 አባል ንግድ ምክር ቤቶች ውስጥ የደቡብ ክልል ንግድ ምክር ቤት ከሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ጋር በተያያዘ ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባቀረበው አቤቱታ መሠረት በወቅቱ ጠቅላላ ጉባዔውን ማካሄድ ባለመቻሉ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ጉባዔም እንዲራዘምለት ጠይቆ ነበር፡፡ ይህንኑ አቤቱታ የተቀበለው ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ላልተወሰነ ጊዜ ይራዘም በማለቱና በመወሰኑ፣ ይህንኑ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት አባል ምክር ቤቶች እንዲያውቁት ተደርጓል፡፡

ንግድ ሚኒስቴር በደብዳቤ ይህን ማሳወቁ እርግጥ ቢሆንም፣ ውሳኔው እስከ መጨረሻው ጠቅላላ ጉባዔ መደረግ የለበትም አላለም፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ግን ጠቅላላ ጉባዔ አልጠራም፡፡ የሥልጣን ዘመኑ ያበቃው ቦርድም በጠቅላላ ጉባዔ የተሰጠውን ኃላፊነት ማስረከብ አልቻለም፡፡ ይህ ተግባር የ70 ዓመታት ዕድሜ ካስቆጠረው ተቋም የሚጠበቅ ካለመሆኑም በላይ፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ሰበብ በማድረግ የንግዱ ምክር ቤቱ ሕገ ደንብ መጣስ አልነበረበትም፡፡ ንግድና ኢንዱስትሪም ቢሆን ይህንን ጉዳይ በማጤን ወደ ቀጣይ ዕርምጃ መግባት ሲገባው ቸልታን መርጧል፡፡ የአንድ ተቋም አሠራር እየተዛባ ለመሆኑ በምክንያትነት መጠቀሱ በራሱ ሚኒቴሩንም ያስጠይቃል፡፡ ይህ ተቋም ብዙ የሚጠበቅበትና ሌሎች ንግድ ምክር ቤቶችንም ጠንክረው እንዲወጣና አገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ሲገባቸው ዝም ማለታቸው አጠያያቂ ነው፡፡

 እንደ ንግድ ኅብረተሰብ ንግድ ምክር ቤቱ አባላትም የሚያነሱት ጥያቄ አለመኖሩ ሲታይ፣ እነዚህ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች አሉ በሕይወት አሉ ወይ? ያሰኛል፡፡ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በወቅቱ የተፈጠረውን ሁኔታ ከግምት አስገብቶ ጠቅላላ ጉባዔው ይራዘም ካለ በኋላ እንዲሁም በእርሱ ምክንያት ንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔውን ማድረግ አይችልም መባሉ በራሱ ምን ያመለክታል? የንግዱ ኅብረተሰብ በገለልተኝነት የሚሠራውን ሥራ መቃወም አይሆንም? ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በንግድና ዘርፍ ማኅበራት ጉዳይ የሚመለከተውና የኃላፊነት ድርሻም ያለበት ቢሆንም፣ አንድን ገለልተኛ ተቋም ጠቅላላ ጉባዔውን ሳያካሂድ ይህን ያህል ወራት እንዲቆይ የማድረግ ሥልጣን አለው ወይ? አባል ምክር ቤቶችስ ማኅበራቸው እንዲህ ባለ ምክንያት ከምክር ቤታቸው ደንብና አሠራር ውጪ እየተፈጸመ ያለውን ተግባር ዝም ማለት ተገቢ ነበር? ወይስ ንግድ ምክር ቤቱን አይፈልጉትም?

ከሕግ አንፃርም ንግድ ምክር ቤቶች ከደንባቸው ውጪ በኃላፊነት ላይ ሲቆዩ ከዚህ ቀደም ጣልቃ ገብቶ ምርጫ እንዲደረግ ይዳኝ እንዲል ነበር አሁን አገር አቀፉን ንግድ ምክር ቤት ጉዳይ እንዲህ ባለ ደረጃ ዝም የማለቱ ሚስጥር ግልጽ አይደለም፡፡ አሁን የኃላፊነት ጊዜው ያለቀውንና የንግድ ምክር ቤቱን አመራር የያዙትን ቦርድ  አባላትስ የኃላፊነት ጊዜያችን ከሕግ አግባብ አልቋልና እናስረክብ ማለት ያልደፈሩበት ምክንያት ምንድነው? ይህ ኃላፊነቱን ካለመልቀቅ ካላቸው ፍላጎት አንፃር ነው የሚለውን አመለካከት እንደሚያስከትል አያውቁም? ነገሩ ጠለቅ ብሎ ሲታይ በቡድን ዝም የተባለ ይመስላል፡፡ ይህም ለተቋሙ አሠራርና ሕግ ተገዥ ያልሆኑ መሆኑን ሊያመላክት ይችላል፡፡ ባይሆን በወቅቱ ምርጫ ማድረግ ድጋሚ ከተመረጡም በዚያው መቀጠል እንጂ ደንብ ማፍለስ አልነበረባቸውም፡፡ ሌላው ቀርቶ አንድ ሰው ወጥቶ ኧረ ጎበዝ ይኼ ነገር ትክክል አይደለም ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ የገጠመው ችግር ይህ ነው ብሎ ይፋዊ መግለጫ አልተሰጠም፡፡ ሕገ ደንቡንና አሠራር አስተጓጉሎ እስከ መቼ ሊጠበቅ ታስቦ ነው? ለሚለው ጥያቄም አፋጣኝ መልስ ያሻል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት