በመላው ኢትዮጵያ የሚደረገው ጠቅላላ ምርጫ በነሐሴ ወር በመሆኑ ችግሮች ቢያጋጥሙም፣ በሙሉ አቅም አፋጣኝ ፍትሕ በአንድ ወር ውስጥ ለመስጠት መልካም አጋጣሚ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ምርጫው የሚደረገው ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሆነ አስታውሰው፣ ይህ ወቅት ደግሞ ፍርድ ቤቶች ከነሐሴ እስከ መስከረም ወር መጨረሻ ድረስ በከፊል ዝግ የሚሆኑበት ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ሌሎች መዝገቦች የማይኖሩበትና ዳኞች ልባቸውና አዕምሯቸው ሳይከፋፈል በሙሉ አቅማቸው ላይ በመሆናቸው፣ በአጋጣሚ ከምርጫው ጋር በተያያዘ አለመግባባት ተፈጥሮ ጉዳዩ ፍርድ ቤት የሚደርስ ከሆነ፣ በአጭር ጊዜ ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ መስጠት የሚቻልበት መልካም አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይኼንን የሚናገሩት ዳኞች ለማንኛውም አገራዊ ጥሪ የተዘጋጁና ኃላፊነትም እንደሚወስዱ ስለሚተማመኑ መሆኑን ወ/ሮ መዓዛ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንቷ ይኼንን የተናገሩት እሳቸው የሚመሩት ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ በምርጫ ጊዜ በሚነሱ አለመግባባቶችና ክርክሮች አፈታት ላይ ከደቡብ አፍሪካና ከኬንያ ከመጡ ዳኞች ጋር፣ የካቲት 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በሐያት ሬጀንሲ ሆቴል የልምድ ልውውጥ በተደረገበት ወቅት ነው፡፡
የልምድ ልውውጡ በቅርቡ በሥራ ላይ የዋለው የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ ሕግ ቁጥር 1162/2011 የሕግ ማዕቀፍን መሠረት ያደረገ ነበር፡፡ በሕጉ ምዕራፍ አራት ላይ ተደንግጎ እንደሚገኘው ውይይቱ በምርጫ ወቅት የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በመራጮች፣ በዕጩ ተመራጮች፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና በፓርቲዎች መካከል በሚነሱ የተለያዩ ጉዳዮች ድምፅ እንዳይሰጥ በመከልከል፣ የምርጫ ሥነ ምግባርን በመጣስ፣ በድምፅ ቆጠራና በውጤቱ ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡
እነዚህ አለመግባባቶች በቀላሉ የማይፈቱ ከሆነ፣ የመጨረሻ ዕልባት እንዲሰጥ አዋጁ ሥልጣን የሰጠው ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው፡፡ በመሆኑም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ ይኼንን መሠረት አድርገው ከላይ የገለጹትን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
የምርጫ ቦርድን መልካም እንቅስቃሴ በመገናኛ ብዙኃን መስማታቸውን ተናግረው፣ እሳቸው የሚመሩት ተቋም በምርጫ ምክንያት የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በምርጫ ቦርድ በየደረጃው በተዋቀሩ ጽሕፈት ቤቶች የተሰጡ ውሳኔዎችን የመመርመር፣ የመሻርና የማፅደቅ ሥልጣን በአዋጅ ስለተሰጠው፣ በአንድ ወር ውስጥ ውሳኔ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡
አገራዊ ምርጫው በተሳካ ሁኔታ ተከናውኖ በሕዝብ ድምፅ መንግሥት መመሥረት የሚገባው የፖለቲካ ፓርቲ፣ ጊዜ ሳያባክን መንግሥት መመሥረት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡ ይህም ለሰላምና ለመረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አክለዋል፡፡
በምርጫ ላይ ያላቸውን ልምድ ለማካፈል ከደቡብ አፍሪካ የመጡት የምርጫ ቦርድ ፍርድ ቤት ዳኛና ሊቀመንበር ቢኤች ምብሃ፣ ልዩ የምርጫ ፍርድ ቤት ስለሚደራጅበትና አገልግሎት ስለሚሰጥበት ሁኔታ አብራርተዋል፡፡
በኬንያ የምርጫ ዳኝነት ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑት ዳኛ ቦግሆሊ ምሳግሃም ተመሳሳይ ገለጻ አድርገዋል፡፡ በዓለም አቀፍ የምርጫ ሥርዓት ፋውንዴሽን ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ የሆኑ ካትሪን ኤሊና ደግሞ በምርጫ ወቅት ከሚፈጠሩ አለመግባባቶች በፍትሕ አሰጣጥ ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በሚመለከት ተሞክሯቸውን አካፍለዋል፡፡