Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቀድሞ ጋዜጠኛና ታጋይ ወ/ሮ ነፃነት አስፋው (1937-2012)

የቀድሞ ጋዜጠኛና ታጋይ ወ/ሮ ነፃነት አስፋው (1937-2012)

ቀን:

በኢትዮጵያ የሴቶች የትግል ታሪክ ውስጥ ስማቸውን ካኖሩት መካከል ይገኙበታል፡፡ የ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ ተክትሎ ሥልጣኑን የተቆናጠጠው ኢሕአዴግ በተለያዩ ኃላፊነት ካስቀመጣቸው መካከል የሚጠቀሱት የጋዜጠኝነትና የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዋ ወ/ሮ ነፃነት አስፋው፣ በሽግግር መንግሥቱ ዘመን የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት የፕሬስና ኢንፎርሜሽን ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡

ኢፌዴሪ ከተመሠረተ በኋላም በሁለተኛው የፓርላማ ዘመን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የመንግሥት ረዳት ተጠሪ፣ የማስታወቂያ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነውም ሠርተዋል፡፡

በ2003 ዓ.ም. መቀመጫውን ጂቡቲ ያደረገው የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) የሰላምና የፀጥታ ዘርፍ ዳይሬክተር ሆነው ካገለገሉ በኋላ፣ በአፍሪካ ኅብረት የኢጋድ ኦዲተር በመሆን እስከ 2010 ዓ.ም. መሥራታቸውን ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በጂኦግራፊ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ያገኙት ወ/ሮ ነፃነት፣ በማስታወቂያ ሚኒስቴር በጋዜጠኝት ካገለገሉ በኋላ ወደ ጀርመን በመጓዝ በዶቼቨሌ ከዘጠኝ ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ በ1972 ዓ.ም. ሕወሓትን በመቀላቀል በትጥቅ ትግል ውስጥ ያለፉ ሲሆን፣ ለጋዜጠኞችና ለኪነት ቡድን አባላት ሥልጠና ይሰጡ እንደነበር ይወሳል፡፡ በሻዕቢያ ወረራ ወቅት ከ1990 ዓ.ም. እስከ 1992 ዓ.ም. በመንግሥት ቃል አቀባይነት ተመድበው ሠርተዋል፡፡ በጦርነቱ የተፈናቀሉትን ወገኖች፣ ምርኮኞች፣ በግንባር የነበረውን ሕዝብ እያነጋገሩ በጦርነቱ የነበረውን መረጃ ለሕዝብ በማቅረብም ይጠቀሳሉ፡፡

ከአባታቸው አቶ አስፋው ንጉሥና ከእናታቸው መምህርት ትበርህ ተወልደ መድኅን ገብሩ መስከረም 17 ቀን 1937 ዓ.ም. በትግራይ ዓድዋ የተወለዱት ወ/ሮ ነፃነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በንግሥተ ሳባ፣ ሁለተኛ ደረጃን በአዲስ አበባ እቴጌ መነን ትምህርት ቤት አጠናቀዋል፡፡ በመቀጠልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተመርቀዋል፡፡

በ1966 ዓ.ም. አብዮት ሲፈነዳ ከጀርመን ኮለኝ ለዘገባ የመጡት ወ/ሮ ነፃነት አዲስ አበባ እንደገቡ ሴት ልጅ የወለዱ ሲሆን፣ ስሟንም አብዮት አማኑኤል ብለው መሰየማቸው ገጸ ታሪካቸው ይገልጻል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ትግርኛ የተረጎሙት አያታቸው አለቃ ተወልደ መድኅን ገብሩ የሥነ ጽሑፍ ፍቅር እንዳሳደሩባቸው የሚነገርላቸው ወ/ሮ ነፃነት፣ የሴቶችን የትግል ታሪከ ለትውልድ ሰንዶ ለማቆየት በተደረገው እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ይወሳል፡፡

በ2011 ዓ.ም. በእግራቸው ላይ በደረሰ ጉዳት በአገር ውስጥና በውጭ ሕክምና ሲደረግላቸው ከቆዩ በኋላ፣ ሰኞ የካቲት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በ75 ዓመታቸው ያረፉ ሲሆን፣ ሥርዓተ ቀብራቸውም የትግራይ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ በተገኙበት በመቐለ ከተማ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በሚገኘው የአርበኞች መካነ መቃብር ተፈጽሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...